‹‹በአቡዳቢ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ውስጥ ጎብኚዎች ፍጥነታቸውን የሚቀንሱበት፣ ድምፃቸውን ዝቅ የሚያደርጉበትና ብዙ ጊዜ ፀጥ የሚሉበት አንድ ልዩ ጋለሪ አለ። ከፊታቸው፣ በጥንቃቄ መብራት የበራላትና መጠኗ እጅግ አነስተኛ የሆነችው የ3.2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ባለቤት የሆነችው የሆሚኒን አፅም (የቅድመ ሰው ቅሪተ አካል) ሉሲ (ድንቅነሽ) ትገኛለች። ምናልባትም ከማንኛውም ሌላ ጥንታዊ የሰው ዘር ዘመዶቻችን ይልቅ፣ ሉሲ ‹ሰው መሆን ምን ማለት ነው?› የሚለውን ጥያቄ በጥልቀት እንድናስብበት ትገፋፋናለች።››


ይህን ኃይለ ቃል ከሁለት ሳምንታት በፊት በዘ ኮንቨርሴሽን (The Conversation) መጽሔት ላይ የጻፉት የአቡዳቢ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየምና የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የጄኔቲክስ፣ ዝግመተ ለውጥና አካባቢ ጥናት ክፍል ዳይሬክተር ፒተር ኪዬርጋርድ እንዲሁም በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የምድር ሥርዓት ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርክ ማስሊን ናቸው፡፡
ካለፈው ኅዳር ወር ጀምሮ እስከ ሐምሌ መጀመርያ ድረስ ለዘጠኝ ወራት በአዲሱ የአቡዳቢ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ለዕይታ የበቃችው ሉሲ የአቡዳቢ ክራሞቷን አስመልክቶ ሁለቱ ምሁራን ሐተታ አቅርበዋል፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ ወደ እስያ አኅጉር ያቀናችው ሉሲ፣ ከዓምና ነሐሴ ጀምሮ እስከ ዘንድሮው ጥቅምት ድረስ ለሁለት ወራት በአውሮፓዊቷ ቼክ ሪፐብሊክ ቆይታ አድርጋ ነበር፡፡ ከሃያ ዓመት በፊት ወደ አሜሪካ ተጉዛ አምስት ዓመታት መቆየቷ ይታወሳል፡፡ የአቡዳቢው ጉዞ ከቀደሙት ጉዞዎች የተለየ የሚያደርገው ጉዞዋ ከመነሻው ምስጢራዊ መሆኑ ነበር፡፡
በጥብቅ ምስጢር የተያዘ ጉዳይ
በዘ ኮንቨርሴሽን ላይ እንደተገለጸው፣ የሉሲ የቅርብ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጭ የተደረገው ጉዞ በጥብቅ ምስጢር የተያዘ ነበር። የአቡዳቢ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም በኅዳር 2018 ዓ.ም. ከመከፈቱ በፊት በነበሩት ወራት ውስጥ፣ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በስተጀርባ ሆነው የእሷን የመጓጓዣ ሎጂስቲክስና ደኅንነት እንዲሁም አዲሱ ቤቷ በሚሆነው ማሳያ የመስታወት ሳጥን ውስጥ ስላለው ጥንቃቄ የተሞላበት የአየር ንብረት ሁኔታ ሲሠሩ ቆይተዋል።
ለዚሁ ተግባር አንድ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣንና ከብሔራዊ ሙዚየም ባለሙያዎች ጋር በቅርበት እንደሠራና እያንዳንዱ ዕርምጃ ጥንቃቄን፣ እምነትንና ትክክለኛነትን ይጠይቅ እንደነበር ተገልጿል።
From The Reporter Magazine
‹‹እያንዳንዱ አጥንት በተለየ ሁኔታ በተዘጋጁ የጉዞ ሳጥኖች ውስጥ በጥንቃቄ ታሽጎና ተጠብቆ ተቀምጧል። ምንም ነገር ለአጋጣሚ አልተተወም። ምንም ዓይነት ስህተት ሊፈጠር አይገባም ነበር፤›› ያሉት ጸሐፍት ፕሮፌሰሮቹ፣ ሉሲ ሙዚየሙ ከመከፈቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ አቡዳቢ በሰላም መድረሷን፣ አሁንም ምስጢር ሆኖ እንደቀጠለ፣ የመጨረሻው የሁኔታ ፍተሻና የጋለሪው ማጠናቀቂያ ሥራዎች እስከሚከናወኑ ድረስ ደኅንነቱ በተጠበቀ ቦታ ተቀምጣ እንደነበር ጠቅሰዋል።
‹‹በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የሉሲ ጠባቂ (ኩሬተር) የሆኑት ሳህለ ሥላሴ መላኩ ተሰባሪ የሆኑትን አጥንቶች በማሳያ ሳጥኑ ውስጥ በጥንቃቄ አስቀመጧቸው። ቁርጥራጮቹ ቀስ በቀስ ወደ ድንቅነሽ ታዋቂ ቅርፅ ሲቀየሩ እያየን ሁላችንም እስትንፋሳችንን የዋጥን ያህል ተሰምቶን ነበር፡፡ በመጨረሻም፣ ከፊታችን ተገኘች፤›› ያሉት ፕሮፌሰሮቹ፣ ኢትዮጵያ እሷን ለማጋራት የወሰነችው ውሳኔ፣ በታሪክ እንዲህ ያሉ ተቋማት እምብዛም ባልነበሩበት ክልል ውስጥ የአዲስ ሙዚየም መከፈትን ለማክበር ትልቅና ጠንካራ መንገድ እንደነበር በመጥቀስ አወድሰዋል፡፡
‹‹ጎብኚዎች ሉሲን ሲያገኟት እንደ ረቂቅ ሳይንሳዊ ነገር ሳይሆን እንደ አንድ ግለሰብ አድርገው ሲመለከቷት አስተውለናል። ውጤቱም አስገራሚ ነበር። ሰዎች እዚያው ይቆያሉ። ያስባሉ። ብዙዎች በግልጽ ስሜታቸው ይነካል፣ እንዲሁም ይህ አምሳያ ሳይሆን ትክክለኛው ቅሪተ አካል፣ ከሚሊዮን ዓመታት በፊት በዓለማችን ላይ ኖሮ ይንቀሳቀስ የነበረ ሕያው ፍጡር መሆኑን ሲረዱ ይገረማሉ፤›› ሲሉም የጎብኚዎችን ስሜት አጋርተዋል፡፡
From The Reporter Magazine
ጥንታዊ አጥንቶቿ የተገኙት በ1967 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አፋር ክልል በአሜሪካዊው ቅሪተ አካል ተመራማሪ ዶናልድ ጆሀንሰን በሚመራ ዓለም አቀፍ ቡድን እንደነበር ያስታወሱት ጸሐፊዎቹ፣ ይህ በሚያስደንቅ ሁኔታ ሙሉ የሆነው የኦስትራሎፒተከስ አፋረንሲስ ዝርያ አምሳያ፣ ስለ ቅድመ ሰው አመጣጥና ዝግመተ ለውጥ (ኢቮሉሽን) ታሪክ ያለንን ግንዛቤ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል ብለዋል።
የአፅሙ መገኘት የተከሰተው የቡድኑ አባል የነበሩት ኢትዮጵያዊው የቅሪተ አካል ተመራማሪ አቶ ዓለማየሁ አስፋው ከተመሳሳይ ዝርያ የተገኘ የመንጋጋ አጥንት ባገኙ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሲሆን፣ ይህም ለቡድኑ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
‹‹የሉሲ አፅም በሁለት እግር ቀጥ ብሎ መራመድ የቅድመ ሰው አንጎል ከማደጉ በፊት እንደቀደመ ግልጽ ማረጋገጫ የሰጠ ሲሆን፣ ይህም ለአያሌ ዓመታት ፀንተው የነበሩ ሳይንሳዊ ትረካዎችን እንደገና እንዲቀረጹ አድርጓል፤›› ያሉት ጸሐፍቱ፣ በምዕራቡ ዓለም ‹ሉሲ› የሚለው ስም የተሰጣት ቢትልስ የተባለው የሙዚቃ ቡድን ‹Lucy In The Sky With Diamonds› ከተሰኘው ዘፈን በመነሳት ቢሆንም፣ የቡድኑ ኢትዮጵያውያን አባላት ግን ‹ድንቅነሽ› (አንቺ ድንቅ ነሽ ለማለት) ብለው መጥራታቸውን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ የባህልና የተፈጥሮ ቅርስ አምባሳደር በመሆን እያገለገለች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሉሲ በዓለም ላይ ካሉ ቅሪተ አካላት ሁሉ እጅግ የታወቀች ብትሆንም፣ በአካል ያገኟት ሰዎች ግን በጣም ጥቂቶች ነበሩ። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ይህንን ለመለወጥ በ1999 ዓ.ም. ከአሜሪካ ተቋማት ጋር በመተባበር ሉሲን ወደ አሜሪካ እንድትጓዝ በማድረግ በ2005 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሷ በፊት በአራት ቦታዎች ላይ ብቻ ቀርባ ነበር።
ከሁለት አሠርታት በኋላ ሉሲ እንደገና ወደ ውጭ አገር ስትጓዝ በቀዳሚነት ያመራችው ወደ ቼክ ሪፐብሊክ ሲሆን ከዚያ በተመለሰች ከወር በኋላ ወደ አቡዳቢ አቅንታለች፡፡ ይህንንም ጸሐፊዎቹ እንደሚከተለው ገልጸውታል፡- ‹‹በዚህ ጊዜ ከእኛ መካከል አንደኛው (ፒተር ኪዬርጋርድ) ዳይሬክተር ወደሆኑበት የአቡዳቢ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም መምጣቷ ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የቅሪተ አካል ጥናት (ፓሊዎአንትሮፖሎጂ) ዘርፍን የሚመለከተው ትረካም በተለወጠበት ወቅት ላይ ነው።››
በቅኝ ግዛት ፈንታ በትብብር መሥራት
በፕሮፌሰሮቹ አገላለጽ፣ ሉሲ ከኢትዮጵያ ወደ አቡዳቢ ያደረገችው ጉዞ ዕውቀት፣ ቅርስና ባለቤትነት እንዴት እንደሚጋሩ የሚያሳይ ሰፊ ለውጥን ያንፀባርቃል።
በዘመናዊው ታሪክ ውስጥ ለአብዛኛው ጊዜ ከአፍሪካ የተገኙ ግኝቶች ከተገኙበት ቦታ ርቀው ይሰበሰቡ፣ ይጠኑ፣ ይተረጎሙና ለዕይታ ይቀርቡ ነበር። አሁን ግን ይህ አካሄድ እየተቀየረ ነው። የአፍሪካ አገሮች በባህልና በሳይንስ ቅርሶቻቸው ላይ ያላቸውን አመራር እያረጋገጡ ሲሆን፣ ቅርሶቹ እንዴት እንደሚጠበቁ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚተረጎሙ፣ እንደሚጋሩና ለዕይታ እንደሚበቁም በራሳቸው እየወሰኑ መሆኑን ፕሮፌሰሮቹ አስረድተዋል።
‹‹የሉሲ በአቡዳቢ መገኘት ይህንን ለውጥ የሚያሳይ ሕያው ማረጋገጫ ነው። እሷ ከራሷ ዓውድ አልተነጠለችም፤ ይልቁንም በትብብር የተጋራች ናት። እሷ አሁንም ኢትዮጵያዊት ሆና ትቀጥላለች፡፡ ጉዞዋም በጠንካራ አጋርነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ሞዴል እምነትን እንደሚገነባ፣ በኤምሬትስና በኢትዮጵያ ያሉ ተቋማትን እንደሚያጠናክር እንዲሁም ለጋራ ምርምርና ትምህርት አዳዲስ መንገዶችን እንደሚከፍት ተስፋ እናደርጋለን፤›› ሲሉም አንድምታውን ገልጸውታል፡፡
በዘ ኮንቨርሴሽን እንደተጻፈው፣ ‹‹ሙዚየሙ ከመሠረቱ የተቀረፀው ዘመናዊውን ታዳሚ እንደ ብዝኃ ሕይወት፣ የተፈጥሮ ጥበቃና የሰው ልጅ ተጽዕኖ ባሉ ወቅታዊ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ ለማሳተፍ ነው። ሙዚየሙ የተከፈተው በርካታ የምዕራባውያን ሙዚየሞችን ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የማላቀቅ (ዲኮሎናይዝ) አስፈላጊነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በታመነበት ወቅት ሲሆን፣ በለንደን ሙዚየም ውስጥ ለረዥም ጊዜ ተቀምጠው የነበሩና ወደ ዓረብ ኤምሬትስ የተመለሱትን ብርቅዬ የኋለኛው ማዮሲን (Late Miocene) ዘመን ቅሪተ አካላትን (ከ11.6 እስከ 5.3 ሚሊዮን ዓመታት በፊት የነበሩ) ያካተተ ነው።
‹‹የሳይንስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በአዳዲስ ግኝቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በትብብር ላይ ጭምር እንደሆነ እናምናለን፡፡ ይህም ክልሎችን፣ አመለካከቶችን እና ታሪኮችን የማገናኘት ችሎታ ነው። ሉሲ ይህ እንዲሆን እየረዳች ነው። በሐምሌ ወደ አዲስ አበባ ስትመለስ፣ የዚህን የዕውቀትና የባህል ልውውጥ አሻራ ይዛ ትመለሳለች። በአቡዳቢ የሚቀረው ነገር ቢኖር ከአስደናቂው ዓውደ ርዕይ ትውስታ በላይ ይሆናል። ይኸውም በተቋማት መካከል፣ በአገሮች መካከል፣ እንዲሁም በሰዎችና በተጋሩት የጋራ ታሪካቸው መካከል የሚፈጠር ዘላቂ ትስስር ነው፤›› ሲልም ያክላል።
የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሮፌሰሮቹ ማርክ ማስሊን እና ፒተር ኪዬርጋርድ (የአቡዳቢ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየምም ዳይሬክተር ናቸው)፣ አዲሱን የአቡዳቢ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየምን ከ19ኛው ክፍለ ዘመኑ የለንደን የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ጋር ያነፃፀሩበት መንገድ ለጥቅስ የሚበቃ ነው፡፡
‹‹የለንደን የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም እ.ኤ.አ. በ1881 ሲከፈት የቪክቶሪያን ምኞት፣ የሳይንስ ጉጉትና የኢንዱስትሪ ኃይል ዋነኛ ምልክት ተደርጎ ይታይ ነበር። በተመሳሳይ መንገድ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአቡዳቢ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም መገንባቱ የአገራዊነት፣ የዓለም አቀፋዊ ማንነትና የሳይንሳዊ ምኞት መገለጫ ምልክት ነው።››
ሉሲ በአቡዳቢ ቆይታዋ ስላስገኘችው ገቢና ስለ ኢትዮጵያ ተጠቃሚነት በይፋ የተገለጸ ነገር ሪፖርተር አላገኘም፡፡ ሉሲ በአሜሪካ የአምስት ዓመት ቆይታዋ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ማስገኘቷ፣ በሉሲና ሰላም የቅርቡ የፕራግ ቆይታቸውም ለኢትዮጵያ ያስገኙት ጥቅም ከቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ጋር የተያያዙ ሦስት ፕሮጀክት በቼክ ሪፐብሊክ አማካይነት እንደሚፈጸም በኃላፊዎቹ በወቅቱ መገለጹ በሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል።