የሱዳን ጦርነት እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 15 ቀን 2023 ዓ.ም. በፈነዳ በአንድ ወሩ በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ከተማ የፓን-አፍሪካ ፓርላማ (Pan-African Parliament) ስብሰባ በመደረግ ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ ገና አንድ ወር ያስቆጠረው የሱዳን ጦርነት 875 ሰዎችን ገድሎ በጥቂት ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ስለማፈናቀሉ የሚነገርበት ወቅት ነበር፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ግን በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ላይ የተሰማቸውን ቁጣ ለዲፕሎማሲ ሲሉም መሸሸግ ተቸግረው ነበር የታዩት፡፡


የጦር መኮንኖችም ሆኑ ወታደሮች የጦር መሣሪያ የሚታጠቁት አገር ለመጠበቅና ሰላም ለማስከበር ተብሎ እንጂ ‹‹ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋዊያንን ለመግደል አይደለም›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሩቶ፣ አንድ ወር በተቆጠረው በሱዳን ጦርነት ግን የታዘቡት ከዚህ የተለየ አለመሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ አክለውም ‹‹እነዚያን የሱዳን ጄኔራሎች ይህን ረብ የለሽ ጦርነታቸውን እንዲያቆሙ ልንነግራቸው ይገባል፤›› (We need to tell those generals to stop that nonsense war) ብለው ቃል በቃል ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
በጊዜው የፕሬዚዳንት ሩቶ ንግግር ሁሉንም አስገርሞ ነበር፡፡ አፍሪካ የሚያስፈልጋት ልክ እንደ ፕሬዚዳንት ሩቶ ከጦርነት አልላቀቅ ያሉ ተፋላሚ ኃይሎችን አደብ እንዲገዙ በድፍረት የሚናገር መሪ ነው ተብሎ በዚያ ንግግራቸው ተወድሰውበት ነበር፡፡ እንደተባለውም ሩቶ ከዚያ ወዲህም የሱዳን ጦርነትን በሚመለከት ደፋር አቋሞችን በማንፀባረቅ ገፍተውበት ታይተዋል፡፡ ለአብነት የዛሬ ሁለት ዓመት በጂቡቲ በተደረገው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ማኅበር (ኢጋድ) የሱዳን ሰላም ማፈላለግ ጉባዔ ላይም ይህን ጠንከር ያለ አቋም አንፀባርቀዋል፡፡
በወቅቱ ‹‹ኳርቴት›› ሲሉ የጠሩት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ የጀመሩት የአራትዮሽ ጥረት በኢጋድ በኩል ውጤታማ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን ፊት ለፊት በማገናኘት ተደራድረው ችግሮቻቸውን በሰላም እንዲፈቱ እንደሚደረግም ገልጸው ነበር፡፡
ሩቶ በሁለት ሳምንት ይገናኛሉ ያሏቸው የሱዳን ተፋላሚዎች ግን እስካሁንም አልተገናኙም፡፡ ጦርነቱ አራት ዓመታት የተቆጠሩበት ሲሆን ከ150 ሺሕ በላይ ዜጎችን ሕይወት ቀምቶ፣ ከ12 ሚሊዮን በላይ አፈናቅሎ፣ ከአራት ሚሊዮን በላይ ለስደት ዳርጎና ከ24 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለዕርዳታ ጠባቂነት አጋልጦ በተለያዩ ቦታዎች ግለቱ ሳይበርድ እንደቀጠለ ነው ያለው፡፡
የሱዳን ጦርነት ለረዥም ጊዜ የቀጠለውና አልበርድ ያለው ደግሞ እንደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅና ኤርትራ የመሳሰሉ አገሮች ጣልቃ ገብ እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉ ነው የሚለው ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ኢትዮጵያን ጭምር አንዳንዶች ሲወነጅሉ የሚሰማ ሲሆን ከዚህ ባለፈም ቻድ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን የመሳሰሉ የቀጣናው አገሮች ጦርነቱን በተመለከተ የሚከተሉት አቋም በጦርነቱ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ይነገራል፡፡
From The Reporter Magazine
ለአብነት በቅርቡ የሱዳን ጦር ኃይል ከአንድም ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ ከኢትዮጵያ የተነሱ ድሮኖች ጥቃት እንዳደረሱበት ውንጀላ ማሰማቱ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ የድሮኖቹን አምራች መለያ ለማፈላለግ የሞከሩ ወታደራዊ የመረጃ አውታሮች በቱርኪዬና በዓረብ ኤምሬትስ የተሠሩ ሆነው እንደተገኙ አረጋግጠዋል፡፡ በሱዳን ጦርነት በየመን፣ በሰርቢያ፣ በሩሲያ፣ በቱርኪዬ፣ በቻይና፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ብቻ ሳይሆን በኢራን ጭምር የተመረቱ ድሮኖችና የጦር መሣሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ማረጋገጣቸውን ዋና ዋና የሚባሉ ዓለም አቀፍ መረጃ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የተመድ ፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የዳርፉር ጦርነት በተቀሰቀሰ ማግሥት እ.ኤ.አ. በ2004 ነበር በሱዳን ላይ ጠንካራ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የጣለው፡፡ የአሁኑ የሱዳን ጦርነት ከተጀመረ በኋላም የመሣሪያ ማዕቀብ በተፋላሚ ኃይሎች ላይ ተጠናክሮ መቀጠሉ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የሚዋጉበት አላጡም፣ ጦርነቱም በቀላሉ አልቆመም ነው የሚባለው፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በቅርብም በሩቅም ያሉ የውጭ መንግሥታት የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን ጎራ ለይተው በመደገፋቸው መሆኑ ይነገራል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለሱዳን ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የተፈጠሩ ‹‹ኳድ›› የሚባለው ስብስብ ውስጥ ያሉም ሆነ፣ ‹‹ኳርቴት›› በመባል የሚጠሩት ስብስብ አንዳንድ አገሮች በሱዳን ግጭት አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው የሚል ክስ ተደጋግሞ ይሰማል፡፡
From The Reporter Magazine
አንዳንድ አገሮች ደግሞ ከሱዳን ጦር ወይም ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጎራ ለይተው አንዱን ቡድን በማስታጠቅና በመደገፍ ብቻ እንደማይወሰኑ ነው አንዳንድ ሪፖርቶች የሚያስረዱት፡፡
የቱርኪዬን ጉዳይ ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚያነሳው የዋሽንግተን ፖስት አንድ የምርመራ ዘገባ ባይካር የተባለው የባይራክታር ቲቢ2 ድሮን አምራች ኩባንያ፣ ከሱዳን ጦር ሠራዊት ጋር አምና የመሣሪያ ግዥ ስምምነት መፈራረሙን ነው፡፡ ሌላው የቱርኪዬ መሣሪያ አምራች አርካ ዲፌንስ የተባለው ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደግሞ በተመሳሳይ ወቅት ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ከጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) ወንድም ከአልጎኒ ሃምዳን ዳጋሎ ሙሳ ጋር ስለመሣሪያ ሽያጭ አደረጉት የተባለው ዝርዝር የስልክ ልውውጥ መጋለጡን ነው ዘገባው ያረጋገጠው፡፡
ሩሲያ ከሱዳን ጦርነት መጀመር ቀደም ብሎ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ስታስታጥቅና ስታሠለጥን እንደቆየች፣ ጦርነቱ ሲጀምርም በዚሁ ሚናዋ መቀጠሏ ይነገራል፡፡ በሒደት ግን የሱዳን ሠራዊት የዩክሬን ጦርን ዕገዛ ፍለጋ ሊሄድ ይችላል ብላ አሠላለፍ እንደቀየረች፣ አሁን ደግሞ የሱዳን ጦር የመሣሪያና ሥልጠና አጋር እንደሆነች አንዳንድ የመረጃ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
የሱዳን ጦርነት ከመነሻው ብቻ ሳይሆን በሒደት የተፈጠሩ ለውጦችን ተከትሎ የውጭ አገሮች ጣልቃ ገብነት ሚናን እየቀያየረ እንደመጣ ተቺዎች ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶች ከመነሻው የሱዳን ሠራዊትን ወይም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የደገፉትን ጎራ በመደገፍ ሲቀጥሉ፣ ሌሎች ግን ጎራ መቀየራቸው ወይም ከአደራዳሪነት ወደ አንድ ጎራ ደጋፊነት መሸጋገራቸውን ይጠቁማሉ፡፡
በሁለቱም የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ላይ ዓለም አቀፍ የመሣሪያ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በውጭ ኃይሎች መሣሪያና ገንዘብ ድጋፍ ጥገኛ ናቸው፡፡ ሁለቱም የሱዳንን ጦርነት ለማስቀጠል የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት የውጭ ኃይሎችን ድጋፍና ወዳጅነት ይፈልጉታል፡፡ ሁለቱም የሱዳንን ወርቅ ሸጠው ነው ጦርነቱን የሚደጉሙት ይባላል፡፡
ሆርን ሪቪው ድረ ገጽ ከሰሞኑ ‹‹Sudan’s War and the Imperative of Ethiopia’s Re-engagement›› በሚል ርዕስ በሱዳን ጦርነት ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚገባውን ሚና የተመለከተ የፖሊሲ መግለጫ (ፖሊሲ ብሪፍ) ሰነድ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡
ከሩቅም ከቅርብም እየተጠራሩ በሱዳን ጦርነት እጃቸውን የሚከቱ አገሮች ጦርነቱ አንድም የጂኦ ፖለቲካ ግብግብ ማድረጊያ ሜዳቸው፣ ሁለትም ቀጣናዊ ተፅዕኖ ማሳደሪያቸው ሊሆን ይችላል የሚለው ይህ ሰነድ የሱዳን ጦርነት ለኢትዮጵያ ግን ከዚህ ፍፁም በተቃራኒው የብሔራዊ ደኅንነት ፈተና ተደርጎ የሚታይ ጉዳይ መሆኑን በጉልህ ያሰምርበታል፡፡ የሱዳን ጦርነት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ፣ በጋራ ድንበርና በጋራ ሰላምና መረጋጋት ላይ፣ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ የኃይል አሠላለፍ ሚዛን ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያለው አጀንዳ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ኢትዮጵያ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ለሱዳን ሰላምና መረጋጋት ያበረከተችው አስተዋጽኦም አቻ እንደ ሌለው ሰነዱ ይገልጻል፡፡
‹‹ጦርነቱ ከጀመረበት ከአፕሪል 2023 ጀምሮ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ቀውሱን በማረጋጋት ላይ አተኩራ ስትሠራ ነበር፡፡ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አመራር ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር ውጤታማ ሥራም መሥራት ችላለች፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ጠላት ሆነው የቆሙት ግብፅና ኤርትራ ግን ወዲያውኑ ከሱዳን ሠራዊት ጀርባ ተሠልፈው ጦርነቱን ለፀረ ኢትዮጵያ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ሊያደርጉት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሱዳን ጦርነት የሚኖራትን አዎንታዊ የዲፕሎማሲ ሚና ለመወጣት ቀዝቃዛ አካሄድን መከተሏ፣ ከራሷ ፍላጎት ፍፁም የሚቃረን ፍላጎት ይዘው የመጡ ኃይሎች አፍራሽ እንቅስቃሴያቸውን ለመግፋት ዕድል አግኝተዋል፤›› በማለት የሚጠቅሰው የፖሊሲ መግለጫው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን ጉዳይ የዳር ተመልካች ከመሆን አዎንታዊ ዲፕሎማሲያዊ ሚናን ወደ መወጣት እንዲገባ ያሳስባል፡፡
ጦርነቱ በጀመረበት ወቅት ስለሱዳን ጠንከር አድርገው ሲናገሩ፣ ለሱዳን ሠላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ ሲንቀሳቀሱ በመቆየታቸው የሚታወሱት የኬንያ ፕሬዚዳንት ሩቶ በሒደት ግን ከዚህ በተቃራኒው በሆነ አቋም መወንጀል መጀመራቸው አሁን በመነገር ላይ ነው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት እ.ኤ.አ. በየካቲት 2025 በናይሮቢ ከተማ በኬንያታ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ማዕከል የሱዳን ተቃዋሚዎች ተሰብስበው የጋራ የሽግግር ቻርተር መፈራረማቸውና አዲስ አገር መሥርተናል ማለታቸው፣ በኬንያና በመሪዋ ላይ ከባድ ቁጣ አስነስቶ ነበር፡፡ የሱዳን ሽግግር መንግሥትን የሚመራው የሱዳን ጦር ኃይል ይህን ስብሰባ ተከትሎ በኬንያ ላይ ከባድ ውግዘት አሰምቷል፡፡ ኬንያ ከተቃዋሚው ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ተሠልፋ ሱዳንን በማበጣበጥና በመከፋፈል ላይ ትገኛለች በማለትም ወንጅሏል፡፡ የሱዳንን ሉዓላዊነት የሚጋፋ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ኬንያንም ሆነች ሌሎች አገሮችን በዝምታ እንደማይመለከት በጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ጠንከር ያለ ዛቻ አሰምቶም ነበር፡፡
የኬንያ ፕሬዚዳንት ሩቶ ኬንያ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትመራ ነፃ አገር መሆኗን በመጠቆም የሱዳን ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የሌሎች አገሮች ተቃዋሚዎችም በናይሮቢ ቢገናኙም ሆነ ቢሰባሰቡ የኬንያ መንግሥት ደግፏቸው ነው ለማለት እንደማያበቃ በወቅቱ የተከሰሱበትን ጉዳይ አስተባብለው ነበር፡፡ እሳቸው የሚመሩት መንግሥት የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች እንዲታረቁና በድርድር ችግራቸውን እንዲፈቱ ጠንካራ ፍላጎት ያለው መሆኑን በመጥቀስ፣ ኬንያ በሱዳን ጉዳይ ገለልተኛ የአደራዳሪነት ሚናን መጫወት እንደምትመርጥ ተከራክረው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ይህን ያልተቀበሉ አንዳንድ ወገኖች የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ በሰሜን ከተባለው ኃይል ጋር አጋርነት እንዲፈጥር ኬንያ መደገፏን ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ የኬንያ አየር ክልልም ሆነ የኬንያ አውሮፕላን ማረፊያዎች ለሱዳን ተፋላሚ ቡድኖች ስንቅና ትጥቅ ማስተላለፊያ እየሆኑ ነው የሚል ክስም አሰምተዋል፡፡ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የሚነሱ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላን በረራዎች በኬንያ አየር ክልል አልፈው ወይም በኬንያ አየር ማረፊያዎች ትራንዚት አድርገው የሱዳን ተቃዋሚዎች ወደ ያዟቸው ግዛቶች እንደሚሸጋገሩም ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ግንቦት 2025 አንድ ኬንያዊ ፓይለት በዳርፉር ሲያርፍ ተገደለ መባሉን እንደ ማስረጃ በመጥቀስ፣ ያበረው የነበረው አውሮፕላንም አንድ የኬንያ ድርጅት ንብረት መሆኑን ጭምር በመግለጽ የሩቶ መንግሥት ከሱዳን ተቃዋሚዎች ጎን መሠለፉን የዘገቡ ነበሩ፡፡ የሩቶ መንግሥት ከዚህ በተጨማሪም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አጋር ከሆነችው ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሚስጥራዊ ስምምነት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር መቀበሉን፣ የሕዝብ ቁጣ ላስነሳበት የኑሮ ውድነት መደጎሚያ እንዳዋለው እንደደረሱበት በመጥቀስ ጭምር የኬንያና የሌሎች አገሮች መረጃ ምንጮች ጉዳዩን ሲያራግቡት ቆይተዋል፡፡
ይህን ክስ ደግሞ የኬንያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (Kenya Human Rights Commission) መግለጫ በማውጣት አጠናክሮታል፡፡ የኬንያ መንግሥት በሱዳን ዳርፉር ግዛት በተፈጸመ የዘር ማጥፋት ዘመቻ የሚወነጀልና አሁን በቀጠለው የሱዳን ጦርነት ውስጥም በንፁኃን ላይ ለሚካሄዱ ግድያዎች በተጠያቂነት ለሚጠቀስ ተፋላሚ ቡድን ድጋፍ እያደረገ ነው በማለት ኮሚሽኑ ወንጅሏል፡፡ የኬንያ የሰብዓዊ መብት መርህም ሆነ ሕግና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መንግሥት ይህንን እንዳያደርግ የሚከለክሉ መሆናቸውን በመጠቆም፣ የሩቶ አስተዳደር የሱዳን ተቃዋሚዎችን ከመርዳት እንዲቆጠብ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
ይህ ሁሉ ቢባልም ግን ኬንያ ከዚያ ወዲህም የሱዳን ተቃዋሚ ኃይሎችን ማስተናገድ ቀጥላለች የሚለው ዜና አልቆመም፡፡ ፕሬዚዳንት ሩቶ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ጄኔራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ)ን ተቀብለው አስተናገዱ መባሉ ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል፡፡
ከሰሞኑ እ.ኤ.አ. ግንቦት 14 ፕሬዚዳንት ሩቶ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ከሆኑት ሄሜቲ ጋር ተገናኝተዋል፣ እንዲሁም ቡድኑን እየደገፉት ነው ተብሎ ለቀረበባቸው ክስ በሰጡት መልስ ሐሰተኛ ዜና መሆኑን ጠቅሰው አጣጥለውታል፡፡ ‹‹ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጎን ተሠልፋችኋል የሚለው ነጭ ውሸት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ክሶች ከየአቅጣጫው ይመጣሉ፣ ነገር ግን መሠረት የላቸውም፡፡ በግሌ ስለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉም ሆነ ስለሱዳን ጦር ያለኝ አመለካከት ተመሳሳይ ነው፡፡ አገራቸውን እየቦጫጨቋት ነው የሚገኙት፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡
ከስድስት ወራት ቀደም ብሎ ለዶቼ ቬሌ እንግሊዝኛ ዝግጅት ክፍል የሱዳን ጦርነት የውጭ አገሮችን ለምን እንደሚስብ ማብራሪያ የሰጡት ሃሚድ ካላፋላ የተባሉ፣ በማንችስተር ዩኒቨርሲቲ የሱዳን ፖሊሲና ሪሰርች ማዕከል ተመራማሪ ይህን ተናግረው ነበር፡፡
አንደኛው መነሻ፣ ‹‹ሱዳን ወርቅን ጨምሮ ብዙ የተፈጥሮ ሀብት ያላት አገር ስለሆነች ነው የውጭ መንግሥታት የሚሳቡት፡፡ የሱዳን ሀብትን ለመቀራመት ነው የውጭ ኃይሎች ጎራ ለይተው ከሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ጀርባ የሚሠለፉት፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ‹‹በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመሠረተ ጠንካራ መንግሥት በሱዳን እንዲፈጠር የማይፈልጉ አገሮች አሉ፤›› ብለዋል፡፡ ሦስተኛውን ነጥብ ሲጠቅሱ፣ ‹‹አንዳንድ አገሮች የሃይማኖት የርዕዮተ ዓለምን መሠረት በማድረግ በሱዳን ካሉ እስላማዊ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር መፍጠርን ይፈልጋሉ፡፡ ሌሎች መንግሥታት ደግሞ የሃይማኖት ኃይሎችን በሱዳን መብቀል ፈጽሞ ስለማይፈልጉ ከእነሱ በተቃራኒ የቆሙ ኃይሎችን ይደግፋሉ፤›› በማለት፣ የሃይማኖት ፖለቲካም አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አራተኛውና ወሳኙ ያሉትን ነጥብ ሲገልጹ፣ ‹‹የውጭ ኃይሎችን ወደ ሱዳን የሚስበው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የግብፅና የሱዳን ጦር ኃይሎች ለረዥም ጊዜ ፈጥረውት የቆዩት ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ነው፤›› ሲሉ ጠንከር ያለ ሐሳብ አንስተዋል፡፡
ተመራማሪው ያነሷቸው እነዚህ መሠረታዊ አመክንዮዎች የውጭ መንግሥታትን በሱዳን ጦርነት እንዲዘፈቁ ወይም እጃቸውን እንዲነክሩ የሚስቡ መነሻዎች መሆናቸውን፣ ስለሱዳን ጦርነት የሚያጠኑ በርካታ ምሁራን ሲስማሙባቸው ይታያል፡፡ ተመራማሪው ባያነሱትም የሱዳን ጂኦግራፊያዊ ተፈጥሮና አቀማመጥም ሌላው የውጭ መንግሥታትን ወደ ጦርነቱ የሚጎትታቸው ምክንያት እንደሆነ በአንዳንድ ወገኖች ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡
ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከግብፅ፣ ከሊቢያ፣ ከቻድ፣ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና ከደቡብ ሱዳን ጋር የምትጎራበተው ሱዳን በሥልታዊ ጠቀሜታው በዓለም ጎልቶ የሚጠቀሰው የቀይ ባህርን የምትጎራበት አገርም ናት፡፡ በቆዳ ስፋት በዓለም 15ኛ፣ በአፍሪካ ሦስተኛ ትልቅ አገር የምትባለዋ ሱዳን ብዙ የውጭ መንግሥታትን ዓይን የሚስብ ሰፊ የተንጣለለ የእርሻ መሬት የያዘችና ታላቁ የዓባይ ወንዝም የሚያቆራርጥባት አገር ናት፡፡ ሱዳን የአፍሪካ ቀንድ ከማዕከላዊው የአፍሪካ ክፍል፣ የምሥራቅ አፍሪካን ከሰሜናዊ አፍሪካ ጋር የምታስተሳስር ምድር ብቻ ሳትሆን የሳህል ቀጣናን ከመካከለኛው የአፍሪካ ክልል ጋር የምታገናኝ መሸጋገሪያ ድልድይም ናት፡፡ ይህ ሁሉ መነሻ ምክንያት የውጭ መንግሥታትን ከሩቅም ከቅርብም ወደ ሱዳን የሚጎትት እንደሆነ ይነገራል፡፡
አራት ዓመታት ያስቆጠረው የሱዳን ጦርነት በዚህ ሁሉ መነሻ ብዙ አገሮች እጃቸውን እንዲከቱ ማድረጉ የሚነገር ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ሱዳን ያሳለፈችው የታሪክ ውጣ ውረድም ቢሆን የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝ መሆኑ ነው የሚነሳው፡፡ ሱዳን በግብፆች፣ በዓረቦች፣ በኦቶማን ቱርኮችና በእንግሊዞች በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ስትወረር መቆየቷ ለዚህ አንድ መነሻ ተደርጎ ይወሳል፡፡ በሌላ በኩል አገሪቱ ከቅኝ ተገዥነት ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮም ቢሆን፣ ያሳለፈችው የፖለቲካ ምስቅልቅልና ግጭት ለረዥም ጊዜ አለመስከኑም ለውጭ ጣልቃ ገብነት ያጋለጣት ታሪክ መሆኑ ይነገራል፡፡
በቅርብ ዓመታት እንዲሁም ወራት ኬንያ ብቻ ሳትሆን እንደ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን ያሉ አገሮችም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ወደ መቀበል መሸጋገራቸው እየተነገረ ነው፡፡ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉና የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ በሰሜን የተባለው ኃይል በጋራ ሆነው አዲስ አገርና መንግሥት ለመፍጠር መፈለጋቸውን፣ የቀጣናው አገሮች ተቀብለውታል እየተባለ ነው፡፡ ሱዳን ጦርነቱ የማይቆም ከሆነ ለሁለት መከፈሏ የማይቀር መሆኑን ኬንያም ሆነች ኡጋንዳና ሌሎች ተቀብለውታል ይባላል፡፡ የኬንያ መንግሥትም ሆነ የኡጋንዳ መንግሥት ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች ይህንኑ ያገናዘበ መሆኑ ይወሳል፡፡ ልክ እንደ ፕሬዚዳንት ሩቶ ሁሉ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ሔሜቲን በይፋና በሚስጥር ተቀብለው ያስተናግዳሉ የሚሉ ሪፖርቶች ተደጋግመው ሲወጡ ይሰማል፡፡ ኡጋንዳ ከዚህ በተጨማሪም የሱዳን ስደተኞችን ጨምሮ ከቀጣናው አገሮች ወደ ሁለት ሚሊዮን ስደተኞች ተቀብላ ታስተናግዳለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሱዳን ጦርነት ለደቡብ ሱዳን ጭምር ተጨማሪ አለመረጋጋትና የቀውስ ምንጭ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከደቡብ ሱዳን ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላት ኡጋንዳ ለዚህና ለሌሎች አሉኝ ለምትላቸው ጥቅሞች መጠበቅ ስትል የሱዳን ጦርነት እንዲቆም ትፈልጋለች ነው የሚባለው፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የያዙትን አካባቢ ይዘው እንዲያስተዳድሩ ትመርጣለችም ይባላል፡፡ ለዚህ ሲባልም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ዕውቅና ሰጥቶ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማድረግን አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኘችው በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡
የሆርን ሪቪው የፖሊሲ መግለጫ ሰነድ በበኩሉ ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚገባውን ሚና እንዲጠናከር ነው የሚያሳስበው፡፡ ከሩቅ የመጡ አገሮች ጭምር በሱዳን ግጭት ገብተው ሲንቦራጨቁና ግጭቱን ሲያባብሱ ኢትዮጵያ ሱዳንን ተጎራብታ በዝምታ መቀመጥ እንደሌለባት ነው የፖሊሲ መግለጫው የሚጠቁመው፡፡ እንደ ሰነዱ ከሆነ የኢትዮጵያ የእስካሁን ዝምታና ዳር መቆም ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ኢትዮጵያ የሱዳን ጦርነትን ለማስቆም ከማንም የተሻለ ስትራቴጂካዊ አቅም አላት፡፡ የሱዳንና የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መፃኢ ዕድልም ላይነጣጠል ሆኖ የተጋመደ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ከጦርነቱ ራሷን አርቃ የቆየችበትን መንገድ በመተው ትርጉም ያለው ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ወደ መፍጠር ብትገባ ለሁለቱ አገሮች፣ ለቀጣናውም ሆነ በአጠቃላይ ለመላው ዓለም በጎ ውጤት እንደሚመጣ ነው ሰነዱ የዘረዘረው፡፡
