
የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት ጠንካራ ቢሆንም፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የኑሮ ውድነት እንደሚያስከትልና የምግብ ዋስትና ሥጋትን ውስጥ እንደሚጥል አስታወቀ፡፡
አይኤምኤፍ ሥጋቱን የገለጸው ከሰሀራ በታች የአፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ ትንተና ሚያዚያ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ ሲያደርግ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2025 የቀጣናው አገሮች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገባቸውን የሚገልጸው የአይኤምኤፍ ትንተና፣ 4.5 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡንና ኢትዮጵያም ባደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ዕድገት ካስመዘገቡ አገሮች መካከል ከቀዳሚዎች ተርታ ትሠለፋለች ብሏል፡፡
ሆኖም የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ቀውስ ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን፣ በተለይም በነዳጅና በምግብ ዋጋ ላይ ከባድ አደጋ መደቀኑን አስረድቷል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ነዳጅ ከውጭ የሚያስገቡ አገሮች ኢኮኖሚ እንደሚፈተን የሚገልጸው አይኤምኤፍ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ፣ የማዳበሪያ፣ የመርከብ ኪራይ ዋጋ ንረት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት እንደሚሆን፣ በተለይም በትራንስፖርትና በግብርና ምርቶች ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር አስጠንቅቋል፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ተጨምሮበት እ.ኤ.አ. በ2025 ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቦ የነበረው የቀጣናው ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ እ.ኤ.አ. በ2026 ወደ 4.3 በመቶ እንደሚቀንስ ተገልጿል፡፡
ይህ ሁኔታ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ንግድ መቀዛቀዝ፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ መናርና በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ የሚኖር ሚናን ሊያጠብ እንደሚችል፣ እ.ኤ.አ. በ2025 መቀነስ አሳይቶ የነበረው የዋጋ ግሽበት እ.ኤ.አ. በ2026 የመጨመር ሁኔታ እንደሚፈጥር ተመላክቷል፡፡
From The Reporter Magazine
አይኤምኤፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት በስተጀርባ ቁልፍ ጉዳይ መሆናቸውን በትንተናውን የገለጸ ሲሆን፣ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውቋል፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ የቀጣናው አገሮች ለውጭ ዕዳ ጫና፣ ለዓለም አቀፍ ቀውስና ለበጀት ውስንነት እንደምትጋለጥ ያለውን ሥጋት ገልጿል፡፡ ከሁሉም በላይ ትልቁ ሥጋት የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ነው ብሏል፡፡
የዓለም የምግብ ዋጋ በ20 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል፣ ይህም በቀጣናው የሚገኙ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለምግብ ዋስትና ዕጦት እንደሚዳርጋቸው፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ተጋላጭ አገሮች ከፍተኛ ሥጋት እንደተደቀነባቸው ትንተናው ያሳያል፡፡
From The Reporter Magazine
አይኤምኤፍ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ እንዲከተሉ፣ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን እንዲያሻሽሉና የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ የሚያስችሉ መዋቅራዊ ለውጦችን እንዲያደርጉ ያሳስባል፡፡