- የአገር ውስጥ የንግድ ምልክት ያገኙ ምርቶችና አገልግሎቶች 14,914 ናቸው ተብሏል

በኢትዮጵያ የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት ብቸኛ መብት (ፓተንት) ጥበቃ የሚደረግላቸው የፈጠራ ሥራዎች ብዛት ከአንድ ሺሕ እንደማይበልጥ፣ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ይህን የገለጸው የአዕምሯዊ ንብረት ዘርፍን፣ ተቋሙንና አገልግሎቶቹን በተመለከተ ሚያዚያ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት ሲያደርግ ነው።
በውይይቱ ወቅት በንግድ ምልክት፣ በቅጅና ተዛማጅ፣ እንዲሁም በፈጠራ ሥራዎች የአዕምሯዊ መብት ምዝገባ ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ ማነስ ችግር እንዳለ ተገልጿል።
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሉ ሞሲሳ፣ ባለሥልጣኑ በኢንዱስትሪያዊ ንብረትና በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ዘርፍ ሥር ሦስት አዋጆችን ማለትም የፈጠራ ሥራ ብቸኛ መብት (ፓተንት)፣ የንግድ ምልክትና ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ የሚሉትን እያስተዳደረ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የጂኦግራፊያዊ ምንጭ አመልካቾች አዋጅ በቅርቡ ፀድቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል። ባለሥልጣኑ በኢትዮጵያ የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት ብቸኛ መብት (ፓተንት) ጥበቃ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር መሆኗ እንደሚነገር፣ ሆኖም ጥበቃ የሚደረግላቸው የዜጎች ፈጠራ ሥራዎች ብዛት በጣም ዝቅተኛ መሆኑንና ከአንድ ሺሕ እንደማይበልጥ ገልጸዋል።
በአንፃሩ ቻይና በዓመት እስከ 2.6 ሚሊዮን ለሚሆኑ የፈጠራ ሥራዎች የመብት ጥበቃ እንደምታደርግ ገልጸው፣ በኢትዮጵያ ያሉትን ፈጠራዎች መዝግቦ በአግባቡ ወደ እሴት ለመቀየር የጋራ ሥራ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
የባለሥልጣኑ የፓተንት መብቶች የምርምራ ባለሙያ አቶ ጀሚል ሙክታር በበኩላቸው፣ ባለሥልጣኑ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ለፈጠራ ሥራዎች የመብት ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
From The Reporter Magazine
ባለፉት 15 ዓመታትም የመብት ጥበቃ የሚያስገኘውን ጥቅም አውቀው ፈጠራቸውን ያስመዘገቡት 1,000 እንኳ እንደማይሞሉ፣ ከእነዚህም ውስጥ በባለሥልጣኑ ሰርተፊኬት የተሰጣቸው ከ300 እንደማይበልጡ ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ ስለአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን ወደ ባለሥልጣኑ በማምጣት አለማስመዝገብ ለቁጥሩ አነስተኛ መሆን ዋናው ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል።
ባለሥልጣኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ግምገማ በማድረግ በዋናነት ጥናትና ምርምር ይደረግባቸዋል በሚባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
From The Reporter Magazine
‹‹ይህም የፈጠራ ሐሳቦችን ወደ እሴትነት በመቀየር ረገድ ለአገር ብልፅግና ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፤›› ብለዋል።
ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች የሚመዘገቡ የፈጠራ ሥራዎች እየጨመሩ እንደሆነ፣ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በዚሁ ረገድ የሚጠቀሱ ተቋማት መሆናቸውን አብራርተዋል።
ባለሥልጣኑ በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ የፈጠራ መብት ጥበቃ ብዛትን ከአምስት ሺሕ በላይ ለማድረግ እንደሚሠራ ጠቅሰዋል።
የባለሥልጣኑ የንግድ ምልክት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ትግሥት ቦጋለ፣ የንግድ ምልክት ሰዎች ምርቶችና አገልግሎታቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ በማድረግ የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ሆኖም በአገር ደረጃ በዘርፉ ምዝገባና የመብት ጥበቃ ሥራዎችን በተመለከተ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል።
ለአብነት ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ የንግድ ምልክት ለማግኘት ከአገር ውስጥ ከቀረቡ 20,803 ማመልከቻዎች ውስጥ ምዝገባ ያገኙት 14,914 ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የውጭ አገር ማመልከቻዎች 17,000 ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ 15,945 መመዝገባቸውን፣ ባለፉት 15 ዓመታት በአጠቃላይ ከአገር ውስጥና ከውጭ 37,803 የንግድ ምልክት ማመልከቻዎች ቀርበው፣ የተመዘገቡት 30,769 መሆናቸውን አክለዋል።
የማመልከቻ ብዛት ትንሽ መሆኑን፣ ሰፊ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚጠይቅና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ወ/ሮ ትግሥት አስረድተዋል።
በዘርፉ ያለውን ችግር በመሠረታዊነት ለመፍታት የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ጥበቃ በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንስቶ እስከ መደበኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች ድረሰ ወርዶ እንዲሠራበት ማድረግ እንደሚገባ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ እንዳሉ ተናግረዋል።
በዚሁ ረገድ ባለሥልጣኑ የአዕምሯዊ ንብረት አካዴሚ እንዲኖርና ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶችን መሠረት ላደረጉ ሥልጠናዎች ሰርተፊኬት ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የባለሥልጣኑ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወሰን ሙሉ በበኩላቸው፣ የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ጥበቃ በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ እንዲሰጥ በተቋሙ ረቂቅ ፖሊሲ ውስጥ እንዲካተት መደረጉን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሥልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችል አካዴሚ እንደሚቋቋም ገልጸዋል።
ይህም የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በበቂ ሁኔታ ማሳደግ እንደሚያስችልና አዕምሯዊ ንብረት የልማት መሣሪያ መሆኑን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
የአዕምሯዊ ንብረት ሥራዎችን ለማስፋፋት፣ ከጊዜው ጋር አብረው እንዲሄዱ ለማስቻልና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ አዋጆችን ማሻሻልን ጨምሮ፣ ሌሎች የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ ገልጿል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የ2018 ዓ.ም. የአዕምሯዊ ንብረትን ቀን ‹‹አዕምሯዊ ንብረትና ስፖርት፣ መዘጋጀት፣ መጀመር፣ መፍጠር›› በሚል መሪ ሐሳብ፣ ሚያዚያ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች እንደሚከበር በለሥልጣኑ አስታውቋል።