በአማራ ክልል እየተካሄደ ካለው የትጥቅ ትግል በመውጣት ሰላማዊ አማራጭን የተቀላቀሉ ኃይሎች፣ የሚደረግላቸው የመልሶ ማቋቋም፣ የሥልጠናና ሌሎች ድጋፎች በቂ እንዳልሆኑ፣ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት አመራር ገለጹ፡፡
አመራሩ ድጋፎቹ በቂ አለመሆናቸውን የተናገሩት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትጥቅ ትግል ላይ ከሚገኙ አካላት ጋር እያከናወናቸው ስላሉ ተግባራት፣ ሚያዝያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተው ነው፡፡
በመግለጫው ላይ የተገኙት የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ወታደራዊ አስተዳደር መምርያ ኃላፊ ኢያሱ አባተ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ሰላማዊ ትግልን የመረጡ ኃይሎች የሚደረግላቸው የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ትጥቅ ለማስፈታትና መልሶ ለማቋቋም የሚሰጡ ሥልጠናዎችና ሌሎች ድጋፎች በቂ አለመሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ በትንሹ ለ90 ቀናት መሰጠት የነበረበት ሥልጠና ለአንድና ለሁለት ሳምንታት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በሒደቱ እንዲያልፍ የሚደረገው ኃይል ውጊያ ላይ የቆየ በመሆኑ፣ የሞራል ድጋፍ ጭምር እንደሚያስፈልገው ጠቁመው፣ ድጋፉ ለተዋጊ ኃይል ብቻ መሆን እንደሌለበት፣ በውጊያው ከፍተኛ ዋጋ ሲከፍል የነበረው ማኅበረሰብም የዚህ አካል በመሆኑ ሊካተት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚሳተፉ አንዳንድ ኃይሎች ወደ ጫካ ለመግባታቸው ምክንያት የሚያደርጉት የኢኮኖሚ ችግሮችን ጭምር መሆኑንና እነዚህን ችግሮች ከሕልውና ጥያቄዎች ጋር አንድ ላይ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
ወደ ሰላም አማራጭ የመጡ ኃይሎች በኢኮኖሚ ራሳቸውንና አገራቸውን ሊጠቅሙ በሚችሉባቸው ጉዳዮች፣ ጥናቶችን በማድረግ እየሠሩ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በፈንድ የሚገኙ ድጋፎች እዚህ ግቡ የሚባሉ አለመሆናቸውንና አገርን ሊያረጋጋ የሚችል ሆኖ ስላላገኙት፣ በአገር ውስጥ አቅም ማተኮራቸውን አመላክተዋል፡፡
From The Reporter Magazine
አሁንም በክልሉ የትጥቅ ትግል ላይ የሚገኝ አካል መኖሩንና ከእነዚህ ኃይሎች መካከልም በዕውቀትና በተንኮል ለአማራ ሕዝብ ከማይጠቅሙ፣ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የተሠለፈ መኖሩንና ባለማወቅም በዚህ ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በትጥቅ ትግል ላይ ከሚገኙ ኃይሎች ጋር ስላላቸው ግንኙነት የተጠየቁት ኢያሱ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ‹‹መስመራችን አልተቋረጠም›› ብለው፣ ‹‹አይደለም አብረን በቆየነውና ጫካ ባለው ኃይል ውስጥ ቀርቶ፣ በመንግሥትና በታጣቂው ኃይል ውስጥ የተቆረጠ መስመር አለ ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ከአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው የወጣነው፣ ተመሳሳይ ትምህርት ቤቶች፣ ተመሳሳይ ማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ ነው ያለነው፣ ስለዚህ የሚለያየን ነገር የለም፤›› ብለው ‹‹መስመራችን አለ›› በማለት አስረድተዋል፡፡
From The Reporter Magazine
ከሚያዝያ 27 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ የሰላም አማራጭ መርጠው ከመጡ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ጋር ምክክር ሲያደርጉ መቆየታቸውንና በቀጣይ ስለሚኖሩ ሥራዎች መመካከራቸውን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ እያደረጋቸው ከሚገኙ በርካታ ጥረቶች መካከል፣ በትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚገኙ ወገኖች በአገራዊ ምክክር ሒደቶች ላይ እንዲሳተፉ መነጋገርና መመካከር እንደነበር አስታውሰው፣ በዚህም ከትጥቅ ትግል ወጥተው ሰላማዊ እንቅስቃሴን ከመረጡ አካላት ጋር ገንቢ ውይይት በማድረግ ወደ ምክክሩ እንዲመጡ የሚረዳ ሥራ አከናውነናል ብለዋል፡፡
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) በአገራዊ ምክክር ሒደት በአጀንዳነት ቢያዙልን ብለው ያሰቧቸውን 17 የአጀንዳ ነጥቦችን ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን፣ ከሰጡት አጀንዳ በተጨማሪም መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች ማቅረባቸውንና ኮሚሽኑም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በአጀንዳነት ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡
ምክክሩ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳተፈ እንዲሆን እስከ ጉባዔው ቀን ድረስ ጥረቱን ይቀጥላል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በሁሉም አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ታጣቂ አካላት ጋር መሰል ምክክሮችና ውይይቶችን ለማካሄድ ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ በትጥቅ ትግል ላይ ከሚገኙ ኃይሎች ጋር ከዚህ ቀደም ስላደረጋቸው ውይይችና ወደ ምክክሩ መምጣት ስላልቻሉበት ምክንያት ሲጠየቁም፣ በምክክር ሒደቱ ላይ ተፅዕኖ ስለሚያመጣ ሁሉንም ነገር በግልጽ፣ በአደባባይ መግለጽ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
