- የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኃላፊዎች ስለጉዳዩ የተለያዩ ምላሾችን ሰጥተዋል
ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት በተገኘ 60 ሚሊዮን ዶላርና የፌዴራል መንግሥት ባቀረበው አንድ ቢሊዮን ብር ድጋፍ፣ የትግራይ ክልል የቀድሞ የፀጥታ ኃይሎችን ትጥቅ በማስፈታት ከሠራዊት የማሰናበትና መልሶ የማቋቋም (DDR) የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ከሦስት ሳምንታት በፊት መቋረጡ ተሰማ።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ያስጀመረው የሠራዊት ብተና (Demobilization)፣ ትጥቅ የማስፈታት (Disarmament) እና መልሶ ከማኅበረሰቡ ጋር የመቀላቀል (Reintegration) ፕሮግራም በመጀመሪያ ዙር በአራት ወራት ውስጥ 75,000 የቀድሞ የፀጥታ ኃይሎችን ለማሠልጠን ቢያቅድም፣ ዕቅዱ ግብ ሳይመታ ሰባት ሺሕ የቀድሞ የፀጥታ ኃይሎች የሥልጠናና መልሶ የማቋቋም ሥራ ከተከናወነ በኋላ መቋረጡን ከሪፖርተር ምንጮች መረዳት ተችሏል።
የብሔራዊ ተሃድሶ የሥልጠናውን መጀመር አስመልክቶ በኅዳር ወር 2017 ዓ.ም. ማብራሪያ የሰጡት ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን፣ ፕሮግራሙን በትግራይ ለማስጀመር በክልሉ ሦስት ቦታዎች በመቀሌ፣ በዕዳጋ ሐሙስና በዓድዋ በሚገኙ ማዕከላት የሚከናወኑ መሆናቸውን፣ በቅድሚያ በመቀሌ ማዕከል በመጀመር፣ በቅደም ተከተላቸው መሠረት ሥራውን የማስፋት ዕቅድ መያዙንና አስፈላጊ ከሆነም ሌሎች ሁለት ማዕከላት እንደሚጨመሩ መግለጻቸው ይታወሳል።
በዚህም መሠረት ሥልጠናው በተጀመረበት ሁለት ቀናት ውስጥ 320 የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቃቸውን በማስረከብ፣ ስድስት ቀናት ለሚፈጅ ሥልጠና ወደ መቀሌ ማዕከል መግባታቸውንም አሳውቀው ነበር።
ፕሮግራሙ ከተጀመረ ከሁለት ወራት በላይ ያለፈ ሲሆን፣ ስለሥልጠናው ሒደትና መልሶ መቋቋም ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቀድሞ ተዋጊዎች እንደገለጹት፣ በመቀሌ ከተማ ከሚገኙ ሰባት ክፍላተ ከተሞች ከእያንዳንዳቸው አንድ ሺሕ የቀድሞ የፀጥታ ኃይሎች በአጠቃላይ ሰባት ሺሕ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ሒደቱ ተቋርጧል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የቀድሞ የፀጥታ አባል፣ ‹‹ሰባት ሺሕ የቀድሞ የፀጥታ አባላት ሠልጥነው ከማዕከሉ ከወጡ ሦስት ሳምንታት አልፏል። በቀጣይ ወደ ማዕከሉ ልንገባ የስም ዝርዝራችን ይፋ የተደረገልን ወደ ማዕከሉ እንድንገባ ጥሪ ይደረጋል ብለን ብንጠብቅም እስካሁን ምንም ነገር አልተነገረንም፤›› ብሏል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከሁለት ወራት በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የተሃድሶና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራሙ ትግበራ በመጀመሪያው ዙር 75,000 የቀድሞ የፀጥታ አባላት ከትግራይ ክልል ብቻ ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ሴቶች፣ ዕድሜያቸው የገፉና የአካል ጉዳት ያለባቸው ቅድሚያ ትኩረት እንደሚያገኙ ተገልጿል።
በሁለተኛ ዙር 100,000 የቀድሞ የፀጥታ አባላት እንደሚካተቱና ከእነዚህም አብዛኛዎቹ ከትግራይ ክልል ሆነው፣ ነገር ግን በኮሚሽኑ አሠራር መሠረት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ወደ ሰላማዊ ሥርዓት የገቡ የቀድሞ አባላትና ድርጅቶች ያሉባቸው ክልሎች እንደሚካተቱም ተገልጿል። በሦስተኛ ዙር 150,000፣ እንዲሁም በመጨረሻው ምዕራፍ 50,000 የቀድሞ አባላት በፕሮግራሙ እንደሚካተቱ ይፋ መደረጉም ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪም በአጠቃላይ የፕሮግራሙን ሁሉንም ምዕራፎች ለማስፈጸም 762 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ፣ ከዚህ ውስጥ በትግራይ ለሚከናወነው የመጀመሪያው ምዕራፍ የተሃድሶ ሥልጠናና መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል 60 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት፣ እንዲሁም አንድ ቢሊዮን ብር ደግሞ ከፌዴራል መንግሥት በድጋፍ መገኘቱን ኮሚሽኑ ማሳወቁን መዘገባችን አይዘነጋም።
ለመልሶ ማቋቋሚያ ሥልጠናቸውን ላጠናቀቁ የቀድሞ የፀጥታ አባላት ስለሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተም፣ ፕሮግራሙ በተጀመረበት በኅዳር ወር ሪፖርተር ያነጋገራቸው በመጀመሪያው ዙር የተካተቱ የቀድሞ ታጋዮች 200,000 ብር እንደሚከፈል እንደተነገራቸው ሲገልጹ፣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የኮሚሽኑ ኃላፊ በበኩላቸው፣ ለእያንዳንዱ የቀድሞ ተዋጊ የሚከፈለው የገንዘብ መጠን የተለያየ መሆኑን፣ ኮሚሽኑም ለሕዝብ ይፋ የማያደርገውና በሚስጥር የሚያዝ መሆኑን ገልጸው ነበር።
ከሦስት ሳምንታት በፊት በነበሩት በመቀሌ ካምፕ በተካሄዱ ሥልጠናዎች የተሳተፉ የቀድሞ የፀጥታ አባላት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እያንዳንዳቸው 90,400 ብር ተከፍሏቸዋል። ይሁንና የቀድሞ አባላት አስቀድሞ የተነገራቸው 1,800 ዶላር እንደሚከፈላቸው እንደነበር፣ ነገር ግን ሥልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ የተጠቀሰው መጠን ያለው ገንዘብ ተከፍሏቸው፣ የተቀረውን አንድ ሺሕ ዶላር በጀት ሲለቀቅ እንሰጣችኋለን መባላቸውን ገልጸዋል።
ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኃላፊ በበኩላቸው፣ ‹‹የተነገረው መረጃ ሁሉ ሐሰት ነው። የተቋረጠ ሥልጠናም የለም፡፡ የበጀት ችግርም የለብንም፡፡ የሠራዊት ብተና፣ ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ ከማኅበረሰቡ ጋር የመቀላቀል ፕሮግራም አፈጻጸም የራሱ ሒደት አለው። እሱን ተከትለን እየሠራን ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሪፖርተር ስለጉዳዩ የበለጠ ማብራሪያ እንዲሰጡ ለኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ክፍል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ የሥራ ክፍሉ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንደማይፈልግ አሳውቋል።