በውጭ አገሮች የተሰደዱና መንግሥትን ሲቃወሙ የቆዩ ፖለቲከኞች ወደ አገር ቤት ገብተው ከመንግሥት ጋርም ሆነ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በጋራ የሚወያዩበት መድረክ ለመፍጠር ጥረት መጀመሩ ተነገረ፡፡
ሆርን ፒስ ኢንስቲትዩት በተባለና አሜሪካ አገር በተመሠረተ ሲቪክ ማኅበር በኩል የተጀመረው ጥረት፣ በተያዘው ዓመት በአገር ቤት ሁሉንም ያቀፈ የሰላም ፎረም ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩም ታውቋል፡፡
በቀድሞዋ የሕፃናት ወጣቶችና ሴቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ የተመሠረተውና በዋና ዳይሬክተርነት የሚመራው ሆርን ፒስ ኢንስቲትዩት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው አገሮች ሰላም ለመፍጠር እንደሚሠራ ተነግሯል፡፡ እንደ ኤፍሬም ይስሃቅ (ፕሮፌሰር) ያሉ ምሁራን የሚሳተፉበት ሲሆን ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ከኬንያ ምሁራንን ማሰባሰቡ ተገልጿል፡፡
ፊልሰን አብዱላሂ በተለይ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያና በቀጣናው አገሮች ዋና የግጭት ምንጭ ከሆኑ ችግሮች አንዱ የጥላቻ ንግግርን ለመዋጋት አተኩሮ ይሠራል፡፡
‹‹የዘር ጥላቻ፣ ግጭትና ጦርነት የሚመነጨው ብዝኃነትን ካለመቀበል ጀምሮ ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ‹‹ቢያንስ የጥላቻ ንግግር ይቁም በሚል የሰላም ግንባታ ጥረት ጀምረናል፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ 12 የተቃዋሚ አመራሮችን አንድ ላይ በማሰባሰብ የሦስት ቀናት ውይይት ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል ፋኖን የሚወክሉ ሰዎችን ጨምሮ ሦስት የትግራይ ፖለቲከኞችን በዚያ ውይይት ማሳተፋቸውን፣ እንደ አቶ በቀለ ገርባና ህዝቅኤል ጋቢሳ (ፕሮፌሰር) ያሉ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ጨምሮ ዮናስ ብሩ (ዶ/ር) እና አቶ ልደቱ አያሌው የተካፈሉበት ጥሩ መቀራረብና ውጤት የተገኘበት ስብሰባ ማካሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡
ይህንን መነሻ የበለጠ በማጠናከር ፖለቲከኞችን ለማቀራረብና በጋራ ተቀምጠው እንዲነጋገሩ ለማድረግ ጥረት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
‹‹እኛ ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር የጀመርነው ንግግርም ሆነ መቀራረብ የለም፡፡ ብሔራዊ ምክክር አገር አቀፍ የውይይትና የንግግር መድረክ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ትኩረት ያደረግነው ሰላም መፍጠር ላይ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር አለ የሚለውን ግንዛቤ መፍጠርና ጉዳዩ የሰላም ዕጦት ዋና ምንጭ መሆኑን ማስረፅ ነው ሥራችን፡፡ ከተለያዩ ቁልፍ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ አመራሮች ጋር እየሠራን ነው፡፡ ከውጭም ከተለያዩ አገሮችም ሆነ እዚህ አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎችን እናሳትፋለን፡፡ ከመንግሥት ጋር እየሠራን ነው፡፡ መንግሥትም ደግፎን ከውጭ ፖለቲከኞች መጥተው የውይይት መድረክ እንዲመቻች እንሠራለን፣ መነጋገር አለብን፣ መወያየት አለብን፣ በሮች ሁሉ መከፈት አለባቸው፡፡ በዚህ ዓመት ትልቅ ዓለም አቀፍ የሰላም ፎረም በአገራችን ለማካሄድም ዝግጅት አለን፤›› በማለት የተቋሙን ዕቅድ አስረድተዋል፡፡
ፊልሰን ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣‹‹ፖለቲካችንን በአጥር አጥረን ኢትዮጵያ የምንላትን የጋራ አገር መገንባት አንችልም፡፡ ከዚያ ክበብ ወጥተን ሁሉንም የሚወክል ፖለቲካ ይዞ መምጣትና ለጋራ አገር መታገል አስፈላጊ ነው፡፡ ለአንድ ወንበር ተብሎ ሕዝብን ውጡ እያሉ ቀስቅሶ ሕዝብን ጥሎ መምጣት አስፈላጊ ነው አልልም፡፡ ለወንበር ሕዝብን ማገዳደል አያስፈልግም፤›› የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡
የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት የሚደነቅ ቢሉትም፣ ነገር ግን በስምምነቱ ማግሥት በአማራ ክልል ጦርነት መፈጠሩን ሰላም ወለድ ጦርነት ብለውታል፡፡ ከትግራይ ጦርነት መማር አስፈላጊ መሆኑን የመከሩ ሲሆን፣ የሕወሓት ለሁለት ተከፍሎ መወዛገብን ከአንጋፋ የፖለቲካ ፓርቲ የማይጠበቅ ነውር መሆኑን በመጥቀስ ብዙ ጉዳት ያስተናገደው የትግራይ ሕዝብ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለደረሱ ቀውሶችና ጥፋቶች ዋነኛ ተጠያቂው የፖለቲካ ልሂቃኑ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሕዝቡን ለወንበርና ለሥልጣን ሲሉ የሚያባሉት ልሂቃኑ ናቸው በማለትም ወቅሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ችግር አንዱን አውጥቶ ሌላውን ለማምጣት በመሯሯጥ እንደማይፈታ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የአገራችን ችግር በእውነት ነው የሚፈታው፡፡ እውነት እውነቱን የማንነጋገር ከሆነ መፍትሔ አይመጣም፡፡ በአንድ አውሮፕላን እየሄድን መርገፍገፍ ቢፈጠር ፓይለቱ ይቀየር አንልም፡፡ ፓይለቱ ነው ይውረድ ለማለት መጀመሪያ አውሮፕላኑ መሬት ላይ ማረፍ አለበት፤›› በማለት ልሂቃኑ የፈጠሩት የሥልጣን ጥምን መሠረት ያደረገ ግጭትና ቀውስ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ መጣሉን አስረድተዋል፡፡
የሆርን ፒስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተሯ ፊልሰን አክለውም እስከ ዛሬ ከተደረጉ ጦርነቶች በመማር፣ በአገሪቱ አሁንም በመካሄድ ላይ ያሉ ጦርነቶችን ማስቆም አንገብጋቢ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ‹‹አሁንም እየሞተና እያለቀብን ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ጦር ሠራዊቱም፣ ፋኖም፣ ኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) በለው ሌላም ቢሆን ሁሉም የእኛው ሰው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነው እያለቀ ያለው፡፡ በሐሳብ ልዩነት ደም ማፍሰስ የለብንም፣ ሕዝብ ማለቅ የለበትም፣ ሕዝብ መሰደድና መጎዳት የለበትም፡፡ ሁላችንም ቆም ብለን ማሰብና ወደ መነጋገር ልንመጣ ይገባል፤›› በማለትም ለሁሉም የፖለቲካ ልሂቃን ያሉትን የሰላም ጥሪም አቅርበዋል፡፡
ሆኖም በዚህ ዓመት ይደረጋል ያሉት የሰላም ፎረም መቼ እንደሚካሄድ፣ እነ ማንንና የትኞቹን የፖለቲካ ኃይሎች እንደሚያሳትፍም ሆነ በምን ሁኔታ እንደሚካሄድ ለጊዜው ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡