የአማራ ክልላዊ መንግሥት ካለበት የተደራረበ ኃላፊነት አኳያ ለአገራዊ ምክክሩ አስቻይ ሁኔታዎች መፍጠር እንዳለበት፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡
ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችንና የወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስተያየት የሰጡት ኮሚሽነር መላኩ ወልደ ማርያም፣ ‹‹መንግሥት በሆደ ሰፊነት አንዳንድ ዕርምጃዎችን መውሰድ አለበት ብዬ አምናለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሦስት ዓመት የሥራ ዘመኑን ያጠናቀቀውን የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ያልተጠናቀቁ ሥራዎቹን ለመጨረስ፣ የሥራ ዘመኑን ለተጨማሪ አንድ ዓመት ማራዘሙ ይታወሳል፡፡
ኮሚሽነሩ በአማራ ክልል ካሉ 267 ወረዳዎች ውስጥ በ259 ወረዳዎች የተሳታፊ ልየታ መካሄዱን ጠቅሰው፣ በክልሉ የሚካሄደውን ምክክር የበለጠ ውጤታማና ተጨባጭ ለማድረግ፣ ከመንግሥት የሚጠበቁ ጉዳዮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምክክሩ ከአንድ ወገን ብቻ በሚዘረጋ እጅ የሚከናወን ባለመሆኑ፣ በሁለቱም ወገኖች ፈቃደኝነት መኖር አለበት ብለዋል፡፡
‹‹ጥያቄ አለን ብለው ጫካ ገባን የሚሉት አካላት እውነት የሕዝብ ጥያቄ ካላቸው ወደ ጠረጴዛ የማይመጡበት ሁኔታ የለም፡፡ በሦስተኛ አገር ጭምር ድርድር ሊያደርጉ የሚችሉበትን ሁኔታ ኮሚሽኑ እንደሚያመቻች ገልጸናል፡፡ ነገር ግን ቢያንስ በመርህ ደረጃ እንኳን እቀበላለሁ ብሎ ወደፊት የመጣ የለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ከመሞት የሚገኝ ነገር የለም፡፡ የአንድ ሰው የሕይወት ዋጋ ትልቅ ነው፡፡ ምድር ብተሸጥ እንኳ የአንድን የሰው ሕይወት ሊተካ አይችልምና ይህ መንገድ አዋጭ ባለመሆኑ፣ በምክክር የሚገኝ ውጤት ከምንም ጋር ሊወዳደር አይችልም›› በማለት አስረድተዋል፡፡
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ የትግራይ ክልል ተወካዮች በሌሉበት ሕጎች ስለመፅደቃቸውና የክልሉ ተወካይ በሌለበት በፓርላማ መቋቋም ፀድቆ መሥራቱን፣ ይህ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ዘንድ እንዴት ይታያል የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው መልስ ሰጥተዋል፡፡
‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምክክር ኮሚሽኑን ብቻ ሳይሆን እጅግ በርካታ አዋጆችን አፅድቋል፡፡ በእነዚህ እጅግ በርካታ አዋጆች ደግሞ አገሪቱ ትመራለች፡፡ በትግራይ ክልል ጦርነት በነበረበት ወቅት ብዙ አዋጆች ወጥተዋል፡፡ ይህ የአገራዊ ምክክርም የተቋቋመው እነሱ ጦርነቱ ላይ በነበሩበት ጊዜ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ይህንን በተመለከተ ከትግራይ ክልል ተሰጠ ያሉትን መልስ ሲገልጹ፣ ‹‹በመጀመሪያ በአገራዊ ምክክሩን አላመንበትም ነበር፡፡ ነገር ግን በኋላ ስናየው በዚያ ሒደት ውስጥ የወጡ አዋጆችና የፌዴራል መንግሥት ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደረጋቸውን አዋጆች በሙሉ እኛ እየተጠቀምንባቸው ነው፡፡ ስለዚህ የምክክሩን ሒደት እንቀበላለን ብለው ርዕሰ መስተዳድሩ ጭምር ባሉበት በዚህ ላይ ተነጋግረናል፤›› ብለዋል፡፡
በመሆኑም በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ ተካሂዶ ሌላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ያን ቦታ የሚወክል አካል እስካልመጣና እስካልወከለ ድረስ፣ በዚያ ሥርዓት የሚወጡና እስካሁን የወጡ አዋጆች ተፈጻሚ ሆነው ይቀጥላሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነር መላኩ በሰጡት ማብራሪያ ከሕገ መንግሥቱ ወጣ ባለ መንገድ አገር የመመሥረት ጥያቄ ካለ ወደ አጀንዳ የመቅረቡ ጥያቄ አጠያያቂ ይሆናል ብለው፣ በዚያ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው የሚቀርቡ ጥያቄዎች ተጣርተውና ታይተው ለአገራዊ ምክክር ቀርበው በሚመጡ ተወካዮች ይታያሉ ብለዋል፡፡
መንግሥት ከምክክሩ የሚወጡ ውጤቶችን የመፈጸም ፍላጎት ይኖረዋል ወይ የሚለውን ጥያቄ ሲያብራሩ፣ ‹‹ጉዳዩ የሚፈትነን ቢሆንም ላይፈጸም የሚቻልበት ምክንያት አይኖርም፤›› በማለት ገልጸው መንግሥት የመፈጸም ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ እንዲቋቋም መንግሥት ማንም አስገድዶት የወሰነው ባለመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መክሮና ዘክሮ ያመጣውን ሐሳብ አልቀበልም ማለት ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ መሆን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
‹‹እስኪገባኝ ድረስ አንድ መንግሥት ተጠሪነቱ ለሕዝብ ነው፡፡ የሕዝብን ድምፅ የመስማትና የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ ያን ባላደረገ ጊዜ ደግሞ ሕዝብ ለምን ብሎ መጠየቅ መቻል አለበት፣ መብቱን መለማመድ አለበት፤›› ብለዋል፡፡
‹‹እንዳለመታደል ሆኖ ሕዝብ ይመርጣል እንጂ መንግሥትን ሲያስገድድ ዓይተን አናውቅም፡፡ ነፃነቱንም መብቱንም አይጠቀምም፡፡ በመሆኑም ሕዝብ መብቱን መጠቀም መቻል አለበት፡፡ ሒደቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሪቱ ባለቤት መሆኑን ማሳያ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
‹‹መንግሥት ተወካይ ስለሆነና ከወካይ ሕዝብ የማይበልጥ በመሆኑ፣ የወካዮች ፍላጎትና ድምፅ ማንፀባረቅና መተግበር አለበት፡፡ ላይተገብር ይህንን ያህል ገንዘብንና ይህንን ያህል ዕውቀት ለምን ይባክናል? ስለዚህ መንግሥት እንደሚፈጸም እናምናለን፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡