- የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ከሚገነባቸው 60 የመንገድ ፕሮጀክቶች አምስቱ ብቻ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቃቸው ተገልጿል
የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና ዘርፉ በፀጥታ ችግር ምክንያት ‹‹ከፍተኛ ስብራት›› እንደገጠመው አስታወቀ፡፡ የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዘመን 12ኛ መደበኛ ሰብሳቢውን ከሐምሌ 23 ቀን ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በባህር ዳር አካሂዷል፡፡
በስብሰባው የክልሉን መንግሥት ዓመታዊ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ፕሬዚዳንቱ አቶ አረጋ ከበደ፣ የክልሉ ጥቅል ምርት በ2013 በጀት ዓመት ከነበረው 242.5 ቢሊዮን ብር በ2017 በጀት ዓመት 400 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በክልሉ በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም የተመዘገበው አበረታች የኢኮኖሚ ዕድገት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው መሆኑ የተረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅለልና ረዘም ብሎ የቀረበውን የፕሬዚዳንቱን ሪፖርት ተከትሎ በምክር ቤቱ የግብርና አካባቢ ጥበቃና ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከፍያለው ሙላቴ ባቀረቡት አስተያየት፣ ‹‹በገጠመን የፀጥታ ችግር ምክንያት ከፍተኛ ስብራት ከገጠማቸው ውስጥ የግብርና ዘርፍ አንዱ ሲሆን፣ ኤክስቴንሽን ደግሞ ዋነኛው ነው የሚል እምነት አለን፤›› ብለዋል።
የአብዛኞቹ ቀበሌዎች ግብርና በሙያተኞች ተደራሽ አይደለም፣ መድረስ ቢቻል እንኳ ተረጋግቶ መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ ጠባብ ነው ያሉት ሰብሳቢው፣ የምርምርና የኤክስቴንሽን ሥራዎች በሚፈለገው ደረጃ ውህደት አልፈጠሩም ብለዋል፡፡ ‹‹በፍላጎታችን ልክ ነው ተብሎ ባይወሰድም ዋጋ ተከፍሎበት እየቀረበ ያለ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በተለያዩ ምክንያቶች ሳይቀርብ ያድራል፤›› ያሉት አቶ ከፍያለው፣ ‹‹ከቢሮው አቅም በላይ በሆነ ሁኔታ የማዳበሪያ ሥርጭቱን ለሌሎች ክፍያዎች ማስገደጃ ወይም ማስያዣ የማድረጉ ጉዳይ የአርሶ አደሩን አቅም ተፈታትኖታል፤›› በማለት ተናግረዋል። ‹‹የምርጥ ዘር ሥርጭት ሥራችንም ከአድልኦ ተፅዕኖ የነፃ አይደለም፤›› ብለዋል።
በመሬት ላይ ያለውን ሕገወጥ ተጠቃሚነትን ለመግታት የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ፣ አሁንም በገጠርም ሆነ በከተማ መሬት፣ የመሬት ወረራና ሕገወጥ ግንባታ አለመቀነሱን፣ በበርካታ ከተሞች በኢንቨስትመንት ስም ታጥረው የተቀመጡ ይዞታዎች እንደሆኑ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
በገጠር አካባቢ በተለይ ለእርሻ ኢንቨስትመንትን መሬት የተሰጠ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ባለሀብቶች ከሥራ ውጪ መሆናቸውንና መሬቱም ለብክነትና ለሕገወጥነት እየተጋለጠ ስለሆነ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የምክር ቤቱ የኢንቨስትመንት ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በላይ ዘለቀ ባደረጉት ንግግር፣ በፌዴራል መንግሥት እየተገነቡ ያሉ በርካታ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት አለመሆናቸውን፣ ከ64 ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁት አምስት ብቻ ናቸው ብለዋል።
From The Reporter Magazine
በሚቀጥለው በጀት ዓመት ችግሮችን በፍጥነት በመፍታት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ማድረግ፣ ተጀምረው የቆዩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ ተጠይቀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በመንገድ ትራፊክ አደጋ በደረሱ 1,512 አደጋዎች 647 የሞት፣ 1,726 ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት፣ በአጠቃላይ 2,373 ጉዳቶች መድረሳቸውን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገልጸዋል፡፡
የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ የጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበራሽ ታደሰ በበኩላቸው፣ በትምህርት ዘርፍ ባቀረቡት አስተያየት የሁለተኛ ደረጃ ተሳትፎ ተገምግሞ ዝቅተኛ አፈጻጸም ላይ በመሆኑ፣ በመጪው ትውልድና በክልሉ ብሎም በአገሪቱ የነገ ዕጣ ፈንታ ላይ ሊያስከትል የሚችለው የተራዘመ ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው በጣም እየቀነሰ የመጣውን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተሳትፎና የሌሎችንም የትምህርት ደረጃዎች ችግሮች በመገምገም የተፋጠነ ሥራ ሊከናወን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
From The Reporter Magazine
በተገባደደው የ2018 ዓ.ም. በጀት ዓመት ብቻ 505 ሕፃናት ያለ ዕድሜ ጋብቻ መፈጸማቸውን፣ በ1,391 ሕፃናት ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር፣ በ115 ሴቶች የጠለፋ ጥቃት፣ በ3,473 ሴቶች ድብደባና ጥቃት፣ እንዲሁም በ13,656 ሴቶች ላይ የንብረት መነጠቅን ጨምሮ የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አረጋ የመንግሥታቸውን አፈጻጸም ሲያቀርቡ፣ በ2018 በጀት ዓመት ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝግብ ታቅዶ አራት ሚሊዮን ተማሪዎችን ብቻ መመዝገብ መቻሉን ገልጸው፣ ‹‹በጣም ከፍተኛ ጥረት ያደረግንበት ዓመት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን 60 በመቶ እንኳን የማይሞላ ማለት ነው፡፡ ይህም ያው በምታውቁት ችግር ምክንያት ዕቅዱን ማሳካት አልቻለም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በግብርና ዘርፍ 427 ሺሕ፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለ283 ሺሕ፣ በአገልግሎት ዘርፍ ለ615 ሺሕ፣ በአጠቃላይ ለ1.3 ሚሊዮን ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ 141 ሺሕ ያህሉ የክልሉ ተወላጆች ሲሆኑ በሕጋዊ የውጭ አገር ሥምሪት ያገኙ ናቸው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል በሲቪል ሰርቪስ ሕግ የሚመሩ ወደ 470 ሺሕ ሠራተኞች እንዳሉ ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡