በምርጫ ማግሥት ሁሉም ነገሮች ወደ መደበኛው የሕይወት እንቅስቃሴ ሊመለሱ የግድ ይላል፡፡ በምርጫ ውጤት ላይ ተመሥርቶ ከሚኖር ውዝግብ አንስቶ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አለመግባባት ከተፈጠረ በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ፣ ከተካሄደው ምርጫ የተገኘው ልምድም ሆነ ትምህርት ለወደፊቱ እንዲያገለግል መሠረት እየተጣለ፣ ሆን ተብለውም ሆነ ባለማወቅ የተፈጠሩ ስህተቶች ካሉም እርማት እንዲደረግባቸው ጥብቅ ማሳሰቢያ እየተሰጠ፣ እንዲሁም ከምንም ነገር በላይ የአገር ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ቅድሚያ እያገኘ መደበኛውን እንቅስቃሴ መጀመር አስፈላጊና ተጠባቂ ጉዳይ ነው፡፡ በሕዝብ ድምፅ ተመርጫለሁ የሚል አካልም ከማንም የበለጠ ኃላፊነት እንዳለበት በመገንዘብ፣ በመላ አገሪቱ ሰላማዊ ድባብ የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡ የምርጫ አንዱ ዓላማ በዴሞክራሲ መሠረት ላይ የተገነባ ሥርዓት እንዲታነፅ ማገዝ በመሆኑ፣ ቢያንስ ሁሉም መብቶችና ነፃነቶች የሚከበሩበት ሥርዓተ መንግሥት ተመሥርቶ በሰላም ለመተዳደር የሚያስችል ዓውድ መፍጠር ይገባል፡፡
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ የሚያኮሩ የበርካታ ማኅበራዊ እሴቶች ባለቤት ነው፡፡ በሁሉም መልክዓ ምድሮች ውስጥ የሚኖረው ሕዝባችን በሕግ አክባሪነቱ አስደናቂ፣ ለሕግና ለሥርዓት ተገዥ፣ ከላይ እስከ ታች ያሉ አስተዳዳሪዎችንም ሆነ ተሿሚዎች የሚያከብር፣ አገሩ ሰላም ውላ እንድታድር ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል የማያንገራግር፣ እርስ በርሱም የሚተሳሰብና የሚደጋገፍ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ በባህላዊ ዳኝነቶችና የሽምግልና ሥርዓቶች የመፍታት ረጅም ታሪክ ያለውና በአጠቃላይ ለአስተዳደር አመቺ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አገሮች በተለያዩ ምክንያቶች አመፅ ለመቀስቀስ ትንንሽ ችግሮች ሳይቀሩ መንስዔ ሲሆኑ ቢታይም፣ በኢትዮጵያ ግን ሕዝቡ ከመጠን ያለፈ ትዕግሥት የሚያሳይ በመሆኑ አስተዳዳሪዎች ሲቸገሩ አይታይም፡፡ ይህንን የመሰለ ጨዋና ታጋሽ ሕዝብ ይዞ በሕግ የበላይነት የሚመራ ሥርዓት ማቆም ፈፅሞ አስቸጋሪ ሊሆን አይገባም፡፡
በተደጋጋሚ ለማስረዳት እንደተሞከረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት ከመጠን በላይ ሰልችቶታል፡፡ በጦርነት ከዕልቂትና ከውድመት በስተቀር የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መንገር ‹‹ለቀባሪው እንደ ማርዳት ይቆጠራል›› እንደሚባለው ስለሚሆን፣ ከንግግር በላይ የግጭት አማራጮች ተዘግተው ሰላም እንዲሰፍን ተግባራዊ ዕርምጃዎች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ በበርካታ አገሮች የነበሩ ጦርነቶች ቆመው ልማት ላይ ትኩረት ሲያደርጉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንዱ ጦርነት ወደ ሌላው እንደ ዋዛ የሚገባባቸውን ምክንያቶች ተረድቶ መፍትሔ ማፍለቅ የግድ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም የግጭቶች መዝገብ ውስጥ ሁሌም ማጣቀሻ እየሆነች መቀጠል አይቻልም፡፡ ለአገር ተስፋ መሆን የሚችሉ ወጣቶች በተለያዩ ጎራዎች ውስጥ ሆነው መፋጀታቸው መቆም አለበት፡፡ ለአገር ልማት መዋል ያለበት ሀብት እሳት ውስጥ እንደሚጣል ወረቀት በከንቱ ተቃጥሎ መውደም የለበትም፡፡
ኢትዮጵያ ከሰሐራ በታች ካሉ አገሮች ጋር ስትነፃፀር አሁንም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያለች አገር ናት፡፡ ድህነት አሁንም የከፋው የኢትዮጵያውያን ጠላት ነው፡፡ ከተወሰኑት በስተቀር በብዙ የአፍሪካ አገሮች በቀን ሦስቴ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ብርቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አሁንም ምግብ ለማግኘት ብርቱ ችግር አለ፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ በርካታ ሚሊዮኖች በምግብ፣ በመጠለያ፣ በአልባሳት፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች እጥረት ይፈተናሉ፡፡ እንዲህ የመሰለውን የመረረ ድህነት መገላገል የሚቻለው በማያባራ ጦርነት ሳይሆን፣ ከዳር እስከ ዳር የልማት ንቅናቄ ለመፍጠር የሚያስችል መግባባት በመፍጠር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከራሷ ተርፈው ለሌሎች ጭምር የሚበቁ በርካታ ፀጋዎች ያሏት አገር ናት፡፡ ከከፋ የምግብ ዕጦት ውስጥ ወጥታ የአፍሪካንም ሆነ የዓለምን ገበያ ማጥለቅለቅ የሚችሉ ምርቶች ማቅረብ አያቅታትም፡፡
ሌላው በብርቱ ሊታሰብበት የሚገባው አገራዊ ችግር ሌብነት ነው፡፡ ሌብነት በርካታ ገጽታዎች ሲኖሩት ተዋንያኑ ደግሞ ኔትወርካቸው ጠንካራና በቀላሉ የማይበገር ነው፡፡ ነገር ግን ሕዝብን አጋሩ አድርጎ የያዘ መንግሥት ሌቦችን አደብ ለማስገዛት አይቸግረውም፡፡ ዋናው የሚያስፈልገው ነገር ቁርጠኝነት ነው፡፡ የመንግሥት መዋቅር ከላይ እስከ ታች ከሌቦች፣ ከዘራፊዎች፣ ከጉቦኞችና ከብልሹ አሠራር አጋፋሪዎች እንዲፀዳ ቁርጠኛ አመራር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሠረት መንቀሳቀስ ሲቻል ማስረጃም ሆነ መረጃ በሚል ሰበብ ጊዜ በማባከን፣ ለሌቦች አመቺ መደላድል እንዲፈጠር ዕድል አይኖርም፡፡ የመንግሥት አሠራር በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ ሲመራ የሙስና ቅርንጫፉ ብቻ ሳይሆን ግንዱ ጭምር ይገነደሳል፡፡ ከዚያ ውጪ በብሔር፣ በሃይማኖትና በተለያዩ የጥቅም ሰንሰለቶች በመተሳሰር ክንዱን ያበረታው የዘረፋ ኃይል ማንም አይበግረውም፡፡ ከሕዝብ ጋር የመቀራረብ ፍላጎት ካለ ግን ውጤቱ በአጭር ጊዜ መታየት ይችላል፡፡
የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ድምፁን ስትማፀኑ የነበራችሁ ፖለቲከኞች፣ ከምንም ነገር በላይ ለሕዝብ ክብር ስጡ፡፡ ሕዝብን ማክበር በቃላት ሽንገላ ሳይሆን በተግባር በሚታይ መልካም ሥራ ነው መገለጽ ያለበት፡፡ ለዚህም ሲባል የሕዝቡ ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ይታሰብበት፡፡ የሚወዳትን አገሩን ከሁሉም ዓይነት ግጭቶችና ጦርነቶች ለማላቀቅ የሚቻለውን ሁሉ አድርጉ፣ ጥረታችሁንም በተግባር አሳዩ፡፡ ይህ የተከበረና ጨዋ ሕዝብ ከአስመራሪው ድህነት ውስጥ እንዲወጣ የሚያግዙ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ንደፉ፡፡ ከዚያም በሕዝቡ ተሳትፎ ወደ ተግባር የሚሸጋገሩበትን አመቺ ሁኔታዎች ፍጠሩ፡፡ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ እንዲሁም ለሕግ የበላይነት መስፈን ፋና ወጊ ሁኑ፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች መከበር አርዓያ ለመሆን ጥረት አድርጉ፡፡ የፖለቲካ ዓላማ ግቡ ሕዝብ ሰላም እንዲያገኝና ድህነት እንዲወገድ ይሁን!
