በሳሙኤል ረጋሳ
ኢትዮጵያ የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ያላት አገር ነች። ይህንን እንቀበልና የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪኳ ምንድነው ብለን እንጠይቅ። ይህ ዘመን አብዛኛው የጋሪዮሽ ዘመን ነው የሚመሰለው። ከዚያ ወዲህ ያለው የባሪያ ሥርዓተ ማኅበር ደግሞ ሌላው ረዥሙ ዘመን ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ዘመናት ውስጥ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከነበረችና መንግሥትም ከነበረን የታሪክ ምሁራን ሊያብራሩልን የሚገባ ነው። አሁን ዋናው ነገር ከኢትዮጵያ የታሪክ ዘመን ላይ ጉዳይ ኖሮኝ ሳይሆን፣ ለአሁኑ መስተጋብራችን ይህ ረዥም ዘመን ምን አስተማረን ነው። ለምንስ ከዓለም ሥልጣኔ ውስጥ የመጨረሻ ኋላቀርና ያልተማረ ሕዝብ ተርታ ተሠልፈን ቀረን። ለምንስ ሕዝባችንን አንድ የሚያደርግና የሚያግባባን ታሪክ አልኖረንም ነው። የሁለትና የሦስት መቶ ዓመታት የሠለጠነ ታሪክ ያላቸው አገሮች የደረሱበትንና የእኛው ሦስት ሺሕ ዘመን ሊነፃፀር የማይችል ነው። ያም ሆነ ይህ ሦስት ሺሕ ዘመን እውነት ከሆነ አልሠለጠንበትም፣ አልለማንበትም፣ አልተማርንበትም፣ አላደግንበትንም።
ስለዚህ ይህ ታሪካችን የሚያጓጓ አይደለም። ለነገሩ ከሃምሳ ዓመት በፊትም፣ ከሃያ ዓመት በፊትም፣ ከሁለት መቶ ዓመት በፊትም ያው ሦስት ሺሕ ዘመን ነው የሚጠቀሰው። አልጨመረም አልቀነሰም። እስኪ ሦስት ሺሕ የሚለውን እንተውና ከአሁን በኋላ ሦስት ሺሕ አንድ ብለን እንቁጠረው። አቆጣጠሩንም ዓመተ ምሕረት ብለን እንውሰደው። ልክ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ያለው ዘመን ዓለም በመንፈሳዊ እምነቱ እንደዳነበት እኛም ተለውጠን በአስተሳሰብ ለመዳን እንሞክር። እስቲ ሁሉንም ትተን ከዛሬ ሃምሳ ዓመት እንጀምር።
በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብም በመንግሥትም የሚታወቅ የሽብር የታሪክ ዘመን ነበረን። ይኼ ሽብር ቀይና ነጭ ተብሎ መልክ ወጥቶለት በሁለት የተከፈለ ነበር። የዚያ ዘመን ፍልስፍና አንድ ትውልድ ጨርሶ አለፈ። ከዚያ ቀጥሎ የመጣው የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ነው። መርሁም አንድ ሕዝብ አይደለንም። የተለያየን ነን። በቋንቋችን ብዛት ልክ የየራሳችንን መንግሥት እናቋቁማለን የሚል ዕሳቤ ነበር። ከእነ ጉድለቱም ቢሆን አንድነታችንን ስናጠናክር እንዳልኖርን የመለያያችንን መንገድ ወለል አድርገን ከፈትነው። ለሁሉም ብሔር የየራሱ የሆነ ጠላት ከሌላ ብሔር ፈጠርንለት። የተነገረውንም ሰምቶ አመነ። ይህ አስተሳሰብ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ስለፈጠረ፣ የአገሪቱ አንድ አካል የነበረችው ኤርትራን ከኢትዮጵያ ገነጠላት። የዚህ የፖለቲካ ዘይቤ በብሔሮች መካከል ጥልቅ የሆነ የጠላትነት፣ የመፈራራትና የመጠራጠር አስተምህሮ ስላለው ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በረባው ባልረባው ሁሉ ትልልቅ ጦርነቶችንና ግጭቶች እየፈጠርን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ለጋ ወጣቶችን አስፈጅተናል።
ባለፈው የሰሜኑ ጦርነት ብቻ ሕወሓቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ለጋ ወጣቶች በጦርነቱ እንደሞቱባቸው ሲገልጹ፣ በመንግሥት በኩልም ሊሞቱ የሚችሉትን ብንገምት እንደ አገር ያጣናቸው ትኩስ ኃይሎችን ቁጥር መገመት አይከብድም። በጣም የሚያሳዝነው ግን ያለፈው ብቻ ሳይሆን መጪው ዘመን በዚሁ ወይም በባሰ ሁኔታ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ሊቀጥል እንደሚችል ምልክቶች መኖራቸው ነው። ትግራይ ውስጥ በአሁኑ ሰዓትም ቢሆን እየተካሄደ ያለው የፖለቲካ አዝማሚያ ክልሉ ራሱን የቻለ ሉዓላዊ መንግሥት እንዳለው የሚያስመስል ወይም በሒደት መፍጠር እንደሚፈልግ የሚያመላክት ነው። ከፌዴራል መንግሥት ውጪ የሆነ የራሱ መከላከያ እንዳለው እየገለጸ ነው። ከውጭ መንግሥታት ጋርም ቀጥታ ግንኙነት ለማድረግ እየዳዳው ነው። አስተዳደሩንም ከፌዴራል ሕገ መንግሥት ውጪ ለመዘወር ይፈልጋል። እንደአገር ያሉትንም ችግሮች ለመፍታት የሚያስቸግረው የዚህ ዓይነት ውስጣዊ የሆኑ የሴራ ፍላጎቶች በመኖራቸው ነው። ለአብነት ያህል ከሰሜኑ ጦርነት በፊት ምርጫ ቦርድ በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት የምርጫውን ዘመን ባስተላለፈ ጊዜ ውሳኔውን ባለመቀበል ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ምርጫ ሕወሓቶች ከሌላው በመለየት በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ምርጫ በማካሄዳቸው የተፈጠረውን እናስታውሳለን። አሁንም ካለፈው ባለመማር የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ሕወሓት ያካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የፈጠረውን ምስቅልቅል እያየን ነው። በክልሉ ውስጥም ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሯል።
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ሕዝብ ከብዙ መከራ በኋላ በከፊልም ቢሆነ ያገኘው አንፃራዊ ሰላም አለ። ሕወሓት ያመጣበት የእንቢተኝነትና የበላይነት ሥነ ልቦና ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ በርካቶች ተገንዝበውታል። ከላይ የተገለጹትና ሌሎችም የሕውሓት የማፈንገጥና ከፌዴራል መንግሥት የመነጠል ሁኔታ ድርጅቱ ጥቅሙንና ጉዳቱን በትክክል ያሰላው አይመስልም። ከጥቂት ፖለቲከኞች በስተቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ትግራይን አንድ የአገራችን አካል መሆኗን ለአፍታም ተጠራጥሮ አያውቅም። በጥልቅ መሠረት ላይ የቆመ ጥንታዊ አንድነት ስላለን በፖለቲከኞች የጥላቻ መንፈስ በመሀላችን ተፈጥሮ አንድነትን የሚሸረሽር ልዩነትን መፍጠር የለብንም። ይኼ ፍላጎት ደግሞ የተጠነሰሰው በሕዝብ ሳይሆን በልዩ ተልዕኮ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች ፍላጎት ነው።
ከዚህ በተረፈ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ከክልሉ ሊያገኝ የሚችለው ወይም የሚፈልገው ልዩ ጥቅም የለም፣ ሊኖርም አይችልም። በአሁን ጊዜ ፖለቲከኞቹ በፈጠሩት አሉታዊ ትርክትና የፖለቲካ ክፍተት ሕዝቡ በጥርጣሬ እንዲኖር ተደርጓል፣ ክልሉም አልተረጋጋም። ሕዝቡ ወደ ሌሎች ክልሎች ተዘዋውሮ እንዳይሠራ ወይም እንዳይኖር ጫና ፈጥሮበታል። አሁን ይህ ሁሉ ውጥረት መርገብ አለበት። በብርቱ ጥንቃቄና በአርቆ አሳቢነት መንፈስ የትግራይ ወጣቶችና ንቁ ፖለቲከኞች ሕዝቡ እንደ ቅድመ ሕወሓት ዘመን ፖለቲካችንን፣ ኢኮኖሚያችንንና ማኅበራዊ መስተጋብራችንን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወደ ነበረበት መመለስ አለበት። ከዚህ ደግሞ ዋናው ተጠቃሚ የትግራይ ሕዝብ ነው። ‹‹በጦር ሜዳ ወንድ ልጅ ይሞታል እንጂ ወንድ ልጅ አይወለድም›› ብላለች የሶማሌዋ እናት። በመመካከር መፍታት የማንችለው አንድም ነገር የለም። ሦስትና አራት ልጆቻቸውን ቦምብ አስታጥቀው ክላሽ አሸክመው ከውጭ ጠላት ሳይመጣ ለእርስ በርስ ጦርነት እናቶች መርቀው ወደ ጦር ሜዳ ሲልኩ ይኼ የጀግንነት ሳይሆን፣ የድፍረትና የዕብደት ምልክት ነው። በአብዛኛው ደግሞ መጨረሻውም ፀፀት ነው።
ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ የተፈጠሩት የአገራችን ሰዎች በሰላም መኖር ምን እንደሆነ አያውቁም። የምንሰማው ዜና፣ ከአቻ ጓደኞች ጋር የምናወራው ሁሉ መከራ ያለበት ነው። በትምህርት ቤት ጭምር የቂመኝነትና የበቀል ትርክት ነው የሚዘዋወረው። ሰው ደግሞ የኖረበትንና የተማረውን ዘመን ነው የሚያውቀው። በመሆኑም ትውልዱ የፍቅርና የሰላም ዘመን እንደነበረ ባይገባው አይገርምም። የሰላም ዘመን ደግሞ እንደ ዋዛ አይመጣም። በጣም በጥንቃቄ በብስለትና በዘዴ አገሪቱን መምራት ሲቻል ነው። በሌላ አንፃር ደግሞ ትውልዱ በፅናት እንዲያምንበት የተፈለገው መሠረት በሌለው ትርክት አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠርና እንዲሠጋ ነው። በዚህ ዘመን በአጭር ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በጦር ሜዳ በማስፈጀት ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ አገር ሳትሆን አትቀርም። ዓለምን ጉድ ያሰኘውን በረቀቁ ሚሳይሎች የሚዋጉት ሩሲያና ዩክሬን ወይም እስራኤልና ፍልስጤም እንኳን አለቀብን የሚሉት ሠራዊትና ሲቪል ከሃምሳ ሺሕ አልበለጠም። ዛሬ ዛሬ ደግሞ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በአዲስ ጉልበት በተመሳሳይ የሚሊዮኖችን ሕይወት ለመቅጠፍ በተለመደውና ባልተሻሻለው መንገድ እየተጓዙ ነው። ይኼ መንገድ ደግሞ ሊያመጣ የሚችለው የተለየ ነፃነት ወይም ጥቅም የለም።
በመላው ክልሎች ከአርሶ አደሩ እስከ ከተሜው ድረስ ትርፉ ረሃብ ለቅሶና ዋይታ ነው። እኛ ስላልሠለጠንን በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ስህተት እየፈጠርን ዕድገታችን ወደኋላ ተመልሷል። ሥልጡኖቹ ሩዋንዳዎች እንኳን ከአንድ ጊዜ ስህተት ተምረውበት ያን መንገድ ላይመለሱበት የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ነው ብለው ትተውታል። ተወደደም ተጠላም ይዘገያል እንጂ እኛም ዘንድ ሰላም መምጣቱ አይቀርም። ያም የሚሆነው በማሸነፍና በመሸነፍ ሳይሆን በጦርነቱ ምክንያት ረሃብ ሲፈታን፣ ጥሪታችን ሲያልቅ፣ ከተሞች ሲፈርሱ፣ በማኅበራዊ ቀውስ በሚከሰተው ችግር አቅማችንን ጨርሰን ስንቆም ነው። እንታገልለታለን የምንለው ሕዝብ ሲንቀንና ትግሉ ትርጉም ሲያጣ ነው። ዕልቂት ተራ የዕለት ጉዳይ ሲሆንና ተከትሎት የሚመጣ ምንም አዲስ ውጤትና ተስፋ ሲጠፋ በመሰላቸት ነው። ለመሆኑ ስንት ዓመት ተዋግተን ስንት ሰው ቢሞት ነው ፖለቲከኞቹ ልባቸው የሚራራልን? ነፃ እናወጣችኋለን የሚሉ ፖለቲከኞች በሚያምር ቋንቋ የሚሰብኩት ማጠንጠኛው ልጆቻችሁን አዋጡና እነሱን ከግንባር እኛ ከምሽግ ውስጥ ሆነን እንዋጋለን ነው። በመጨረሻ ግን ባንዲራ ለብሶ፣ መትረየስ አንግቦ፣ በጦር መኪና ታጅቦ ድል አድራጊነትን እየዘመረ የሚገባው ፖለቲከኛው ነው። ከየቤቱ እንደ ገንዘብ በመዋጮ ተለቅሞ የተወሰደው ወጣት እናቶቻቸው ዕድለኞች ከሆኑ መርዶ ከረዥም ጊዜ ጭንቀት በኋላ ሊደርሳቸው ይችል ይሆናል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ጦርነቱ ሲቆም የሚመጣው ሰላም በሞራል ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ፣ በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ጉዳት ሌላ ከችግር በላይ የሆነ ግዙፍ ችግር ነው። አዲስ ልማት ሳይሆን ከጦርነቱ በፊት የነበሩትና የወደሙትን በከፊል እንኳን ለመመለስ አስቸጋሪ ነው። በሰሜኑ በተከሰተው ጦርነት የወደሙትን መሠረተ ልማቶች መልሶ መገንባት አልተቻለም። ዩኒቨርሲቲ ይገንባልን ስንል የነበረው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም አጥተናል። አዲስ ሆስፒታል ይሠራ ማለት ቀርቶ የነበሩትን ጤና ጣቢያዎች መልሶ ለማደራጀት እየጠየቅን ነው። ‹‹የሚወዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይቀላውጡ›› እንደሚባለው ነው። የነበረንን ሁሉ መልሰን ካገኘን በኋላ ሌላ ተጨማሪ አዲስ ልማት ለመጀመር ምን ያህል ዘመን እንደሚፈጅ አይታወቅም። ያንን በጥናት ሲታወቅ በስንት ዘመን ከዕድገት ወደኋላ እንደተመለስን ይገባናል። ልምዳችንና ተሞክሯችን ይኼ ስለሆነ ነው ከላይ የጠቀስነውን ሦስት ሺሕ ዓመት ባለህበት ሂድ የሆነው።
እነዚህ ሁሉ ችግሮች በፖለቲከኞቻችን የሥልጣን ጥምና ጉጉት የሚመጣ ቢሆንም ከበስተኋላው ገፊ ኃይሎችም አሉት። አገር የማያስፈልገን ይመስል በአገራችን እንቀልዳለን። ይኼንን የእርስ በርስ መተላለቅ የውጭ ጠላቶቻችን የሚመኙልን ብቻ ሳይሆን በስፖንሰርነት የሚደግሱልን ድግስ ነው። እኛ ግን አብዛኞቻችን ባለማወቅ ጥቂቶች ደግሞ ተልዕኮ በመቀበል የሚፈጸም ነው። በእኛ አገር ጦርነትን እንደ ጀግንነት መለኪያ ነው የምንወስደው። ከውጭ ጠላት ሳይመጣ እርስ በርሳችን ምክንያት ፈልገን ጀግንነታችንን ለማሳየት እንጠፋፋለን። ፖለቲከኞች በወጣቶች ሕይወት በመተማመን ፎክረውና አስፎክረው ጦርነት ያስጀምራሉ። ጦርነቱ ከተጀመረ ደግሞ በድል አድራጊነት ማስጨረስ እንደ ማስጀመሩ ቀላል አይደለም። በአብዛኛው አሁን በአገራችን እንደምናየው ሁሉም ነገር ከቁጥጥራቸው ውጪ ይሆንና ሕዝብን የመኖር ተስፋውን ጭምር ያሳጣዋል። ጦርነትን ረሃብና ስደት ተከትለውት ይመጣሉ። ጦርነት ሲፈጀን በሚሊዮን ነው፣ ረሃብ ሲፈጀን በሚሊዮን ነው፣ ስንሰደድ በሚሊዮን ነው፡፡ በሁሉም ወገን የአገሪቱን የአሁንና የወደፊቱን ሁኔታ አጢነው ችግሮችን ለመፍታት አይሞክሩም።
ቁጥሮቹን ሁሉ ከሌላው ዓለም ለይቶ በአንድ ዙር ጦርነት የሚሊዮን ዜጎችን ዕልቂት ያስከተለው ጀግንነታችን ከሌላው በልጦ አይደለም። ዕውቀታችን ከሌሎች አንሶ ነው። ድፍረትና ጀግንነት የተለያዩ ናቸው፣ ጀግና ማለት ዕውቀትና ብልኃት ያለው ደፋር ሰው ነው። ድፍረት ብቻውን ለድል አያበቃም። ለዚህ ነው ሰዎች ወደ ጦር ትምህርት ቤት ገብተው በቂ ሥልጠና የሚወስዱት። በእኛ አገር ብዙዎች ድፍረት ብቻውን ለድል የሚያበቃና የሚያስከብር ይመስለናል። ስለዚህም ጨካኝና ገዳይ እንሆናለን። የአገራችን ታሪክ በአብዛኛው የጦርነት ታሪክ ነው ይባላል። እውነት መሆኑንም በተጨባጭ አየነው። ሥልጣን የሚያዘው በጦርነት፣ ሥልጣን የሚለቀውም በጦርነት ነው። ከሥልጣን መያዝ እስከ መልቀቅ ያለችው አጭር ጊዜም ራስን ከሥልጣን ማማ ላይ ለማቆየት የሚደረግ ዝግጅትና ትግል በመሆኑ፣ ለተቀናጀ ልማትና ለዘላቂ ሰላም ጊዜ አልነበረንም። ከቅርቡ የአሜሪካ ምርጫ የምንማረው የተመረጠው ሰው የሥልጣን ዘመኑን በዛቻና በሽኩቻ የሚፈጅ ሳይሆን፣ ወዲያው እንደ ተመረጠ በአገሪቱ ፖሊሲ መሠረት ወደ ተጨባጭ ሥራ ገብቶ ዕድገት የሚያሳይበት ነው። ስለዚህ በሁለት መቶ ዓመት የደረሱበትን አየን። ከእኛው ሦስት ሺሕ ዘመን ጋር ስናወዳድረው የእኛው የጦርነትና የመደናቆር ዘመን ነው፣ ከዚህ መውጣት አለብን።
በዚህ የመረጃ ዘመን እንኳን ዓይተንና ሰምተን መለወጥ አልቻልንም። ለነገ የሰላም ጊዜ አገሪቱን ይጠቅማሉ ብለን የምንቆጥበው ወጣትና ምሁር፣ ሀብትና ንብረት እንኳን የለንም። ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር የሚለው የደንቆሮ መፈክር ተዋህዶናል። ይኼን መፈክር ሁሉም ነገር ወደ ሰላም ግንባር በሚል ብንተካው ብዙዎች የሚስማሙ አይመስልም። ይኼውም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እየታየ ነው። ከዓለምና ከራሳችን የቅርብ ተሞክሮ ተምረን መስተካከል ሲገባን፣ በሌሎች አገሮች ላይ የምናየውን የአገር ማፍረስ፣ የሕፃናት ስቃይና ረሃብ ወደ እኛ እንዲመጣ እየጋበዝን ነው። በጠላቶቻችን የተዘጋጀልንን መርዝ ተቀብለን እንድንጨልጥ የሚያደርጉ ዜጎች መኖራቸው ግን የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን የሚገርም ነው። የሦስት ሺሕ ዘመን ሌላ ታሪክ ካለን ይነገረን። ያለ በለዚያ ከታሪካችን በአብዛኛው የጦርነት ታሪክ ነው ካልን የደካሞች ታሪክ ስለሆነ እንለውጠው። እንደ ቀደሙን አገሮችም በአጭር ጊዜ የሚያለማንን፣ የሚያስማማንንና የሚያሳድገንን አዲስ ታሪክ አንድ ብለን እንጀምር።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡