- ዛሬ ደግሞ ምንድነው ያሰናዳሽው?
- ለየት ያለ ቆንጆ እራት ነው።
- እንዴ?
- ምነው ምን ሆንክ?
- ለምንድነው አትክልት የበዛው?
- አልሰማህም እንዴ?
- ምን?
- መንግሥት ራሱ መቅመስ አለበት ሲባል።
- ምኑን?
- ያለማውን ነዋ።
- ታዲያ ይኼ ምንድነው?
- ትሩፋት ነው።
- የምን ትሩፉት?
- የሌማት።
- ምን?
- አዎ። መንግሥት የራሱን የልማት ውጤት ቀምሶ ማኅበረሰብን ማበረታታት የለበትም ትላለህ?
- አለበት።
- ስለዚህ እኔም ይኼ ነገር ከቤት መጀመር አለበት ብዬ…
- እ… ምን አደርግሽ?
- መሪ ቃል አወጥቼ እራት አሰናዳሁ።
- መሪ ቃል?
- አዎ።
- ምን የሚል መሪ ቃል?
- ‹‹ከሌማት ትሩፋት ለሚኒስትሩ እራት›› የሚል መሪ ቃል።
- እየቀለድሽ ነው?
- ኧረ በፍፁም። የምሬን ነው ቆንጆ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
- ተይ …ተይ እሱን ነገር እንዳታደርጊልኝ።
- የቱን?
- ቀይ ሥሩን።
- ለምን?
- ቀይ ሥር እንደማልወድ ዘነጋሽ እንዴ?
- አልዘነጋሁትም።
- ታዲያ?
- ከዚህ በኋላ ግን መብላት አለብህ።
- ለምን?
- ትክክል አይመጣማ?
- እንዴት?
- አንተኑ ልጠይቅህ?
- እ…?
- ቀይ ባህርን በደፈርንበት ዘመን ቀይ ሥር አልባላም ማለት ትክልል ነው?
- እየቀለድሽ ነው?
- ኧረ በፍፁም። ይልቅ እየበላህ?
- ከየቱ ልብላ?
- ከሁሉም።
[ክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጃቸው ከሆነች አንድ ባለሀብት የተደወለላቸውን ስልክ አንስተው በኮሪደር ልማቱ ላይ የምታቀርበውን ቅሬታ እየሰሙ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር እኔ የኮሪደር ልማቱ ላይ ተቃውሞም ሆነ ጥላቻ እንደሌለኝ የሚያውቁ ይመስለኛል?
- በዚህ እንኳን አትታሚም።
- የእውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር።
- አውቃለሁ ስልሽ?
- ለኮሪደል ልማቱ አዋጡ ሲባልም ያለማመንታት አምስት ሚሊዮን ብር ነው ያዋጣሁት።
- ይህንን እንኳን አልነገርሽኝም ነበር። ቢሆንም ጥሩ ነው ያደረግሽው።
- አሁን ግን ልማቱ መስመር እየሳተ ነው። እየሆነ ያለው ነገር ግን ትክልል አይደለም።
- ምን ተፈጠረ። ያንን ሕንፃሽን ይነካዋል ተባለ እንዴ?
- እሱንማ እንዴት ሆኖ? አምስት ሚሊዮን ብር ያዋጣሁት ለምን ሆነ እና?
- ታዲያ ልማቱ መስመር እየሳተ ነው ያልሽው ለምንድነው?
- ከሕንፃው በላይ ገቢ የማገኝበትን ቤት ይፈርሳል ብለውኝ ነዋ?
- የትኛው ቤት?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር እረሱት እንዴ?
- ምን ላድርግ… የአንቺ ንብረቶች በሁሉም አካባቢ ናቸው?
- ያንን ቤት ነዋ ይፈርሳል ያሉት ክቡር ሚኒስትር…?
- የቱን?
- በእረፍት ጊዜ የሚያዘወትሩበትን ማለቴ ነው…?
- ቆይ አጠገብሽ ሰው አለ?
- የለም ክቡር ሚኒስትር።
- በይ ቀስ ብለሽ ንገሪኝ። የትኛውን ቤት ነው?
- ማሳጅ ቤቱን!
- አትይኝም?
- ስነግርዎት?
- እሱን ከነኩትማ…
- እ…?
- አንቺ እንዳልሽው ልማቱ በትክክል መስመር እየሳተ ነው።
- ይኸው እጄ ላይ ደብዳቤ ይዤ እኮ ነው ወደ እርስዎ የደወልኩት።
- የምን ደብዳቤ?
- ቤቱ በልማት ምክንያት እንደሚነሳ የሚገልጽ ደብዳቤ ሰጥተውኝ ነው የሄዱት።
- ቆይ የሚመለከታቸውን አነጋግሬ እደውላለሁ።
- ማንን ነው የሚያነጋግሩት ክቡር ሚኒስትር?
- የፕሮጀክት ኃላፊውን።
- ኃላፊውን በቀጥታ ማነጋገር ይሻላል?
- አታስቢ በዘዴ አናግረዋለሁ።
- ምን ብለው ?
- ባሀለብቷ ለኮሪደር ልማቱ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓንና ቤቱ ደግሞ…
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር…?
- ምነው ደነገጥሽ?
- ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚመጡበት ሚስጥራዊ ቤት ስለሆነ ማሳጅ ቤት መሆኑ መታወቅ የለበትማ ክቡር ሚኒስትር?
- እሱንማ አውቃለሁ።
- ታዲያ ምን ብለው ያናግሩታል?
- የሁላችንም ነው ብዬ እነግረዋለሁ።
- የሁላችሁም ምን?
- ምሽግ!
