በርካታ ተማሪዎች ከአካባቢያቸው ርቀው ለመማር ይገደዱ ነበር፡፡ በርካቶች ደግሞ ከፊደል ገበታ እንዲርቁ ሆነዋል፡፡ በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የተነሳም ትምህርት የሚያቋርጡት በርካታ ነበሩ፡፡
ዛሬ ይህ ችግር መቀረፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ልጆቻቸውን ያለሥጋት ትምህርት ቤት መላክ ጀምረዋል፡፡ ይህንን የመማር ተስፋ የፈነጠቀው ደግሞ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከተሰማሩና ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ከሚገኙ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ነው፡፡
ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል ባቱና በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ሁለት ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ ባለፈው ሳምንት ለማኅበረሰቡ በይፋ አስረክቧል፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ በባቱ ከተማ ያስገነባው ‹‹አባ ገዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት›› በተመረቀበት ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሄርቬ ሚልሃድ እንደተናገሩት፣ የትምህርት ቤት ግንባታው ለከተማዋና እንደ አገር የትምህርት መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት አንፃር ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባውና በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀው ትምህርት ቤት፣ አስፈላጊ ቁሳቁሶች የተሟሉላቸው ስምንት የመማሪያ ክፍሎችና ንፅህናቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶች ያሉት ነው፡፡ ከ600 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችል ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
‹‹ድርጅቱ ለማኅበረሰቡ የሚያደርገውን ድጋፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል›› ያሉት ሄርቬ፣ እነዚህና መሰል የማኅበራዊ ኃላፊነት ፕሮጀክቶች ለጋራ ዕድገት ያለንን ራዕይ የሚወክሉ ናቸው፡፡ በተያዘው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር ከትምህርት ቤት ግንባታ በተጓዳኝ በአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራምና በጤና ዘርፎች ላይ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ባሉት የማምረቻ ቦታዎች ከ3‚000 በላይ ለሚሆኑ አባዎራዎች የጤና መድን ሽፋን በመስጠት የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆኑንም ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል፣ የባቱ ከተማ ከንቲባ አህመዲን እስማኤል እንደገለጹት፣ የተማረና በዕውቀት የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የትምህርት ቤት ግንባታ ቁልፍ ነው፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት እንደ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ያሉ ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍና አስተዋጽኦ የሚያስመሰግን ነው፡፡
ድርጅቱ ትምህርት ቤቱን ባስገነባበት ቦታ የሚገኙ ሕፃናት ትምህርት ቤት በማጣት ዕድሜያቸውን ያለትምህርት የሚያሳልፉ መሆናቸውን፣ የትምህርት ቤቱ መገንባት የአካባቢው ማኅበረሰብ ያለምንም እንግልት ልጆቹን እንዲያስተምር ዕድል እንደሰጠና ትውልድ ላይ ለሚሠራው ሥራም መሠረት የጣለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ አህመዲን እንደሚገልጹት፣ በባቱ ከተማ ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ በሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ50 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ዘንድሮ የከተማ አስተዳደሩ ሰባት የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት ገንብቶ ሕፃናት ትምህርት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡
ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ተማሪዎችን በምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ዓምና 17 ሺሕ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ማግኘታቸውንና በ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ቁጥሩ ወደ 21 ሺሕ ማደጉንም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
በአባ ገዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አማን ነገሶ እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ትምህርት ቤት የሌለ በመሆኑ ማኅበረሰቡ እስከ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ልጆቹን ልኮ ሲያስተምር ቆይቷል፡፡
ትምህርት ቤቱ ከኬጂ እስከ ሦስተኛ ክፍል የመማር ማስተማር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በአካባቢው የትምህርት ቤቱ መገንባት ለማኅበረሰቡ ታላቅ እረፍት የሰጠ፣ ደስታን የፈጠረና ተስፋን የፈነጠቀ ነው ብለዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ በበቃ ዋሪዩ በበኩላቸው፣ በሥፍራው ትምህርት ቤት መገንባቱ ታላቅ ደስታ ፈጥሮባቸዋል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በአካባቢው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ሁለትና ሦስት ኪሎ ሜትር በመሄድ ትምህርት የሚያገኙ ሕፃናት ጥቂት ነበሩ፡፡ አብዛኛው ሕፃን ግን ከፊደል ገበታ ርቆ ለመቆየት ተገዷል፡፡
በመሆኑም በአካባቢው ትምህርት ቤቱ እንዲገነባ ላደረጉና ለሕፃናቱ ተስፋ ለሆኑ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ቢጂአይ ኢትዮጵያ በሐዋሳ ከተማ በሚገኘው ‹‹ጨፌ ቆንቦዬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት›› ውስጥ ያከናወነውን የማስፋፊያ ፕሮጀክት አስመርቋል፡፡
የጨፌ ቆንቦዬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕስ መምህር አብርሃም ጊልቦ እንደገለጹት፣ ትምህርት ቤቱ ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ሥራ ተደርጎለታል፡፡ ማስፋፊያ ሥራውም ሰባት አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎችና ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤቶችን ያካተተ ነው፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የተማሪዎችን የቅበላ አቅም ያሻሻለና በአንድ ፈረቃ ከ525 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ያስቻለ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡