- ዩኒቨርሲቲው ሰፋ ያለ የኦዲት ክፍተት አለበት ተብሏል
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከሠራዊት አባልነት ኮብልለው የነበሩ ከ1,300 በላይ የፖሊስ አባላትን አፈላልጎ ወደ ሥልጠና ማስገባቱን አስታወቀ፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተለያየ ምክንያት ከአባልነት ጠፍተው የነበሩ አባላት ‹‹በፀረ ሰላምና እና ኃይል›› በወንጀል ድርጊት እንዳይጠለፉ በሚል ሥጋት፣ የተጠረጠሩ የቀድሞው ሠራዊት አባላት፣ በአስቸኳይ ሥልጠና እንዲያገኙ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶ ወደ ሥልጠና መግባታቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሸነር መስፈን አበበ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያስታወቁት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲን የ2015 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ታኅሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ሲገመግም ነው፡፡
ኮሚሽነሩ የፖሊስ አባላት ከተለመደው አገልግሎት ወጣ ያሉና ከአቅም በላይ የሆኑ ሥራዎችን በአገር መከላከያ ሠራዊት በመታገዝ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡
በአገር ደረጃ የሠራዊት እጥረት ስላለ በየዓመቱ ዩኒቨርሲቲው አሥር ሺሕ ሠራዊት እያሠለጠነ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል የሚገኘው የደብረ ማርቆስ ፖሊስ ማሠልጠኛ በ2015 ዓ.ም. በደረሰበት ጥቃትና ወድመት መዘጋቱንና ምንም ዓይነት ሥልጠና እያከናወነ አለመሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ሰፋ ያለ የኦዲት ክፍተት የተገኘበት ዩኒቨርሲቲው በሰጠው ምላሽ፣ ወቅታዊ ግዳጅን ለመስጠት በሚያስችለው ቁመና ላይ ተገኝቶ ለግዳጅ ዝግጁ ለመሆን በሚሠራበት ወቅት ክፍተት መፈጠሩን አስታውቋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያቀረበውን የኦዲት ግምገማ የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴው፣ ዩኒቨርሲቲውን ምላሽ ይስጠኝ ሲል ገዘፍ ያሉ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡
የኦዲት ሪፖርቱ ይዟቸው ከመጣው ክፍተቶች መካከል የገንዘብ ሚኒስቴርን ፈቃድ ሳይጠይቅ፣ በዩኒቨርሲቲው ፍላጎት ብቻ ለኮርስ ማስፈጸሚያ ተብሎ በተከፈተ አካውንት ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ይገኝበታል፡፡
በተመሳሳይ በገንዘብ ሚኒስቴር የማይታወቁና ፈቃድ ሳይሰጥ በዩኒቨርሲቲው በታተሙ ደረሰኞች የተሰበሰበውን ገንዘብ በተመለከተ የሚያስረዳ ማስረጃ ባለመኖሩ፣ የተሰበሰበውን ገቢና ወጪ ገንዘብ ማወቅ አለመቻሉ በኦዲቱ ተመላክቷል፡፡
ለአሠልጣኞች የሙያ አበልና ለካሎሪ በሚል ከደንብ ውጪ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙ፣ በተለያዩ ጊዜያት የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ከሥራ ቦታቸው ሳይንቀሳቀሱ በሥራ ገበታቸው እያሉ 137 ሺሕ ብር ያላግባብ አበል መከፈሉን በሪፖርቱ በመቅረቡ ቋሚ ኮሚቴው ማብራሪያ ጠይቋል፡፡
በሚመለከተው አካል ሳይፀድቅ ቀድሞ የነበረውን የአንድ ተማሪ ቀለብ 1,500 ብር እንዲሆን በማድረግ ያላግባብ ሃያ ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙ፣ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ ከማን እንደሚሰበሰብ ማስረጃ ሊቀርብ ያልተቻለበት 1.6 ሚሊዮን ብር በኦዲት መገኘቱ ተገልጿል፡፡
ለበጀት ዓመቱ ከተደለደለው መደበኛ በጀት ውስጥ ሥራ ላይ ያልዋለ 267 ሚሊዮን ብር በጥናት ሳይረጋገጥ 16.4 ሚሊዮን ብር ለተማሪዎች የሚውል የምግብ ግብዓቶችን በጨረታ መግዛት ሲገባ፣ በለቀማ ግዥ መፈጸሙን የኦዲት ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
ከመመርያ ውጪ ከተለያዩ ድርጅቶች ጨረታ ሳይወጣ በቀጥታ ግዥ 38 ሚሊዮን ብር ለተሽከርካሪ ጎማ ወጪ መደረጉ፣ ያለ ግልጽ ጨረታ የተፈጸመ ከ2.3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ፣ እንዲሁም የሚመለከተው አካል ሳይፈቅድ ወጪ የተደረገ ሦስት ሚሊዮን ብር መገኘቱን በኦዲት ሪፖርቱ ቀርቧል፡፡
በተመሳሳይ የኒቨርሲቲው ዓመታዊ የንብረት ቆጠራ የማያደርግ መሆኑን፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች በተማሪዎች ክሊኒክ መገኘታቸውን፣ ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ ምርመራ ተደርጎላቸው እንደሚያውቅና በሊትር ምን ያህል ኪሎ ሜትር መሄድ እንደሚችሉ የማይታወቅ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴውም ገልጿል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የነዳጅ ግዥ ፈጽሞ ከነዳጅ ተሽከርካሪ ወደ ማደያ ዴፖ ገቢ ሲያደርግ በተባለው መጠን ለመቅረቡ የሚረጋገጠው በኮሚቴ ሳይሆን በአንድ ግለሰብ መሆኑን፣ በዴፖው ውስጥ ምን ያህል ነዳጅ እንደሚገለበጥ እንደማይታወቅ በኦዲት ሪፖርት መረጋገጡ ተጠቅሷል፡፡
በተሽከርካሪዎች የነዳጅ ታንከር ውስጥ ያለው ነዳጅ ለታለመለት ዓላማ መዋሉ ሳይረጋገጥና አሽከርካሪዎች የማንንም ፈቃድ ሳይጠይቁ ከነዳጅ ዴፖ ነዳጅ የሚቀዱ መሆኑና ሌሎችም ክፍተቶች በዩኒቨርሲቲው ላይ ቀርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አብዛኞቹን ችግሮች ከፖሊስ ሥራ ጋር የተያያዙ ጊዜ የማይሰጡና ምላሽ የሚፈልጉ በመሆናቸው የተፈጸሙ ስህተቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሠራተኞች ደመወዝ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ መኖር ስለማይችሉ መደጎም ካልተቻለ ሥልጠና ማቆም የግድ ነው ብለዋል፡፡