በአገር ውስጥ መዋዕለ ንዋይ ለሚያፈሱ ባለሀብቶች ምቹ የኢንዱስትሪ ምኅዳር መፍጠር፣ የፋይናንስ አቅርቦት ማመቻቸት፣ የኢንቨስትመንት የመሠረተ ልማት ማነቆዎችን መፍታት ጨምሮ የሚገጥሟችውን ችግሮች በማስተካከል፣ ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች ጥገኝነት መላቀቅ እንደሚያስፈልግ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አሳሰቡ፡፡
ባለሙያዎቹ ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን 23ኛውን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ዓርብ ሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ሲያካሂድ ነው፡፡ በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብረሃም ንጉሤ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ የተለያዩ ድርጅቶች ተወካዮችን ጨምሮ በርካታ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የአሶሴሽኑ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕሮፌሰር) የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዓለም አቀፍ ደረጃ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት በተፈጠረ የሸቀጦች የዋጋ ንረት ዝቅተኛ ገቢ ያለቸው ዜጎች የመግዛት አቅም መፈተኑን፣ በውጭ ብድር ጫና መብዛትና የውጭ ምንዛሪ ላይ አለመረጋጋት አለመታየቱ ፈታኝ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ገቢ ሳይሻሻል ኢኮኖሚው አደገ መባሉ በቂ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት የመጨረሻ ውጤቱ ምርታማና በየዓመቱ ለሥራ ዝግጁ ለሚሆን ሁለት ሚሊዮን አዲስ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የዜጎች ገቢ መጨመር፣ ድህነት መቀነስ፣ የዜጎች ሕይወት መሻሻል ከኢኮኖሚያ መሻሻል በላይ ለማኅበራዊ መረጋጋት፣ አገራዊ መተማመንና ለረዥም ጊዜ የልማት ዕቅድ መሳካት ቁልፍ ጉዳይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ስኬት በኢኮኖሚው ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣትን እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ምርታማ የግብርና ዘርፍና የአየር ንብረት ቀውስን የሚቋቋም፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪና ለዓለም አቀፍ ገበያ ብቁ የሆኑ ምርቶችን እንዲያመርት ማድረግ ተገቢነትን አብራርተዋል፡፡
አገሪቱ ለግሉ ዘርፉ አስተማማኝና ጠንካራ ምኅዳርን መገንባት አለባት ብለው፣ ይህንን ለማደረግ የኢንቨስተመንት ምኅዳሩ አስተማማኝ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ ተገማች የሎጂስቲክስና ጠንካራ የታክስ ሥርዓት፣ ተደራሽ የፋይናንስ አቅርቦት፣ ተፈጻሚ ውሎችን ማረጋገጥ፣ ውጤታማ ተወዳዳሪንትን መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የተወሰኑ የልማት ተግባራትን ከመንግሥት ወደ ግል ማሸጋገር የልማት ሥራ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ያሉት ጣሰው (ፕሮፌሰር)፣ ወጤታማ የሆነ አምራችና ምርትን ለማስገኘት ተወዳዳሪ ገበያና ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠርን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
በአገልግሎት ዘርፉ የሥራ ዕድልን መፍጠር፣ ሴቶችና ወጣቶች የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በሚፈጥረው ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ፣ የፖሊሲ ዝግጅቶችና አፈጻጸሞች በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ ማነቆዎችን የሚፈቱ ሊሆኑ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ የስኬታማ ፖሊሲዎች ውጤት በሁሉም መዋቅሮች ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራሮችን ይፈልጋል ያሉት ጣሰው (ፕሮፌሰር)፣ አንድ ሪፎርም ወጤታማ ነው የሚባለው መግለጫዎች አይደለም ብለዋል፡፡ አገራዊ ሪፎሩሙ በምግብ ራስን መቻልን፣ ሥራ መፍጠርን፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት መጨመርን፣ በከተማና በገጠር፣ እንዲሁም በሴቶችና በወጣቶች መካከል የድህነት ልዩነት መጥበቡን፣ ምርታማ ኢንቨስትመንት መገኘቱን፣ የፋይናንስ ሥርዓቱ መሻሻሉንና የዋጋ ንረት በቀጣይነት መቀንሱን መፈተሽና ይህን ማረጋገጥ የሪፎርሙ አንዱ አካል ሊሆን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
From The Reporter Magazine
ፕሬዚዳንቱ ግጭት ምርታማ ሀብቶችን ያወድማል፣ ገበያን ያምሳል፣ ልዩነትን ይፈጥራል፣ ኢንቨስትመንትን ይቀንሳል፣ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለመሠረተ ልማትና ለምርምር መዋል የሚገባውን ሀብት ይበላል ብለዋል፡፡ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ሽግግር ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በውይይት መፍታትን ይጠይቃል በማለትም አክለዋል፡፡ የኮንፈረንሱ ወጤት ለፖሊሲ አማራጭ የሚቀርቡ ምክረ ሐሳቦች ይገኙበታል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የምርታማነት መሰናክሎች የጠለቁ መዋቅራዊ ችግሮች ናቸው ያሉት ደግሞ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና ናቸው፡፡ ኢኮኖሚው ከውጭ በሚገቡ ማሽነሪዎች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ መሠረታዊ ፍጆታዎችና የኢንዱስትሪ ምርቶች የተሞላ ስለሆነ የግሉ ዘርፍ በውጭ ገበያና በውጭ ምንዛሪ ላይ ጥገኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን ራስን ለማቆየት በሚደረግ የማምረት ሥልት፣ እንዲሁም በውጭ ገበያ ጥገኛ በሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ የግሉ ዘርፍ የሚደግፍ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ክቡር፣ አንድ ኢንቨስትመንት መለካት ያለበት በተመዘገው የኢንቨስተር ቁጥር ሳይሆን ኢንቨስተሩ ባመጣቸው ለውጦች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተገኘው የሥራ ዕድል፣ የምርታማነት አቅምና በተገኘው የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከውጭ የሚገባ ምርትን መተካትና የውጭ ጥገኝነትን ማስቀረት መቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አገሪቱ ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የውጭ ባለሀብት መሳብ እንደምትችል፣ ነገር ግን ዋነኛ ዓላማው ምርታማ ኢንቨስትመንት ማየትና አገራዊ ለውጥ የማምጣቱን ፋይዳ መረዳት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስትመንትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ዘርፎችን መምረጥ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ክቡር፣ ፋብሪካ ስለቆመ ብቻ ኢንዱስትሪያል እንደማያደርጋት ታውቆ ውጤት ለሚጠበቅበት ኢንቨስትመንት መሠረታዊ የሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የተማረ የሰው ኃይል፣ የተመቻቸ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊነትን ጠቁመዋል፡፡ መሬትና የኢንዱስትሪ ፓርክ ሼድ ከማቀረብ ያለፈ ሥራን መሥራት ያሰፈልጋል ብለዋል፡፡ ይህ ሲደረግ በአገር ውስጥ የሚመረተው ምርት ከውጭ የሚመጣውን ሽቀጥ መተካቱን በግልጽ ማየት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡
From The Reporter Magazine
የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ሲወጣ ለኢንቨስተሩ መቅረብ ያለበት ፋይናንስ ካልኖረ ፖሊሲው ብቻውን የፍላጎት መግለጫ ብቻ ይሆናል ብለው፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ከአጭር ጊዜ የማስታገሻ አካሄድ ባለፈ የረዥም ጊዜ ዕቅድን ለማስፈጸምና ለማሳካት የሚረዳ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ማስታወቂያዎች በብዛት አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶችን መሳብ ላይ ያተኮሩ ናችው ያሉት አቶ ክቡር፣ በርካታ ፕሮጀክቶች ሥራ ከጀመሩ በኋላ በሚገጥሟቸው ችግሮች ሳቢያ የሚቆሙ ስለሆነ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድን ከመሳብ ባላፈ ለአገር ያስገኙት ወጤት ሊገመገምና ሊፈተሽ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የኢኮኖሚክስ አሶሴሽን በሚያቀርባቸው የምርምር ሥራዎች ሚኒስቴሩ ለረዥም ጊዜ ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅስው፣ ዓለም አቀፍ ጫናዎች በበዙበት ወቅት ከዚህ ተቋም የሚወጡ ገለልተኛ ጥናቶችና የምርምር ሥራዎች ወሳኝ ናቸው ብለዋል፡፡
በውጭ ምንዛሪ ላይ የተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ በመሠረታዊነት የምንዛሪ ልዩነት በመጥበቡ፣ የውጭ ምንዛሪ ሥርጭት በመሻሻሉ በኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ መተማመን ፈጥሯል ያሉት አቶ አህመድ፣ የውጭ ዕዳ ጫና ላይ መሠረታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የሚያከናውናችው የፖሊሲ ሪፎርሞች ከመገለጫ ባለፈ የረዥም ጊዜ ጠንካራ ኢኮኖሚ መሠረት ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በኢንቨስትመንት ላይ የሚታዩ መሰናክሎችን በመፍታት ተወዳዳሪነትንና ሰፊ ዕድሎችን የመፍጠር ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡