የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) የነገሡበትን የብር ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር የተገነባው ዘመናዊ ቤተ መንግሥት የተ ጠናቀቀው በ1947 ዓ.ም. ነበር። 25ኛ ዓመት ኢዮቤልዩም የተከበረው ጥቅምት 23 ቀን 1948 ዓ.ም. ሲሆን አዲሱ ቤተ መንግሥትም “ኢዮቤልዩ” ተብሎ ተሰየመ። አፄው ከሁለት አሠርታት በላይ የተገለገሉበት ቀዳሚው ቤተ መንግሥታቸው ስድስት ኪሎ የሚገኘው ያሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ሲሆን መጠሪያውም “ገነተ ልዑል” ነበር።
በዘውዳዊው ዘመን የኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ተብሎ ይጠራ የነበረው ታላቁና የአገር ምልክት የሆነው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በመሀል አዲስ አበባ 27 ሔክታር መሬትን አካሎ እስከ ግርማ ሞገሱ ከዘመን ወደ ዘመን ተሸጋግሮ ዛሬም ከነሙሉ ክብሩ ተቀምጧል፡፡
አገራዊው ቤተ መንግሥት ዘመናት ተፈራርቀውበት መንግሥታት ወድቀው ተነስተውበት ሐዘን ደስታቸውን አሳልፈውበት አልፈዋል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ወታደራዊው ደርግ ከሥልጣን እስካስወገዳቸው መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ድረስ በዚሁ ቤተ መንግሥት ብዙ ሁነቶችን አከናውነውበታል፡፡
የተለያዩ የውጭ አገር አምባሳደሮችና የአገር መሪዎች ሲመጡ ከታላቅ ክብርና ከፍ ካለ መስተንግዶ ጋር ተቀብለው አነጋግረውበታል፡፡
ይህ ብዙ ሁነቶች የተደረጉበት የኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት የንጉሡን የንግሥናና የልደት በዓልን ጨምሮ ሌሎች ብሔራዊና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ሲደረጉበት እንደነበር አሁን ላይ በውስጡ ያሉ ቁሳቁሶች ምስክር ናቸው፡፡
አፄው የሥልጣን ዘመናቸው ተጠናቆ ወታደራዊ መንግሥት ደርግ ሲተካ ዘውዳዊው ሥርዓት ማክተም አለበት በሚል ሁሉም ነገር እንዳልነበር ተደርጓል፡፡
ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥትም ‹‹ብሔራዊ ቤተ መንግሥት›› የሚል ስያሜን ያገኘው በዚሁ ወቅት ነበር፡፡ የደርግ መንግሥትም ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን አቋቁሞም በተራው በዚሁ ቤተ መንግሥት የተለያዩ ሁነቶችን ሲፈጽምበት ኖሯል።
ይህም መንግሥት ጊዜው ደርሶ በኢሕአዴግ መንግሥት ሲገረሰስ ይህ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ስሙን ሳይቀይር ባለበት ቀጥሏል፡፡
የኢሕአዴግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ከግንቦት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን መሥርቶ የአገሪቱ ርዕሰ መንግሥትና ርዕሰ ብሔር ተብሎ ለሁለት ሲከፈል ርዕሰ ብሔሩ ወይም ፕሬዚዳንቱ መቀመጫውን በዚሁ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በማድረግ እስከ 2014 ዓ.ም. ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
የመንግሥታትን አመጣጥና አወዳደቅ በአርምሞ ሲታዘብ የነበረው ታላቁ ቤተ መንግሥት ዕድሳት ሳይደረግለት በመቆየቱ ጣሪያና ግድግዳው ከማፍሰስ ጀምሮ እርጅና ተጫጭኖት አካባቢውም ጥሻ ለብሶ ቆይቷል፡፡
ይህ እርጅናና ጉስቁልና የተጫጫነውን ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በውስጡ የአገር ታሪክና መልክን አካቶ የያዘው የአገር ሀብት ወደ ቀደመ ግርማ ሞገሱ ይመለስ ዘንድ ሐሳብ ያስፈልገው ነበር፡፡ በውስጡ ያሉ ዕንቁና ውድ ሀብቶች ተገላልጠው ለውጭና ለውስጥ ጎብኝዎች ክፍት ይሆን ዘንድ አዲስ ሐሳብን ይሻ ነበር፡፡
ይህም ጊዜው ደርሶ በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት ከፈረንሣይ መንግሥት በተገኘ 25 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ሙሉ ዕድሳት ተደርጎለት ለሕዝብ ዕይታ በቅቷል፡፡
‹‹እዚህ ግቢ ውስጥ ያለው ሀብት ተስተካክሎ ለጎብኝዎችና ለዜጎች ቢገለጥ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የአገራቸችንን ልክ ያሳያል ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ነገሮችንም ለመፍጠር ዕድል ይፈጥራል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹አቧራ የለበሰና የተሸፈነ ሁሉ ሸክላ አይደለም የሸፈነውን ማራገፍና ገባ ብለን ማየት ከቻልን ለትውልድ ሊሸጋገር የሚችል እጅግ ውድ የሆነ ነገር ልናገኝ እንችላለን፤›› በማለት ዕድሳቱ ከመጀመሩ በፊት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ሐሳቡ በተነሳ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሙሉ ዕድሳቱ ተጠናቆ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሕዝብና ለጎብኝዎች ክፍት በመሆኑ ሰዎች ሁሉ አስገራሚውን ቤተ መንግሥት በአግራሞት እየጎበኙት ይገኛሉ፡፡
በዋናው በር ግራና ቀኝ ጫፍ ላይ ባማረ ቅርፃ ቅርፅ ተቀምጠው የሚገኙት አንበሶችን የተመለከተ ወደ ውስጥ ሲገባ አስገራሚ ነገሮችን ማየት እንደሚችል መገመት ቀላል ይሆናል፡፡
የታደሰውን ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የተለያዩ አካላት እየጎበኙት ሲሆን ታኅሣሥ 22 ቀን ከሚዲያና ከቱሪዝም ቢሮ የተውጣጡ አካላት ጎብኝተውታል፡፡ በነበረን ምልከታም በብሔራዊ ቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ያሉ ታሪካዊና ጥንታዊ መገልገያዎችን አልባሳትና መመገቢያ ዕቃዎችን ከወርቅና ከአልማዝ እንዲሁም ከብርና ከነሐስ የተሠሩ ጌጣጌጦችንና ዘውዶችን አፄ ኃይለ ሥላሴ ይገለገሉባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎች የመሰባሰቢያ አዳራሾች ዲፕሎማቶችን ይቀበሉባቸው የነበሩ እጅግ ሰፋፊና ቅንጡ አዳራሾችና ሌሎች እጅግ በጣም በርካታ ቅርሶች በአግባቡ ተሰንደው ቦታ ቦታቸውን ይዘው ለትውልድ በሚታይበትና ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሚቀመጥበት ሥፍራ ተቀምጠዋል፡፡
ኤርትራን ጨምሮ ከተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች የተበረከቱ ልዩ ልዩ ስጦታዎች በዚሁ አዳራሽ ይገኛሉ፡፡
“የዘውድ ጠረጴዛ” በመባል የሚታወቅ ንጉሡንና እቴጌዪቱን ፓትርያርኩን ጨምሮ አሥር አባላትን የሚይዝ ነው። ሌሎችንም አባላትን በመያዝ ትልልቅ የአገር ጉዳዮች ሹም ሽር የሚያደርጉት በዚሁ ጠረጴዛ ነበር፡፡
በጉብኝታችን ላይ እንደተገለጸው የዘውድ ምክር ቤት አባላት አንዳንድ ጥፋቶችን ሲመለከቱ ተው የማለትና አንዳንድ ውሳኔዎችን የማሻር ሥልጣንም ነበራቸው፡፡ በዚህ ታላቅ ቤተ መንግሥት የልዩ ዝግጅት መከወኛ የክብርና ለእራት ግብዣ የሚሆኑ ልዩ ጠረጴዛዎች በሚገርምና በሚያምር አቀማመጥ ተቀምጠዋል፡፡
የንጉሡና የእቴጌዪቱ እንዲሁም የቤተሰባቸው ቅንጡ የእራት ጠረጴዛዎች በዕድሜ አሊያም በዝምድና ደረጃቸው በተዋረድ ተደርድረው ይቀመጡበት እንደነበር ይነገራል፡፡
በዚሁ ኢዩቤልዩ ቤተ መንግሥት የበሬ ማረጃ፣ የእህል ማስቀመጫ የጠጅ መጣያና ሌሎች አገልግሎቶች ን ይሰጡ የነበሩ ክፍሎች በአግባቡ ታድሰው ታሪካዊነታቸውን ጠብቀው ይገኛሉ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶችና አውራጃዎች በሚሄዱበት ወቅት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ተሸከርካሪዎች ሠረገላዎችና ባቡሮች የዕቃ ማጓጓዣ የነበሩ ተሸከርካሪዎች ባሉበት ታድሰው ለዕይታ ክፍት ሆነዋል፡፡ በተለይ ንጉሡ ወደ ተለያዩ አውራጃዎች ለጉብኝት አሊያም ለሥራ ሲሄዱ ይገለገሉባቸው የነበሩትን የመሰብሰቢያና የቢሮ፣ የመታጠቢያና መኝታ ክፍሎችን እንዲሁም የምግብ ማብሰያና ሌሎች ነገሮችን ያሟሉ ተሽከሪካሪዎች ዛሬም ተጠብቀውና ታድሰው በክብር ተቀምጠዋል፡፡
አውቶማቲክ ተሽከርካሪዎች የተለያዩ ሞዴል ያላቸው ሠረገላዎች ንጉሡ የክብር እንግዶቻቸውን ይቀበሉባት የነበረች ሮልስ ሮይስ ሊሞዚን የተባለች ቅንጡ ተሽከርካሪ ዝርያዋ ሞሮኮን ጨምሮ በሌሎች ሰባት አገሮች ብቻ የምትገኘዋ አውቶሞቢል በዚሁ ትገኛለች።
በሌላ በኩል ንጉሣውያን ቤተሰቦች ሲታመሙ ወደ ጤና ተቋም የሚሄዱበት አሊያም ለመስክ ጉብኝት ራቅ ወዳለ ቦታ ሲጓዙ የሕክምና መሣሪያዎችን ይዛ የምትከተላቸው የቀይ መስቀል ተሸከርካሪ፣ የምዕራብ ጀርመን ስሪት የሆነች በውኃና በየብስ ላይ መረማመድ የምትችል ሁለገብ ተሸከርካሪ እንዲሁም ንጉሣዊ ቤተሰብና ዲፕሎማቶች ወደ ምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ሐረርና ድሬዳዋ መጓዝ ሲፈልጉ የሚሔዱበት ከእንግሊዝ ንግሥት ኤልሳቤጥና ከፈረንሣይ መንግሥት የተሰጡ ሁለት ባቡሮች ከነሐዲዳቸው በክብር ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡
ባቡሮቹ እያንዳንዳቸው 1717 እና 2020 ቶን የሚመዝኑ ሲሆን፣ በውስጣቸው መታጠቢያና ማብሰያ ክፍሎች፣ ከሚኒስትሮቻቸው ጋር ሲጓዙ ይወያዩበት የነበረ መሰብሰቢያ አዳራሽና መኝታ ቤት እንዲሁም የጸሎት ቤትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን የያዙት ሁለት ባቡሮች በከፍተኛ ጥንቃቄ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ተነስተው በቤተ መንግሥቱ ተቀምጠዋል፡፡
ከጅማው አባ ጅፋር ለንጉሡ የተበረከተ ጠረጴዛ ከጌጠኛ ወንበሮች ጋር ተቀምጠዋል፡፡
ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሣይ፣ ከጣሊያን፣ ከደቡብ ኮሪያ ከዑጋንዳና ከሌሎች አገሮች ለንጉሡ በስጦታ የተበረከቱ ልዩ ልዩ ሽልማቶች፣ የንጉሣውያን ቤተሰቦች የመመገቢያና ሌሎች ከወርቅና ከአልማዝ የተሠሩ የመገልገያ ዕቃዎች በክብር ይታያሉ፡፡
ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፎቶግራፍ ጀምሮ የፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሮቹ መለስ ዜናዊና ኃይለማርያም ደሳለኝ ፎቶ በቅደም ተከተል ግድግዳ ላይ ተሰቅለው ይታያሉ። የቀድሞዎቹ ፕሬዚዳንቶች የጋና ክዋሜ ንክሩማ፣ የኬንያ ጆሞ ኬኒያታና የግብፅ ጋማል አብዱል ናስር፣ እንዲሁም ከ1963 እስከ 1997 ዓ.ም. የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶችን የመሩት ሸህ ዛይድ ቢን ሡልጣንና የሌሎች አገሮች መሪዎች ፎቶግራፎች ከግርጌ ማስታዎሻቸው ጋር በክብር ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡
ከተለያዩ መሪዎች ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የተሰጡ ስጦታዎች፣ በልዩ ጥበብ የተሠሩ ከፈረንሳይና ከእንግሊዝ የተበረከቱ የሸክላ የፈረሶች፣ ሰዓቶችና ሌሎች ጌጣጌጦች እጅግ ባማረና ለእይታ በሚማርክ ቦታ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ እስራኤል፣ ቱርክ፣ ቱኒዚያ፣ ጣሊያን፣ ሜክሲኮ፣ አውስትራሊያና ፈረንሣይ ስጦታዎቻቸው ከተቀመጡላቸው መካከል ይገኛሉ።
በአፖሎ 11 ጠፈርተኞች ጨረቃ ላይ የተቀመጠ የመሪዎች የመልካም ምኞት መግለጫና ጨረቃ ደርሶ የተመለሰ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና ከጨረቃ የተገኘ አካል የተወሰደ ናሙና ለንጉሡ ያበረከተችው አሜሪካ ናት፡፡
ከእንግሊዝ የተበረከተ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የታተመ የአፍሪካ የቄስ ንጉሥ ዮሐንስ ግዛት ካርታና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች መሪዎች ፊርማ ያረፈበት መዝገብ እንዲሁም ከሌሎች ቅርሶች ጋር በዚሁ ታላቅ ቤተ መንግሥት ውስጥ ከትመው ይገኛሉ፡፡
ሌላውና በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ በስታሊንግራንድ ጦርነት የተነሳው የሶቪየት ኅብረት ወታደሮች ደም የፈሰሰበት በደም የተለወሰ አፈር በልዩ ክብር ተቀምጧል፡፡
የአፄ ቴዎድሮስ በስማቸው የተቀረፀና በእንግሊዝ ተዘርፎ የነበረ ማኅተም ከወርቅ የተሠራ ዘውድ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የሻይና የወተት መጠጫዎች፣ እንዲሁም አሜሪካ አፄ ምኒልክን ለኤክስፖ ጉብኝት ከጋበዘችበት የመጥሪያ ደብዳቤ ጋር የተላከና ከ120 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ከብር የተሠራ ትሪ በሙዚየሙ ውስጥ ተቀምጠዋል። በደርግ ዘመነ መንግሥት የነበረ የርዕዮቱ መገለጫ መዶሻና ማጭድ፣ ከካባዎችና የክብር ዘውዶች እንዲሁም ቅንጡ የመመገቢያ ዕቃዎች ጋር በዚሁ በታላቁ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ በክብር ይገኛሉ፡፡
እነዚህና ሌሎች ያልተዘረዘሩ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ አቶ መለስ ዜናዊ ዘመነ መንግሥት ከተለያዩ አገሮች የተበረከቱና ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተሰበሰቡ የአገር ምልክቶችና ቅርሶች ኅብረተሰቡ እንዲጎበኛቸው፣ ደኅንነታቸው ተጠብቆም በክብር እንዲታዩ ተደርጓል፡፡
የግዙፉ ቤተ መንግሥት የውጭ ገጽታውም ቢሆን ለዕይታ ምቹና ግርማ ሞገስን የተላበሰ ቅጥር ግቢ ነው፡፡ በውስጡም የመዋኛ፣ የስፖርት ማዘውተሪያና ሌሎች መዝናኛዎችን ይዞ ለሕዝብ ክፍት ሆኗል፡፡