ከሰሞኑ በፌስቡክ በርካቶች በተቀባበሉት አንድ አጭር ቪዲዮ ላይ አንድ የደቡብ አፍሪካ ማኅበራዊ አንቂ የሚናገረውና ለእሱ የተሰጠው የሰዎች አስተያየት ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ ‹‹እኛ የማንዴላ ንብረት አይደለንም፣ ማንዴላ ስለውጭ ዜጎች የሚናገረውም እኛን አይወክለንም፡፡ ማንዴላ የራሱን ቤተሰብ ብቻ ነው የሚወክለው፡፡ ማንዴላ ከነጮች ጋር ከመደነስ ውጪ ለእኛ ምን አደረገልን? ማንዴላ እኛን እንዲያውም ሸጦናል፤›› በማለት በእልህና በቁጭት ወጣቱ ሲናገር፣ በመድረኩ ከጎኑ ተቀምጠው የነበሩ ሌሎች ሰዎች ‹‹በትክክል›› እያሉ ሲያዳምቁ ይደመጣሉ፡፡ ከዚህ አጭር ቪዲዮ ሥር አስተያየታቸውን ያጋሩ የአንዳንድ ሰዎች ሐሳብ የበለጠ ያስገርማል፡፡


‹‹አንዲት ቀን በእስር ቤት አሳልፎ የማያውቅ ሰው ለአገሩ ሲል ለ27 ዓመታት እስር ቤት ያሳለፈ ሰውን አገር የሸጠ ብሎ ለመናገር የሞራል ድፍረቱን ከየት ነው የሚያገኘው? ማንዴላ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ምንም ዓይነት ውጤት ቢኖራቸው ነገር ግን ለአገሩ የከፈለውን መስዋዕትነት ክብር መስጠት አስፈላጊ ነው፤›› በማለት ነበር አንድ አስተያየት ሰጪ በሳል የሚባል ሐሳብ ያጋራው፡፡
ከሰሞኑ በደቡብ አፍሪካ የውጪ ስደተኛ ጠል የሆነ ጥቃት ዳግም አገርሽቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን ይውጡልን፣ ጋናዎች ጥርግ ይበሉልን፣ ናይጄሪያውያንን ዓይናቸውን እንዳናይ የሚሉ በእልህና በቁጣ የተሞሉ ደቡብ አፍሪካውያን ንግግሮች በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሰፊው ሲሠራጩ ሰንብተዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ጊዜ ጠብቆ የሚያገረሽ ችግር የሆነው የውጭ ስደተኞችን ጠል (ዜኖፎቢያ) እንቅስቃሴ ብዙ ጊዜ በማኅራዊ ሚዲያዎች ቁጣና ተቃውሞ ብቻ ሲያልፍ አይታይም፡፡ በደቡብ አፍሪካ ዜኖፎቢያ ባገረሸ ቁጥር በተደጋጋሚ የውጭ ስደተኞችን ሕይወት ሲቀማ ነው በተደጋጋሚ የተስተዋለው፡፡
የዜኖፎቢያ ጥቃት በደቡብ አፍሪካ ተቀሰቀሰ በተባለ ቁጥር በተለየ ሁኔታ የአፍሪካ ስደተኞች የጥቃት ዒላማ እንደሚደረጉ በተደጋጋሚ ዓለም ተመልክቶታል፡፡ ከሰሞኑ የተከሰተው የዜኖፎቢያ ጥቃትም የኢትዮጵያውያንን ሕይወት ሲቀማ፣ ሱቅና ንብረት ሲያወድም ዓለም እየተመለከተው ነው፡፡ የሰሞኑ ጥቃትም ቢሆን ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የጋና፣ የናይጄሪያ፣ የሶማሊያ፣ የኤርትራና የሌሎች አገሮች ስደተኞችን ሕይወት፣ አካልና ንብረት ዒላማ አድርጎ ነው የሰነበተው፡፡
አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት አንድ የጋና ስደተኛን፣ ‹‹አንፈልጋችሁም ወደ አገራችሁ ተመለሱ…›› እያለች በጠንካራ ቃላት ስትዘልፍና ስታዋርድ የሚታይበት ቪዲዮ ከሰሞኑ በርካታ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች በርካታ ተመልካቾች አትርፏል፡፡ አንድ የናይጄሪያ ዜጋን በርከት ያሉ ደቡብ አፍሪካውያን ከበው በቡጢ ሲደበድቡትና እንደ ወንጀለኛ ሲያዋክቡት የሚያሳይ ሌላ ቪዲዮም በርካታ ቅብብሎሽ በመገናኛ ብዙኃን አግኝቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሰዎች በተሰበሰቡበት የንግድ ቦታዎች በጥይት ጭንቅላታቸውና ደረታቸው እየተደበደበ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያን ያህል ድንጋጤ የሚፈጥርና ትኩረት የሚስብ አደገኛ ትዕይንት አልነበረም፡፡
ኒውስ 24 የተባለው የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃንና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ፣ ከሰሞኑ በተቀጣጠለው ዳግም የዜኖፎቢያ ጥቃት ብቻ በትንሹ አምስት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከመጋቢት ወር ጀምሮ እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ አምስት ኢትዮጵያውያን በአደባባይና በጠራራ ፀሐይ በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል፡፡ በጆሀንስበርግ ከተማ ወድሜነህ አየለና አብርሃም ይመር የተባሉ ሁለት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን የተለያዩ ዘገባዎች አረጋግጠዋል፡፡ በመኪና ማቆሚያና በገበያ ሥፍራ ሲገደሉ የሚያሳዩ የደኅንነት ካሜራ ቪዲዮዎችም አብረው ተሠራጭተዋል፡፡ ሁለት ዜጎች ደግሞ በማክዶናልድ ሬስቶራንት ውስጥ እንዳሉ በጥይት ተመተው መገደላቸውን፣ በተመሳሳይ በተሠራጨው ደኅንነት ካሜራ ምሥል ታይቷል፡፡ ከሰሞኑ የተቀሰቀሰው የዜኖፎቢያ ጥቃት የሌሎች የአፍሪካ አገሮች ዜጎችንም ሰለባ ማድረጉ ተረጋግጧል፡፡ ሁለት ናይጄሪያውያን መገደላቸው ሲረጋገጥ፣ የሞዛምቢክና የዚምባቡዌ ዜጎችም ሰለባ ሆነዋል ተብሏል፡፡
ከጆሀንስበርግ በተጨማሪም በደርባንና በፕሪቶሪያ ከተሞችም የውጭ ስደተኞችን ዒላማ ያደረጉ ንቅናቄዎች በተከታታይ እየተደረጉ ነው፡፡ በጆሀንስበርግ እንደ ‹‹ኦፕሬሽን ዱዱላ›› የተባለ ዓይነት የጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን ማኅበር (ስብስብ) ከተማውን እያሰሰ ስደተኞችን እየተከታተለ በማጎሳቆል ስሙ ይጠቀሳል፡፡ በፕሪቶሪያ ደግሞ ‹‹ማርችና ማርች›› (March and March) የሚባለው ዓይነት ቡድን ተመሳሳይ ፀረ ስደተኞች እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካዊያኑ ስደተኞችን ሥራችንን ነጥቀዋል፣ እንዲሁም አገራችንን በወንጀል እንድትበከል አድርገዋል በሚል ሰበብ ነው ዘመቻ የከፈቱት፡፡ በቡድን ሆነው በሚወስዷቸው የመንጋ ፍርዶችም የአፍሪካ አገሮች ስደተኞችን ሕይወትና ንብረት አደጋ ላይ ጥለዋል፡፡
From The Reporter Magazine
ደቡብ አፍሪካውያኑ በተለይ ለይተው የአፍሪካ አገሮች ስደተኞች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ፣ የአገሬው የፀጥታ ኃይሎችም ሆነ መሪዎች የረባ ዕርምጃ አይወስዱም ተብለው ይተቻሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በሕገወጥ ስደተኞች ላይ ቁጥጥር ይደረግ የሚለው የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ጥያቄ ተገቢነት ያለው ቢሆንም፣ ነገር ግን በዚህ መንገድ ችግሩን መፍታት እንደማይቻል ከሰሞኑ ተናግረዋል፡፡ ታዋቂው ተቃዋሚ የኢኮኖሚ ነፃነት ታጋዮች ፓርቲ መሪ ጁሊየስ ማሌማ በበኩላቸው፣ የውጭ ስደተኞች ካጠፉም ሆነ ወንጀል ከሠሩ በመንጋ ፍርድ ሳይሆን በደቡብ አፍሪካ ሕግ ነው መዳኘት ያለባቸው በማለት ንግግር አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኞች ንግግር ለአፍ የተደረገ ልፈፋ እንጂ በቂ ጥረት አይደለም በሚል ሲተች ነው የሰነበተው፡፡
የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎችና ኤምባሲዎች ለዜጎቻቸው ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ወደ አገራችሁ ተመለሱ ከሚሉ ጀምሮ ከቤት ባለመውጣት ራሳችሁን ከጥቃት ተከላከሉ የሚሉ ማሳሰቢያዎች በርከት ብለው ተሰጥተዋል፡፡ በፕሪቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ‹‹በግፈኞች በዜጎቻችን ላይ በደረሰው ግድያና በደል የተሰማንን ሐዘን እንገልጻለን፤›› ሲል ባወጣው መግለጫ፣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን ዜጎች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ማሳሰቡን አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው (አምባሳደር) ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ፣ የተፈጠረውን ችግር የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ እንደሚቆጣጠረው ኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚተማመን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ ሲሆን እንደሚታየው የአሁኑን ችግር የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ተቆጣጥሮ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ይታደጋል ወይ የሚል ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡ ከሰሞኑ ኢትዮጵያውያኑ ምን ገጠማቸው የሚለው ጉዳይም ቢሆን ብዙዎችን እያሳሰበ ነው የሚገኘው፡፡ አንዳንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ኢትዮጵያውያኑ የዜኖፎቢያ ሰለባ ከመሆን ባለፈ ውስብስብ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
From The Reporter Magazine
የጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ አመራር አባል በመሆን የሚታወቁትና ከዚህ ቀደም በደቡብ አፍሪካ የኖሩት አቶ ጀሚል ሳኒ ፓርቲያቸውን በመወከል ሳይሆን፣ በግላቸው የታዘቡትን የግል አስተያየት እንደሚሰጡ በማስታወስ ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ እየገጠማቸው ነው ያሉትን መሠረታዊ ችግር ተናግረዋል፡፡
‹‹ከሰሞኑ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው ግድያ ከዜኖፎቢያ ጥቃት ጋር ቢገናኝም፣ ነገር ግን በሌላ ምክንያት መከሰቱን እዚያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጠይቄ አረጋግጫለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያኑን ያስገደሉት ደግሞ እንዲገደሉ የፈለጉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ገንዘብ ከፍሎ በቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች ሰውን ማስገደል በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደ ሆኗል፡፡ ትንሽ ሠርተው የተለወጡና ጥቂት ሀብት የያዙ ኢትዮጵያውያን የግድያ ዒላማ መሆን ከጀመሩ ቆይቷል፡፡ ከሰሞኑ ከሞቱት መካከል በስልካቸው እየተደወለ ይህን ያህል ገንዘብ ክፈሉ የሚል ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው የነበሩ አንዳሉ አረጋግጫለሁ፡፡ አይኤስ የሚል ስም የወጣለትና ራሱን ያደራጀ ኃይል ነው የገደላቸው የሚል መረጃ አለ፡፡ ራሳቸው ኢትዮጵያውያን ከደቡብ አፍሪካውያን ነፍሰ ገዳዮች ጋር ተመሳጥረው ነው ግድያውን የሚያስፈጽሙት፡፡ ገንዘብ ሊከፍሉ ይችላሉ የሚባሉ ሰዎች ጋር እየደወሉ እንዲከፍሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡ አልከፍልም ያሉትንም ይገድላሉ፡፡ አጋጣሚው ሰሞኑን ከተፈጠረው የዜኖፎቢያ ጥቃት ጋር ተገጣጥሞ እንጂ፣ በራሳችን ዜጎች ነው ዜጎቻችን እየተጎዱ ያሉት፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ይህ ከዚህ ቀደም ያልተሰማ ቢሆንም ከሰሞኑ ስለኢትዮጵያውያኑ ሞት ሰፊ ሀተታን ያስነበበው ኒውስ 24 የዜና ምንጭም፣ የሰዎቹ አሟሟት በቡድን በተደራጁ የገዳይ ቡድኖች ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ መጠርጠሩን አመልክቷል፡፡ ዘገባው ሲቀጥልም ከዚህ ቀደም የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ሁኔታም በተመሳሳይ መንገድ ሊሆን እንደሚችል የፖሊስን ግምት አስነብቧል፡፡
ስለዚሁ ጉዳይ መረጃ እንዳላቸው ሪፖርተር የጠየቃቸው በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የአንድ የኢትዮጵያውያን ማኅበር መሪ የሆኑ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ኢትዮጵያዊ፣ ጉዳዩ የተጨበጠና ሁሉም የሚያውቀው መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
‹‹እዚህ አገር ዕቁብ ደርሶታል ሲባል ገንዘብ ለመዝረፍ ሲባል የተገደሉ ግለሰቦች ብዙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ ብዙ ችግር ተጋፍጠው ነው የሚኖሩት፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው በኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚገጥማቸው አደጋ ከባድ ነው፡፡ እኔ የማረጋግጥልህ እዚህ አገር በየአጋጣሚው ከሚገደሉ ኢትዮጵያውያን መካከል 85 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ሰዎች ነው ሕይወታቸው የሚያልፈው፡፡ ጥቂት የነገደ፣ ሀብት ያገኘ፣ ዕቁብ የወጣለት ወይም ሻል ያለ ሕይወት ላይ የደረሰ ሰውን ንብረት ለመቀማት ነው ግድያዎቹ በአብዛኛው የሚደረጉት፤›› በማለት፣ ከሰሞኑ የሞቱት ሰዎች አጋጣሚም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው የሚል ሰፊ ግምትና ወሬ በኢትዮጵያውያኑ መካከል እንደሚናፈስ አስረድተዋል፡፡
ሁለቱም አስተያየት ሰጪዎች በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ እትዮጵያዊያን ዘንድ ባለመግባባት፣ በቅናትና በስግብግብነት ምክንያት የራሳቸውን አገር ልጅ ለወሮበሎች ከፍሎ ማስገደል እየተስፋፋ የመጣ ከባድ ችግር መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ባለው ከፍተኛ መጠን ባለው የግድያ ወንጀልና ሕገወጥነት እንደሚሳበብ ገልጸዋል፡፡ አልፎ አልፎ ከሚፈጠረው የዜኖፎቢያ ጥቃት ጋር ድርጊቱ እየተገናኘ እንደሚታለፍ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ነገር ግን እርስ በእርስ መገዳደሉና ማስገደሉ ሥር የሰደደ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ጀሚል እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያውያኑ ይህ ችግር ቢያጋጥማቸውም በተጨማሪም የዜኖፎቢያ ሰለባም እየሆኑ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ ጠንካራ ኮሙኒቲ አልገነቡም፡፡ ለመብታቸው የሚከራከር ወይም ጥበቃ የሚያደርግላቸው ኅብረት አልፈጠሩም፡፡ በብሔርና በሃይማኖት ተከፋፍለው በሰው አገርም ተነጣጥለው መኖራቸው በሰፊው ለጥቃት አጋልጧቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑን ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ የሚመጡ ስደተኞችን የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ይጠላሉ፡፡ ከእነሱ በስተጀርባ ሆነው ህንዶቹና ነጮቹም ጥላቻውን የሚያባብስ መርዝ ይዘራሉ፡፡ ነጮቹና ህንዶቹም ልክ እንደ ጥቁሮቹ የአፍሪካ ስደተኞች ኢኮኖሚውን ተሻምተውናል ይላሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ በተለይ ምርጫ በደረሰ ቁጥር ዜኖፎቢያ መፈንዳቱ የተለመደ ነው፡፡ ምርጫ በአገሪቱ በደረሰበት በዚህ ወቅት ጥቃት የተፈጸመው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት ደግሞ በኢትዮጵያዊያኑ ዘንድ እርስ በእርስ መገዳደሉ ከባድ አደጋ ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የደቡብ አፍሪካ ነዋሪው በበኩላቸው ደቡብ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት እየገጠሟት ያሉ በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎችም ጭምር ለዜኖፎቢያው ጥቃት መነሻ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ከ257 ከተማ ማዘጋጃ ቤቶች ውስጥ ወደ 47 የሚሆኑት ተዘግተዋል፡፡ ከመቶ በላይ ራሳቸውን ማስተዳደር አቅቷቸዋል፡፡ ለዜጎቻቸው ውኃ፣ መብራት፣ ትምህርት፣ ጤና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን ማቅረብ እያቃታቸው ያሉ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከ1.7 ቢሊዮን ራንድ በላይ የክሊኒክና የሌሎች መሠረተ ልማቶች ወጪ መጥፋቱን ሰምተናል፡፡ ከተሞች ለዜጎች ሥራ መፍጠር እያቃታቸው አገሪቱ በኢኮኖሚ እየደከመች ነው ያለችው፡፡ ይህ ሁሉ የኢኮኖሚ ችግር ሕዝቡን እንዲቆጣና በውጭ ስደተኞች ላይ እንዲነሳ ያደርገዋል፡፡ ሕዝቡ ስደተኞች ይሁኑ የራሱ አገር ፖለቲከኞች ለውድቀቱ ጥፋተኞቹን ሳይለይ ነው በስሜት የሚወጣው፡፡ ከበስተኋላ ይህን የሚቀሰቅሱ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞችም ብዙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ደቡብ የአፍሪካውያንን ሥራ ሁለት በመቶ እንኳን አይሻሙም፡፡ ሱቅ በደረቴ ሠርተውና ለፍተው ነው የሚተዳደሩት፡፡ እንዲህ ለፍተው ለአገርና ለወገን ለመትረፍ ከሚታትሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ግን እከሌ ዕቁብ ደርሶታል ብለው በገንዘብ የአገራቸውን ልጅ ለማስገደል የሚያሴሩ ጥቂቶች አሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ በመክፈል ሰዎችን ከሚያስገድሉ ኮሙዩኒቲዎች መካከል ኢትዮጵያውያን በሦስተኝነት ተቀምጠዋል፡፡ ናይጄሪያውያን በአደገኛ ዕፅና በወጣቶች ወንጀል እንደሚጠሩት ሁሉ በጥቂት መጥፎ ሰዎች የተነሳ ኢትዮጵያውያን እየተወቀሱ ነው፡፡ የኮሙዩኒቲ ወኪልና የማኅበር መሪ ነን የሚሉ ጥቂት የማይባሉ የማኅበረሰቡን ችግር ሳይሆን፣ የራሳቸውን ኪስ እየሞሉ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ተረማምደዋል፡፡ ማኅበረሰባችን እዚህ አገር የተበደለ ነው፡፡ አንዳንድ ዲፕሎማት ወይም የቆንስላ ሰው ነን የሚሉም ቢሆኑ እስከ ሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ወንጀል ድረስ በሕገወጥ ድርጊት ሲነከሩ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያውያኑ ብሶት ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ዘንድ ካልደረሰ በቀር የሚፈታ አይመስለኝም፡፡ እዚህ እሳቸው ሲመጡ ወጥቶ በሞቀ ሁኔታ የተቀበላቸው ዳያስፖራ ዕርዳታቸውን ይፈልጋል፡፡ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ገንዘብ ይዋጣ ሲባል፣ ለመከላከያና ለአገር ጥሪ ሲደረግ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ የአቅሙን በማድረግ የሚታወቅ ነው፡፡ መንግሥት ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ ሁኔታ ግለቱና ትኩሳቱ የሚፈጥረው የዜኖፎቢያ ጥቃትም ቀላል መነሻ አለመሆኑን አስተያየት ሰጪው ጠቁመዋል፡፡ በቅርቡ በሰኔ ወር አካባቢ በደቡብ አፍሪካ ምርጫ እንደሚደረግ በመጥቀስ፣ የአሁኑ ጥቃትም የዚያ አንዱ ነፀብራቅ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ኤኤንሲ ፓርቲ፣ የነጮች ፓርቲ፣ የህንዶችና የክልሶች ቡድን እየተባለ በሚደረገው የመመረጥ ፉክክር የውጭ ሰዎችን የሁሉም ነገር ችግር አድርጎ መወንጀልና በእነሱ ላይ መዝመት የተለመደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው የሃይማኖትና የብሔር መከፋፈል፣ እንዲሁም እርስ በእርስ የመጠራጠር አኗኗር ለተለያየ ወንጀል እያጋለጣቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሁለት መልክ ያለው ችግር ነው የሚስተዋለው፡፡ አንድ መጤ ተብለው በደቡብ አፍሪካውያን የጥቃት ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ የራሳቸውን ወገን እየተጠራጠሩ በሥጋት ነው የሚኖሩት፤›› በማለት ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡
የአፍሪካ ደኅንነት ጥናት ኢንስቲትዩት (ISS Africa) አንድ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአፍሪካ የውጭ አገሮች ስደተኞችን በመቀበል ቀዳሚ አሥር አገሮች ዝርዝር ውስጥ ደቡብ አፍሪካን የሚቀድሙ አገሮች አሉ፡፡ በዚህ ዝርዝር ኮትዲቯር አምስት ሚሊዮን ስደተኞችን በማስተናገድ ቀዳሚ ስትባል፣ ደቡብ አፍሪካ 3.6 ሚሊዮን ታስተናግዳለች፡፡ ኡጋንዳ 1.7 ሚሊዮን፣ ሱዳን 1.3 ሚሊዮን፣ ናይጄሪያ 1.3 ሚሊዮን፣ ኢትዮጵያ 1.1 ሚሊዮን፣ ኬንያ አንድ ሚሊዮን፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ 950 ሺሕ፣ ደቡብ ሱዳን 880 ሺሕ፣ ሊቢያ 830 ሺሕ የውጭ አገሮች ዜጎችን በማስተናገድ በቅደም ተከተል ተዘርዝረዋል፡፡ ካላት የሕዝብ ቁጥር፣ የኢኮኖሚ ጥንካሬና የቆዳ ስፋት አኳያ ደቡብ አፍሪካ የተቀበለችው የውጭ ስደተኛ ተፅዕኖውም ሆነ ብዛቱ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ይነገራል፡፡ ይህም ሆኖ ደቡብ አፍሪካ በዓለም ብቸኛዋ ስደተኛ ተቀባይ የሆነች ይመስል፣ በውጭ ስደተኞች ላይ ከባድ የጥላቻ ዘመቻ እንደሚካሄድ በትችት ሲቀርብባት በስፋት ይደመጣል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በቢቢሲ አፍሪካ አይ ፕሮግራም ላይ ስለዜኖፎቢያ ሰፊ ዘገባ ያቀረበችው ደቡብ አፍሪካዊቷ ጋዜጠኛ አያንዳ ቻርሊ፣ የዜኖፎቢያ ጥቃትን ምንም ዓይነት አመክንዮ ትክክል እንደማያደርገው ተናግራ ነበር፡፡ ‹‹ኦፕሬሽን ዶዶላ›› የተባለውን ስደተኞችን የሚያሳድድ ቡድን በቅርበት የመረመረችው ዘጋቢዋ ሥራችንን ነጠቁን፣ በወንጀል መረዙን፣ እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ ገብተው ወረሩን የሚሉ ሰዎችን ፊት ለፊት ተጋፍጣቸዋለች፡፡
በስተመጨረሻም፣ ‹‹እኔም ከደሃ ቤተሰብ የወጣሁ ደቡብ አፍሪካዊት ነኝ፡፡ እዚህ ያለሁበት ቦታ ለመድረስ ቀላል ልፋት አልጠየቀኝም፡፡ አሁንም ከቤተሰቦቼ መካከል በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ችግር ሌሎችን በጠላትነት እንድመለከትና እንዳጠቃ በቂ ምክንያት ሊሆን በፍፁም አይችልም፤›› በማለት ነው ጋዜጠኛዋ ጠንካራ መልዕክት በዶክመንተሪ ዘገባዋ ያስተላለፈችው፡፡
ደቡብ አፍሪካ በአሰቃቂው የአፓርታይድ አገዛዝ ዘመን ስትማቅቅ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮች መንግሥታትና ዜጎች ከጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ጎን ተሠልፈው ድጋፍ ሲሰጡ እንደነበር ታሪክ ከትቦታል፡፡ ታዋቂው የኦፌኮ ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹በእኛ ዘመን የነበረው ለውጥ ጠያቂ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከራሱ አልፎ የአፓርታይድ አገዛዝ ከደቡብ አፍሪካ ይወገድ፣ እንዲሁም የቬትናም ወረራ ይቁም የሚል ጥያቄ ሳይቀር ያቀርብ ነበር፤›› ሲሉ እንደተናገሩት ሁሉ፣ በቀደመው ዘመን የነበሩ ተራማጅ ኢትዮጵያውያን ለደቡብ አፍሪካ ነፃነት ድምፅ ሆነው ነበር፡፡
በጊዜው የነበረው ዘውዳዊው የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ይህን እንደ አንድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ተቀብሎ ሲያራምደው መቆየቱን ታሪክ ከትቦታል፡፡ ለአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲና ለጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን ትግል የአፄው መንግሥት ቀጥተኛ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ዛሬ በደምፍላት ተሞልተው ለነጮች ሸጠውናል ሲሉ የሚወነጅሏቸውን ኔልሰን ሮሂላላ ማዲባ ማንዴላን የመሳሰሉ የነፃነት ታጋዮችን ኢትዮጵያ ድረስ በማስመጣት፣ ወታደራዊ ሥልጠና ሰጥቶ ለትግል በማሰማራት ትልቅ አስተዋጽኦም አድርጓል፡፡ ዘውዳዊውን መንግሥት የተካው የደርግ መንግሥትም ይህንኑ ድጋፍ አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ከአፓርታይድ የዘር መድልኦ ሥርዓት እስኪላቀቁ ይኸው አጋርነት ከኢትዮጵያ አልተለያቸውም፡፡ ማንዴላ ራሳቸው፣ ‹‹አውሮፓና አሜሪካ ከምመላለስ ኢትዮጵያን ብረግጥ እመርጣለሁ፤›› በማለት ‹‹ረዥሙ የነፃነት ጉዞ›› በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደከተቡት ሁሉ፣ የደቡብ አፍሪካ የነፃነት አባቶች ለኢትዮጵያ ውለታ ያላቸውን ክብርና አድናቆት ሳይሰስቱ በመግለጽ ይታወቃሉ፡፡ ይህ ሁሉ የቅርብ ጊዜ የታሪክ ትዝታ ቢሆንም፣ አሁን ባለችው ደቡብ አፍሪካ አንዳንድ ፖለቲከኞችና የሚከተሏቸው ዜጎች ኢትዮጵያውያንና የአፍሪካ ስደተኞችን በማሳደድ ተጠምደዋል፡፡
