ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 Best and reliable news source in Ethiopia
[ክቡር ሚኒስትሩ የሹፌራቸው ሁኔታ አላምር ብሏቸው ምን እንደሆነ እየጠየቁት ነው]
- ዛሬ አነዳድህ አላማረኝም።
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- አነዳድህ አላማረኝም! የሆንከው ነገር አለ?
- ጤንነት እየተሰማኝ አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
- እስኪ ዳር ያዝና አቁመው።
- እሺ ክቡር ሚኒስትር …ይኸው።
- ምን ሆነሃል?
- ምን ያልሆንኩት አለ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት ምንድን የሆንከው።
- ግፊት አለብኝ። ስኳሬም ጨምሯል…. ኩላሊቴንም ይሰማኛል።
- መቼ ነው የጀመረህ?
- ከለውጡ ወዲህ ነው።
- እንዴ …ስድስት ዓመት ሙሉ ደብቀኸኝ እያስታመምክ ነው የቆየኸው?
- ኧረ እንደዚያ አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
- እና መቼ ነው የጀመረህ?
- በዚህ ሳምንት ነው የጀመረኝ።
- ቅድም ከለውጡ ወዲህ ነው አላልክም እንዴ?
- አዎ፣ ብያለሁ።
- ምንድ ነው የምታወራው?
- ክቡር ሚኒስትር ከለውጡ ወዲህ ነው የጀመረኝ እያልክዎት ነው።
- የትኛው ለውጥ?
- የውጭ ምንዛሪ ለውጥ።
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሕዝብ የቀረበ የግብር ቅሬታን በተመለከተ ከታክስ ጉዳዮች አማካሪያቸው ጋር እየተወያዩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ እያቀረበ ነው።
- ቅሬታ?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሆንኩኝ ብሎ?
- በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ መሆን በጀመረው የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) አዋጅ ላይ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ቫት ከሁለት አሠርት ዓመታት በፊት ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ እንጂ አዲስ የተጣለ ግብር ነው እንዴ?
- እሱማ የቆየ ነው። ነገር ግን በአዲሱ አዋጅ ቫት የሚጣልባቸው ሸቀጦች ሰፊ መሠረት እንደኖረው ተደርጓል።
- ተጨማሪ ዕሴት የተፈጠረበት ምርት እስከሆነ ድረስ ቫት ሊከፈልበት ይገባል። ቅሬታ ከተነሳም ለምን ዘገያችሁ የሚል ቅሬታ ነው መሆን ያለበት። እንደዚያ ነው?
- አይደለም።
- እና ቅሬታው ምንድነው?
- በአንድ ሸቀጥ ላይ ተደራራቢ ቫት ተጥሏል የሚል ነው።
- ተደራራቢ ቫት?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር።
- ምን ዓይነት ሸቀጥ ላይ ነው ተደራራቢ ቫት የተጣለው?
- ለምሳሌ በአዲሱ አዋጅ ዶሮ ላይም እንቁላል ላይም ቫት ተጥሏል ነው የሚሉት።
- ትክክለኛ ነው?
- ምኑ ክበር ሚኒስትር?
- ዶሮ ላይም እንቁላል ላይም ቫት ተጥሏል?
- እራሷ ዶሮዋ ላይ ቫት አልተጣለም።
- እና ምኗ ላይ ነው የተጣለው?
- ሥጋዋ ላይ ነው።
- ማለት?
- የዶሮ ሥጋ ከሱፐር ማርኬት የሚገዙ ከሆነ ቫት ሊከፍሉ ይችላሉ።
- እንቁላልስ ቫት ይከፈልበታል?
- አዎ። ይከፈልበታል።
- ስለዚህ ትክክለኛና ተገቢ ቅሬታ ነዋ የቀረበብን?
- እንዴት?
- ተደራራቢ ቫት ነዋ የጣላችሁት።
- ግን እኮ ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው ክቡር ሚኒስትር?
- የተለያዩ አይደሉም።
- ቆይ ላስረዳዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ታስረዳኛለህ? የቫት መሠረትን አስፉ አልን እንጂ ሕዝቡን አሰቃዩት አልን እንዴ?
- ማሰቃየት እኮ አይደለም ክቡር ሚኒስትር? ስላልተረዱኝ ነው።
- ከዚህ በላይ ምን እንድረዳ ነው የፈለግከው?
- ቆይ ልንገርዎት ክብር ሚኒስትር?
- ምን ትነግረኛለህ! እንቁላሏ ላይም ሥጋዋ ላይም ቫት እንደጣላችሁ ነገርከኝ አይደለም አንዴ? በሉ ይህንን ተደራራቢ ግብር ቶሎ አስተካክሉ!
- እንዴት አድርገን ክቡር ሚኒስትር?
- እንደጣላችሁት አንሱ። አንዱ ላይ ብቻ ከተጣለ ይበቃል።
- እሺ፣ እንዳሉት እናስተካክላለን። ግን ክቡር ሚኒስትር …
- ግን ምን?
- ከየትኛው ላይ ቢነሳ ይሻላል?
- ማለት?
- ከዶሮዋ ላይ ቢነሳ ይሻላል ከእንቁላሉ ላይ?
- ማናቸው ይቀድማሉ?
- ከዶሮ እና ከእንቁላል?
- እ…?
- እኔ እንጃ ክቡር ሚኒስትር።
- በሉ አጣሩና ግብሩን ቀድሞ ከመጣው ላይ አንሱ።
- እ….?
- ቀድሞ የመጣውን አጣሩና ግብሩን አንዱ ላይ ብቻ ጣሉ!
- እሺ ክቡር ሚኒስትር። ማረጋገጥ ካልቻልን ግን…
- እ… ካልችላችሁ ምን?
- ቀደሞ የመጣውን ለማረጋገጥ ከተቸገርን…?
- እ… ምንታደርጋላችሁ?
- መግለጫ እናውጣለን።
- ምን ብላችሁ?
- መንግሥት በዶሮና በእንቁላል ላይ የተጣለው ቫት ተደራራቢ መሆኑን በመገምገምና ኅብረተሰቡን ለምሬት የዳረገ መሆኑን በማጤን…
- እ …?
- ከዶሮና ከእንቁላል ቀድሞ የመጣው ላይ ብቻ ቫት እንዲከፈል ወስኗል እንላለን።
- ይኼ ጥሩ ሐሳብ ነው።
- ወደዱት?
- በጣም እንጂ። ሕዝብ የሚያዳምጥ መንግሥት መሆናችንን ያሳያል።
- የእኛንም ችግር ያቀለዋል።
- የቱን ችግር?
- የመለየቱን ችግር።
- ምን መለየቱን?
- ቀድሞ የመጣውን!
The post [ክቡር ሚኒስትሩ የሹፌራቸው ሁኔታ አላምር ብሏቸው ምን እንደሆነ እየጠየቁት ነው] first appear on ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 Best and reliable news source in Ethiopia and is written by በጋዜጣዉ ሪፓርተር