- ቀጣይነት ያለው የውጭ ምንዛሪ የአቅርቦት ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባ ተመላክቷል
በቅርቡ ይፋ የተደረገው አዲሱ የንግድ ፖሊሲ የገቢ ንግድ ታሪፎችን በማንሳት ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ፣ ከአገሮች ጋር የምታደርገውን የንግድ ልውውጥ ያቀላጥፋል ተባለ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀናት በፊት ያፀደቀው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት የሚመራ፣ ምርታማነትን ለማሳደግና የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የሚያገለግል ዋነኛ መሣሪያ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ከአገሮቹ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ ለማቀላጠፍ፣ የንግድ ፖሊሲው ዓይነተኛ መፍትሔ እንደሚሆን በፖሊሲ ሰነዱ ሠፍሯል። ለዚህም የገቢ ንግድ ታሪፎችን በማንሳት ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ እንደሚያስችል የወጣው ሰነድ ያሳያል፡፡
የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና በአገሮች መካከል የኢኮኖሚ ትስስርን ለማመቻቸት የተነደፈ በመሆኑ፣ ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት ለሚፈጥሩ የውጭ ኩባንያዎች የተለያዩ ማበረታቻዎችን መስጠት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ፖሊሲው እንደሚረዳ ተጠቁሟል።
አገራዊ ተወዳዳሪነትን የማሳደግ፣ የወጪ ንግድ ዕድሎችን የማስፋፋትና የወጪ ምርቶችን በዓይነት፣ በመጠንና በመዳረሻ ገበያ የማስፋት፣ ፈጠራን የማበረታታት፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ፣ በጠረፍ ንግድና በመዳረሻ ገበያዎች ያሉትን መሰናክሎችን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የሚያስችል እንደሚሆን ሰነዱ ያስረዳል፡፡
ፖሊሲው በአገሪቱ ያሉ የንግድ ተዋናዮችና አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በዓለም አቀፍ የምርት እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያላቸውን የንግድ ልውውጥ እንዲያጠናክሩ ያስችላል ተብሏል። ኢትዮጵያ በተለይ በአግሮ ኢንዱስትሪ ንግድ፣ በጨርቃ ጨርቅና በአልባሳት ዘርፎች አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ለመሳተፍ ዕድል እንዲኖራት እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡
የንግድ ልውውጡ ከታሪፍ ውጪ የሆኑ መሰናክሎችን ማለትም የጉምሩክ ሒደት መዘግየትን፣ ከመነሻው እስከ መድረሻ ያሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አቅርቦቶች እጥረትን፣ እንዲሁም ተደጋጋሚ የሆኑ የወረቀት ሥራዎችን ለማስወገድ ፖሊሲው አጋዥ እንደሚሆን ተብራርቷል።
From The Reporter Magazine
የአገሪቱ የንግድ ሥርዓት በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ያለ መሆኑን የሚገልጸው ሰነዱ፣ ዋጋ አሳንሰው ወይም አስበልጠው የሚያስመጡ፣ የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን የሚያመርቱና የሚያስመጡ እንዳሉ ጨምሮ ገልጿል። የሎጂስቲክስ አቅርቦቱ አለመጣጣምና በዘርፉ ያሉ ሕጎችና አሠራሮች በየጊዜው መለዋወጥ ሌሎች የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸው በፖሊሲው ሰነድ ተገልጿል፡፡
የንግድ ፖሊሲው የአገሪቱን የእሴት ሰንሰለት ትስስር ውስጥ በማስገባት የኤክስፖርት ገቢን ለመጨመር፣ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር ለመዘርጋትና የዕውቀት ሽግግር ለመፍጠር አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
ይህም ጠንካራ፣ ዘርፈ ብዙ፣ አስተማማኝና በውድድር ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ለመፍጠርና በአፍሪካ የኢንቨስትመንት ማዕከል ለመሆን ፖሊሲው ዓይነተኛ መሣሪያ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡
From The Reporter Magazine
በተመሳሳይ በባለድርሻ አካላት፣ በኢንዱስትሪውና በኢንቨስተሮች መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር ልማትን ለማምጣትና ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ፖሊሲው ይረዳል ተብሏል።
ፖሊሲው ለሴቶችና ወጣቶች በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ላይ ያለመ በመሆኑ፣ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ሀብት ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተጠቁሟል፡፡
የገንዘብ፣ የፊስካል፣ የወጪና የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች ገንዘብ እንዲመደብና ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ፣ እንዲሁም የሥራ ዕድልን በመፍጠር ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን የንግድ ሥርዓት (Multilateral Trading System) ውስጥ ለማስገባት ፖሊሲው ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተብራርቷል፡፡
ቀጣይነት፣ ተገማችና ግልጽነት ያለው የውጭ ምንዛሪ የአቅርቦት ሥርዓት በመዘርጋት ለንግዱ ማኅበረሰብ፣ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶች መተማመንን ለመፍጠር ጭምር ፖሊሲው እንደሚያገለግል ተመላክቷል።
የዓለም ንግድ ድርጅት ተሳትፎ ሒደትን ማጠናቀቅና ወደ ትግበራ ማስገባት፣ የሸማቾች ጥበቃና ፍትሐዊ የገበያ ውድድርን ማረጋገጥ ናቸው ከፖሊሲ የሚጠበቁ ሌሎች ቁልፍ ውጤቶች ተብለዋል።
ለፖሊሲው ውጤታማነት በሥራ ላይ ያሉ አዋጆች፣ ደንቦች በዝርዝር መታየትና መከለስ ሲኖርባቸው ከእነዚህም መካከል የንግድ ምክር ቤትና የዘርፍ ማኅበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/1995 ማሻሻያ፣ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/206 ማሻሻያ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ደንብ ማሻሻያ፣ የቅባት እህሎችና የጥራጥሬ ማርኬቲንግ ደንብ ማሻሻያ ተጠቃሾች ተደርገዋል። በኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ትግበራ የበርካታ አጋር አካላት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻሻል ጥረት እንደሚደረግም ተገልጿል።
