ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 reliable news source in Ethiopia

ፍርፋሪ!
ከቀጨኔ ወደ አውቶቡስ ተራ ለመጓዝ የጠዋቱን ቅዝቃዜ ተቋቁመው የታክሲ ሠልፍ ላይ የተገኙ መንገደኞች ሰላምታ እየተሰጣጡ ይሳሳቃሉ፡፡ የጥንቷ ቀጨኔ በቅርብ ርቀት ከፒያሳና ከአዲሱ ገበያ ጋር ተጎራብታ ስትኖር ብዙዎቹ ነዋሪዎቿም ለበርካታ ዓመታት አንድ ላይ በመኖራቸው ትውውቃቸው የዝምድና ያህል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስላል የቀጨኔ ታክሲ ተራ ሠልፍ ላይ ሰላምታውና ሳቁ ደመቅ ያለው፡፡ የዛሬው ማለዳ ሳቅ ግን የሰሞኑን ግራና ቀኝ አጀንዳዎች የተንተራሰ ስለሆነ፣ ከሳቁ በስተጀርባ ያለው የኑሮ ክብደት በተረብና በስላቅ መታጀቡ አይደንቅም፡፡ ከጥንት ጀምሮ ከሸማ ሥራ እስከ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ከእህል ንግድ እስከ ሸቀጣ ሸቀጥና የተለያዩ ተግባራት የምትታወቀው ቀጨኔ ዛሬም ከኑሮ ጋር ከባድ ፍልሚያ የያዙ የልጅ ልጆች አፍርታለች፡፡ በዚህ ፍልሚያ ውስጥ ግን ሁሌም ሳቅና ተረብ ጠፍተው አያውቁም፡፡ ሳቁና ተረቡ ውስጥ ከአገር በቀል እስከ ዘመናዊ ዕውቀት የተላበሱ ዕድሜ ጠገብ ቁምነገሮችም አሉ፡፡ ጨዋነትና ትህትና ከስክነት ጋር ተዳምረው ሕይወትን ያለመልማሉ፡፡ የቀጨኔ ሕይወት ወትሮም እንዲህ ነው!
የታክሲ ጥበቃ ሠልፉ ላይ የጦፈው ወሬና ሳቅ ደርቶ ሳለ ተረኛ ሚኒ ባስ ደርሶ ተረኞችን ከጫነ በኋላ ወያላው ‹‹ሳበው!›› ብሎ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ደላላውና ሾፌሩ አብሮ አደግ ይመስላሉ፡፡ አንዱ ከሌላኛው ጋር ሲነጋገሩ በተለመደው የአራዳ ቋንቋ ስለሆነ ለቀጨኔ ተሳፋሪዎች እንግዳ አልነበረም፡፡ ወያላውና ሾፌሩ በተለመደው ሁኔታ እያወሩና በፊት ገጽታቸው በዚያች ማጮንቆሪያ መስተዋት እየተያዩ ሲሳሳቁ፣ ‹‹እነ አጅሬው ዛሬ ደግሞ ምን ተገኝቶ ነው ኮዱን ከበድ አድርጋችሁ የምታወሩት…›› የሚለው በአካባቢው በአናጢነት የሚታወቀው ቀዩ ጎልማሳ ሲሆን፣ ‹‹እነሱ እኮ አንድ ቀን ቴሌቪዥን ላይ ተጋብዘው የአገሩን ሁኔታ ተንትኑ ቢባሉ እንደ ቻርሊ ቻፕሊ በሳቅ ነበር የሚፈጁን…›› ብሎ የዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዓመት ተማሪ እንደሆነ የተነገረለት ወጣት ይመልሳል፡፡ ወያላው ሒሳብ መቀበል እየጀመረ፣ ‹‹የዛሬው ማለዳ ታሪፍ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምንዛሪ ተመን መሠረት መሆኑን ሳሳውቃችሁ በታላቅ አክብሮት ነው…›› ከማለቱ፣ ‹‹አንተ ደግሞ ተሳስተህ እንዳታሳስት በዶላር ሳይሆን በዩሮ ምንዛሪ ተመን ነው…›› ብሎ ሲጨምርበት በረጅሙ ተሳቀ፡፡ ምን ይደረግ!
‹‹አንተ ሾፌር ዶላርም ሆነ ዩሮ ከእኛ ሊግ ውጪ ስለሆነ ብታባዛውም ብታጣፋውም በዚህ በፈረደበት ብር መከፈሉ አይቀርም፡፡ ለማንኛውም እንዳልከው በጠዋቱ የምንዛሪ ተመን መሠረት ታሪፉ አሥራ አምስት ብር መሆኑን ሳበስርህ በጣም ደስ እያለኝ ነው…›› ብለው መሀል መቀመጫ የተሰየሙት አዛውንት ለወያላው ያረጁ አሥርና አምስት ብሮች ከፍለው ጨዋታውን ሲያደሩት ሳቁም አብሮ ደራ፡፡ ‹‹አገር በልማትና በዕድገት ጎዳና ገስግሳ እንድትለወጥ መላ በሉ እየተባለ፣ እናንተ ግን ዓይናችሁም ልባችሁም ያለው እዚያው መከረኛ የምንዛሪ ተመን ላይ ነው…›› ብላ መንገዱ ጫፍ ላይ አነስተኛ ሱቅ ያላት ቀጭን ወይዘሮ ሌላ አጀንዳ ስትመዝ፣ ‹‹ሰውዬው ነገ ዓይንህ ይበራልሃል ቢሉት ዛሬን እንዴት አድሬ እንዳለው መሆኑ ነው…›› የምትላት አጠገቧ የተቀመጠች ጠይም ቆንጆ ናት፡፡ ‹‹ሰውየው እኮ እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ሰው ሰላሳ ዓመት ሙሉ ዓይኑ አያይም ነበር…›› ከማለቱ ሾፌሩ፣ ‹‹አገር የምትፈልገው ታጋሽ፣ ትሁት፣ አርቆ አሳቢና ሁሉንም የሰው ልጆች በእኩል የሚመለከት ነው፡፡ ያላደለው ደግሞ ይህንን የመሰለ መልካም ፀጋ ተገፎ ራዕይ አልባ ሆኖ ኖሮ ያልፋል፡፡ በስተመጨረሻም ‹ተኖረና ተሞተ› ተብሎ ይተረትባል…›› ሲሉ አዛውንቱ ዝም አልን፡፡ ምን ማለት ይቻላል!
‹‹እኛ መቼም በምሳሌ ካልተነገረን አይገባንም እንጂ፣ ፈጣሪ በሰጠን አዕምሮ ትንሽ አሰብና መርመር ስናደርግ ብዙ ነገሮች እንደሚለገጹልን ለእናንተ መናገር ይከብደኛል፡፡ ለማንኛውም አንድ ጉዳይ ሲነገር ለምን ብለን በአዕምሮአችን ማሰብ ብንጀምር መልካም ይመስለኛል…›› ብሎ የዩኒቨርሲቲ ተማሪው አዲስ ሐሳብ ሲያመጣ፣ ‹‹ወንድሜ እሱ የአንተ የንድፈ ሐሳብ ትንተና ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥም በዚህ ሴረኛ ዘመን አይሆንም ብሎ ማስተባበል አይቻልም፡፡ ነገር ግን ነገርን አውጥቶና አውርዶ ለማሰብ እኮ ፋታ ያስፈልጋል፡፡ የተረጋጋ ኑሮ፣ ሰላም፣ ማኅበረሰባዊ መተሳሰብ፣ ከቂምና ከጥላቻ የፀዳ አርቆ አስተዋይነትና ሞራላዊ ከፍታ ሲኖር አንተ ያልከው አይቸግርም፡፡ ነገር ግን አሁን በየአቅጣጫው ሴረኛው በዝቶ በአንድ በኩል ኑሮን ያጨናንቅብሃል፣ ሠርተህ እንዳትኖር መሰናክል ይደረድርብሃል፣ የመንግሥት ትዕዛዝ ወይም አቅጣጫ ነው እያለ ሕግ የማያውቀው ትርምስ ይፈጥርብሃል…›› ብላ ያቺ ጠይም ወጣት ስታብራራ አፋችንን ከፍተን ሰማናት፡፡ ጎበዝ ‹ተሸፋፍነው ቢተኙ ገልጦ የሚያይ አምላክ አለ› ይሉ የነበሩት የድሮ ሰዎች ምንኛ የታደሉ እንደሆኑ ለማወቅ ይህንን የታመቀ ነገር ግን የሚንበለበል ብሶት መታዘብ ብቻ ይበቃል፡፡ ድንቅ ነው!
ወያላው ለሾፌሩ፣ ‹‹አየህ ሕዝባችን እየደረሰበት ያለው የንቃተ ህሊና ደረጃ ማንንም መፈናፈኛ እንደሚያሳጣ…›› ሲለው፣ ‹‹እኔን ግርምና ድንቅ የሚለኝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁሉም ሰው ቆቅ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ ዕድሜ ለእነዚያ ጠዋት ትምህርት ቤት ለምናደርሳቸው ጩጬዎች ብዙዎቹ ቤተሰቦች ነቃ እያሉ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ከራሱ አልፎ ቤተሰቡንና ማኅበረሰቡን የሚለውጥ ንቃትና ዕውቀት መጎናፀፉ ያስደስታል፡፡ አለ እንጂ የእኛ ትውልድ ቢማር ያልገባው፣ ሥራ ጠልቶ ሱስ የሠፈረበት፣ ከመጠየቅና ከመመራመር ይልቅ በሌሎች አጀንዳ ተጠልፎ የሚወሰድና እንደ ጋሪ ሲጎተት የሚኖር…›› እያለ ተነተነው፡፡ ‹‹ሾፌር እውነትህን ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ‹ጄኔሬሽን ዚ› የሚባለው ለቀድሞ እንኩቶ ጉዳዮች ሳይሆን ልቡንና አዕምሮውን አሳልፎ የሰጠው ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ስለዚህም ውድድሩ እርስ በርስ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መሆኑ ገብቶት ቴክኖሎጂን እንደ ፈረስ ተፈናጦበት እየጋለበ ስለሆነ ለትርኪ ምርኪ ነገሮች ጊዜ የለውም፡፡ ስለዚህ ቤተሰብም ሆነ ማኅበረሰብ ወዶ ሳይሆን ተገዶ ከአዲሱ አስተሳሰብ ጋር ለመራመድ ትግል መጀመር አለበት…›› በማለት የዩኒቨርሲቲው ወጣት ሲያክልበት አዳመጥን፡፡ የግድ ነው!
ጉዞው ቀጥሏል፡፡ የቀጨኔ ሰዎች በስክነትና በጨዋነት ሐሳባቸውን እየተለዋወጡ መንገዱ ተጋምሶ፣ የወረደው ወርዶ ሌሎች ተተክተው ጉዞ ሲጀመር ደፍረስ ያሉ ነገሮች መደመጥ ጀመሩ፡፡ ከመንገድ የተሳፈረች ብስል ቀይ ሎጋ ከውጭ በስልክ የጀመረችውን ወሬ እየቀጠለች፣ ‹‹በትናንት ማታና በዛሬ ጠዋት መካከል ምን ተዓምር ቢፈጠር ነው በአንድ ፒስ ላይ የአንድ ሺሕ ብር ልዩነት የሚፈጠረው እባክሽ…›› እያለች ስትቆጣ ከወዲያ በኩል የሚሰጣት ምላሽ ምን እንደሆነ ባይሰማም ጭማሪውን ያፀና እንደሆነ ከፊቷ ገጽታ ያስታውቅ ነበር፡፡ ‹‹አይ ዘንድሮ፣ መንግሥት በአንድ በኩል ከቡና ረከቦት እስከ የስፌት መኪና በግብር ምክንያት ያሽጋል፣ በሌላ በኩል የዋጋ ግሽበቱ ቀነሰ በተባለ ማግሥት ምክንያቱ የማይታወቅ የዋጋ ጭማሪ በሁሉም ዕቃዎች ላይ ይጨምራል…›› የሚሉት ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ እናት ናቸው፡፡ እሳቸው በትካዜና በመከፋት ውስጥ ሆነው ለብቻቸው ማውራት ሲጀምሩ፣ ‹‹ዘንድሮማ እንዲሁ በዋዛ አንላቀቃትም፣ አሁንስ አልበዛም እንዴ ማንም እየተነሳ ገንዘባችንን መና ሲያደርገው ዝም የሚባለው እስከ መቼ ነው…›› የምትለው በስልክ ረጅም ንግግር የያዘችው ናት፡፡ ይገርማል ይደንቃል!
ታክሲያችን ከፊት ለፊት አውቶቡስ ተራን እያየች ስትከንፍ፣ ‹‹ጎበዝ የዘንድሮ ነገራችን እንደ ሰናኦር ግንበኞች ድብልቅልቁ እየወጣ ያለው ፈጣሪ ቢቆጣን እንጂ በሌላ ምክንያት አይመስለኝም፡፡ በመጨረሻው ዘመን ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥት በመንግሥት ላይ እንደሚነሳና በየቦታው ድርቅ፣ ቸነፈር፣ ረሃብ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የውኃ ሙላትና መሰል ጥፋቶች የመጨረሻው የጥፋት ዘመን ምልክቶች እንደሆኑ በቅዱስ መጽሐፉ ውስጥ የሠፈረውን ይኸው በዓይናችን እያየን ነው…›› በማለት አዛውንቱ ሲናገሩ፣ ‹‹ከጊዜው ጋር የማይራመድ፣ ለዘመኑ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ጀርባውን የሚሰጥ፣ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ በመፍታት ሰላም አስፍኖ ለአገር ዕድገትና ልማት የማይለፋ፣ በብሔርና በእምነት እየተቧደነ አገር የሚያምስና የሚዘርፍ፣ ለባዕዳን ተላላኪ ሆኖ አገር የሚያስደፍር፣ ለሳይንሳዊ አመራርና የኑሮ ዘይቤ የማይመች ድንቁርና የሚያስፋፋ፣ እንዲሁም በስንፍና ድንኳን ውስጥ ተኝቶ የሚያንቀላፋ ደግሞ መጥፊያውን በገዛ እጁ ያቃርባል…›› የሚለው መጨረሻ ወንበር ጥግ ላይ የተቀመጠ ገብስማ ጎልማሳ ነበር፡፡ ወጣቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ ‹‹ሁለቱም ሐሳቦች ትክክል ናቸው፡፡ የተሰጣቸውን ኃላፊነት አደራ በልተው አገር የሚዘርፉና የሚያዘርፉ የእጃቸውን ያገኛሉ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን አገርን ለታሪካዊ ጠላት ፍርፋሪ ለመሸጥ የሚያደቡ ፍርዳቸውን የሚያገኙበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ይሰመርበት…›› ሲለን ታክሲያችን አውቶቡስ ተራ ደርሳ በወያላው ‹‹መጨረሻ…›› ስንባል ሰላምታ ተሰጣጥተን ወደ ጉዳያችን ስናመራ፣ የጠላት ፍርፋሪ ያለው ጉዳይ ከበድ ብሎ ነበር የተሰመረበት፡፡ መልካም ጉዞ!
The post ፍርፋሪ! first appear on ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 reliable news source in Ethiopia and is written by በጋዜጣው ሪፓርተር