- ቦርዱ በፕሮጀክት የተቀጠሩ 55 ሠራተኞችን ያላግባብ በቋሚነት መቅጠሩ የሕጋዊነት ጥያቄ አስነስቶበታል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀድሞ ሰብሳቢው መኖሪያ ቤት ዕድሳትና አደገኛ የሽቦ አጥር ለማሠራት ወጪ ያደረገው 233 ሺሕ ብር፣ ለአጃቢዎችና ለሾፌሮች ለምሣና ለእራት ያላግባብ የተከፈለ 218 ሺሕ ብር በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኦዲት ግኝት ትችት ቀረበበት፡፡
ትችቱ የቀረበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የ2015 በጀት ዓመት ሒሳብ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ ኅዳር 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ ውይይት ሲደረግ ነው፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የኦዲት ግኝት ሪፖርቱን ካየ በኋላ ባቀረበው ጥያቄ በ2013 በጀት ዓመት 218,500 ብር ለአጃቢዎችና ለሾፌሮች ያለአግባብ የምሣና የእራት አበል ክፍያ መከፈሉ በዋና ኦዲተር ተረጋግጦ ገንዘቡ ተመላሽ እንዲሆን በኦዲተር አስተያየት ቢሰጥም፣ ቦርዱ ግን ምላሽ አለመስጠቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በ2013 ዓ.ም. ለቦርዱ ሰብሳቢ መኖሪያ ቤት ዕድሳትና አደገኛ የሽቦ አጥር ለማሠራት በአጠቃላይ ከ233 ሺሕ ብር በላይ ገንዘብ ለቦርዱ ከተፈቀደው በጀት ላይ ያላግባብ ወጪ መደረጉን፣ ገንዘቡም ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲተካ አስተያየት ቢሰጥበትም ቦርዱ መልስ እንዳልሰጠበት በቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ ቀርቧል፡፡
የዋና ኦዲት ግኝት ሪፖርቱን ተመሥርቶ የቀረበው የኮሚቴው ጥያቄ እንደሚያሳየው 981 ሺሕ ብር መነሻ የምዝገባ ሰነድ የሌለው የተከፋይ ሒሳብ ላይ የተመዘገበ ገንዘብ፣ 6.5 ሚሊዮን ብር በተገቢው የሒሳብ መደብ ሳይመዘገብ የተገኘ ገንዘብ፣ በ2014 ዓ.ም. 19 ሚሊዮን ብር ሥራ ላይ ያልዋለ ገንዘብ፣ 138 ሺሕ ብር ለሐረር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ያለ ውድድር በቀጥታ የተፈጸመ ግዥ ይገኝበታል፡፡
በተመሳሳይ 24.5 ሚሊዮን ብር በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተከፋይ ሒሳብ፣ ሁለት የቦርዱ ሠራተኞች ንብረት ሳያስረክቡ መልቀቃቸውና ቦርዱ የራሱ የሆነ የተሽከርካሪ ጋራዥ እያለው ተሽከርካሪዎቹ በውጭ ጋራዥ እንደሚጠገኑ ጥያቄ ተነስቷል፡፡
ምርጫ ቦርድ ሠራተኞችን ማስታወቂያ በማውጣት መቅጠር ሲገባው፣ በፕሮጀክት ተቀጥረው የነበሩ 55 ሠራተኞችን ያለ ውድድርና ማስረጃዎችን ሳያሟሉ ያላግባብ መቀጠራቸውን ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አንስቶበታል፡፡
በተጨማሪም ከሐምሌ 2011 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም. ከቦርዱ ዋና ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢዎች በመመርያው መሠረት ከደመወዛቸው ያልተቀነሰ የሕክምና ሁለት በመቶ ወጪ፣ በድምሩ 40,000 ብር የሚጠጋ ተቀናሽ ተደርጎ ወደ መንግሥት አለመግባቱ ጥያቄ ቀርቦበታል፡፡
ቦርዱ በ2013 ዓ.ም. 2.7 ሚሊዮን ብር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ መክፈሉን ቢገለጽምና ፓርቲዎቹ መቀበላቸውን የሚያሳይ የገንዘብ ገቢ ደረሰኝ እንዲያቀርብ ከኦዲተር ጥያቄ ቢቀርብም፣ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ደረሰኝ ማቅረብ አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ በሰጡት ምላሸ የኮንትራት ሠራተኞችን ወደ ቋሚነት ለመቀየር ያስፈለገው ቦርዱ እንደገና በአዋጅ ከተቋቋመ በኋላ በአብዛኛው ሠራተኞችን ሲቀጥር የነበረው በአጋር ድርጀቶች፣ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅትና በአውሮፓ ኅብረትና መሰል አካላት ደመወዝ እየተከፈላቸው ሲሠራ በመቆየቱ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአጋር አካላት ሲከናወን የነበረው ሥራ ተጠናቆና ከእነሱ ጋር የነበረው የአምስት ዓመት ኮንትራት ሲያበቃ፣ በኮንትራት ተቀጥረው የነበሩ ሠራተኞች ለአራትና ለአምስት ዓመታት ስላገለገሉ፣ በምርጫ ልምምድ ያደረጉ፣ ነፃነታቸውና ገለልተኝነታቸው ተፈትኖ የተረጋገጠ በመሆኑ እንዲቆዩ መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህ መነሻ የቦርዱ ሥራ መቆም ስለማይችል ሠራተኞቹን በማስቀጠልና በማዘዋወር ወደ ቋሚ የሥራ መደብ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ሰብሳቢዋ ያልተሰበሰበ የሕክምና ወጪን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ የቦርዱ ኃላፊዎች የሕክምና ፈቃድ የተሰጣቸው በ2015 ዓ.ም. ስለሆነ የሕክምና ፈቃድ ሳይሰጥ ከደመወዛቸው ላይ እየተቆረጠ ለሕክምና የሚወጣበት ምክንያት አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡
ለፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰጥቶ ደረሰኝ ያልተገኘለት አንድ ሚሊዮን ብር በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ የምርጫ ወቅት በመድረሱና ፓርቲዎች ገንዘብ ያስፈልጋቸው ስለነበሩ ወደ ባንክ አካውንታቸው በመላክ የገባበትን ደረሰኝ ለዋና ኦዲተር መቅረቡን ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ሜላተወርቅ ለሾፌሮችና ለአጃቢዎች የተከፈለ አበልን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚሠራው የዘመቻና የጦርነት ያህል መሆኑንና በምርጫ ወቅት 24 ሰዓት ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች ከመደበኛ የሥራ ቦታቸው ተነስተው ከአሥር እስከ 15 ኪሎ ሜትር ቦታ እየተጓዙ በቀንና በምሽት በሚሠሩበት ወቅት ለምሣ አበል የተፈጸመ ክፍያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህንን ለማድረግ ሕግ እንደሚፈቀድልን እየተከራከርን ነው ያለነው፤›› ብለዋል፡፡
ለቀድሞዋ ሰብሳቢ የመኖሪያ ቤትና የአጥር ዕድሳት ስለወጣው ገንዘብ ሲያብራሩ፣ ‹‹በምርጫው ወቅት በጣም አሳሳቢና አስጨናቂ የሆነ የደኅንነት ችግር ስለሚኖር አደገኛ አጥር ሽቦ ተሠርቷል፤›› ብለው፣ ሰብሳቢዋ ይኖሩ የነበሩት በኪራይ ቤቶች ውስጥ በመሆኑ ይህን ገንዘብ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲመልስ ክትትል እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቦርዱ ያላወራረደውና ያልዘጋው ብዙ ሒሳብ አለ ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፣ የ15 እና የ16 ዓመታት ታሪክ እንጂ የ2015 እና የ2016 በጀት ዓመት የገንዘብ አጠቃቀም ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡
በፓርላማው ፀድቆ ቦርዱ ያልተጠቀመበትን በጀት መመለሱን በተመለከተም፣ ቦርዱ በ2016 ዓ.ም. ቀሪና ድጋሚ ምርጫ እንደሚያካሂድ ጠቅሶ መስከረም 2016 ዓ.ም. ለገንዘብ ሚኒስቴር ቢያቀርብም ሚኒስቴሩ የተጠየቀውን ገንዘብ የለቀቀው መጋቢት 2016 ዓ.ም. በመሆኑ ገንዘቡ ለታቀደው ሥራ በወቅቱ አለመድረሱን አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ ምርጫ ያካሄደው በሰኔ 2016 ዓ.ም. በመሆኑና ለምርጫውም የሚያስፈልገው ገንዘብ በወቅቱ ባለመለቀቁ ወደ መንግሥት ካዝና መመለሱን አስታውቀዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር በወቅቱ ባለመልቀቁ እንጂ መጠቀም ባለመቻሉ እንዳልነበረ አክለዋል፡፡
ያለ ግልጽ ጨረታ የተፈጸመ ግዥን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ አመቺ ባልሆነ ሒደት ውስጥ ግልጽ ጨረታ አካሂዳችሁ ማለት ‹‹ምርጫው አይካሄድ የሚለውን›› አንድምታ የሚይዝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፋይናንስ ሰነድ አይደለም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለቃሉና ለድምፁ የሚያምነው ተቋም ነው፤›› ያሉት የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ ‹‹ቦርዱ በግልጽነትና በተጠያቂነት ሥራውን እያከናወነ ያለ ተቋም ነው፡፡ ሰነዶችን በአግባቡ ባለመያዝ ሊወቀስ አይገባም፤›› ብለዋል፡፡
ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው አጃቢዎችና ለሾፌሮች የተከፈለውን ገንዘብ በተመለከተ መከፈል የለበትም እንዳልተባለ፣ ነገር ግን አከፋፈሉ በወጣው ሕግ መሠረት መሆን እንዳለበት ታስቦ ኦዲት እንደተደረገ አስታውቀዋል፡፡
ከኮንትራት ወደ ቋሚ የተቀየሩ ሠራተኞችን ማንም ይቅጠራቸው ማንም አንድ ሰው ቅጥር ሲፈጽም ማሟላት ያለባቸው ሰነዶች መሟላት እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ የኦዲት ክፍተቱ የመጣው ቦርዱ የራሱ የሠራተኞች አስተዳደር ስለሌለው በመሆኑ የሲቪል ሰርቪስ ሕጉን መከተል ነበረበት ብለዋል፡፡ ቦርዱ የኮንትራት ሠራተኞችን ገበያ ውስጥ እንደማያገኛቸው ቢረዳ እንኳ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር ተነጋግሮ ሕጋዊ መሠረት እንዲይዝ ማደረግ እንጂ፣ በራሱ ይህንን ማድረግ እንደማይችልና ይህም የኦዲት ክፍተት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹ቦርዱ ለምርጫ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ሕዝቡም እኛም እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ምርጫ ለማስፈጸም የሚመደብለትን በጀት በሕጉ መሠረት የመምራት ግዴታ አለበት፤›› ሲሉ ወ/ሮ መሠረት አስረድተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) በሰጡት የማጠቃለያ ሐሳብ፣ ‹‹ለቦርዱ አንድ አስተያየት መስጠት የምፈልገው ሁላችንም አንድ ዓላማ ነው ያለን፡፡ አገራችን ባወጣችው ሕግና ሥርዓት መሠረት የተሰማራንበትን ሥራ ማስፈጸምና ሕግን መሠረት ያደረገ አሠራር ማስፈን ስላለብን፣ አንዱ ተነስቶ ሌላውን የሚኮንንበት አካሄድ ባለመኖሩ የቀረበው የኦዲት ግኝት ከዚህ ዓላማ ተነስቶ የሚደረግ ግምገማ በመሆኑ፣ ግኝቱም ክፍተት እንደሚያሳይ መስታወት ተደርጎ እንዲወሰድና በዚህ መሠረት እንድትቀበሉት ማሳሰብ እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡