- አየር መንገዱ ውሳኔውን ማሻሩንና ድርጊቱን ፈጽመዋል ባላቸው ግለሰቦች ላይ ክስ መመሥረቱ ታውቋል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ በሰጠው የግንባታ ውል መሠረት ‹‹ቁልፍ›› ለተባሉ 1992 መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ከቀረጥ ነፃ መብት የገቡ የግንባታ ዕቃዎች፣ በተለያዩ መንገዶች ያላግባብ ጥቅም ላይ መዋላቸው በጉምሩክ ኮሚሽን ኦዲት በመረጋገጡ 362 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል እንደተወሰነበት ታወቀ።
በውሳኔው ላይ አየር መንገዱ ቅሬታ አቅርቦ እንዲሻር ማድረጉንና ሕገወጥ ድርጊቱን ፈጽመዋል ባላቸው አካላት ላይ ክስ መሥርቶ በክርክር ሒደት ላይ መሆኑም ተጠቁሟል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ታኅሳስ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት የሥራ ሒደት አስተባባሪ ወ/ሮ አልማዝ ስብሃት ተፈርሞ፣ ለአየር መንገዱ በተላከ የኦዲት ውጤት ሰነድ ጋር አያይዞ የላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መካከል እ.ኤ.አ. ሐምሌ 17 ቀን 2015 የሠራተኞች መኖሪያ ቤቶች ለመገንባትና የግንባታ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ መብት አማካይነት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ውል መፈጸሙን አስታውሷል።
ሪፖርተር ከሰነዶች ማረጋገጥ እንደቻለው የ1,992 የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለአየር መንገዱ ቁልፍ ሠራተኞች ማለትም ከአንድ ዓመት የአገልግሎት ጊዜ በላይ ላላቸው ፓይለቶችና ቴክኒሺያኖች፣ በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ የተከናወነው፣ ወደ ተለያዩ አገሮች የሚፈልሰውን የዘርፉን የሥራ ኃይል አገር ውስጥ በማስቀረት ለአገሪቱ ኢንዱስትሪ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማስቻል በሚል ምክንያት ነው። የገንዘብ ሚኒስቴር የግንባታ ዕቃዎቹ ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲገቡ ፈቃድ የሰጠውም ይህንኑ ምክንያት በማገናዘብ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
የጉምሩክ ኮሚሽን የኦዲት ውጤት ማሳወቂያ እንደሚለው፣ በአየር መንገዱ ስም ከቀረጥና ታክስ ነፃ የገቡ የግንባታ ዕቃዎች ‹‹ያላግባብ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን በመጥቀስ፣ ተገቢው ዕርምጃ እንዲወሰድ በሚል ለኮሚሽናችን ከሁለት ዓመት በፊት ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ በሰጠው ጥቆማ መሠረት›› የምርመራ መስክ ውስን ኦዲት (Field Issue Audit) እንዲከናወን ተደርጓል።
ይሁንና ሪፖርተር የተመለከተው አየር መንገዱ ለጉምሩክ ኮሚሽን በተጠቀሰው ዕለት ያስገባው ደብዳቤ፣ በኮሚሽኑ ከተገለጸው ጥቆማ ባሻገር ተጨማሪ ዝርዝር አቤቱታንም አካቷል።
አየር መንገዱ በደብዳቤው ከሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ሳይት ቀረጥ ያልተከፈለባቸው ዕቃዎች ያላግባብ እየተወሰዱ መሆኑን ገልጾ፣ ንብረቶቹ ከተወሰዱበት እንዲመለሱ፣ እንዲሁም ይህንን ያደረጉ ግለሰቦች በፈጸሙት ሕገወጥ ድርጊት ላይ ማጣራት ተደርጎ ተገቢው ዕርምጃ እንዲወሰድ አቤቱታ ማቅረቡ ተገልጿል። የድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲቱም ይህን አቤቱታ ተከትሎ የተከናወነ መሆኑም ታውቋል።
የኮሚሽኑ ኦዲት አየር መንገዱ ለሠራተኞች ሠርቶ ለሚያቀርባቸው ቤቶች እንዲውሉ ከውጭ አገር የሚያስመጣቸው የግንባታ ቁሳቁሶች፣ እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2018 ድረስ በሁሉም የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከቀረጥና ታክስ ነፃ ሆነው በገቡ ዕቃዎች ላይ ብቻ ተወስኖ የተደረገ ነው።
በዚህም መሠረት በተደረገው ኦዲት ይፋ የተደረጉ ግኝቶች ከተፈቀደው መጠን በላይ የገቡ ዕቃዎችን፣ ከተፈቀደው በላይ በሥራ ላይ የዋሉ ዕቃዎችን፣ በመጋዘን ውስጥ ያልተገኙ ዕቃዎችን፣ ከጉምሩክ ኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ ክትትልና ቁጥጥር የሥራ ሒደት የቀረበ የቆጠራ ውጤት፣ እንዲሁም ከመንግሥት የተሰጡ መብቶች ክትትልና ቁጥጥር በኩል የቀረበ ማስረጃን አካቶ ቀርቧል።
በግኝቶቹ እንደተገለጸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የግንባታ ቁሳቁሶች ግምታዊ መጠን (Estimated Bill of Quantity) ላይ ከተፈቀደው በላይ የገቡ ዕቃዎች ድርጅቱ ካቀረበው ሰነድና ከአዲስ አበባ ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከተገኙ ሰነዶች ላይ ባደረገው ማጣራት፣ የብዛት ልዩነት መኖሩን የኦዲት ቡድኑ አረጋግጧል ተብሏል።
በሰነዱ እንደተጠቀሰው ይህንን አስመልክቶ የአየር መንገድ ተወካዮች በመውጫ ስብሰባ ተገኝተው በገለጹት መሠረት፣ ግምታዊ ወጪ በተፈቀደው መጠንና ወደ አገር ውስጥ በገባው መጠን ልዩነት መኖሩን አምነው፣ በወቅቱ ለግንባታ የሚያስፈልገውን መጠን በትክክል ማወቅ ስላልተቻለ፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር በግምት ቀርቦ የፀደቀ በመሆኑ የተፈጠሩ ጥቃቅን ልዩነቶች ናቸው በማለት ምላሽ መስጠታቸው ተገልጿል።
‹‹አየር መንገድ ትልቅ ተቋም እንደመሆኑ የመንግሥትን ቀረጥና ታክስ ለማሳጣት ተብሎ የሚሠራ ሥራ የለም በማለት ምላሽ ሰጥቷል፤›› ይላል የጉምሩክ ኮሚሽን ሰነድ።
ይሁንና የኦዲት ቡድኑ ጉዳዮን አስመልክቶ በሰጠው ውሳኔ፣ በጉምሩክ አዋጅ 859/2006 አንቀጽ 157(1) መሠረት፣ መከፈል ያለበትን ፍሬ ግብርና ቅጣት በማሥላት፣ በአጠቃላይ አየር መንገዱ ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ያድርግ ብሏል።
በሁለተኝነት በታየው ከተፈቀደው በላይ በሥራ ላይ የዋለ ዕቃዎችን በተመለከተ የኦዲት ቡድኑ ሰነዶችን በሚያጠራበት ወቅት፣ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የገባው መጠን በሥራ ላይ ከዋለው መጠን በልጦ የተገነባ መሆኑን ከቀረበለት የሰነድ ማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል ብሏል።
እንደ ጉምሩክ ኮሚሽን ሰነድ ገለጻ፣ ይህንን አስመልክቶ የአየር መንገድ ተወካዮች በመውጫ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ምላሽ፣ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የገባ መጠንና በሥራ ላይ የዋለ መጠን ልዩነት መኖሩን አምነው፣ በወቅቱ ኮንትራክተሩ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከአገር ውስጥ ግዥ ፈጽሟል በማለት ምላሽ እንደሰጡት አብራርቷል።
ሆኖም አየር መንገዱ ይህንን ሊያስረዳ የሚችል ተጨባጭ ማስረጃ ሊያቀርብ አለመቻሉን፣ በተጨማሪም በአየር መንገዱና በሥራ ተቋራጩ መካከል የተደረጉ ስምምነቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ቁሳቁስ አቅርቦትና የማስረከብ ሒደት የሚያሳዩ ውሎች በኦዲት ቡድኑ የታዩ ቢሆንም፣ በስምምነታቸው መሠረት ከአገር ውስጥ የተፈጸሙ ግዥዎችን የሚያሳይ ማስረጃ አልቀረቡልኝም ብሏል።
በዚህም መሠረት ከዚህኛው የኦዲት ግኝት ጋር በተያያዘ አየር መንገዱ የፍሬ ግብርና ቅጣትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ91.06 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፍል መወሰኑ ተገልጿል።
በመጋዘን ውስጥ ያልተገኙ የግንባታ ዕቃዎችን በተመለከተ ተደረገ በተባለው የኦዲት ምርመራ፣ ከአየር መንገዱ ከቀረቡ ሰነዶች በተደረገው ማጣራት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የገባው መጠን፣ በሥራ ላይ የዋለ መጠንና የቀሪ መጠን (Stock Balance) የኦዲት ቡድን በሚያጠራበት ወቅት፣ በመጋዘን ውስጥ የቀሪ መጠን መኖሩን ማረጋገጡን ኮሚሽኑ አሳውቋል።
ይህን አስመልክቶ የአየር መንገዱ ተወካዮች ለኮሚሽኑ ሰጥተዋል በተባለ ምላሽ፣ የግንባታ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ከኮንትራክተሩ ጋር ቆጠራ ተደርጎ ርክክብ የተደረገ መሆኑን፣ ሆኖም በድርጅቱ ስም ከቀረጥና ከታክስ ነፃ የገቡ የግንባታ ዕቃዎች ያላግባብ ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን በመጥቀስ፣ ኮሚሽኑ ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወስድ ነሐሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በደብዳቤ መጠየቃቸውን ማሳወቃቸው ተጠቅሷል።
የሪፖርተር ምንጮች በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 በሚገኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች መኖሪያ ግቢ ውስጥና የአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ በሚያስተዳድረው የመንግሥት ይዞታ መጋዘን፣ እንዲሁም በግቢው ውስጥ ተከማችተው የሚገኙ በርካታ ንብረቶች መኖራቸውን፣ የአየር መንገዱን ቀረጥና ታክስ ነፃ መብት በመጠቀም ለፕሮጀክት ወደ ሥፍራው ከገቡ ንብረቶች የተረፉ ንብረቶችን የሥራ ተቋራጭ ኩባንያው ተወካይ ነን ያሉ ግለሰቦች መጠነ ሰፊ የሆነ በቡድንና በጦር መሣሪያ በመደገፍ ንብረቶች ማጓጓዛቸውን እንደሚያውቁ ገልጸዋል።
በወቅቱም የግንባታ ኩባንያው ተወካይ ነን ባሉ ግለሰቦች ንብረቶች በአይሱዙ አምስት የጭነት ተሽከርካሪዎች ተጭነው መወሰዳቸውን፣ አየር መንገዱም ለኮሚሽኑ ጥቆማ ማቅረቡን፣ ለአካባቢው ፖሊስም ጉዳዩን ማሳወቁንና በጉዳዩ ላይም ክስ መመሥረቱን ምንጮች ገልጸዋል።
ሰነዶች እንደሚጠቁሙት በተጨማሪ አየር መንገዱ ቀረጥ ያልተከፈለባቸውን ዕቃዎች በመመሳጠር ለመውሰድ ጥረት አድርገዋል ባላቸው ግለሰቦች ላይ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ውል ችሎት ክስ አቅርቦ፣ ችሎቱ ንብረቱ ከቦታው እንዳይንቀሳቀስ መሰከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕግድ ሰጥቶና በመዝገቡ ላይ የጉሙሩክ ኮሚሽንም ጣልቃ ገብቶ ክርክሩ አሁንም ድረስ ቀጥሎ እየታየ ነው።
ይሁንና ታኅሳስ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ለአየር መንገዱ የተላከው የኮሚሽኑ የኦዲት ግኝት፣ በመጋዘን ውስጥ ያልተገኙ የግንባታ ዕቃዎችን በተመለከተ፣ የኦዲት ቡድኑ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/06 አንቀጽ 163(ሐ) ድንጋጌ፣ ‹‹መንግሥት ማግኘት የነበረበትን ቀረጥና ታክስ ዕቃው በተያዘበት ጊዜ ወደ አገር እንደገባ ተቆጥሮ፣ ለዕቃው ሊከፈል የሚገባው ቀረጥና ታክስ መክፈሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የቀረጥና ታክሱን 50 በመቶ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፤›› በሚለው መሠረት፣ አየር መንገዱ ፍሬ ግብርና ቅጣት ተጨምሮ በድምሩ 171.62 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ እንዲያደርግ ተወስኖበታል።
ከዚህ በተጨማሪ በኮሚሽኑ የኢንተለጀንስና የኮንትሮባንድ ክትትልና ቁጥጥር የሥራ ሒደት የቀረበ የቆጠራ ውጤት ጋር በተያያዘ ግብር፣ ወለድና ቅጣት ተሠልቶ 21.93 ሚሊዮን ብር እንዲከፍልም ውሳኔ ተላልፎበታል።
በኮሚሽኑ ኦዲት በአራተኝነት የሰፈረው ግኝት ከመንግሥት የተሰጡ መብቶች ክትትልና ቁጥጥር በኩል የቀረበ ማስረጃን በተመለከተ የኦዲት ቡድኑ፣ በመንግሥት የተሰጡ መብቶች ክትትልና ቁጥጥር ቡድን የሰነድ ማስረጃዎች በጠየቀው መሠረት፣ አጠቃላይ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ በኩል የተገኙ ማስረጃዎች በውስጥ ማስታወሻ ኅዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በተላከው መሠረት የቀረበውን የሰነድ ማስረጃ መነሻ በማድረግ በኦዲት ማረጋገጥ መቻሉ ተጠቅሷል።
በኦዲት ሪፖርቱ ሰነድ እንደተገለጸው፣ ከዚህ በመነሳት ከቀረጥና ታክስ ነፃ የገቡትን ዕቃዎች በከሳሽና ተከሳሽ የይገባናል ጥያቄዎች የሰነድ ማስረጃ ዝርዝር በሪፖርቱ የተያያዘ ሲሆን፣ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀረጥና ታክስ ነፃ ሆነው እንዲገቡ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጥር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ለግንባታው የሚያስፈልገው መጠንና ብዛት የተፈቀደ ደብዳቤ መኖሩንና ይህንንም በምን ዓይነት አግባብ እንደተፈቀደ የኮሚሽኑ ኦዲት ቡድን ሲያጣራ፣ በሕጉ መሠረት ስለመፈቀዱ በኦዲት ማረጋገጥ መቻሉ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያና አየር መንገዱ ከቀረጥና ታክስ ነፃ የገቡት የግንባታ ተረፈ ምርት ዕቃዎችን ከግንባታው ውል በተጨማሪ፣ የተረካከቡበት የውል ስምምነት መኖሩንም የኦዲት ቡድኑ ከመንግሥት የተሰጡ መብቶች ክትትልና ቁጥጥር ከቀረበው ማስረጃ ማረጋገጥ ችሏል ተብሏል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኦዲት ክፍል ግኝቶቹን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መንግሥት ማግኘት የነበረበትን ቀረጥና ታክስ ፍሬ ግብር፣ ቅጣትና ወለድ በማሥላት በአጠቃላይ ከ361.68 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ እንዲያደርግ ማሳወቁን በአንድ የኦዲት ቡድኑ አስተባባሪና በሁለት ኦዲተሮች ስምና ፊርማ የወጣው ሰነድ ያሳያል።
ይሁንና ሪፖርተር አየር መንገዱ በዚህ ውሳኔ ላይ አየር መንገዱ ቅሬታ አቅርቦ የጉሙሩክ አቤቱታ አጣሪ ዳይሬክቶሬት፣ በኦዲተሮቹ የተወሰነውን ውሳኔ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ መሻሩን፣ ጉዳዩም እንደገና በመታየት ላይ እንደሚገኝ ሪፖርተር ከተመለከታቸው ሰነዶች ማረጋገጥ ችሏል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም አየር መንገዱ ቀረጥ ያልተከፈለባቸውን ዕቃዎች በመመሳጠር ለመውሰድ ጥረት አድርገዋል ያላቸው ግለሰቦች ላይ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ውል ችሎት ክስ አቅርቦ፣ ችሎቱ ንብረቱ ከቦታው እንዳይንቀሳቀስ በመሰከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕግድ ሰጥቶና በመዝገቡ ላይ ጉሙሩክ ኮሚሽንም ጣልቃ ገብቶ የቀጠለው ክርክር፣ ለመጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ እንደተሰጠበትም ታውቋል።
አየር መንገዱ የመንግሥት ታክስና ቀረጥን በሚመለከት ጥብቅ አሠራር የሚከተል በመሆኑ፣ ቀረጥ ያልተከፈለበትን ዕቃ ፍርድ ቤትን በማሳሳት ለግል ጥቅም ለማዋል ጥረት ያደረጉ ግለሰቦች ላይ የሕግ ክትትሉን ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለኮሚሽኑ ማሳወቁንም ምንጮች ጠቁመዋል።