
የኢትዮጵያ ታምርት የአሥር ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን መስፈርት እንዲሰጠው በቀጣዩ ዓመት እንደሚጠይቁ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጹ
ይኼ የተገለጸው የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የሆነው፣ የ2018 ዓ.ም ኤክስፖ የአሥር ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድርን አስመልክቶ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋራ ዛሬ ሚያዚያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ነው።
መግለጫውን የሰጡት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የሆነው የ2018 ዓ.ም ኤክስፖ የአሥር ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር አስተባባሪ አቶ አብድልፈታ የሱፍ፣ ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ስምምነት በማድረግ፣ ከዘንድሮ ጀምሮ የአገር አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድርን መስፈርት እንዲያሟላ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም በውድድሩ የሚገኘው ውጤት ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑንና በቀጣዩ ዓመት ደግሞ የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን የአሥር ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድርን መስፍርት እንዲያሟላ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ጊዜ አድነው በበኩላቸው፣ ውድድሩ በዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እውቅና እንዲያገኝ ለማድረግ የሚከብድ ነገር አለመኖሩን፣ መስፈርቱን ማሟላት ብቻ እንደሚጠይቅ፣ ዘንድሮም ያልተሳካው ጥቂት መስፈርቶች ባለመሟላታቸው ብቻ መሆኑን፣ በቀጣይ ዓመት ግን ይሳካል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በቀጣይ በኢትዮጵያ የሚደረጉ ተመሳሳይ ውድድሮች በዘርፉ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች የመስፈርት ልኬት ተከደርጎባቸው ብቻ እንዲዘጋጁ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ጊዜ፣ ይህንን የልኬት ሥራ የሚከውኑ ሦስት በ “ኤ” ሁለት ደግሞ በ “ቢ” ደረጃ በድምሩ አምስት ባለሙያዎች መኖራቸውንና አራቱ በሥራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አካላት ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
From The Reporter Magazine
መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ በመጪው እሁድ ሚያዚያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው በዘንድሮው ውድድር 15 ሺሕ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ፣ ከእነዚህም ውስጥ 500 ያህሉ በክለብና በግል የሚወዳደሩ ታዋቂ አትሌቶች መሆናቸውን አቶ አብድልፈታ ገልጸዋል።
የተሳታፊዎች ምዝገባ እስከ ነገ ሚያዚያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ስለሚካሄድ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል አቶ ጊዜ ተናግረዋል።
በውድድሩ በወንድና በሴት ዘርፍ አንደኛ ደረጃ ለሚወጡ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 550 ሺ ብር፣ ሁለተኛ ለሚወጡ 300 ሺሕ ብር፣ ሦስተኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁ ደግሞ 200 ሺሕ ብር ሽልማት እንደሚበረከትላቸው አስተባባሪው ገልጸዋል። የዘንድሮው ውድድር ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑ ተነግሯል።
From The Reporter Magazine
በዘንድሮው ውድድር አንደኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ አትሌቶች የሚያገኙት ሽልማት በኢትዮጵያ በሚደረጉ የአትሌቲክስ ውድድሮች ታሪክ ከፍተኛው ሽልማት መሆኑ ተገልጿል።
ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት፣ ማኅበረሰቡ የአገሩን ምርቶች እንዲጠቀም ማበረታታትና በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ዓላማ ያደረገው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የሆነው የ2018 ዓ.ም ኤክስፖ ከሚያዚያ 24 እስከ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ “ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬሽን ሴንተር በተለያዩ መርሐግብሮች እንደሚካሄድ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።