በኢትዮጵያ ብቸኛው የግል ሞርጌጅ ባንክ በመሆን ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው ጎህ ቤቶች ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በኋላ 80.1 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑንም የባንኩ የ2016 ሒሳብ ዓመት ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ባንኩ በቀዳሚው የ2015 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው ትርፍ 6.4 ሚሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህም ማለት ባንኩ በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት የ77 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ያመለክታል፡፡
ጎህ ቤቶች ባንክ ዘግይተው የባንኩ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀሉ ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ከሞርጌጅ ባንክ ጋር በተያያዘ ምቹ ሁኔታ አለመኖር ባንኩ ላይ ተፅዕኖ እያሳረፈ መሆኑን ነገር ግን ከቀዳሚው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ በላቸው ሁሪሳ ተናግረዋል፡፡
‹‹የብድር ጣሪያ ወሰን፣ ለሞርጌጅ በባንክ ሥራ አስቻይ ሁኔታ አለመኖርና የረዥም ጊዜ ፈንድ አለመኖር የጎህ ቤቶች የሥራ አፈጻጸም ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፤›› በማለት ያጋጠሙ ችግሮችን አመላክተዋል፡፡
የቦርድ ሊመቀንበሩ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚው በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ መቆየቱን፣ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የመንግሥት የነዳጅ ድጎማ ቀስ በቀስ መነሳትና በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የዘለቀው የፀጥታ መደፍረስ በኢኮኖሚው ላይ ጫና ማሳደራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም፣ የባንክ ዘርፉ በፈታኝና ባልተረጋጉ ሁኔታዎች ውስጥ ያሳለፈ ቢሆንም ባንካቸው በሁሉም የአፈጻጸም አመልካቾች ጉልህ ዕድገት ያሳየበት ዓመት እንደነበር በመጥቀስ የባንኩን ዓመታዊ አፈጻጸሞች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
ከነዚህም መካከል አጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 1.02 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ይህም ካለፈው ዓመት 911.8 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ112.6 ሚሊዮን ብር ወይም የ12.3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞች ቁጥርም በቀዳሚው ዓመት ከነበረበት 21,932 በ2016 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በ8,598 ወይም በ39.2 በመቶ በመጨመር 30,530 መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ከብድር ሥርጭት አንፃርም የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 1.55 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል፡፡ ይህም በቀዳሚው ዓመት ከነበረው 1.32 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ233 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡ ከተሰጡት ብድሮች ውስጥ የሕንፃ እንዲሁም የቤትና የግንባታ ብድር 60.7 በመቶውን ይዟል፡፡ የወጪና ገቢ ንግድ ብድር 19.8 በመቶ፣ የአገር ውስጥ ንግና አገልግሎትና ሌሎች ብድሮች የቀረው 19.5 በመቶ ድርሻ እንደያዘ የቀረበው ሪፖርት ያመለክታል፡፡
የባንኩ ዓመታዊ አጠቃላይ ገቢ 414.1 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት 212.6 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 201.5 ሚሊዮን ብር ወይም የ94.8 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡
የጎህ ባንክ አጠቃላይ ሀብት 2.86 ቢሊዮን ብር ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ከቀዳሚው ዓመት የ234.1 ሚሊዮን ብር ወይም የ8.9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ደግሞ 1.68 ቢሊዮን ብር ሲደርስ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ1.4 ቢሊዮን ብር ሆኖ መመዝገቡ ተጠቅሷል፡፡