በያሬድ ነጋሽ ሐሰን
ሥነ ጽሑፋዊ ዳራው
ሽግግር የመጪውን ጊዜ ይወስናል። ትናንትናና ዛሬን እያነፃፀሩ የሽግግሩን ሁኔታና ያመጣውን ለውጥ ለመረዳት ወይም ምስክር ለመሆን ከሽግግሩ በፊትና በኋላ መኖር ሊጠይቅ ወይም ተጨባጭ ማስረጃ ያሻ ይሆናል። ከዚህ አንፃር፣ በሥነ ጽሑፍ ዓለም፣ አንዳንድ ድርሰቶች፣ ከታሪካዊ ሽግግር በፊት ላልነበሩ አንባቢያን ሥነ ልቦና ሊርቁ ይችላሉ።
‹‹አደፍርስ›› በተሰኘው የዳኛቸው ወርቁ መጽሐፍ ውስጥ፣ ደራሲው አጀንዳ አድርጎ የተነሳበት ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ በድርሰቱ የሚታየው አካባቢያዊና ቤተሰባዊ አወቃቀር፣ ከዚህ ዘመን ወጣት ሥነ ልቦና እሩቅ ከመሆኑ አንፃር፣ መጽሐፉ ንድፈ ሐሳባዊ አድርገን በመረዳት አንብበን ጨርሰናል ወይም በልብ ወለድ ደረጃ ብቻ ተቀብለነው አልፈነዋል።
መቼቱ ደብረሲና ላይ የተሣለውና በአለቃ ደስታ ተክለ ወልድ አማርኛ ወደ አማርኛ መዝገበ ቃላት [ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት] ድጋፍ ካልሆነ በቀር ለማንበብ በሚያዳግተው አደፍርስ በተሰኘው ልብወለድ ውስጥ (በተለይ የመጽሐፉ መግቢያ ክፍል)፣ በእኛ ዘመን አጠራር ‹‹ክልል አራት›› ከምንለው ሥፍራ የሆነው የገበሬዎቹ አለቃ ‹‹ወርዶፋ›› ዋሽንት እየነፋ ከተፍ ይላል (አደፍርስ፣ ገጽ 32)። ‹‹ክልል አንድ ከምንለው ወይም ከኤርትራ አካባቢ ውሉድ የሆኑት የደብረ ቢዘኑ አባ ዮሐንስ ደብረ ሲና ስላለ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ መዋጮ ያሰባስባሉ። (አደፍርስ፣ ገጽ 75)
በዚህ አያበቃም፣ ሁሉም እምነት ተከታይ በአንድ አድባር ሥር ያሰባስባል። ‹‹ወደ ደሴ እሚወርደው መኪና መንገድ አቅራቢያ የማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ ከበታቹ ደሞ ወደ አረጋዊ ደብር መገንጠያው ላይ የድንጋይ ቁልል ይታያል። የድንጋዩን ቁልል አድባር ይሉታል። ክርስቲያኑም፣ እስላሙም፣ ዛር ፈረሱም፣ ጠንቋዩም ሃይማኖት የለሹም፣ በዚያ ጎዳና የሚያልፉ ከሆነ፣ ከሩቅ ሥፍራ እጃቸው የገባውን ነገር፣ እንጨትም ሆነ ድንጋይ ይዘው መጥተው እላዩ ላይ መጨመር ይኖርባቸዋል። ያልታሰበ አደጋ እንዳይመጣ ይከላከላል›› የሚል እምነት አለ ። (አደፍርስ ገጽ 74)
እንዲሁ፣ 1990ዎቹ እና 2000ዎቹን ዘልቀን፣ ‹‹በአደፍርስ መጽሐፍ በተሳለው ቤተሰባዊና አከባቢያዊ መልክ ዓይነት የኖረች ኢትዮጵያ ነበረች?›› በሚል የሚያጠያይቁ ማመሳከሪያዎች፣ በጎራ መከፋፈል፣ አብሮ መኖር ይቅርና፣ ማዶ ለማዶ ቆሞ መነጋገር የሚቻል የማይመስልበት የአገራችንን ገጽታ ተመለከትን። እዚህ ላይ ሳለን ዓለማየሁ ገላጋይ ሸኖ አከባቢ የተሳለ መቼት ‹‹ቤባንያ›› በሚል ርዕስ በመጽሐፍ መልክ ለንባብ አቀረበልን።
‹‹አደፍርስ››ን ሳንውጥ ጉሮሮዋችን ላይ እንደቆመ፣ ‹‹ቤባንያ››ም ነገሩን በአንድ ቤተሰብ መስሎ፣ ‹‹መፍትሔ›› የተሰኘውን ዋና ገጸባህሪ፣ ከአንድ እናትና አባት ተወልዶ፣ ከተለያየ ሥፍራ በመጡ ሁለት የእንጀራ አባቶች፣ እና በአንድ የእንጀራ እናት የእንክብካቤ እጅ ላይ እንዲያድግ ፈቀደለት። የመፍትሔ የመጀመሪያ የእንጀራ አባት የሆኑት ወለዬው ጋሽ ይማም ከራማውን ይለማመኑለታል፣ መንገድ እንዲቀናው ይመረቁታል። ‹‹አብረኸት የተሰኘች ትግራዊት እንጀራ እናቱ የእናት እቅፍ አልነሳችውም። ሁለተኛው የእንጀራ አባቱና ኦቦ ሳፎይ የተሰኙት የቦረና ኦሮሞ ወገን፣ ‹‹ፈያ ኢሳኒ ሀኬት (ጤና ይስጣችሁ)፣ ሆራ ብላ (በልጽጉ)፣ ፈያ ሀሲከኑ (ጤና ይስጥሽ)፣ ለፍ ነጋ ሀኑቶልቹ (ሠፈር ደና ይሁን)፣ ረራ ነጋ (መንደሩ ደና ይሁን)›› በሚል ለታመመው፣ ለጤነኛውና ለሳር ቅጠሉ ሳይቀር እንትፍ እያሉ ምርቃቱን ያወርዱታል። ‹‹መፍትሔ›› ጠፍቶ መቅረቱን የተመለከተች ወላጅ እናቱ ‹‹ትከና ትከና›› (ልጄ ልጄ) እያለች በጉራግኛ ስታለቅስ እናነባለን (ቤባንያ፣ ገጽ 129 )።
1983 ዓ.ም. ካለፈ ተወልዶ፣ ከ1995 ዓ.ም. በኋላ ጉርምስናን ማጣጣም የጀመረና የማንበብ ልምድ ላለው ወጣት፣ ከአንዱ ቀዬ ሌሎች ሲፈናቀሉ እንጂ በአንድ ቀዬ ውስጥ ከሌላ ሥፍራ የመጡ ሰዎች ተሰባስበው፣ ሳቅ ጨዋታ ሲለዋወጡ፣ ቅድሚያ ሲሰጣጡና ለመኖር ሲቻላቸው፣ አንደኛው ከራሱ አካባቢ አልፎ ለሌሎች ክልሎች ሲቆረቆር፣ ልማት ሊያመጣ ሲጣጣር አልተመለከተምና፣ ሃይማኖቶች አንዳቸው በአንዳቸው ሲነወሩ፣ ዘለፋ ውስጥ ሲገቡና ቤተ እምነታቸው ሲቃጠል እንጂ ሁሉን የሚያስማማ አንድ አድባር የመሰናዳቱ ነገር ዘበት ሆኖበታልና፣ የሁለቱ መጻሕፍትም ይሁን በዚህ መልኩ የተዘጋጁ ሌሎች ልብወለዶች አቀራረብ ንድፈ ሐሳባዊ አድርጎ ሊረዳው ወይም ከልብወለድ ያልዘለለ አድርጎ መቁጠሩ የማይቀር ነው። ከአንዳንድ ሰዎች የቃል ምስክርነት አግኝቶ ወይም ከዚህ አንቀጽ አዘጋጅ መረጃ የማግኘት ወሰን ውጪ ሆኖ ካልሆነ በቀር፣ ‹‹’እንዲህ ኖሬያለሁ’ የሚል ተጨባጭ (Empirical) የኑሮ ምስክርነት በሰነድ መልክ አግኝቷል›› ለማለት ያስቸግራል።
2016 ዓ.ም. ‹‹እንዲህ ኖረናል›› የሚል ድምፅ በሰነድ መልክ ቀረበልን። ይኸውም ‹‹አገር በአንድ ሺሕ ቀን›› የተሰኘው የፍሬዓለም ሽባባው መጽሐፍ ነበር። ይህ መጽሐፍ የሕይወት ተሞክሮዋን ያካፈለችበት ሆኖ፣ ከላይ ላየናቸው ሁለት ድርሰቶች ተጨባጭ ማስረጃ ሆኖ መቅረብ ይቻለዋል።
‹‹ቤታችን የእንግዳ ቤት ነው (አገር በአንድ ሺሕ ቀን፣ ገጽ 13)።… እጅጋየሁ በዘፈኗ ውስጥ የሳለቻት ኢትዮጵያ እኛ ቤት ውስጥ ያየችውን ነው። ያደግነው ሁሉም ሰው እኩል ተከብሮ ከሚስተናገድበት ቤት ነው። እጅጋየሁ ሙሉውን ባትናገረውም ‹‹ናፈቀኝ›› በሚለው ዘፈኗ ያንን ነው ልትገልጽ የሞከረችው (ገጽ 16)።›› ትለናለች።
የወቅቱ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተክለሃይማኖትን እንግዳ አድርጎ የተቀበለው ቤት፣ ለሙስሊሙ የቤኒሻንጉል ሰው ፊት አውራሪ አልገመርም ክፍት ነበር። ሙስሊምም ክርስቲያንም ካልሆኑትና ማንዱራ ከሚባል አከባቢ ለሚመጡ ጉምዞች፣ ጳጳሱና ፊታውራሪን የተቀበለ ቤት አልተዘጋባቸውም (ገጽ 15)። በደርግ አገዛዝ ተጽዕኖ ሥር ወድቆ ለስደት የተገደደው በርካታ ወጣት፣ በሽባባው ደጅ ያለፈ እንደሆነ፣ ማደሪያ ተሰናድቶለትና ስንቁ ተቋጥሮለት በጠዋት ይሸኝ ነበር።
ይኼኔ ታዲያ፣ ቤቱ የ‹‹አደፍርሱ›› ሁሉን የሚሰበስብ የቁልል ድንጋይ አድባር ሆኖ ያርፈዋል።
ከጎንደር ፈልሰው የመጡት ማሲንቆ ተጫዋቾች ቤቱን ሲያሞቁት ባየንበት ቅጽበት፣ ከወንበራ አካባቢ የሚመጡ ኦሮሞዎችና ሺናሻዎች ሳቅ ጨዋታውን ይቀላቀላሉ (ገጽ 14)። ይበላል፣ ይጠጣል። የአቶ ሽባባው እናት እማሆይ ደብሬና ለእማሆይ ደብሬ አገልጋይ የነበሩት እቴቴ ትሁን፣ በስተመጨረሻ ተጎራባች ጎጆ ተቀልሶላቸው ይጦራሉ (ገጽ 35)፣ የፍሬዓለም እናት ወይዘሮ ተናኜ ምሽት ላይ ሠራተኞቻቸውን ሰብስበው መጽሐፍ ይተርኩላቸዋል። ሠራተኞች ያርፉና የቤቱ ልጆች እንዲያስተናግዷቸው ይደረጋል። (ገጽ 24)። ጨዋታው ይደራል። እጅጋየሁ ‹‹ጠይም ዘለግ ያለ ጎራዴ ታጣቂ›› እያለች ታዜማለች። ‹‹አዲስ ዘፈን ጽፌያለሁ አድምጡኝ›› ትላለች። የእናታቸው እናት እማማ ዘውዲቱ ‹‹እዚህ ቤት ሳቅ ጨዋታ ይበዛል›› ብለው እስኪቆጡ ድረስ።
በዚህ ቤት ያደጉ ልጆች፣ በዓለማየሁ ገላጋይ ድርሰት ‹‹ቤባንያ›› ውስጥ በሁሉ እቅፍ ካደገው ‹‹መፍትሔ›› ምን ለያቸው?
ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ያለ አጋር ወድቀው የነበሩትና በአቶ ሽባባው ቤት ለእንክብካቤ የመጡት እማማ ሁሌ፣ ይህንን የቤቱ ሁኔታ ከተመለከቱ በኋላ ቤቱን ‹‹ቤተ እግዚሃር ነው›› ሲሉ ሰየሙት።
‹‹እማማ ሁሌ፣ የእኛን ቤት ስም አውጥተውለታል። በተለይ ሰው የሚሰበሰብበትን ትልቁን ቤት የሚጠሩት ‘ቤተ እግዚሃር’ እያሉ ነው። በዚህ ስያሜ ዙሪያ እማማ ሁሌና እናቴ ተከራክረው ያውቃሉ። ተናኘ ከቤተ ክርስቲያን እኩል ቤታችንን ቤተ እግዚሃር ማለታቸውን ተቃውማ ልታስቆማቸው ሞክራ ነበር።
‹እማማ ሁሌ፣ ይሄኮ ቤተ እግዚሃር አይደለም። ለምንድን ነው የሚሉት?› አለቻቸው።
እማማ ሁሌ፣ ‹አንቺዬ፣ ይሄኮ ቤተ እግዚሃር ነው። የመጣ ሁሉ (ሙስሊሙም፣ ክርስቲያንኑም፣ ከሁለቱም ያልሆነውም) የሚገባበት፣ የሚበላበት የሚጠጣበት፣ የሚስተናገድበት፣ የሚያድርበት ቤት ከሆነ እሱ ቤተ እግዚሃር ይባላል። ቤተ ክርስቲያንማ ክርስቲያን ብቻ ተሰብስቦ የሚጸልይበት ሥፍራ ነው›› ብለው ዝም አሰኟት። (ሀገር በአንድ ሺሕ ቀን፣ ገጽ 23)። ይህንን የሁሉ መሰብሰቢያ ትልቅ ቤት ያነጸው የዓድዋ ሰው ነበር (ገጽ 12)።
ያኔ ሰዎች ስለክልላቸው ብቻ የሚወያዩበት አልነበረም። ኦሮሞው ከአማራው፣ ትግራይ ከአፋሩ ስለዳር ድንበሩ ይወያይ ነበር። ‹‹ከማንኩሽ አካባቢ የሚመጡት ፊት አውራሪ አልገመር ከአባቴ ጋር በዓባይ ዙሪያ፣ ከወንዙ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች፣ አንዳንድ ጠረፍ ላይ ስላለው የፀጥታ ሁኔታ ይወያዩ ነበር።›› (ሀገር በአንድ ሺሕ ቀን፣ ገጽ 15)
ያኔ በአንድ አገር ላይ ሐጎስ፣ ግደይ፣ ህሉፍ በአንድ ወገን፤ ክንዴ፣ ድፋባቸው፣ ደባልቄ በሌላ ወገን ጦር የተማዘዙበት፣ የአንድ አገር እናቶች ለየጎራው ሁለት ስንቅ ያዘጋጁበት ወቅት አልነበረም። ትግራዩ የአማራው፣ አማራው የትግራዩ አዛኝና ደጋፊ ነበር። ደርግ ሥልጣን ሲይዝ በአድሃሪነት የተፈረጀው ይህ ቤተሰብ፣ ኢሕአዴግ አገር ሲቆጣጠር ደሞ ‹‹ኢሠፓ ናችሁ›› የመባል ዕጣ ገጥሞት ብዙ ንብረት ተወረሰበት። ንብረታቸውን ለማስመለስ የሚያደርጉትን ጥረት ፍሬዓለም ስታስታውስ፣ ‹‹አንዱ እስካኒያ ከባድ መኪና ወላጆቼ ቀጥረውት አብሯቸው ይሠራ የነበረው ‹ጋሽ ግደይ› ከእናቴ ጋር በስውር እየተገናኙና እየተመካከሩ ከብዙ ወራት በኋላ መኪናውን አስመልሶላታል (ገጽ 45)።
ባለንበት ወቅት፣ ከእንዲህ ያለ የመተዛዘን፣ የመተባበርና የወንድማማችነት ዘመናችን ይልቅ ለግጭት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዩች አጀንዳ ሆነው ለትውልዱ ሲነገር ማድመጥ ያማል።
ያኔ ‹‹እንዲህ ያደረጉኝ፣ ያንገላቱኝ፣ ግፍ የደረሰብኝ አማራ፣ ትግራይ፣ ጉራጌ ስለሆንኩ ነው›› አይባልም ነበር። የሽባባው ቤተሰብ በየሥርዓት ለውጡ የደረሰበትን በደል ‹‹በእኛ ብቻ የመጣ ሳይሆን የአገር ችግር ነው (ሀገር በአንድ ሺሕ ቀን፣ ገጽ 46)›› እያሉ አልፈውታል።
በማጠቃለያው አደፍርስ፣ ቤባንያ በተሰኙና ሌሎች መሰል መጽሐፎች ውስጥ የቀረበው ልቦለዳዊ ወይም ንድፈ ሐሳባዊ መልክ ኢትዮጵያውያን በተጨባጭ ይኖሩበት የነበረ መሆኑን ‹‹ሀገር በአንድ ሺሕ ቀናት›› መጽሐፍ፣ በተለይም ከ1983 በኋላ አዋቂነትን ማጣጣም ለጀመርን ልጆች በቃል ሲነገር ከምናደምጠው ይልቅ ተጨባጭ ማስረጃ ወይም ሰነድ ሆኖ ማገልገል ይቻለዋል። ሥነ ጽሑፋዊ ዳራው ይህ ነው።
አካዴሚያዊ ዳራው
የሕይወት ዘመን ተሞክሮዎች በጽሑፍ መልክ ሲሰነዱ፣ ዕውቀት ይደራጃል። በውጭው ዓለም ውኃ ጉድጓድ ለመቆፈር ወደ ታዳጊ አገር የተላከ ዜጋ፣ ማንም ሳያስገድደው፣ ስለሰማይ ምድሩ አንዳች ሳያስቀር በሰነድ መዝግቦ ወደ አገሩ ይመለሳል። ለአገሩ መረጃና ዕውቀት ሆኖ ይደራጃል።
‹‹ሰበዝ›› በተሰኘ የዓለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር) መጽሐፍ ውስጥ፣ የሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ነፍሱን ከማትረፍ ይልቅ ሰነድ ማዘጋጀት ስለቀለለው የውጪ አገር ፕሮፌሰር ይነግረናል።
‹‹ፕሮፌሰሩ፣ በባህር ዳርቻ ላይ አንድ መርዛማ እባብ በመያዝ ለተማሪዎቹ ገለጻ በማድረግ ላይ ሳለ፣ እባቡ ያመልጥና እጁን ይነድፈዋል። በሥፍራው ሕክምና ለማግኘት የማይታሰብ ነበር። ፕሮፌሰሩ ተማሪዎቹን ማስታወሻቸውን እንዲያወጡና እንዴት አድርጎ እንደሚገድለው ሒደቱን እንዲጽፉ ትዕዛዝ አስተላለፈ።›› (ሰበዝ)። እንዲህ ናቸው።
በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መመልከት ከጀመርነው የአንዳንድ ሙያተኞች ማስታወሻ በቀር፣ አያሌ ሙያተኞች፣ አይደለም መላ ዘመናቸው፣ ከተሞክሯቸው ቅንጣት ተቆንጥሮ ቢጻፍ ሊታደግ የሚችለው በርካታ ነገር ቢኖርም፣ ይኼ ሳይሆን እንደተዳፈነ ወደ መቃብር ሲወርዱ ተመልክተናል። ነገሩን ትምክህት አድርጎ በመቁጠር ዝምታ ለመረጡ ሙያተኞች ተቆርቋሪ በመሆንና ጠቀሜታውን በመረዳት የሕይወት ታሪካቸውን ሰንዶ ለንባብ ማብቃት የተቻላቸው የሥነ ጽሑፍ ሰዎችም እምብዛም አልታዩም።
ፍሬዓለም ‹‹ሀገር በአንድ ሺሕ ቀናት›› በሚል ባዘጋጀችው መጽሐፍ፣ ተሞክሮዋን በመቀመር ዕውቀት አደራጅታለች። ‹‹በዴቨሎፕመንታል ስተዲስ›› የትምህርት መስክ ሥር ላሉት፣ በተለይም ለሴፍቲኔት ፕሮግራሞች፣ ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው ጠቃሚ ሰነድ ትታለች። አካዴሚያዊ ዳራው ይኼ ነው።
ሆኖም፣ ‹‹ሀገር በአንድ ሺሕ ቀን›› የተሰኘውን መጽሐፍ ፍሬ ነገር መዘንጋት አይገባም።
‹‹ብዙ ጥናቶችና ተሞክሮዎች እንደሚያረጋግጡልን የአገሮች ጤናማ ዕድገትና ቀጣይነት ያለሥጋት የሚረጋገጠው በቤት፣ በትምህርት ቤትና በማኅበረሰቡ መካከል ሕፃኖቻቸውን በሚይዙበትና በሚያሠለጥኑበት መንገድ ነው። ያደጉ አገሮች የዕድገታቸው መሠረትም ይኼ ነው›› ትላለች በመግቢያዋ። ስለዚህ ‹‹የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያረጋግጥ ትውልድ ለማግኘት፣ የኢትዮጵያ ሕፃናትን አቅም ከጅምሩ ማሰናዳት ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ ነው፤›› እያለችን ነው ።
የአገራችን የሕፃናት አያያዝ ነባራዊ ሁኔታ ግን ለዕድገት መሠረት ከመሆን ይልቅ እንባ እንዲቀድማት የሚያስገድድ ሆኖ፣ ሁለት ሦስት ቀን ምግብ የማያገኝ ታዳጊ በርክቶ አገኘችው። ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ‹‹ሀ›› ብላ የጀመረችውን መንገድ በመጽሐፏ ታስቃኘናለች።
‹‹በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በስዊዲን ኤምባሲ በኩል መጥተው ‹‹ፋፋ›› የተባለ የመጀመሪያውን የሕፃናት የምግብ ማምረቻ ያስጀመሩልንን ስዊዲናዊ አቶ ኑትሰንን ታሪክ አይዘነጋቸውም›› በማለት ከሷ በፊት በዘርፉ የተደረጉትን ታሪካዊ ጥረቶችን አመስግናለች።
ፍሬዓለም፣ ስለ ረሃብ ስታነሳ፣ አንድ ትልቅ ጥያቄ እንድንጋፈጥ ታስገድደናለች። ልጅነቷን ባስታወሰችበት በመጽሐፉ ምዕራፍ፣ ረሃብ በማያውቅ ቤተሰብ ማደጓን እንመለከታለን። ቤታቸው፣ ከ200 በላይ ከብቶች ያሉበት፣ ወተት ለመንደሩ ሰው እንዲሁ የሚታደልበት፣ ሽሮ እንኳን ከውኃ ይልቅ በወተት ይሠራ እንደነበር አስነብባናለች።
ታዲያ ‹‹ጥጋብ ላይ ሳሉ ስለረሃብ ማሰብ እንደምን ያለ ነው? እንደምን ተቻላት?›› ያሰኛል።
ሆኖም ቀጠል ብለን በምናነበው የመጽሐፉ ገጾች፣ ረሃብ የሚለውን ድምፅ የሰማችበትን ቅጽበት ታስታውሳለች።
በልጅነቷ፣ የተጎዱ ሰዎች በስደት ወደ ፓዊ የመጠለያ ጣቢያ በደጇ ሲያልፉ ተመልክታለች። ‹‹አዳፋ የለበሱ፣ የተጎሳቆሉ›› ትላቸዋለች። ‹‹ምንድን ናቸው?›› ስትል ጠይቃ፣ ‹‹ከወሎ አከባቢ በርሃብ ምክንያት የተፈናቀሉ›› የሚል ምላሽ አግኝታ፣ ‹‹ርሃብ›› የሚል ድምፅን አሐዱ ብላ አደመጠች። እንባ ቀናት።
ፍሬዓለም፣ ያስለቀሳት ይህ ክስተትም ይሁን በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ የሚነሱ የረሃብ ወቅታት የነበራቸውን ጥልቀት የሚያስመለክተን አንድ ታሪክ እናንሳ።
ገጣሚና ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ፣ ወሎ አካባቢ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ጀምሮ በነበረ የጃፓን ተራድኦ ድርጅት ውስጥ በሚሠራበት ወቅት፣ መልቀቂያ እንኳን ሳያስገባ ሥራውን ለቆ ወደ ሱዳን የተሰደደበትን ምክንያት ለማንም ሳይናገር ምስጢር አድርጎ ከኖረ በኋላ፣ በመጠጥ ኃይል ገፋፊነት ለአንድ ወዳጁ እኩለ ለሊት ላይ አጫውቶት ነበር።
ከዕለቱ ቀደም ብሎ ምስር ወደ ታደለበት መንደር፣ የሥራውን ግብረ መልስ ለመመልከት ሙሉጌታ ይገባል። ምስሩ የሚታደለው፣ ተጠቃሚው ቀቅሎ ጥቅም ላይ እንዲያውለው ነበር። ሙሉጌታ ወደ መንደሩ ዘልቆ አንድ ሕፃን እያደረገ ያለውን ተመለከተ። የተቀቀለ ምስር ሳይፈጭ ከሰውነታችን ሊወገድ ይችላል። ሙሉጌታ የተመለከተው ሕፃን፣ ሳይፈጭ ከሰው ሆድ የተወገደውን ምስር እየለቀመ ሲመገብ ነበር። ሙሉጌታ ይህንን ከተመለከተ በኋላ ‹‹ማቄን ጨርቄን፣ እዚህ ነኝ እዚያ ነኝ›› ሳይል፣ የሥራ መልቀቂያ ሳያሻው ወደ ሱዳን ተሰደደ። (ታሪኩ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ሲዘዋወር የሰነበተ ነው)።
እንዲህ ያለ ነገር፣ አይደለም የጥበብ ውቃቢ ወዳሻት ለምትመራው ባለቅኔ ይቅርና ለማንስ ቢሆን አይከብድም? ‹‹ባገኙት ሰርጥ ግቡ፣ በበረሃው ተሰደዱ›› አያሰኝም? ይህንን መልካችንን ለመቀየር መረባረብ አልነበረብንም? የዚህ አገር ሕዝቦች ከዶማ ይልቅ መሣሪያ ለማንገት ይገባን ነበር? ሞራሉንስ ከወዴት አገኘነው?
ፍሬዓለም፣ በጥልቀቱ እጅግ አሳዛኝ የነበረው የረሃብ ወቅት አልፎ አገር ብትለቅም፣ በምትኖርበት አሜሪካ ነገሩን ለዘለፋ ጥቅም ላይ አውለው ‹‹አይዞሽ፣ እዚህ ምግብ አለ›› ያሏትም አልታጡም።
‹‹የራበኝ እንጀራው- እህሉ መስሏቸው
የጠማኝ ወይን ጠጅ- ወተቱ መስሏቸው
ያች ቆንጆ ተራበች- ሲሉኝ ሰማኋቸው
እኔን የራበኝ ፍቅር ነው›› ስትል ስንኝ ቋጠረች። (ጂጂ ሌሎች ስንኞች ጨምራ ‹‹የራበኝ ፍቅር ነው›› በሚል በዜማ ተጫውታዋለች።)
ፍሬዓለም፣ የአባቷ ድብ አንበሳ ሆቴል ግንባታ ሥራ ላይ ‹‹መሥራት አልቻለችም፣ በአቅም ማነስ እየወደቀች ነው›› በሚል የግንባታው ኃላፊ ሊያባርራት የነበረችን እናት አስጠርታ ብትጠይቃት፣ ‹‹ለአምስት ቀን ምግብ ስላልበላሁ ነው›› የሚል ምላሽ አደመጠች። ሴትየዋን አስወጥታ ግድግዳ ተደግፋ አነባች።
ልጇን ለማስተማር የተደራጀ ትምህርት ቤት በማጣቷ፣ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ያመቻቸውን የግል ኢንቨስተሮች የትምህርት ቤት የግንባታ ቦታ ሊዝና ብድር ተጠቅማ በገነባችው ትምህርት ቤት፣ የነፃ የትምህርት ዕድል የሰጠችው ታዳጊ ባዶ ምሳ ዕቃ አንጠልጥሎ የሚመጣ መሆኑ መረጃው ደረሳት። ይህም አንብታ የምታልፈው ብቻ ሳይሆን ወደ ጉዳዩ የበለጠ እንድትቀርብ፣ ጥናት እንድታደርግና ዳሰሳዋን ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት እንድታሰፋ አስገደዳት።
‹‹የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቀድመው ተለቀው፣ ወደ ፍሬዓለም ትምህርት ቤት ደጃፍ በመገኘት፣ ከተማሪዎች ትራፊ ምግብ ይጠብቁ ነበር። የፍሬዓለም ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ፍርፋሪ ከደጅ ለሚጠብቁ ተማሪዎች መስጠት እንዲያስችላቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው ‹‹ምሳቃው አልበቃኝም›› በማለት የምሳቃውን መጠን ያሳድጉ፣ ቁጥሩን ይጨምሩ ነበር።›› (ሀገር በአንድ ሺሕ ቀን)
እንግዲህ፣ የእነዚህ ሩሩሃንና ንጹሃነ ልቦና ጨቅላዎች ላይ መልካሙን ዘር ዘርተን ቢሆን የት በደረስን !!! የዘራንባቸው ግን ሌላ ነው።
በዚህ አንቀጽ ዝግጅት ለመዳሰስ ከሞከርነው በላይ ዝርዝር ጉዳዩችን የያዘና ሥነ ጽሑፋዊ ይዘቱም የተስማማ በመሆኑ አንባቢያን መጽሐፉን (ሀገር በአንድ ሺሕ ቀን) እንዲያነቡት እየጋበዝን ወደማብቂያችን እንድረስ።
በግል ትምህርት ቤቷ ባዶ ምሳ እቃ ይዞ የሚመጣ ሕፃን በማግኘቷ ‹‹ሌሎችስ ይኖሩ ይሆን?›› ብላ ለማሰሷ፣ በራሷ ትምህርት ቤት ቢታጣ ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ለማፈላለጓ፣ ከባህር ዳር ከተማ አልፋ ለመሻገሯ ሰበብ ሲሆናት እንመለከታለን። ከዚህ አንፃር ፍሬዓለም፣ ‹‹በአገሯ የተራበ ሕፃን የለም›› ቢሏት እንኳን ምናቧ ወደ ጎረቤት አገር የሚሻገር፣ አልፎ አኅጉር የሚያቋርጥና ዓለምን የሚያስስ ነውና ‹‹ሩጫዬን ጨርሻለሁ›› ብላ እንደማታስብ እሙን ነው።
በአሜሪካ አገር የተማሪዎች ምገባ የተጀመረው በ1946 ዓ.ም.፣ በፕሬዚዳንት ትሩማን ጊዜ ሲሆን ጅማሬውም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካስከተለው የምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሲቪል ሶሳይቲው ጫና በማሳደሩ ምክንያት እንደነበር፣ በመጽሐፏ ውስጥ አስነብባናለች። አድናቆታችንን ከፍ የሚያደርገው ጉዳይ፣ ፍሬዓለም ሌሎች እንዲህ በማኅበር ደረጃ የሚሞግቱለትን ጉዳይ፣ በአንድ በሬ ትስበው የነበረ መሆኑን ነው።
ፍሬዓለም የተሳካላት ሴት መሆኗን ማስረገጥ ያሻል።
አንድ ዜጋ ልቡን በነካው አገራዊ ችግር ውስጥ የመጀመሪያ ጉዞውን ይጀምራል። ፈተናውን አልፎ ማኅበረሰባዊ ግንዛቤ ይፈጥራል። በፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲካተትና የበጀት ድጎማ እንዲኖረው መንግሥት ላይ ጫና ያሳድራል። እንደ ጥንካሬው መጠን ማኅበረሰብ ይገነዘብለታል። መንግሥት የፖሊሲ አጀንዳው አድርጎ ጉዳዩን በበጀት ይደግፋል። የፍሬዓለም ዕቅድ ከዳር ዳር መድረስ ቢሆንም ይህንን ሁሉ እርከን አሳክታለች። በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ደረጃ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ፍሬዓለም በአንዲት ነፍሷ፣ በአንዲት ቦታ የጀመረችው ተጋድሎ ውጤት ነው። ሐሳቧ ከአገር አልፎ ለዓለም እንዲተርፍ እንመኛለን።
በማኅበረሰብ ዘንድ ትኩረት የተነፈጋቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ጉዳዩ አድርጎ፣ እሷ በተጓዘችው ልክ መጓዝ ቢቻል፣ ችግሮቹ በጊዜ ሒደት ከአገራችን ገለል የሚሉበት ጊዜ ሩቅ አይሆኑም።
ሰላም!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡