- ሃሎ?
- ሃሎ ክቡር ሚኒስትር… ከምኔው መምጣቴን ሰማህ?
- የቅርብ ወዳጄና ባለውለታዬ ወደ አገር ቤት ሲመለስ ካልሰማሁማ ምኑን ወዳጅ ሆንኩት?
- እንዴት ነዎት ታዲያ አምባሳደር?
- አምባሳደር ብለህ ባትጠራኝ ደስ ይለኛል?
- ለምን?
- በስሜ እንድትጠራኝ ነው የምፈልገው።
- እንደዚያማ ትክክል አይሆንም?
- ምን ችግር አለው?
- አገርዎትን በሚኒስትርነት አሁን ደግሞ በአምባሳደርነት እያገለገሉ አይደለም እንዴ?
- ቢሆንም በስሜ እንድትጠራኝ ነው የምፈልገው ካልሆነ ግን…
- እ… ካልሆነ ምን?
- ካልሆነ እኔም አንተን ክቡር ሚኒስትር ብዬ አልጠራህም፡፡
- ታዲያ ምን ብለው ሊጠሩኝ ነው?
- የወደፊት አምባሳደር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ የቢሮ ስልክ ላይ ደጋግመው ቢደውሉም ሊያገኟቸው ስላልቻሉ ወደ እጅ ስልካቸው ደወሉ]
- ጤና ይስልጥልኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ትናንት የቢሮ ስልክዎ ላይ ብደውል ለሥራ ወጥተዋል የሚል ተባልኩ፣ ዛሬም ስደውል ለሥራ ወጥተዋል ተባልኩ።
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር ቢሮ አልገባሁም ነበር።
- እኔ ሳላውቅ የጀመሩት ነገር አለ እንዴ?
- እርስዎ ሳያውቁ ምን እጀምራለሁ ክቡር ሚኒስትር?
- ሌላ ከተማ ማስተዳደር?
- ትናንትም ዛሬም የመስክ ጉብኝት ፕሮግራም ነበረኝ ክቡር ሚኒስትር። ለአስቸኳይ ጉዳይ ፈልገውኝ ነው?
- ሁለት ቀን ሙሉ ጉብኝት?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አዎ?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር። ሁሉም የካቢኔ አባል የተሰጠውን ቪ8 አቁሞ ፒክ አፕ እየነዳ የመስክ ጉብኝት ላይ ነበር።
- ብቻ ለዚህ ብላችሁ ግዥ ፈጽማችሁ እንዳይሆን?
- የምን ግዥ ክቡር ሚኒስትር?
- የፒክ አፕ?
- ወጪ ላለማውጣት ብለን ከፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ለመዋስ ጠይቀን ነበር ግን…
- ግን ምን?
- የጠየቅናቸው የፌዴራል ተቋማትም ፒክ አፕ ተሽከርካሪዎቻቸውን ለአስቸኳይ ጉዳይ እንደሚፈልጓቸው ነገሩን።
- ለምንድነው የሚፈልጓቸው?
- ለጉብኝት።
- ስለዚህ እናንተ ምን አደረጋችሁ?
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን አደረጋችሁ? ብቻ ገዛን እንዳይሉኝ?
- ገዛን፡፡
- ለከተማ ጉብኝት ፒክ አፕ?
- ክቡር ሚኒስትር ባለፈው የሰጡትን ማሳሳቢያ ዘንጉት እንዴ?
- የምን ማሳሰቢያ?
- ውረዱ አላሉንም እንዴ?
- ከምን ላይ?
- ከቪኤት ላይ።
- ምን?
- ብለዋል እኮ ክቡር ሚኒስትር። እንደውም ያሉትን ሙሉ በሙሉ ላስታውስዎት?
- እሺ…
- ብልፅግና የሚመጣው ቢሮ ቁጭ ብሎ በመዋል፣ ወይም ቪኤት እየነዱ በመዝናናት አይደለም፣ ፒክ አፕ እየነዱ ነው አላሉም?
- አዎ። እንደዚያ ማለቴን አስታውሳለሁ።
- እኮ፡፡
- ስለዚህ?
- እኛም የሰጡትን ማሳሰቢያ ተቀብለን…
- ተቀብላችሁ ምን አደረጋችሁ?
- ፒክ አፕ ገዛን፡፡
- ይገርማል፡፡
- ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ እንኳን ፒክ አፕ እየነዳችሁ ያልኩት ቢሮ አትቀመጡ፣ የጀመራችሁትን ፕሮጀክትና ሕዝቡ ያለበትን ሁኔታ ወርዳችሁ ተመልከቱ ለማለት ነበር።
- እኛም እኮ ፒክ አፕ ተሽከርካሪዎቹን ከተረከብን በኋላ ቁጭ አላልንም።
- ምን አደረጋችሁ?
- የመስክ ጉብኝት ላይ ነበርን።
- ምን ላይ?
- የመስክ ጉብኝት። እኔ ብቻ መስልኮት?
- እ…?
- አይደለም ሁሉም የካቢኔ አባል የመስክ ጉብኝት ላይ ነበር።
- ሁሉም የካቢኔ አባል?
- አዎ። ሁሉም የካቢኔ አባል የተመደበለትን ፕሮጀክት በየክፍለ ከተማው እየተዘዋወረ ሲጎበኝ ነበር።
- ሁሉም የካቢኔ አባል ለጉብኝት ወጣ?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር። ለዚያውም በተናጠል አይደለም የወጣነው።
- እ…?
- ጥንድ ጥንድ ሆነን!