
ኢትዮጵያ ከንፋስ የምታገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል 504 ሜጋ ዋት ማድረሱ የተነገረለትና በ145 ሚሊዮን ዮሮ ወጪ የተገነባው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ዛሬ ሚያዚያ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር) ተመረቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ(ኢንጂነር) እንደተናገሩት፣ ፣ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሂጦሳ ወረዳ የተገነባው የንፋስ ኃይል ማመንጫ 100 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል ነው። የፕሮጀክቱ መጠናቀቅም ኢትዮጵያ ከንፋስ የምታመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ 504 ሜጋ ዋት ከፍ ያደረገ ነው ብለዋል።


የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ 29 ተርባይኖች ያሉትና እያንዳንዱ ተርባይንም 3 ነጥብ 465 ሜጋ ዋት የሚመንጨት አቅም አለው ።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ የግንባታ ሥራው ታህሳስ 2014 ዓ.ም መጀመሩን የተናገሩት ሥራ አስፈፃሚው ፣ የፕሮጀክቱን ስራ በተቋራጭነት የስፔንና የዴንማርክ ኩባንያዎች በጥምረት ያከናወኑት ነው ። ዳር አል ሃንዳሳህ ሼር እና ፓርትነር የተሰኘ የተባበሩት አረብ ኢምሬት ኩባንያ ከተቋሙ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ጋር በመተባበር የፕሮጀክቱ አማካሪ በመሆን የተሳተፉ ናቸው ብለዋል ።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ በተርባይኖች የማመንጨት አቅም የማማና የክንፎቹ ርዝመት ከፍ ያለ መሆን እስከ አሁን ከተገነቡ ተመሳሳይ ማመንጫ ጣቢያዎች ልዩ የሚያደርገው መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ፣ ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ 4000 ሜጋ ባይት የኃይል አቅርቦት የነበራትና ከዘርፉም የምታገኘው ገቢ ከሰባት ቢሊዮን ያልበለጠ ነበር ።
ከለውጡ ማግስት በኋላ በተሰሩ የሪፎርም ስራዎች የኃይል አቅርቦቱን ከነበረበት 4000 ወደ 10 ሺህ ለማሳደግ ተችሏል። ሰባት ቢሊዮን ብር ሲያስገባ የነበረው ተቋምም አሁን ላይ 75 ቢሊዮን መድረስ ችሏል ።
From The Reporter Magazine
የፕሮጀክቱ ወጪ ከዴንማርክ መንግስት በተገኘ 145 ሚሊዮን ዮሮ መሸፈኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ገንዘቡም ግማሹ በብድር ፣ ግማሹ ደግሞ በዕርዳታ መልክ የተገኘ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ከሁለት ዓመት በኋላ ዕዳውን ሙሉ በሙሉ ሸፍኖ ትርፍ የሚያመጣ ይሆናል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከአዳማ 1 እና 2 ፣ ከአሸጎዳ ፣ ከአይሻ 2 ፣ እና ከአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ 504 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ታገኛለች ። እነዚህ ጣቢያዎች በተለይ በደረቅ ወቅት የውኃ ግድቦች መጠናቸው ሲቀንስ ክፍተቱን በመሙላት የኃይል መቆራረጥን በመቀነስ ረገድ እየተጫወቱ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ከ 400 ሺህ ለሚሆኑ የአከባቢውን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ብርሃን ተደራሽ የሚያደርግና በአከባቢው ላሉ ፋብሪካዎችና አካባቢዎች ወጥ የሆነ ያልተቆራረጠ ኃይል እንዲያገኙ ያስችላቸዋልም ተብሏል