ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 reliable news source in Ethiopia

[ክቡር ሚኒስትሩ ከኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪዎቻቸው የቀረበላቸውን ሪፖርት አድምጠው ተጨማሪ ውይይት እያደረጉ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር የቀረበው ሪፖርት እንደሚያስረዳው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከታቀደው በላይ ውጤት አስገኝቷል።
- በትክልል።
- ክቡር ሚኒስትር ያስታውሱ እንደሆነ ሪፎርሙ ሲጀመር የዋጋ ንረትን ወደ ዘጠኝ በመቶ ዝቅ ማድረግ ይቻላል ብሎ የገመተ አልነበረም።
- ልክ ነው። እንኳን እኛ የሚደግፉን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጭምር ተጠራጥረው ነበር።
- አሁን ግን ተችሏል። ከሁሉም የሚልቀው ስኬት ግን ይህ አይደለም።
- ምንድነው?
- ከእልህ አስጨራሽ ድርድር በኋላ ያለብንን የውጭ ዕዳ የመክፍያ ጊዜ ማራዘም መቻላችን ነው። ይህ ትልቅ ስኬት ነው።
- በዚህ ድርድር ያገኘነው የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ ብቻ ነው እንዴ?
- አዎ። ክቡር ሚኒስትር።
- ዕዳችንን አልሰረዙልንም?
- አልተሰረዘም። የመክፈያ ጊዜያቸው የደረሱ ብድሮች እስከ 14 ዓመታት እንዲራዘም ነው የተወሰነልን።
- ታዲያ ይህንን ነው ትልቅ ስኬት ያልከው?
- አዎ። በጣም ትልቅ ስኬት ነው ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት እንደ ትልቅ ስኬት ይቆጠራል?
- ይቆጠራል ብቻ ሳይሆን ትልቅ ስኬት ነው።
- ለምን?
- የውጭ ዕዳችን መክፈያ ጊዜ ተራዘመ ማለት…
- እ…?
- ተጨማሪ አቅም ይፈጥርልናል።
- ተጨማሪ?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር።
- የምን?
- የመበደር።
- ተጨማሪ መበደር ያስችለናል?
- በትክክል ክቡር ሚኒስር።
- እንደዚያ ከሆነ ትልቅ ስኬት ነው።
- እስኪ ከስኬቱ ውጪ ያጋጠሙን ወይም ሊገጥሙን የሚችሉ ተግዳሮቶች ካሉ ደግሞ በዚህ ላይ እንወያይ።
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር።
- ዕድሉን የሰጠሁት ለአንተ አልነበረም…
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- አንተ ሥጋት መቀስቀስ እንጂ መልካም ነገር ስታነሳ ሰምቼ አላውቅም… ቢሆንም ቀጥል…
- በድጋሚ አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። በሪፖርቱ የቀረቡትን የሪፎርሙ ስኬቶች በሙሉ የምጋራቸው ሆኖ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ግን ከሕዝባችን የሚነሱ ቅሬታዎችን ማድመጥ እንዳለብን ይሰማኛል።
- ይኸው…!
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ቀጥል ቅሬታህን።
- የእኔ ቅሬታ አይደለም።
- ያው ነው።
- ምን አሉኝ?
- ለማንኛውም ቀጥል።
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። ስኬቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው ሕዝባችን ላይ ጫና እንዳያመጡ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። ቅሬታዎችንም ማዳመጥና መፍትሔ መስጠት ይኖርብናል።
- የምን ቅሬታዎች?
- እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎችን ማለቴ ነው።
- ተነሳ የምትለው ቅሬታ ምንድነው?
- ለምሳሌ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪና ድጎማ ማቆማችን በማኅበረሰባችን ላይ ጫና ፈጥሯል። አሁንም የደመወዝ ጥያቄ እየተነሳ ነው። በአጠቃላይ ሪፎርሙ የወለዳቸው መንገራገጮች ላይ ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው። ስለዚህ …
- እሺ ስለዚህ ምን?
- ሪፎርሙ ዘላቂ መፍትሔ ቢሆንም በመካከል እንቅፋት እንዳይገጥመን አማራጭ መፍትሔዎችንም እየሰጠን መሄድ ይኖሮብናል።
- መጨረሻ ላይ ያነሳኸው ሐሳብ ጥሩ ነው። ነገር ግን አታስተውልም።
- ምንድነው ያላስተዋልኩት ክቡር ሚኒስትር?
- መፍትሔ እየሰጠን መሆኑን አላስተዋልክም።
- ምን መፍትሔ ሰጠን?
- የኦጋዴኑ መፍትሔ አይደለም?
- የኦጋዴኑ ምን?
- የተፈጥሮ ጋዝ።
- እሱ አሁን ላለብን ችግር አይደርስማ ክቡር ሚኒስትር?
- ዋናው ጉዳይ መድረስ አለመድረሱ አይደለም…
- እ…?
- መፍትሔ መሆኑ ነው።
- ጥሩ ክቡር ሚኒስትር።
- በተጨማሪም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከማድረጋችንና ድጎማውን ከማንሳታችን አስቀድመን ሌሎች የመፍትሔ ዕርምጃዎችንም ወስደናል። ይህንን ታውቃለህ?
- አላውቅም ክቡር ሚኒስትር።
- አዎ፣ አታውቅም። ሁላችሁም ይህንን በደንብ እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ።
- መልካም ክቡር ሚኒስትር።
- አዎ። የመፍትሔ ዕርምጃዎች እንደወሰድን ልትገነዘቡ ይገባል።
- የነዳጅ ድጎማ በመነሳቱና የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ በቀዳሚነት የሚጎዱት የተሽከርካሪ ባለቤቶች መሆናቸው ይታወቃል። አይደለም?
- ትክክል ነው።
- ይህን አስቀመድን በመለየት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ አቅጣጫ አላስቀመጥንም።
- ልክ ነው። ተቀምጧል።
- ስለዚህ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን መቋቋም የማይችሉ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ምን ማድረግ ይችላሉ ማለት ነው?
- በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ተሽከርካሪ መግዛት ይችላሉ።
- ስለዚህ አስቀድመን መፍትሔ አላስቀመጥንም?
- ተቀምጧል። ነገር ግን ክቡር ሚኒስትር።
- ግን ምን ?
- በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የሚጎዱት የተሽከርካሪ ባለቤቶች ብቻ አይደሉም።
- ተጎጂ ነው የምትለውን ጥቀስልኝ?
- አብዛኛው የከተማ ነዋሪ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ነው።
- አዎ … ልክ ነህ።
- የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ደግሞ የትራንስፖርት ዋጋም ይጨምራል። ይህ ደግሞ አብዛኛውን ማኅበረሰብ ይነካል።
- ልብ አትሉም እንጂ ለዚህም መፍትሔ አስቀምጠናል።
- ምን?
- በመላ የአገሪቱ ከተሞች የኮሪደር ልማቶችን አላከናወንም?
- አከናውነናል።
- ዘመናዊ የእግረኛ መንገዶችን አልሠራንም?
- ሠርተናል።
- ከእግረኛ መንገዶቹ ጎን ለጎን የሳይክል መንገዶችን አልገነባንም?
- ገንብተናል።
- ስለዚህ ተሽከርካሪ ለሌላቸውና የትራንስፖር ዋጋ ጭማሪውን መሸከም ለማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መፍትሔ አልሰጠንም?
- ሰጥተናል።
- ስለዚህ እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ምን ማድረግ ይችላሉ ማለት ነው?
- ዎክ ማድረግ።
- ዎክ ማድረግ የማይችሉት ደግሞ ምን ሊጠቀሙ ይችላሉ?
- ሳይክል።
The post [ክቡር ሚኒስትሩ ከኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪዎቻቸው የቀረበላቸውን ሪፖርት አድምጠው ተጨማሪ ውይይት እያደረጉ ነው] first appear on ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 reliable news source in Ethiopia and is written by በጋዜጣው ሪፓርተር