- ባለፈው በጀት ዓመት ከ170 ተቋማት 112 ያህሉ በኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ ዕርምጃ አልወሰዱም ተብሏል
የገንዘብ ሚኒስቴር በ2018 ዓ.ም. ተጨማሪ በጀት የጠየቁ መሥሪያ ቤቶች በመኖራቸው ከፍተኛ የወጪ ፍላጎት እንደነበር፣ ነገር ግን ተጨማሪ በጀት ወጪ የተደረገው በበጀት ዓመቱ ተግባራዊ ለተደረገው የደመወዝ ጭማሪ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ይህን የገለጹት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ሲገመግም መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያጋጠመውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ከግምጃ ቤት ሰነድና ከቦንድ ሽያጭ፣ በአገር ውስጥ ብድር በመውሰድ መሸፈኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከብሔራዊ ባንክ የቀጥታ ብድር እንዳልተወሰደ ለቋሚ ኮሚቴው የመሥሪያ ቤታቸውን ሪፖርት ሲያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ተጨማሪ በጀት የጠየቁ መሥሪያ ቤቶች መኖራቸውንና አብዛኞቹ በተፈቀደላቸው በጀት በማብቃቃትና በቁጠባ እንዲጠቀሙ በማድረግ የዋጋ ንረት እንዳይባባስ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን የሌሎችን ወጪዎች ጫና በመቀነስ በበጀት ዓመቱ ተግባራዊ የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ላይ ብዙ ገንዘብ እንዲውል መደረጉንና በተቋማት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች፣ በተለይም ከውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ፣ ከነዳጅ ዋጋ ጋር የተገናኙ የመደበኛ ወጪዎች መስተናገዳቸውን አመላክተዋል፡፡
‹‹ነዳጅ ከፍተኛ ድጎማ ተደርጎበታል፣ ለክልሎች ማዳበሪያ መግዣ ዋስትና በመስጠት በተዘዋዋሪ ደጉመናል፣ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ከቀረጥ ነፃ አንዲገቡ ማድረግ ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2018 በጀት ዓመት 1.93 ትሪሊዮን ብር በጀት ማፅደቁን ያስታወሱት አቶ አህመድ፣ በዚህም መሠረት መሥሪያ ቤቶች በጀታቸውን ወዲያው እንዲያውቁ መደረጉን፣ ሆኖም በበጀት ዓመቱ ለደመወዝ ጭማሪና በተለያዩ ምክንያቶች የበጀት እጥረት ላጋጠማቸው ክልሎችና የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች፣ ከመጠባበቂያ ላይ 204.9 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መተላለፉን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ውስጥም አብዛኛው ገንዘብ የተላለፈው ለክልሎች የደመወዝ ጭማሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ተሰብስቦ የነበረው የፌዴራል የታክስ ገቢ 518.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰው፣ በ2018 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 910.7 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ከተገባ በኋላ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ ከዓለም ባንክና ከሌሎች የልማት አጋሮች የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት የሚጠበቁ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት በዘጠኝ ወራት ለበጀት ድጋፍ የሚውል 171 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
From The Reporter Magazine
የወጪ በጀት አፈጻጸምን በሚመለከት ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ አንድ ትሪሊዮን 927.7 ቢሊዮን ብር ምክር ቤቱ ፈቅዶ እንደነበር አስታውሰው፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ደግሞ አንድ ትሪሊዮን 345.1 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ታቅዶ እንደነበር፣ በአፈጻጸሙም አንድ ትሪሊዮን 203 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን ከዕቅዱ አኳያ 89.4 በመቶ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከተከፈለው ውስጥ 615 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 261 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ፣ እንዲሁም 326.6 ቢሊዮን ብር ለክልሎች መዋሉን አስረድተዋል፡፡
የአገሪቱ የውጭ ብድር 33.5 ቢሊዮን ዶላር፣ የአገር ውስጥ ብድር ደግሞ 18.2 ቢሊዮን ዶላር፣ በአጠቃላይ 51.8 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውሰው፣ ይህም የፌዴራል መንግሥትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በበጀት ዓመቱ ለአገር ውስጥና ለውጭ ዕዳ ክፍያ 463.4 ቢሊዮን ብር፣ በዘጠኝ ወራት ደግሞ 277.3 ቢሊዮን ብር ተመድቦ እንደነበርና በዘጠኝ ወራት 226.8 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን፣ ይህም ከዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አኳያ 81 በመቶ፣ ከዓመቱ ዕቅድ አኳያ ደግሞ 48.9 በመቶ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
From The Reporter Magazine
በተጨማሪም በ2017 በጀት ዓመት ከ170 የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ 112 መሥሪያ ቤቶች በኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ ዕርምጃ ባለመውሰዳቸው፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሪፖርቱ መቅረቡንና በተለያየ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በዋና ኦዲተር ኦዲት ሪፖርት መሠረት በ2016 በጀት ዓመት ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት በተሰጣቸው አሥር የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መወሰዱን፣ ሰባት ለሚሆኑት ደግሞ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መጻፉንና በሁለት መሥሪያ ቤቶች የበላይ ኃላፊዎችና በሰባት የፋይናንስ ኃላፊዎች ላይ የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ተናግረዋል፡፡
የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ግምገማ በምክር ቤቱ አዳራሽ ተገኝተው እንዲከታተሉ ሪፖርተርን ጨምሮ ለሌሎች የግል ሚዲያዎችም ጥሪ ተላልፎ የነበር ቢሆንም፣ በሰዓቱ ተገኝተው ወደ ምክር ቤቱ ለመግባት ሲጠይቁ ግን የግል መገናኛ ብዙኃን መከልከላቸው ተነግሯቸዋል፡፡ የክልከላው ምክንያት ምን እንደሆነ የሪፖርተር ባልደረባ ቢጠይቅም እንደማይታወቅ ተነግሮታል፡፡
