
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ክትፎን ጨምሮ ከጉራጌ ማንነት መገለጫ ውስጥ የሚጠቀሱትን አራት ዕሴቶች በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ እየሠራ ይገኛል፡፡
ሚያዝያ 6 ቀን 2018 ዓ.ም. የጉራጌ ዞን መስተዳድር ምክር ቤት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራትን በወልቂጤ ከተማ በገመገመበት ወቅት ሪፖርት ያቀረቡት የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ እንደገለጹት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተከናወኑ ሥራዎች የጉራጌ ማኅበረሰብ መገለጫ ከሆኑት የተወሰኑትን በማስቀደም በዩኔስኮ የማስመዝገብ ሥራዎች መከናወናቸው ይገኙበታል፡፡
ይህንን አስመልክቶ ከሪፖርተር ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ወ/ሮ መሠረት፣ የጉራጌ ማኅበረሰብ ከጥንት ጀምሮ በርካታ መገለጫዎች ያሉትና ባህልና ታሪክን ገንብቶ ለትውልድ ያሻገረ ቢሆንም፣ ከጢያ መካነ ቅርስ በስተቀር አብዛኞቹ ቅርሶቹ በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመዝግበው እንደማይገኙ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ማኅበረሰቡ ካሉት ቅርሶች የተወሰኑት ቢወጡና በዩኔስኮ የቅርስ መዝገብ ቢመዘገቡ ዓለም ይማርባቸዋል፣ እንደ አገርም ለቱሪዝም ዘርፍ ይጠቅማል፣ እንደ ማኅበረሰብም ዕሴቱ እንዲታወቅ ይረዳል በሚል ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከቅርስ ባለሥልጣንና ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በቅርስነት የማስመዝገብ ሥራ ከተጀመረባቸው አንዱ ክትፎ ሲሆን፣ የገጠር ኮሪደር ልማት ተምሳሌት የሆነው ጀፎረ ወይም የጉራጌ ባህላዊ መንደር ደግሞ ሌላው ነው፡፡
የጉራጌ ማኅበረሰብ ዴሞክራሲን ተግባራዊ የሚያደርግበት የጆካ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓትም፣ በዓለም ቅርስነት መዝገብ እንዲሰፍር ለማድረግ ሥራ ከተጀመረባቸው መገለጫዎች ይገኝበታል፡፡
ማኅበረሰቡ ከጥንት ጀምሮ ለሴት ልጅ መብት የሰጠ መሆኑን በ‹‹የቃቄ ውርዶት››፣ የእናቶችን ቀን በ‹‹አንትሮሽት›› እንዲሁም የልጃገረዶችን ቀን በ‹‹ነቆ›› ማሳየቱን ያስታወሱት ወ/ሮ መሠረት፣ የጆካ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓትን ማስመዝገብ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
From The Reporter Magazine
የራሱ የሆነ አገር በቀል ዕውቀት የታከለበት፣ እስከ 150 ዓመት ድረስ የሚያገለግል፣ ከወላጅ እየተወራረሰ የሚቆይና በአገር በቀል ዕውቀት ዲዛይን የሚደረገውና ጥበብ የሚታይበት የጉራጌ ባህላዊ ቤትም ‹‹ጎጆ ቤት›› በድርጅቱ እንዲመዘገቡ ሥራ ከተጀመረባቸው ውስጥ ተካቷል፡፡
እንደ ወ/ሮ መሠረት፣ አንድ ማኅበረሰብ ወካይ ቅርሱን ባንድ ጊዜ ሁለትና ከዚያ በላይ ማስመዝገብ ስለማይቻል ቅድሚያ ለጉራጌ ክትፎ ተሰጥቶ ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ ጥናት ሲደረግና ሲገመገም ቆይቷል፡፡
ክትፎን ለማስመዝገብ የተቀመጡ መሥፈርቶች ስለመሟላታቸው የቫሊዴሽን ሥራው በ2018 ሁለተኛ ሩብ ዓመት መገምገሙን፣ የሁለቱም ጉራጌ አስተዳደር፣ ቅርስ ባለሥልጣን፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ሌሎችም በተገኙበት አስተያየት እንደተሰጠበትም አክለዋል፡፡
From The Reporter Magazine
በዩኔስኮ ለመመረጥ በተቀመጡ የግምገማ ደረጃዎች መሠረትም አስተያየት ተሰጥቶበት ለዩኔስኮ የሚላክበትና ወረፋ የሚያዝበት ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
ጀፎረን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስመዝገብ ቀድሞ የተጠየቀውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የማሟላት ሥራ መጀመሩንና በዞኑ ደረጃ ጀፎረ ደረጃውንና ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እንክብካቤና ጥበቃ እንዲደረግለት እየተሠራ እንደሚገኝ ያስታወሱት ወ/ሮ መሠረት፣ የማስዋብ፣ አላግባብ የታጠሩትን ወደ ቦታቸው የመመለስ፣ ባህላዊ ልኬቱን እንዲጠብቅ የማድረግ እንቅስቃሴ መኖሩንም ገልጸዋል፡፡
ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ወደ 600 ኪሎ ሜትር ጀፎሮች መልማታቸውንና 138 ጀፎረዎችም በየአካባቢው ተለይተው ወደ መረጃ ቋት የማስገባት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በጉራጌ የክትፎ አሠራር
በጉራጌ ሕዝብ ማዕድ አይብ በጎመን (ዝማሞጃት) በቆጮ፣ ኧቆት በቆጮ፣ አዴ በቆጮ፣ የጎመን ክትፎ በቆጮ፣ አይብና ሌሎችም የሚቀርቡ ቢሆንም፣ ክትፎ ብሔረሰቡ በዋናነት የሚታወቅበት ባህላዊ ምግብ ነው። በልዩ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ለምግብነት የሚቀርበውን ክትፎ ለማዘጋጀት ቀይ ሥጋ ያስፈልጋል። የክትፎ ሥጋ የሚከተፈው በእጅ ነው፡፡ የተከተፈውን ሥጋ ለመደባለቅም ኮረሪማ፣ ጥቁርና ነጭ አዝሙድ፣ ኮሰረት እንዲሁም ዋች ቅመሞች ተከተው የተነጠረ ቅቤ ያስፈልጋል፡፡ ሚጥሚጣውም የሚዘጋጀው ቅቤ ላይ የሚጨመሩ ቅመሞች ተጨምረውበት ነው፡፡ የተከተፈውን ቀይ ሥጋ በሸክላ ከተሠራ (ሴራ) የሚባል የክትፎ መደባለቂያ በማድረግ፣ ሚጥሚጣና ቅቤ ጨምሮ በማዋሃድ ይዘጋጃል፡፡
የጆካ ቂጫ ባህላዊ የዳኝነት ሥነ ሥርዓት
ቂጫ የጉራጊኛ ቃል ሲሆን፣ ጥሬ ትርጉሙም ደንብ፣ ሥርዓት፣ ሕግ ማለት ነው፡፡ መደበኛ የሕግ ክፍሎችም አሉት፡፡ የፍትሐ ብሔር፣ የወንጀልና የቤተሰብ (የጋብቻ) ሥነ ሥርዓት (ሕግጋት) በውስጡ ይዟል፡፡
የአንቂት ቂጫ – ይህ ደንብ በአጠቃላይ የጋብቻና የፍቺ ሥነ ሥርዓት የተደነገገበት ሲሆን፣ የአተጫጨት፣ የቸግ ወይም የኒካና የሠርግ እንዲሁም የፍቺ አፈጻጸም የሚዳኝበት ሥርዓት ወይም ደንብ ነው፡፡
የቅየ ቂጫ – በሁለት ወሰንተኞች መካከል የድንበር መገፋፋት እንዳይኖር በሁለት ወገኞች ስምምነት በሚመረጡ ሽማግሌዎች አማካይነት በቃለ መሐላ (ጉርዳ) የድንበር ድንጋይ የሚተከልበትና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ግጭቶች የሚፈቱበት ደንብ ነው፡፡
የጉርዳ ቂጫ- የቃል ኪዳን ስምምነት ሲሆን፣ ሥርዓቱ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ወገኖች በመካከላቸው መጠቃቃት፣ መከዳዳት፣ አለመተማመን እንዳይኖርና በመተጋገዝ፣ በመተማመንና በመግባባት ግጭትን አስወግደው ጉዳያቸው መልካም ፍጻሜ እንዲያገኝ የሚጠቀሙበት፣ እርስ በእርሳቸው የሚገቡት የቃል ኪዳን ሥርዓት ነው፡፡
የደም ቂጫ – ለጠፋ ወይም ለተፈጸመ ወንጀል ማካካሻ የሚሆን በዳይ ወገኖች ለድርድር የሚቀርቡትና በጉርዳ ሥርዓት የጉዳት ካሳ እንዲከፍሉ የሚደረግበት አሠራር ነው፡፡
የጀፎረ ቂጫ – በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ መንደርተኞች ፊት ለፊት ወይም መካከል የሚገኘው ጎዳና ለአካባቢው ኅብረተሰብ መተላለፊያነት ከማገልገል ባለፈ እርሻ እንዳይደርስባቸው ተገቢው ቁጥጥርና ክትትል እንዲደረግ የሚያስገድድ ሥርዓት ነው፡፡
የጆካ ቂጫ የዳኝነት ሥርዓት፣ በየእርከኑ በተዋረድ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን፣ በመጨረሻም የተፈረደበት አካል ትክክለኛ ውሳኔ አላገኘሁም ብሎ ካመነ፣ የሥልጣኑን ተዋረድ ተከትሎ ይግባኝ ሊጠይቅ ብሎም እስከ አጠቃላይ የቤተ ጉራጌ ሸንጎ ሊሄድ የሚችልበት ነው፡፡
የጉራጌ ባህላዊ ቤት አሠራር
ከጉራጌ ዞን የጉመር ወረዳ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ገጽ ባገኘነው መረጃ መሠረት፣ ከጉራጌ ሕዝብ መገለጫዎች አንዱ ባህላዊ የሳር ቤት ‹‹ጎጆ ቤት›› አሠራር ነው፡፡ በጉራጌ ሕዝብ ባህላዊ የቤትና የመንደር አመሠራረት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት የሚከናወን ተግባር ነው። ማህበረሰቡ ዘመናዊ የምሕንድስና ትምህርት ምን እንደሆነ ሳያውቅ ጀምሮ የሳር ቤት አወቃቀርና የመንደር አመሠራረት እንዲሁም የቤት አያያዝና አጋጌጥን የሚያውቅ ነው፡፡ የጉራጌ ባህላዊ ጎጆ ቤት አንድ ምስማር ወይም የፋብሪካ ውጤት ሳይገባበት ተሠርቶ ከ100 እስከ 150 ዓመት ምንም ሳይሆን አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው፡፡ ባህላዊ ቤቶቹ በሦስት ደረጃ የሚከፈሉ ሲሆን፣ እነሱም ጎየ ‹‹ትልቅ ቤት››፣ ኸራር ‹‹እልፍኝ ቤት›› እና ዘገር ‹‹የሙሽሮች ቤት›› በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከስንደዶ፣ ከሸክላ፣ ከእንጨት፣ ከእንሰት ዉጤቶች ‹‹ቃጫና ገመድ›› በመጠቀም እንዲሁም ከእንስሳት ተረፈ ምርቶች ማለትም ከቆዳ፣ ከቀንድ፣ ከጭራና ከመሳሰሉት የተዘጋጁ ቁሳቁሶችም ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡
ባህላዊ ቤቱ ሲገነባ ቤት የሚሠራው አባወራ ለቤቱ መሥሪያ የሚሆኑ ቁሳቁስ ያሰባስባል፡፡ በአካባቢው ኅብረተሰብ ደግሞ አንድ አባወራ ቤት ሲሠራ ሌላ ዳር ሆኖ መመልከት የማይታሰብና እንደ ነውር የሚታይ ስለሆነ፣ ሁሉም ተባብረው ቤቱን በጋራ የመሥራት ባህል የተለመደ ዕሴት ነው፡፡
ጀፎረ/ጀፎሮ
በጉራጌኛ ‹‹ጀፎረ›› ማለት አውራ መንገድ ማለት ነው፡፡ ጀፎረ ከመሠረታዊ ጠቀሜታው ባለፈ ለጉራጌ መንደሮች ውበትን በማላበስ የጎላ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በጉራጌ የመንደር አመሠራረት ያለ ጀፎረ አይታሰብም፡፡ ጀፎረ አረንጓዴ ሳር የለበሰና በሁለት ትይዩ መንደርተኞች መካከል የሚገኝ ሰፊና ማራኪ አውራ መንገድ ነው፡፡ ለአካባቢው ነዋሪዎች መግቢያና መውጫ እንዲሁም መተላለፊያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ እስከ 60 ሜትር ድረስ ስፋት ያለው ይህ የወል መንገድ፣ ከመንገድነት ባሻገር ለተለያዩ ማኅበራዊ ኩነቶች ያገለግላል፡፡ እንደ ሠርግ ያሉ የደስታ፣ እንደ ለቅሶ ያሉ የሐዘን ማኅበራዊ ሥነ ሥርዓቶች መከወኛ ሥፍራም ነው፡፡ በሠርግ ወቅት ሠርገኞች የሚጨፍሩበት፣ አባቶችና እናቶች እንዲሁም የሠፈር አዛውንቶች ልጆቻቸውን መርቀው የሚሰጡበት ቦታ ነው፡፡ ጀፎረ የለተለያዩ ስብሰባዎች፣ የፈረስ ጉግስ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትዕይንቶች የሚካሄዱበትም ነው፡፡ እረኞች ከብቶቻቸውን የሚያመላልሱበት በዚሁ ጀፎረ በተባለው የወል ሥፍራ ነው፡፡ በጉራጌ ባህል ጀፎረ ወይም ባህላዊ አውራ መንገድን አጥሮ ወደ ግል ማካለል የተወገዘ ተግባር ነው፡፡ ይህን ሥርዓት ተላላልፎ የተገኘ ግለሰብ ቢኖር፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያጣል፡፡ ከማንኛውም ማኅበራዊ ግንኙነት ይገለላል፡፡ ጉራጌ ጀፎረን መቀየስ የጀመረው ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት እንደሆነ ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡