የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሚያዝያ 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ለ33ኛ ጊዜ ታስቦ መዋሉን አስመልክቶ የወጡ መግለጫዎችና ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፤ የኢትዮጵያ የሚዲያ ድባብ በአገራዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች፣ በቀጣናዊ ውጥረቶችና የሚዲያ ነፃነትን በሚፈትኑ ሁኔታዎች ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደሚገኝ ቀኑን አስመልክቶ የወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ።
በምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ ላይ ያተኮረው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል በዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ዋዜማ ላይ ይፋ የተደረገ ግኝት፣ በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸሙ እንግልቶችን፣ ያላግባብ መታሰርን፣ በእስር ማቆየትንና የሕግ ማዕቀፎችን፣ ጋዜጠኝነትን ለመገደብ መጠቀምን ጨምሮ ሰፋ ያለ ቀጣናዊ የሚዲያ ነፃነት ገደቦች መኖራቸውን ያስረዳል።
በመላው ቀጣናው የሚገኙ ባለሥልጣናት ሚዲያዎችን በመዝጋት፣ ጋዜጠኞችን በማሰርና ‹‹ለማጥፋትና ለማስፈራራት የሚያገለግሉ ሰፊና ግልጽ ያልሆኑ ሕጎችን›› በመጠቀም ድርጊቶቻቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጿል።
ከዚህ ቀጣናዊ ሁኔታ አኳያ፣ ኢትዮጵያ በጋዜጠኞችና በሚዲያ ተቋማት ላይ ‹‹አዲስ የጭቆና ማዕበል›› እያስተናገዱ ካሉ አገሮች መካከል ትገኛለች ተብሏል። ሪፖርቱ እንደ ዋዜማ ራዲዮና አዲስ ስታንዳርድ ያሉ የሚዲያ ተቋማት የሥራ ፈቃድ መሰረዝን፣ እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎችን ማሰርን፣ በክትትል ውስጥ ማቆየትንና አፍኖ መውሰድን የመሳሰሉ ክስተቶችን እንደ ምሳሌ ጠቅሷል።
ይህንኑ ጉዳይ ሲያብራራ ለአብነት የጠቀሰው አንድ ጉዳይ፣ እ.ኤ.አ በሚያዝያ 2026 በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ፈቃዱ የተሰረዘው የአዲስ ስታንዳርድ ‹‹ማኔጂንግ ኤዲተር›› ታፍኖ ተወስዶ ለሁለት ሳምንታት የት እንዳለ ሳይታወቅ ከቆየ በኋላ መለቀቁን ገልጿል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት ዒላማ ከሚደረጉባቸው ሰፊ አዝማሚያዎች ጋር የሚያያይዛቸው ሲሆን፣ ዕርምጃዎቹም እስከ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ድርጅቶች መድረሳቸውን ይጠቁማል ብሏል።
በተጨማሪም የአምነስቲ ሪፖርት እነዚህ ክስተቶች እየተፈጸሙ ያሉት በሚዲያው ዘርፍ ላይ ካለው የገቢ መቀነስን ከመሰሉ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ጋር ተዳምሮ፣ ዘርፉ ጫና ውስጥ ባለበት ወቅት መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህም የሕግና የፖለቲካ ገደቦች በፕሬስ ነፃነት ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ይበልጥ እንደሚያባብሰው አመልክቷል።
From The Reporter Magazine
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ቲገሬ ቻጉታ፣ ‹‹በመላው ቀጣናው የሚገኙ መንግሥታትና በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ መንግሥታዊ ያልሆኑ ታጣቂዎች ሚዲያዎችን በመዝጋት፣ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ ያላግባብ በእስር በማቆየትና በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጽሙትን አፈና አጠናክረዋል። ጋዜጠኞችን ለማጥቃት የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱን እንደ መሣሪያ የተጠቀሙ ሲሆን፣ እነሱን ዝም ለማሰኘትና ለማስፈራራትም ሰፊና ግልጽ ያልሆኑ ሕጎችን መጠቀማቸውን ቀጥለዋል። ይህ ሁሉ የሆነው የሚዲያ ተቋማት ገቢዎቻቸው ዝቅተኛ በሆነበት ወቅት በመሆኑ፣ በፕሬስ ነፃነት ላይ በይበልጥ ከባድ ጫና ፈጥሯል፤›› ማለታቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ (RSF) እ.ኤ.አ. የ2026 የዓለም የፕሬስ ነፃነት ደረጃ ሪፖርት (World Press Freedom Index) ኢትዮጵያን በፕሬስ ነፃነት 148ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው፣ ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ረገድ በቅርብ ዓመታት አሳይታው የነበረው መሻሻል በተለይም ከብሔር ተኮር ግጭቶችና ከእርስ በርስ ጦርነት ጋር ተያይዞ በአብዛኛው ወደኋላ ተመልሷል።
እንደ ግኝቱ ከሆነ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነትና ተከታዩ የአማራ ክልል ግጭት በጋዜጠኞች ዘንድ ሰፊ ፍርሃትን ዳግም ቀስቅሰዋል፣ በተለይም ከዘገባቸው ጋር በተያያዘ ሊደርስባቸው የሚችል የአፀፋ ዕርምጃ ሥጋት ሆኗል ብሎ፣ ይህ ሁኔታ እ.ኤ.አ ከ2018 በኋላ የሚዲያ ምኅዳሩ መከፈት በጀመረበት ወቅት የታዩትን ቀደምት ድሎች ወደኋላ እንዲመለሱ ማድረጉም ተገልጿል።
From The Reporter Magazine
ዓለም አቀፉ ተቋም የአሁኑን የሚዲያ ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ ጽንፍ የረገጠና እውነቱን ከማረጋገጥ ይልቅ፣ አስተያየትን የተመረኮዘ ጋዜጠኝነት (Opinion Journalism) የተጫነው ሲል ይገልጸዋል። ይህም እውነታን መሠረት ካደረገ ዘገባና ማረጋገጫ ይልቅ በግል አስተያየት ላይ የተመሠረተ ጋዜጠኝነት እንዲቀድም አድርጓል ብሏል።
ምንም እንኳን የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ከቀደሙት መንግሥታት ከነበረበት በተሻለ ብዝኃነት ያለው ቢሆንም፣ ከ2010 ዓ.ም. መገባደጃ ወዲህ ብቻ ከ200 በላይ ቀደም ሲል የታገዱ ተቋማት ፈቃድ አግኝተው የነበረ መሆኑን ጠቅሶ፣ ይሁንና ዘርፉ በፖለቲካዊና ክልላዊ መስመሮች የተከፋፈለ ሆኖ ቀጥሏል ብሏል። በሚድያ አጠቃቀም ረገድ ሬዲዮ አሁንም እንደ ዋነኛ የመረጃ ምንጭነቱ ማገልገሉን ቀጥሏል ብሎ፣ የኅትመት ውጤቶች ግን በአብዛኛው በከተማ ነዋሪዎች በመነበብ ላይ የተገደቡ ናቸው ሲል አብርራቷል።
ሪፖርቱ በፖለቲካው መስክ የመንግሥት አካላትም ሆኑ ተቃዋሚ ቡድኖች የፕሮፓጋንዳ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ይህም በአብዛኛው በማኅበራዊ ሚዲያ ተሠራጭቶ በሚዲያ ተቋማት እንዲጎላ እንደሚደረግ ይገልጻል።
መንግሥት የራሱን ትርክቶች በሕዝቡ ዘንድ ለማስረፅ በሚያደርገው ጥረት ‹‹የእውነታ ማጣሪያ›› (Fact-Checking) የሚመስል መድረክ (Platform) ማቋቋምን የሚያካትት መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የአርኤስኤፍ ሪፖርት ይህ መድረክ ነፃ የእውነታ ማጣሪያ መንገድ ከመሆን ይልቅ ይፋዊ መልዕክቶችን ለማስተላለፊያነት የሚያገለግል የመገናኛ መስመር ነው በማለት ገልጾታል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ነፃ ጋዜጠኝነትን በማስተዋወቅ ረገድ ውጤታማነት ይጎድለዋል ተብሏል።
በሕግ ረገድ የኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2021 የፀደቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ የስም ማጥፋትን ከወንጀል ተጠያቂነት በማውጣትና ለጋዜጠኞች የመረጃ ምንጮች ጥበቃ በማድረግ በወረቀት ላይ የተሻለ ጥበቃ እንደሚሰጥ ይታመናል ያለ ሲሆን፣ ሆኖም ሪፖርቱ እነዚህ የሕግ ከለላዎች በተግባር ሲታዩ ግን ብዙ ጊዜ እንደሚጣሱ ገልጿል።
ሌሎች ሕጎች በተለይም የፀረ ሽብርተኝነትና የጥላቻ ንግግር ሕጎች፣ በጋዜጠኞች ላይ ሊተገበሩ የሚችሉና ከባድ ቅጣቶችን የሚያስከትሉ ሰፊ ትርጉም ያላቸው ድንጋጌዎችን የያዙ ስለመሆናቸው ጠቅሶ፣ እ.ኤ.አ. በ2023 ተጥሎ የነበረው የአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የመሳሰሉ ድንጋጌዎች ደግሞ ባለሥልጣናት ነባር የሕግ ጥበቃዎችን ወደ ጎን እንዲሉ ዕድል ስለመስጠታቸውም አትቷል።
የኢኮኖሚ ጫናዎችም በሪፖርቱ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ይዘዋል። ዝቅተኛ ደመወዝ፣ እየጨመረ የመጣ የኑሮ ውድነትና የሚዲያ ባለቤትነት በጥቂት ነጋዴዎች እጅ መጠቅለል ለኤዲቶሪያል ነፃነትና ለሙያዊ ታማኝነት ፈተና መሆናቸው ተለይተው ተጠቅሰዋል። በተመሳሳይ አዳዲስ የሚዲያ ተቋማትን ለማቋቋም የሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ ወደ ገበያው መግባትንና የዘርፉ አካላት ብዝኃነትን እንደሚገድብ ተጠቁሟል።
ከማኅበራዊና ባህላዊ ዕይታ አንፃር ሪፖርቱ በሚዲያ ተቋማት ውስጥ የብሔርና የፖለቲካ ጉዳዮች ተፅዕኖ መኖሩን፣ ይህም ራስን በራስ ሳንሱር ለማድረግ (Self-censorship) እንዲሁም ሚዛናዊ ዘገባዎችን ለመገደብ አስተዋጽኦ ማድረጉን ያስረዳል። እነዚህ ጫናዎች ከደኅንነት ሥጋቶች ጋር የሚተሳሰሩ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ጋዜጠኞች ከግጭት ዘገባዎቻቸው ጋር በተያያዘ እስራት፣ እንግልትና በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተገልጿል። አር ኤስ ኤፍ አሁንም አንዳንድ ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙና ሌሎች ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ ሥራቸውን መቀጠል ባለመቻላቸው አገር ጥለው መሰደዳቸውንም አክሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ ከቀናት በፊት ቮክስ ትግራይ (Vox Tigray) የተባለ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት፣ በክልሉ የመረጃ ነፃነትና የጋዜጠኞች ሁኔታ በተመለከተ አድርጌያለሁ ባለው ጥናት ግኝቶቹን ይፋ አድርጓል።
እንደ ቮክስ ትግራይ ሪፖርት ከሆነ፣ የኢትዮጵያ የሚዲያ ምኅዳር እ.ኤ.አ. ከ2018 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍተኛ ለውጦችን አስተናግዷል። ምንም እንኳን መጀመሪያ ላይ የምኅዳሩ መስፋፋት ምልክቶች ቢታዩም፣ ይህ ጉዞ ግን በአገራዊ የፀጥታ ሁኔታ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና በተደጋጋሚ በታወጁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ምክንያት ወደኋላ ተመልሷል ብሏል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቱ ሪፖርት ለዚህ ለውጥ አስተዋጽኦ ያደረጉ በርካታ ጉዳዮችን ለይቷል። እነዚህም የቁጥጥር ጫናዎች፣ የሥራ ፈቃድ ዕገዳዎች፣ እስራቶች፣ አፈናዎችና በጋዜጠኞች እንቅስቃሴ ላይ የተጣሉ ገደቦችን እንደሚያካትቱ ገልጾ፣ በተጨማሪም ባለሥልጣናት የሥራ ፈቃዶችን በመሰረዝና የዘጋቢዎችን ዕውቅና በማገድ በወሰዷቸው ዕርምጃዎች፣ የአገር ውስጥም ሆኑ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተፅዕኖ እንደደረሰባቸው ገልጿል።
የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችም ለሚዲያ ምኅዳሩ መጥበብ እንደ ዋነኛ ምክንያት አድርጎ የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ በፌዴራልና በትግራይ ክልል ባለሥልጣናት መካከል ያለው ውጥረትና በክልሉ አመራር መዋቅሮች ውስጥ ያለው ውስጣዊ ክፍፍል ለነፃ ዘገባዎች የሚሰጠው ቦታ እንዲጠብ ማድረጉንም አመላክቷል።
ከዚህ አኳያ የሚዲያ ዘገባዎች ለሕዝብ ተጠያቂነት ወይም ለሲቪክ ውይይት እንደሚያገለግሉ ተደርገው ከመታየት ይልቅ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፀጥታና ከደኅንነት ጉዳዮች ጋር ተያይዘው እየተቃኙ ይገኛሉ ያለው ድርጅቱ፣ ይህ አመለካከትም መረጃ የማግኘት ዕድልንና ጋዜጠኞች በነፃነት መሥራታቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ጠቅሷል።
የቮክስ ትግራይ ግኝቶች ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በክልሉ የሚዲያ ምኅዳር ውስጥ ‹‹ከባድ መበላሸት›› ማጋጠሙን የሚያሳዩ ሲሆን፣ በተለይም እ.ኤ.አ. ከ2026 መጀመሪያ አንስቶ ሁኔታው እየተባባሰ መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡ ሪፖርቱ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ጫናዎች ያላቸው ዛቻዎች፣ ያላግባብ መታሰር፣ ክትትል፣ ስም የማጥፋት ዘመቻዎች፣ አካላዊ ጥቃቶችና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንም እንደሚያካትቱ ገልጿል።
በተለይ ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከልም በትግራይ ክልል በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት የታሰሩትን እንደ ሸዊት ገብረ እግዚአብሔርና ዮሐንስ በርኸ ያሉ ጋዜጠኞችን ለአብነት ጠቅሶ፣ ሁለቱም ቆይተው በዋስ መለቀቃቸውን ጠቅሷል።
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ጋዜጠኞቹን ለረዥም ጊዜ ከሚቆይ እስራት የተወሰነ የሕግ ከለላ እንዲኖራቸው ማድረጋቸውን ገልጾ፣ ፍርድ ቤቶች አሁንም የጋዜጠኞችን ደኅንነት ከማስጠበቅ አንፃር ያላቸው ሚና ወሳኝ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብሏል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቱ ሰነድ እንደሚያብራራው፣ በትግራይ ክልል በመስክ ላይ ተገኝቶ የመዘገብ ሁኔታዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ አደገኛ እየሆኑ ናቸው። በአንድ ክስተት በዓዲ ጉዶም በሥራ ላይ በነበሩ ጋዜጠኞች ላይ ታጣቂዎች ተኩስ መክፈታቸውንና በጥቃቱም አንድ የአካባቢው ቃለ መጠይቅ ተደራጊ መገደሉን፣ ጋዜጠኞቹም አካባቢውን ጥለው ለመሸሽ መገደዳቸውን አብራርቷል።
እነዚህን ከመሳሰሉ የተናጠል ክስተቶች ባለፈ፣ ሪፖርቱ በግልም ሆነ በመንግሥት የሚዲያ ተቋማት ላይ የሚደርሱ መዋቅራዊ ጫናዎችን ይጠቁማል። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ሰባት የግል ሚዲያዎችና ስምንት ከሚዲያዎቹ ጋር ሲሠሩ የነበሩ ጋዜጠኞች ክልሉን ጥለው መውጣታቸውን አስረድተዋል።
የትግራይ ቴሌቪዥንና ድምፂ ወያነን ጨምሮ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሠራተኞች መልቀቅን፣ የኤዲቶሪያል ጫናንና የኢኮኖሚ ጫናዎችን ጨምሮ ውስጣዊ ፈተናዎች እያጋጠሟቸው መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2026 መጀመሪያ አንስቶ ቢያንስ 23 የሚዲያ ባለሙያዎች ሥራቸውን ለቀው መሄዳቸውም ተጠቅሷል።
በክልሉ የሚድያ ምኅዳር ውስጥ የኤዲቶሪያል ነፃነት እንደ ዋና ጉዳይ ተነስቷል፡፡ በዜና ክፍል ውሳኔዎችና ይዘቶች ላይ ቀጥተኛ የፖለቲካ ተፅዕኖ ስለመኖሩ የገለጸው ሪፖርቱ፣ እንዲህ ያሉ ጫናዎችን የተቃወሙ ጋዜጠኞች ከሥራ መታገድን ጨምሮ የተለያዩ ዕርምጃዎች እንደተወሰዱባቸውም አመልክቷል።
የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላምና ፀጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴኦዬ (አምባሳደር) የፕሬስ ነፃነት ቀንን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትና መረጃ የማግኘት መብት ‹‹ለዴሞክራሲ፣ ለሰላም ግንባታና ግጭትን ለመከላከል መሠረታዊ ምሰሶዎች›› መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል። በመግለጫቸው አክለውም፣ ‹‹ነፃና ኃላፊነት የሚሰማው ፕሬስ የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለማጋለጥና ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ውይይትን ለማሳደግ ወሳኝ ነው፤›› ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ወቅታዊ ሁኔታዎችን በቴክኖሎጂ ለውጥ (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ) በፍጥነት እየተቀየረ ካለው የሚዲያ ገጽታ አንፃር ይቃኛል። እነዚህ ዕድገቶች መረጃ የማግኘት ዕድልን ቢያሰፉና የተለያዩ ድምፆችን ቢያጎሉም፣ በተቃራኒው የተሳሳቱ መረጃዎች (Misinformation)፣ ሆን ተብሎ የሚሠራጩ የሐሰት መረጃዎች (Disinformation) እና የጥላቻ ንግግር የመሳሰሉ ሥጋቶችን ይዘው መጥተዋል በማለት እነዚህም በአኅጉሪቱ ለሚገኙ ማኅበራዊ ትስስሮች፣ ለዴሞክራሲያዊ ሒደቶችና ለሰላምና ፀጥታ ሥጋት ናቸው ይላል።
በዚህ ሰፊ አኅጉራዊ ማዕቀፍ ውስጥ ኅብረቱ ተቋማዊ ምላሾችንም ጠቁሟል። መግለጫው ይህን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ በፖለቲካ ጉዳዮች፣ በሰላምና በፀጥታ ዲፓርትመንት (Department of Political Affairs, Peace and Security) በኩል የሚመራውንና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የሚያስችል ‹‹ሁለንተናዊ፣ ቅድመ መከላከል ላይ ያተኮረና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ›› አሠራርን ያጠቃልላል። ይህ አሠራር አስተዳደርን፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያንና ሰብዓዊ መብቶችን የሚያስተሳስር ነው ተብሏል። በተጨማሪም በአባል አገሮች፣ በሚዲያ አካላትና በሲቪል ማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ የጥላቻ ንግግር ምላሽ ማስተባበሪያ አኅጉራዊ መድረክ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ሲልም ያስረዳል።
በተመሳሳይ ጊዜ የአፍሪካ ኅብረት ዘላቂ ለሆኑ መዋቅራዊ ሥጋቶች፣ በተለይም በጋዜጠኞች ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት አለመኖር (Impunity) ትኩረት ሰጥቷል። ይህ የተጠያቂነት ማጣት ‹‹በአፍሪካ ለፕሬስ ነፃነት ትልቁ ሥጋት›› ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን በመግለጽ፣ በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ ጠንካራ የደኅንነት አጠባበቅ ዘዴዎች እንዲኖሩና ፍትሕ እንዲሰፍን ጥሪ አቅርቧል።
