የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ አንፃራዊ ዕድገት የሚታይበት ቢሆንም የተሸከመው ሥጋት (ሪስክ) የመሸከም አቅም መጠን 12.5 ትሪሊዮን ብር መድረሱ ተገለጸ፡፡ ኢንዱስትሪው ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ሊደረግ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ዘርፍ ቁጥጥርና ክትትል (ሱፐር ቪዥን) ዳይሬክተር አቶ በላይ ቱሉ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በኅብረት ኢንሹራንስ 30ኛ ዓመት ክብረበዓል ላይ ተገኝተው እንደገለጹት እስከ ሰኔ 30 ድረስ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሥጋት የመሸከም አቅማቸው 12.5 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ ኩባንያዎች ትልቅ ሥጋት መሸከማቸውን የሚያሳይ ስለመሆኑም ካደረጉት ንግግር ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ዕድገት ከዓረቦን ገቢ አንጻር ብቻ በመመልከት መፈረጅ ከማይቻልባቸው ምክንያቶች አንዱና ዋናው ኢንዱስትሪው የተሸከመው የሪስክ መጠን በዚህን ያህል የሚገለጽ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ኩባንያዎቹን በዓረቦን ገቢ መመዘን ትክክል እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱ የበዓሉ ታዳሚዎችም ይህንን ንግግራቸውን በጭብጨባ አጅበውት ነበር፡፡ የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው በዓረቦን ገቢው ብቻ መመዘን የለበትም የሚለውን አገላለጽ የደገፉበት ምክንያት የኢንሹራንስ ዘርፍ ለኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦ የሚለካው የዓረቦን ገቢውን በማስላት ብቻ የነበረና ይህም የተሳሳተ ምሥል የሰጠ በመሆኑ ነው ሲሉ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡ ዘርፉ ለኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦ መለካት ያለበት በተሸከመው ሥጋት ልክ መሆን እንደሚገባው ዳይሬክተሩ በግልጽ ማሳወቃቸው ባለሙያዎቹን ያስደሰተውም ለዚህ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር አቶ በላይ በአብዛኛው የኢትዮጵያን የኢንሹራንስ ዘርፍ የ30 ዓመታት ጉዞ ባመላከቱበት በዚሁ ንግግራቸው በተለይ በዓረቦን ገቢ አንጻር መሻሻሎች መታየታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም. 254 ሚሊዮን ብር የነበረው ዓመታዊ ጥቅል ወይም ያልተጠራ የዓረቦን ገቢ መጠን በ2016 መጨረሻ ላይ 28.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከካሳ ክፍያ አንጻርም ከ30 ዓመታት በፊት 111.7 ሚሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰው በ2016 መጨረሻ ላይ ግን ዓመታዊ የኩባንያዎቹ የካሳ ክፍያ መጠን ወደ 9.7 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡
ኢንዱስትሪው አሁን የደረሰበትን ጠቅላላ ሀብትና ኢንቨስትመንት በተመለከተም እስከ 2016 መጨረሻ ላይ የኢንዱስትሪው አጠቃላይ የሀብት መጠን 65.8 ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት መጠኑም 36.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ተመንና የዋጋ ግሽበት በዕድገቱ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ በ1981 ዓ.ም. የነበረው የዓረቦን ገቢ 45.7 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን ከ30 ዓመታት በኋላ ለአራት እጥፍ አድጎ 471 ማሊዮን ዶላር መድረሱንም ጠቅሰዋል፡፡
የመጀመርያው የግል የኢንሹራንስ ኩባንያ ወደ ሥራ ከገባበት 1986 ዓ.ም. ጀምሮ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው በአንጻራዊ ዘርፍ ብዙ ዕድገት ስለማስመዝገቡ ሌላው ማሳያ ይሆናል ብለው በአኃዝ ከጠቀሷቸው ውስጥ ባለፉት 30 ዓመታት የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ቁጥር ከአንድ ወደ 18 ሲደርስ የቅርንጫፎች ቁጥር ደግሞ ወደ 812 ማደጉን ነው፡፡
በገበያ ውስጥ ካሉት 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች 14ቱ በሕይወት ነክ ባልሆነ መድን ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ አራት የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ደግሞ በሕይወት ነክ ባልሆነ የመድን ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ሰባት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የእስላሚክ ኢንሹራንስ (ታካፉል) በመስኮት ደረጃ የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የሥራ ዕድል በመፍጠሩ ረገድ የኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ 2,958 ሽያጭ ወኪሎች፣ 115 ንብረት ገማቾች ለ62 ብሮከሮችና ወደ 8,600 ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ዘርፍ በዓይነትም በብዛትም መለወጡን ለማሳየት የጠቀሱት ደግሞ አንድ የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ሲሆን ይህ አገራዊ የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ የዘርፉን አጠቃላይ ሥጋት የመሸከም አቅም ከፍ የሚያደርግ ወደ ውጭ ይወጣ የነበረውን የካፒታል ፍሰት በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ የሚያስችልና የኩባንያውን አድማስ ከኢትዮጵያ ውጭ በማስፋት ተጨማሪ ገቢ እያስገኘ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኢንሹራንስን ጨምሮ የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሕጎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ከልማት አጋሮች ጋር በመቀናጀት ሰው ተኮር ጥናት የማካሄድና አዳዲስ አገልግሎትና ሥልጠናዎችን የማዘጋጀት፣ መሣሪያዎችን የማውጣትና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢንሹራንስ ዘርፉ ለመሰማራት እንዲችሉ ለማድረግ ሕግ የማሻሻል ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡
የኢንሹራን ኢንዱስትሪው ዕድገት የተደረጉ ጥረቶች የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፍ የሚገባው ደረጃ ላይ ለማድረስና ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም የታለሙ የተለያዩ ሥራዎች ቢሠሩም በተመሳሳይ ኢኮኖሚ ካላቸው አገሮች ጋር ሲነጻጸር በብዙ መሥፈርቶች ወደኋላ የቀረ ስለመሆኑ ግን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በመሆኑም ከዚህ በኋላ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ሊወሰዱ የሚችሉ ዕርምጃዎች ስለመኖራቸው ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም ከሌሎች መሠረታዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ሥራዎች ጋር በተሰናሰለ መንገድ ኢንዱስትሪውን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ ጠንካራና ንቁ የሆነ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋትና ይህንን ለማስፈጸም የሚችል ተቋማዊ አቅም በመፍጠር ላይ እንደሚገኙ ገልጸው ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት የሚደረግበት አሠራር እንደሚተገበር አመላክተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኅብረት ኢንሹራንስ የተመሠረተበትን 30ኛ ዓመት ክብረ በዓል በዕለቱ ያስጀመረ ሲሆን ኩባንያው ሊታይ የሚችሉ ለውጦችን እያሳየ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ የኅብረት ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መሠረት በዛብህ ያለፉት 30 ዓመታት በጠንካራ ሥራ እና በታላላቅ ስኬቶች የታጀቡ እንጂ እንዲሁ በዋዛ ያለፉ አልነበሩም›› ብለዋል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ ለዛሬ ታላቅነቱ ያበቁትን በርካታ ስትራቴጂክና ቁልፍ ተግባራትን ያከናወነባቸው ዓመታት ነበሩ ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ አንበሳ ኢንሹራንስ ይባል ከነበረው ኩባንያ ጋር በማዋሃድ ያከናወነውም ተግባሩ በተለየየሚታይ ነው ተብሏል፡፡
በአቶ በላይ ንግግርም ኅብረት ኢንሹራንስ ሊጠቀስለት ከሚችሉ ተግባራቱ መካከል አንዱ ኩባንያዎቹን የማዋሃድ ተግባሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በኢንዱስትሪው የተለየ ክንውን ብለው እንደተናገሩት ‹‹ለኢንዱስትሪው አዲስ ነገር ከመፍጠር አኳያ በአገራችን የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እጅግም ባልተለመደ ሁኔታ የአንድ ኩባንያ ፈቃድ መሰረዝ፣ (ዩኒቨርሳል ኢንሹራንስ) እና የአንበሳ ኢንሹራንስና የኅብረት ኢንሹራንስ ውህደት በኢንዱስትሪው ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ የሚይዙ ክስተቶች መሆናቸው የሚታወቅ›› ብለዋል፡፡ ለኅብረት ኢንሹራንስ ደግሞ በ30 ዓመታት ውስጥ የጎላ ቦታ ከሚይዙ ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሚሆን መገመት ይቻላል ብለዋል፡፡
ኅብረት ኢንሹራንስ ለኢንዱስትሪው አበርክቷል ተብሎ ከተገለጹት ተግባራት መካከል በኢንዱስትሪው ታሪክ የመጀመሪያ የሆኑትን ሴት ዋና ሥራ አስፈጻሚ እ.ኤ.አ. በ2011 በመምረጥ መሾሙ ኩባንያው በተለየ ሊታወስበት የሚችል መሆኑን የኩባንያው ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ወንድወሰን ተሾመ ገልጸዋል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ወ/ሮ መሠረት በአፍሪካ የ2024 የዓመቱ ምርጥ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በመመረጥ ዕውቅናና ሽልማትን መቀበላቸው እንደ ስኬት የሚታዩ ተግባራቱ ነው ተብሏል፡፡
ኩባንያው ጥንካሬ ሌላው ማሳያ በየጊዜው እያደገ መምጣቱ አንዱ ማሳያ ይሆናል ብለው የጠቀሱት በየዓመቱ ዕድገቱን ጠብቀን መሄድና በተለያዩ አትራፊ ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ የባለቤትነት የአክሲዮን ድርሻ በመያዝ በየዓመቱ ጠቀም ያለ የትርፍ ድርሻ ተካፋይ መሆን መቻሉ እንደሆነ አቶ ወንድወሰን ገልጸው ለባለአክሲዮናች እየከፈለ ያለው የትርፍ ድርሻ ምጣኔ እያደገ መምጣቱም በተመሳሳይ የሚታይ ነው ተብሏል፡፡
ዓመቱን በሙሉ በሚከበረው የኩባንያው 30ኛ ዓመት ከአዲስ አገልግሎት ጋር የሚቀርብ ስለመሆኑ የገለጹት ወ/ሮ መሠረት በበኩላቸው ይህም የታካፉል ኢንሹራንስ አገልግሎት ሲሆን ለአገልግሎቱ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የወሰደ በመሆኑ በቅርቡ ሥራ ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ኩባንያው እስካሁን በተጓዘባቸው ሰላሳ ዓመታት ዘርፈ ብዙ ዕድገትና አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በዚህም ረገድ በተሰብሳቢ ዓረቦን መጠን፣ በካሳ ክፍያ፣ በኢንቨስትመንት፣ በጠቅላላ ሀብት፣ በትርፍ ድርሻ ምጣኔ፣ በሰው ሀብት፣ በአገልግሎት ማዕከል ሥርጭትና በመሳሰሉት ከፍተኛ ዕድገትን በማስመዝገብ ዛሬ ላይ መድረሱንም አቶ ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው ለዚህ እንዲበቃ ከ30 ዓመት በፊት በመሥራች አባላትነት የሚታወቁት ሰዎች የተመሠገኑ ሲሆን፣ በዕለቱ ፕሮግራም ላይም ኅብረት ኢንሹራንስን በመመሥረት በዋናነት የሚጠቀሱ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉና ሌሎች አራት መሥራቾች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡