
በሔኖክ አብርሃም
በአገራችን የዕለት ተዕለት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን በተግባር ሊፈቱ የሚችሉ ለፈጠራና ለአዳዲስ የንግድ ሥራዎች ትልቅ አቅምና ተነሳሽነት ያላቸው በርካታ ዜጎች አሉ። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤናና በፋይናንስ ዘርፎች ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ አዳዲስ የፈጠራ ሐሳቦችን የሚያቀርቡ ሥራ ፈጣሪዎች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል። ይሁን እንጂ የእነዚህ ሥራ ፈጣሪዎች ብሩህ አዕምሮና ጥረት ከፋይናንስ ተቋማትም ሆነ ከግለሰብ ባለሀብቶች የገንዘብ አቅም ጋር ተጣምሮ በሚፈለገው ልክ ወደ ሥራና ምርት ሲቀየር አይታይም።
ለዚህም ዋነኛው ማነቆ ሐሳብን ብቻ መነሻ አድርጎ ከገንዘብ ጋር በማስተሳሰር ወደ ተግባር የሚቀይር ጠንካራ የ‘ሐሳብ ፋይናንስ’ (Idea Financing) ሥርዓት በአገራችን ገና በአግባቡ አለመዘርጋቱ ነው። የሐሳብ ፋይናንስ መሠረታዊ ባህሪ የሚያጠነጥነው ገና በጅማሪ ላይ ባሉ አዳዲስ ሐሳቦችና በእጅ በማይዳሰሱ እሴቶች ላይ ነው። በዚህ ዘርፍ ገንዘብ የሚፈሰው በሰዎች ዕውቀት፣ በፈጠራ ሐሳቦችና ወደፊት በሚገነባው የድርጅት ስም ላይ ነው። ይሁን እንጂ የኢንቨስትመንት ሥርዓታችን በአብዛኛው በሚዳሰሱ ንብረቶች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ገና በዕቅድ ደረጃ ላይ ላሉና በራዕይ ላይ ብቻ ለተመሠረቱ የፈጠራ ሐሳቦች መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ያልተለመደ ሆኖ ቆይቷል።
ይህ ክፍተት በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ የፈጠራ ሥራዎችን ከፋይናንስ አቅርቦት በማራቅ በአገራችን የንግድ ሥነ ምኅዳር ላይ ትልቅ ጥላ አጥልቷል። ወደፊት አድገው ትርፍ ሊያስገኙ በሚችሉ የፈጠራ ሐሳቦች ላይ ደፍሮ ገንዘብ የሚያፈስ የኢንቨስትመንት ባህል ገና አልዳበረም። በዚህም የተነሳ ድንቅ ሐሳብ ይዘው የሚነሱ ሰዎች በመያዣነት የሚያቀርቡት ሕንፃ ወይም መኪና ስለሌላቸው ብቻ ሐሳባቸው በእንጭጩ ይቀጫል። ከዚህ የንብረት ዋስትና ችግር በላይ ግን የሐሳብ ፋይናንስን ዕድገት የገታው ዋነኛ ማነቆ በባለሀብቱና በሥራ ፈጣሪው መካከል ያለው የመተማመን ክፍተት ነው።
የባለሀብቱና የሥራ ፈጣሪው አለመተማመን
በኢትዮጵያ የንግድ ምኅዳር ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችና ባለሀብቶች በከፍተኛ ጥርጣሬና አለመተማመን ነው የሚተያዩት። በአንድ በኩል በሥራ ፈጣሪዎች ዘንድ ሐሳቤን ይሰርቁብኛል የሚል ጠንካራ ፍርኃት ሲኖር በሌላ በኩል ደግሞ በባለሀብቱ ዘንድ ገንዘቤ ይባክናል የሚል ጥርጣሬ ይኖራል።
የሐሳብ አመንጪዎችና ሥራ ፈጣሪዎች የፈጠራ ሐሳባቸውን የተሻለ የካፒታል አቅም ያላቸው ትልልቅ የንግድ ተቋማት ቀድተው ይወስዱብናል ከሚል ከፍተኛ ሥጋት ጋር ይታገላሉ። በዚህም ምክንያት አዕምሯዊ ንብረታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ዋናውን የፈጠራ ሐሳባቸውን፣ ልዩ የንግድ ሥልታቸውን እንዲሁም የረጅም ጊዜ ዕቅዳቸውን ለባለሀብቶች በግልጽ ለማካፈል ያመነታሉ። ይህ መረጃዎችን የመደበቅ አዝማሚያ ደግሞ ባለሀብቶች ስለሥራው ጥልቀትና አዋጭነት በቂ ግንዛቤ እንዳያገኙ በማድረግ የፋይናንስ አቅርቦቱን ያደናቅፋል።
From The Reporter Magazine
በተቃራኒው ደግሞ የካፒታል አቅራቢዎች ጀማሪ መሥራቾች ሥራውን በአግባቡ አይመሩትም አሊያም ያለ በቂ ዲስፕሊን ገንዘቡን ያባክኑታል የሚል ሥጋት አላቸው። አንድ ባለሀብት በዓይን በማይታይ ራዕይ ላይ ገንዘቡን ለማፍሰስ ቢወስን እንኳን ‹‹ያፈሰስኩትን ገንዘብ መቼና እንዴት ነው የምመልሰው?›› የሚለው ወሳኝ የመውጫ ሥልት (Exit Strategy) ጥያቄ ከፊቱ ይጋረጣል። በሐሳብ ፋይናንስ አሠራር ውስጥ ማንኛውም ባለሀብት ገንዘቡን የሚያፈሰው ለዘለዓለም ከኩባንያው ጋር ለመቆየት ሳይሆን ድርጅቱ ሲያድግ የባለቤትነት ድርሻውን ሸጦ ትርፉን ይዞ ለመውጣት ነው። ይሁን እንጂ እስካሁን በአገራችን የተደራጀ የአክሲዮን ገበያ ባለመኖሩ ሕጋዊና ግልጽ የሆነ የመውጫ ሥልት ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት በአዳዲስ ሐሳቦች ላይ የሚፈሱ ኢንቨስትመንቶችን በፍጥነት ወደ ጥሬ ገንዘብ መቀየር አይቻልም። ይህ ሁኔታ የባለሀብቱን ካፒታል ለረጅም ጊዜ ስለሚያስር በዘርፉ ላይ ያለውን አለመተማመንና ሥጋት በእጅጉ አክብዶታል።
አለመተማመኑን ይበልጥ እንዲሰፋ ያደረገው ዘመናዊና ግልጽ የሆነ የንግድ አሠራር በስፋት ባለመዳበሩ እንዲሁም የተገቡ ስምምነቶች ቢጣሱ በሕግ ወይም በፍርድ ቤት በኩል ፈጥኖ መፍትሔ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ነው። እነዚህ ውስብስብ የሆኑ የመረጃ መደበቅ፣ የመተማመን ማጣትና የመውጫ ሥልት ዕጦት ፈተናዎች የሐሳብ ፋይናንስን በማቀጨጭ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
የሐሳብ ፋይናንስ ሌሎች ማነቆዎች
From The Reporter Magazine
የሐሳብ ፋይናንስን ጉዞ ወደኋላ ከሚጎትቱት ፈተናዎች መካከል አንዱ ሥር የሰደደው የአሠራርና የመመርያ ማነቆ ነው። የፋይናንስ ዘርፋችን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ‹‹በንብረት ዋስትና›› (Collateral) አስተሳሰብ ላይ የተንጠለጠለ ነው። ይህ አመለካከት የመነጨው አካላዊ ንብረቶችን እንደ ብቸኛ አስተማማኝ የሀብት ማከማቻ አድርጎ ከሚቆጥረው የረጅም ጊዜ ልማዳችን ነው። በዚህም የተነሳ በመያዣነት የሚያቀርቡት ሕንፃ ወይም መኪና የሌላቸው ነገር ግን በዕውቀትና በአዕምሯዊ ንብረት ላይ የተመሠረቱ ፈጠራዎች ከካፒታል ገበያው ገሸሽ እንዲሉ ሆነዋል።
ምንም እንኳን የፈጠራ ሐሳብን ወይም አዕምሯዊ ንብረትን እንደ ማስያዣነት መጠቀም በሕግ ቢፈቀድም ባንኮቻችን እነዚህን በእጅ የማይዳሰሱ ሐሳቦች ምን ያህል የገንዘብ ዋጋ እንደሚያወጡ የመተመን ልምዱ የላቸውም። በተጨማሪም ብድሩ ባይመለስ እንኳን የፈጠራ ሐሳቡን መልሰው የሚሸጡበት ገበያ ስለሌለ አሠራሩ በተግባር ላይ ሊውል አልቻለም። በሌላ በኩል የመንግሥት ተቋማት የሚያደርጉት ጥረትም ፈተናዎች አልጠፉበትም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለጀማሪ የፈጠራ ሥራዎች ብድር ለመስጠት ‘የፈጠራ ባለቤትነት’ ፓተንት ማስረጃን በግዴታ ይጠይቃል። ይሁን እንጂ የፓተንት ሕግ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ግኝቶችና ማሽነሪዎች ላይ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በስፋት የሚታዩት የዲጂታል መተግበሪያዎች፣ የሶፍትዌር ውጤቶችና አዳዲስ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥልቶች ከሕጉ ማዕቀፍ ጋር ለመጣጣም ሊቸገሩ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው።
ከዚህ ባለፈ የፓተንት መብት ለማግኘት የፈጠራ ሥራው በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘ፍፁም አዲስ’ (Absolute Novelty) የመሆን ጥብቅ መሥፈርትን እንዲያሟላ ይጠበቃል። አብዛኞቹ የአገራችን ሥራ ፈጣሪዎች በሌሎች አገሮች የተሳኩ ቴክኖሎጂዎችን ከአገራችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማላመድ (Localization) ችግር ፈቺ ሥራዎችን የሚሠሩ በመሆናቸው እነዚህ ሥራዎች እንደ አዲስ ግኝት ተቆጥረው የፓተንት ዕውቅና ለማግኘት አዳጋች ሊሆንባቸው ይችላል። የምዝገባው ሒደት የሚወስደው ረጅም ጊዜ፣ ያለው ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድና የተለያዩ ወጪዎችም በቶሎ የፋይናንስ ድጋፍ አግኝቶ ወደ ሥራ ለመግባት ለሚፈልግ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪ የራሱ የሆነ ጫና ይፈጥራል።
የፓተንት ማስረጃ ለሌላቸው ጀማሪዎች በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል የሚሰጠው የግዴታ ሥልጠና እንደ አማራጭ ቢቀመጥም አተገባበሩ ከጀማሪ ሥራዎች ፈጣንና ተለዋዋጭ ባህሪ ጋር አለመጣጣሙ ሌላው የፋይናንስ ማነቆ ሆኖ ይጠቀሳል። ሥልጠናው የሥራ ፈጣሪዎችን የንግድ ክህሎት በማሳደግና ለተቋማዊ ስኬት በማዘጋጀት ረገድ የጎላ ድርሻ ቢኖረውም ያለው የአፈጻጸም ሒደት ግን በቶሎ የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተው ወደ ተግባር ለመግባት ለሚሹ ጀማሪዎች ምቹና ቀልጣፋ አይደለም።
የፋይናንስ ዘርፉን የሚፈትኑት ሌሎች ጉዳዮች ደግሞ ከንግድ ባህላችን ጋር የተያያዙ ናቸው። በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው እንደ አስመጪና ላኪ፣ የጅምላ ንግድና ኮንስትራክሽን የመሳሰሉት ዘርፎች ፈጣን የካፒታል ዝውውርና በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፍ የሚያስገኙ በመሆናቸው በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ በስፋት የተለመዱ ናቸው። ይህ የዳበረ የንግድ ልምድ ደግሞ ከሐሳብ ፋይናንስ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር ይጋጫል። የፈጠራ ሥራዎች ገበያ ውስጥ ገብተው ትርፍ ማምጣት እስኪጀምሩ ድረስ መታገስን ይጠይቃሉ። በመሆኑም ፈጣን የገንዘብ ዝውውር በለመደው የንግድ ምኅዳር ውስጥ ለወራት ወይም ለዓመታት ገንዘብን አዲስ ሐሳብ ላይ አስሮ ማቆየት አዋጭነቱ ያልታወቀ ከፍተኛ የፋይናንስ ሥጋት ተደርጎ መታየቱ የሚጠበቅ ነው።
ሌላው ፈተና ደግሞ የሕግ ማነቆው ነው። ሐሳብን ወደ ተግባር ለመቀየር ድፍረቱ ቢኖርም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበሩት የንግድ ሕጎቻችን የሐሳብ ፋይናንስን አሠራር በሚመለከት ከፍተኛ ክፍተት ነበረባቸው። የተንዛዛ የንግድ ምዝገባ ሒደት፣ እንዲሁም ባለሀብቶች ለጀማሪ ሥራዎች ዛሬ ፋይናንስ አቅርበው ወደፊት የድርጅቱ ባለቤትነት ድርሻ የሚወስዱባቸውን ዘመናዊ አሠራሮች ሕጉ አለማካተቱ ደፋር ባለሀብቶችንና ሥራ ፈጣሪዎችን ሲያሸሹ ቆይተዋል።
በሌላ በኩል ለፋይናንስ ሥርዓቱ ጤናማነትና ደኅንነት ሲባል የወጡት የብሔራዊ ባንክ አዳዲስ መመርያዎች ለፈጠራ ሥራዎች የሚቀርበው የገንዘብ ድጋፍ ላይ በተዘዋዋሪ መንገድ ጫና ፈጥረዋል። ባንኮች ብድር ሲሰጡ አስተማማኝነቱን ለማረጋገጥ መከተል ያለባቸውን ዓለም አቀፍ የጥንቃቄ ሕጎች ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት ንግድ ባንኮች ቤት ወይም መኪና ሳይያዝ በሐሳብ ላይ ብቻ ለተመሠረተ ሥራ ብድር ከሰጡ ለሚገጥማቸው ሥጋት ማካካሻ የሚሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በካዝናቸው አግደው ማስቀመጥ ግዴታ ይሆንባቸዋል። ይህ ጥብቅ አሠራር ባንኮች ሥጋት ወዳለበት አዲስ የሐሳብ ፋይናንስ ከመግባት ይልቅ ንብረት እያስያዙ ወደ ሚሰጡት የተለመደው የብድር አሠራር እንዲያዘነብሉ አድርጓቸዋል። እነዚህ የሕግ፣ የአሠራርና የባህል ማነቆዎች ተደማምረው የአገራችን የሐሳብ ፋይናንስ አብቦ ፍሬ እንዳያፈራ አስረው አቆይተውታል።
ተስፋዎችና መፍትሔዎች
በኢትዮጵያ የሐሳብ ፋይናንስን የሚያደናቅፉትን ማነቆዎች ለመፍታት በቅርቡ የተወሰዱ የሕግ ማሻሻያዎች ተጠቃሽ ናቸው። ከእነዚህም መካከል የጀማሪ የንግድ ሥራዎች (ስታርታፕ) አዋጅ ቁጥር 1396/2017 መፅደቅ አንዱ ነው። አዋጁ ባለሀብቶች በጀማሪ ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት አድርገው ኪሳራ ቢያጋጥማቸው ያጡትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ከሚከፍሉት የገቢ ግብር ላይ እንዲቀነስላቸው ይፈቅዳል። ይህ አሠራር ባለሀብቱ የሚወስደውን የፋይናንስ ሥጋት በመቀነስ ገንዘባቸውን ወደ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች እንዲያዞሩ የሚያበረታታ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የስታርታፕ አዋጁ በአገራችን ያልተለመዱ አዳዲስ የፋይናንስ አቅርቦቶች በሕጋዊ መንገድ እንዲሠሩ መንገድ ከፍቷል። እነዚህም ‘ኤንጅል ኢንቨስተሮች’ (Angel Investors) እና ‘ቬንቸር ካፒታል’ (Venture Capital) በመባል የሚታወቁት የ‘ሐሳብ ፋይናንስ’ ዋነኛ ሞተሮች ሲሆኑ ከንግድ ባንኮች ፈፅሞ የተለዩ ናቸው፣ ብድር ለመስጠት የንብረት ዋስትና በመያዣነት አይጠይቁም። ከዚህ ይልቅ የሚያምኑት በሐሳቡ አዋጭነትና በሥራ ፈጣሪው ብቃት ላይ ነው። ‘ኤንጅል ኢንቨስተሮች’ ገና በወረቀት ላይ ያሉ አዳዲስ የፈጠራ ሐሳቦች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ የራሳቸውን የግል ገንዘብ አውጥተው የሚረዱ ደጋፊ ግለሰቦች ናቸው። ‘ቬንቸር ካፒታል’ ደግሞ ተስፋ ያላቸውን ነገር ግን ሥጋት የበዛባቸውን ጀማሪ ሥራዎች በከፍተኛ ገንዘብና በሙያዊ ምክር ደግፈው ትልቅ ደረጃ የሚያደርሱ ተቋማት ናቸው።
ሌላው ተስፋ ሰጪ ለውጥ የመውጫ ሥልትን (Exit Strategy) እና የካፒታል ገበያን የሚመለከተው ነው። በሐሳብ ፋይናንስ አሠራር ውስጥ ‘የመውጫ ሥልት’ ማለት ባለሀብቶች በአዲስ ሐሳብ ላይ ገንዘባቸውን ካፈሰሱ በኋላ ድርጅቱ አድጎ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ያላቸውን የባለቤትነት ድርሻ በመሸጥ ካፒታላቸውንና ትርፋቸውን ይዘው የሚወጡበት መንገድ ነው። ይህ ዓይነቱ ግልጽ የሆነ ሥርዓት መኖሩ የገንዘብ ዝውውርን ያፋጥናል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ሴኩሪቲስ ኤክስቼንጅ (ESX) መከፈት ባለሀብቶች በቀላሉ አክሲዮናቸውን በሕጋዊ የገበያ ሥርዓት ለሌሎች ሸጠው ወደ ጥሬ ገንዘብ እንዲቀይሩ ከማገዙም በላይ ገንዘብ ከአንዱ የፈጠራ ሥራ ወደ ሌላው ሳይቋረጥ እንዲዘዋወር በማድረግ አዲስ አማራጭ ያቀርባል።
በሌላ በኩል አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ ትልልቅ ኩባንያዎችን ከሚያስተናግደው ዋናው ገበያ በተጨማሪ ለጀማሪና አነስተኛ ሥራዎች ታስቦ የተዘጋጀ ‘የዕድገት ገበያ’ (Growth Market) የተባለ ልዩ አሠራርን አካቷል። በዚህ ገበያ ውስጥ ገብቶ አክሲዮን ለመሸጥ የሚጠየቀው የመነሻ ካፒታል 50 ሚሊዮን ብር የገንዘብ መጠን በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ለጀማሪዎች ቀላል ባይሆንም፣ ትልልቅ ኩባንያዎች አክሲዮን ለመሸጥ ከሚጠየቁት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር መሥፈርት አንፃር ሲታይ ለጀማሪዎች ትልቅ ዕድል ነው። ዋናው ቁምነገር የፈጠራ ሥራዎች በኤንጀል ኢንቨስተሮችና በቬንቸር ካፒታል ታግዘው አድገው ወደዚህ የ50 ሚሊዮን ብር የካፒታል ደረጃ ሲደርሱ መጀመሪያ ገንዘባቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች ድርሻቸውን ለሕዝብ ሸጠው ትርፋቸውን የሚያገኙበትና ቀጣይ ሥራዎችን የሚደግፉበት ‘የመውጫ ሥልት’ መፍጠሩ ነው።
ከሕግ ማሻሻያው ባለፈ ትልቁ መዋቅራዊ መፍትሔ በዘርፉ ‘ቅይጥ ፋይናንስ’ (Blended Finance) ተብሎ የሚታወቀውን አሠራር በስፋት መተግበር ነው። ይህ አሠራር ባንኮች ለጀማሪ የፈጠራ ሥራዎች ብድር ለመስጠት የሚኖራቸውን ሥጋት እንደ ዓለም ባንክ ካሉ ተቋማት ጋር በመጋራት የሚቀርፍ ነው። ለምሳሌ ለጋሽ ድርጅቶች ብድሩ ባይመለስ እንኳን ኪሳራውን በከፊል ለመሸፈን ዋስትና በመግባት ባንኮች በልበ ሙሉነት ብድር እንዲሰጡ ያበረታታሉ። ከገንዘብ ድጋፉም ባሻገር ሥራ ፈጣሪዎቹ በገበያ ውስጥ ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ሥልጠናና ሙያዊ ዕገዛ እንዲያገኙ በማድረግ የንግድ ዕውቀታቸውን ያዳብራሉ። በተጨማሪም ባንኮች የሚጠይቁትን ከፍተኛ ወለድ በመቀነስ አዳዲስ ሐሳብ ያላቸው ዜጎች ያለ ከባድ የገንዘብ ሸክም ሥራቸውን እንዲጀምሩና ሐሳባቸውን ወደ ተጨባጭ ምርትና አገልግሎት እንዲቀይሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። ይህ ዋስትና ንግድ ባንኮች ንብረቶችን ማስያዝ ለማይችሉ አዳዲስ የሐሳብ ባለቤቶች በድፍረት ብድር እንዲሰጡ ያበረታታቸዋል።
ከላይ የተጠቀሱት የሕግ ማሻሻያዎችና የካፒታል ገበያ ጅማሮዎች ቢኖሩም የሐሳብ ፋይናንስ በነገው ተስፋ ላይ ዛሬ የሚደረግ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት በመሆኑ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ውጤት ለመቀየር የተቀናጀ ዕርምጃ ያስፈልጋል። በመጀመሪያ በመንግሥት በኩል በስታርታፕ አዋጁ የተቀመጡትን የግብር ቅነሳ መብቶች በተግባር ለማዋል የሚያስችሉ ዝርዝር መመርያዎችን በፍጥነት ማውጣትና አፈጻጸማቸውን ግልጽ ማድረግ ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ ባለሀብቶች ከተለመደው የንግድ አሠራር ወጥተው አዳዲስ የፈጠራ ሐሳቦችን በድፍረት ወደሚደግፍ የአስተሳሰብ አድማስ መሸጋገር ይኖርባቸዋል። የካፒታል አቅራቢዎችን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የፈጠራ ባለቤቶችን አቅም ማጎልበትና በተግባር መደገፍ እንዲሁም በባለሀብቱና በሥራ ፈጣሪው መካከል ፅኑ የጋራ መተማመንን መገንባት የሐሳብ ፋይናንስ ሥርዓትን በተጨባጭ ለማሳደግ ወሳኝ ዕርምጃ ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡