ወርኃ ታኅሣሥና ጥር በክርስቲያኖች ዘንድ በትውፊታቸው መሠረት የሚያከብሯቸው በዓላት ልደት፣ ጥምቀት፣ አስተርእዮ በድምቀታቸው ለየት ይላሉ፡፡ ከዘመነ ልደት እስከ ዘመነ አስተርእዮ ከባህላዊ መገለጫዎች ጋር ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ ትግራይ ነው፡፡
ክብረ በዓላት በመጡ ቁጥር ከሚከናወኑት የጨዋታ ዓይነቶች አንዱ ‹‹ሁራ ሰለስተ›› የሚባለው ሲሆን በተለይ በትግራይ ምሥራቃዊ እና ደቡባዊ ምሥራቅ ዞኖች ይዘወተራል፡፡
የትግራይ የማይዳሰሱ (ኢንታንጀብል) ባህላዊ ቅርሶችን የሰነደው የቅርስ ባለሥልጣን በአንድ ኅትመቱ እንደገለጸው፣ ሁራ ሰለስተ በምሥራቃዊ ትግራይ አካባቢ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚታወቅ ጎልማሶችና ወጣቶች የሚጫወቱት የሚደሰቱበት ባህላዊ ጭፈራ ነው፡፡
ሁራ ሰለስተ በመንፈሳዊና በሠርግ፣ መንግሥታዊ በሆኑ በዓላትም ላይ ይከናወናል፡፡ ይህ ጨዋታ ተሳታፊዎች እግራቸውን በቅደም ተከተል ከአጫፋሪው ከሁራ ሰለስተ አጫዋች እኩል በማንሳትና በማሳረፍ አስተካክሎ የሚስብ ጭፈራ ነው፡፡ ተጫዋቾቹ ክብ ሠርተው እየዞሩ ግጥሙን እየተቀባበሉ ይከውኑታል፡፡ ይህን ባህላዊ ጭፈራ ሲጨፍሩ በከበሮ፣ በጭራ (በመሲንቆ)፣ በአዝማሪና በክራር ይታጀባሉ፡፡
ገና እና ሁራ ሰለስተ
ስለ ሁራ ሰለስተ ሃይማኖታዊ ይዘት የጻፉት ሰለሙን በርሀ እንደገለጹት፣ የገና በዓል በኣፅቢ፣ ወንበርታ፣ ክልተ ኣውላዕሎ፣ ሳዕሲዕ ፃዕዳ እንባና አካባቢዎች ከፍ ባለ ሥርዓት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ነው።
የገና ልጆች ሲሰበሰቡ ፈጣሪያቸውን ለማወደስና ለማመስገን በአቅራቢያው ወዳለው ቤተ ክርስቲያን ብርብር የሚባለውን በትራቸውን ይዘው ይሄዳሉ። የቤተ ክርስቲያን በራፍ ላይ ሲደርሱ እያንዳንዱ የገና ልጅ የእንጨቱን ጫፍ ቆርጦ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ይጥለዋል። እያንዳንዱ የገና ልጅ ከሁራ ሰለስተ በተለየ ‹ሁራ ክልተ› እግሮቻቸውን አመሰቃቅለው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይገባሉ። ከቤተ ክርስቲያን ሲመለሱ ደግሞ በሰለስተ ሁራ ጨዋታቸው ይመለሳሉ።
‹‹ሁራ ክልተ ለ5500 ዓመታት ታስረን ነበር የሚል መልዕክት ሲኖረው፣ ሁራ ሰለስተን መርገጣቸው ደግሞ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልደህ ከእስር አዳንከን ማለት ነው። ለአንተ ምስጋና ይግባህና ሐዘናችን ወደ ደስታ ተለወጠ።››
[5500 ዓመት ማለትም ከአዳም ክርስቶስ እስከተወለደበት ዓመት የነበረውን የሚያመለክት ነው፡፡]
በክብረ በዓሉ መጨረሻም የመንደሩ ሽማግሌዎች ልጆቹን መርቀው የሚቀጥለው ዓመት መልካም ዓመት እንዲሆንላቸው ይመኙላቸዋል።
የሁራ ሰለስተ ድባብ በሌሎች መድረኮች
የሁራ ሰለስተ አጀማመርና ታሪካዊ አመጣጥ ከአክሱም ጥንታዊ ሥልጣኔ ጋር የተያያዘ ነው ቢሚለው የቅርስ ባለሥልጣን ሰነድ አገላለጽ፣ በእነዚያ የነገሥታት ዘመን ወታደራዊ ሥልጠና ሲሰጥ የእግርና የእጅ እንቅስቃሴ ነበር፡፡
ሁራ ሰለስተ ከመጨፈሩ በፊት ቀረርቶ የሚሰማው የሚጨፍሩት ሰዎች ስሜታቸውን ለመቀስቀስ፤ ከበሮ ማሲንቆና ክራር የሚመታውና ጥሩንባ የሚነፋው ሁራውን በተናበበ መልኩ እንዲያጅቡት፣ የታዛቢዎችንም ትኩረት ለመሳብ ነው፡፡ በጭፈራ መሀል ላይ ቀረርቶ የሚሰማው ደግሞ የሁራውን ዘፈን ለመቀየር፣ የሙዚቃ መሣሪያዎቹና ጭፈራው ቅድ ለማዋሀድ ሲፈለግ ነው፡፡
ሁራ ሰለስተ የከበሮ ምትን በመከተል የሚከወን ጨዋታ ሲሆን የመጀመርያ የከበሮ ምት ሰብስብ የሚባል የሁራ ዓይነት እንዲጨፈር ነው የሚመታው፡፡
በደቡባዊው ምሥራቅ ዞን ኅብረተሰቡ ተሰብስበው ደስታቸውን የሚገልጹበት አንዱ የጭፈራ ዓይነት ሁራ ይባላል፡፡ በእንቅስቃሴ የሚከወን ምቱ ፈጠን የሚል ሲሆን የከበሮውን ምት ጠብቆ እግርን ወደ መሬት በመርገጥና እግርን እስከ ጉልበት ድረስ እያጠፉ በመርገጥ ወደ ላይ ወደ ታች እያሉ የሚከወን ባህላዊ ጭፈራ ነው፡፡
የባህል ባለሙያዎቹ እነ አንዱ ዓለም አሰፋና ቀለሟ መኮንን እንዳብራሩት፣ ሁራ ሲጨፈር ወጣቶችና አዛውንቶች የራሳቸው የሆነ አለባበስ አላቸው፡፡ የራሱ ዜማዎች ያሉት ሲሆን ተቀባይና አውጪ ዘፋኞችን አሉት፡፡ በአጠቃላይ ሁራን በደስታ ጊዜ የሚጠቀሙበት ባህላዊ ጭፈራ ሲሆን፣ የሚሳተፉትም ወጣት ወንዶች እንዲሁም አንዳንዴም ሴቶች ለማድመቅ ሲሉ ይሳተፋሉ፡፡ አጋጣሚውን ለመጠቀም የምትወደው ወንድ ወይም የሚወዳት ሴት ካለች እንዲግባቡ ብለው ሁራ ላይ ይሳተፋሉ፡፡ ሁራ በቡድን የሚከወን ጭፈራ ሲሆን ጥሩ የረገጠ ጥሩ ነው ተብሎ ይወሰዳል፡፡