በስንታየሁ ገብረ ጊዮርጊስ
በሪፖርተር ጋዜጣ እሑድ ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ቅጽ 30 ቁጥር 2562 ላይ፣ ‹‹ችግሮችና መፍትሔዎች ከፖለቲካ፣ ሕጋዊና ባህላዊ ዳኝነቶች (ሽምግልና) አኳያ›› በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሑፍ ውስጥ በርካታ ሐሳቦችን ለማንሳት ሙከራ አድርጌያለሁ፡፡ ሐሳቦቹ ሰፊና አከራካሪ ሊሆኑ ስለሚችሉ ሌሎችም ቢጽፉበት የሚል ምኞትን በመያዝ ያቀረብኩኝ መሆኔን መናዘዝ እፈልጋለሁ፡፡ በግሌ በጉዳዩ ላይ ከሌሎች መስማትና መማርን እፈልጋለሁ፡፡ በተለይ በሕግና በፖለቲካል ኢኮኖሚ ዘርፍ ምርምር የሚያደርጉ ባለሙያዎች ቢሳተፉበት ምንኛ መልካም ነበር? በማለትም ተመኝቼያለሁ፡፡ ሌሎች የሚጽፉትን እየጠበቅሁ፣ የእኔን ሐሳብ ግን ልቀጥልበት፡፡
ዛሬም ሐሳቤን የማቀርበው የሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ‹‹ከሕዝብና ከአገር በፊት ቀዳሚ ነገር የለም›› በማለት በርዕሰ አንቀጹ ያሰፈራቸውን ሐሳቦች መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በርዕሰ አንቀጹ ከተነሱት መካሪና አስተማሪ ናቸው በማለት ከተመረኮዝኩባቸው ሐሳቦች ጥቂቶቹ፣ ‹‹ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የግጭት አፈታት ሥልቶችና የሽምግልና ሥርዓቶች ሰላም ማስፈን የሚችል ብልህ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ፣ ምን ችግር ቢገጥማት ነው የንፁኃንን ደም ከመፍሰስ መታደግ ያቃተው፡፡፣ ‹‹ብዙዎቹ በፖለቲካም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ልሂቃን፣ ለአገር ዘላቂ ሰላም በሚያስገኙ ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ዳተኝነት እያሳዩ መሆናቸው ችግሮችን እያከበዳቸው ነው››፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ህልውና ሲባል ቀና ቀናውን ብቻ ማሰብ የትም አያደርስም›› የሚሉ ቁጭት አዘል መብሰልሰሎችን ያቀፉ ዓረፍተ ነገሮችን እንዳሉ ተቀብያቸው ነው፡፡ ካለፈው በቀጠለው የዛሬ ሐሳቤ ላይ ላተኩር፡፡
በአንድ አገር ውስጥ እንደየ ርዕዮተ ዓለሙና የተቋም አወቃቀር የሚለያዩ ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሕግ የሚወጣው በሕግ አውጪ አካላት ነው፡፡ ሕግ አስፈጻሚ የመንግሥት አካላት ደግሞ ሕገወጥነትን ለመከላከል/ሕግን ለማስከበርና ሕጋዊነትን ለማስፈን በመንግሥት ይቋቋማሉ፡፡ ሕግን ካለአድልኦ ማስከበር በአገሪቱ የተቋቋሙ የሕግ ተርጓሚና አስፈጻሚ/አስከባሪ የመንግሥት አካላት ዓቢይ ተግባር ነው፡፡ ማንኛቸውም የተጻፉ ሕጎችና በኅብረተሰቡ የተለመዱ ያልተጻፉ ሕጎች ሲጣሱ በሁለት መንገዶች ዳኝነት ሲሰጥባቸው ኖረዋል ሽምግልና (በባህላዊ ዳኝነት) እና በዳኞች (በመንግሥት ፍርድ ቤቶች)፡፡ ባህላዊ ዳኝነቱ በገጠር አካባቢዎች ሽምግልናን ፊታ’ውራሪ በማድረግ፣ በተለያዩ ደም-አድርቅ በሆኑ እንደ አውጫጭኝ’ና ሌባ ሻይ በመሳሰሉት ወንጀል ፈጻሚዎችን መርምሮ የማውጣጣት ተግባራት፣ አስተዋጽዖ ሲያደርግ የነበረና ያለ ባህላዊ እሴት ነው፡፡
ሕዝብ እንደ አግባቡ በመንግሥት ሕግ ተርጓሚ ተቋማት (ፍርድ ቤቶች)፣ አስፈጻሚ/አስከባሪ አካሎችና (ፖሊስ፣ ደህንነት፣…) ‹‹በባህላዊ ዳኝነት›› (ሽምግልና) እስከዛሬም እየተገለገለ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ሕግን በማስከበር ረገድ ሕዝብ በየትኛው ዳኝነት (በሽምግልና ወይስ በመንግሥት ፍርድ ቤቶች) ላይ የበለጠ ይመካል የሚለው ሐሰብ በእጅጉ የሚለያይ በመሆኑ ጥናት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በርካቶች፣ በመንግሥት ሕግ አስፈጻሚዎችና ሕግ ተርጓሚዎች ላይ ብዙ እምነት ያላቸው አይመስልም፡፡ ለምን? በሁለቱም የዳኝነት አሰጣጥ ውስጥ በእጅጉ የተወሳሰቡ ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ ችግር አለ፡፡ ያንን ማጥራት ነው፡፡
በተጻፉ ሕጎች ላይ ተመሥርተው የሚከናወኑ ዳኝነቶች የሕግ ትምህርትን ይሻሉ፡፡ ካለ ሕግ ዕውቀት በፍርድ ቤቶች ውስጥ ሕግን መተርጎም (ዳኝነት) አይቻልም፡፡ ይህ አንዱ እውነት ነው፡፡
በሽምግልና መዳኘትም እንዲሁ የራሱ የሆኑ ባህርያት ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ሽማግሌዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚኖሩ በዕድሜና በማስተዋል (በዕውቀትም) አንጋፋ የሆኑ ተዓማኒ ሰዎች ናቸው እንጂ፣ በተጻፉ ሕጎች ላይ ዕውቀት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ሽምግልና (በሽማግሌዎች የሚሰጥ ዳኝነት) በተጻፉ ሕጎች ላይ ሳይሆን፣ በኅብረተሰቡ የሞራል ልዕልና፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ የመልካም አስተሳሰብ (ዕርቅ) ዕሴቶች ላይ ይመረኮዛል፡፡ በሌላ በኩል የሽምግልና ሥራ ለችግሮች ቀጥተኛ መፍትሔን መሻት ብቻ ሳይሆን፣ በዳይንና ተበዳይን ወይም ሁለት ባላጋራዎችን ማቀራረብና ማወያየት ሊሆን ይችላል፡፡
ባህላዊ ዳኝነት (ሽምግልና) እንደ ማኅበረሰቡ የአኗኗርና የአመለካከት ደረጃ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔ በመስጠት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ በሁሉም ሥፍራ (በሁሉም ችግሮች ዙሪያ) ሽምግልናን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ማየት ግን ይጠቅማል? ሽምግልናን (‹‹ባህላዊ ዳኝነት››) እና ‹‹ሕጋዊ ዳኝነት›› (በሕግ አግባብ የሚዳኝ ዳኝነትን) በንጽጽር ለማመልከት ልሞክር፡፡
‹‹ባህላዊ ዳኝነት›› አይቶ ማለፍን እንደ አንድ የመፍትሔ አካል አድርጎ ይወስዳል፡፡ ‹‹አይቶ ማለፍ››፣ ባህላዊና የመልካም ባህርይ ማሳያ ተደርጎ በአገሪቱ ውስጥ ተግባር ላይ ሲውል የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ አይቶ ማለፍ መጥፎም ጥሩም ጎኖች ሊኖሩት ይችላል፡፡ አይቶ ማለፍ ጎጂ መሆኑን በመረዳትና ወንጀሎች እንዳይደበቁ ካለው ግፊት ጭምር ይመስለኛል አውጫጭኝና ሌባ ሻይን የመሳሰሉ ባህላዊ የወንጀል ምርመራዎች አስፈላጊ በመሆን ሲሠራባቸው የቆዩት፡፡
‹‹ሕጋዊ ዳኝነት›› (በሕግ አግባብ የሚዳኝ ዳኝነት) ደግሞ ጥፋትን አይቶ ሕግን ለሚተረጉሙና ለሚያስፈጽሙ/ለሚያስከብሩ አካላት (ለፖሊስና ለፍርድ ቤቶች) ማቅረብን ያስቀድማል፡፡ ሕግ፣ ማንም ይሁን፣ አጥፊን አይቶ አያልፍም፡፡
‹‹ባህላዊና›› ‹‹ሕጋዊ›› ዳኝነቶች የሚቃረኑበትና የሚስማሙበት ሁኔታዎች አሉ፡፡
‹‹ሕጋዊ ዳኝነት››፣ አንድ ሕጋዊ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጸም ያንን የሕግ መጣስ (ጣ ይጠብቃል) ሊዳኙ በተሰየሙ ዳኞች አማካኝነት ጉዳዩ ተጣርቶ ድርጊቱን የፈጸመው ሰው በሕግ በተደነገገው መሠረት ቅጣቱን/እርምቱን እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ ዳኛው ይዳኛል (ዳ ይላላል)፡፡
ባህላዊ ዳኝነት ግን ያልተገባ ድርጊት በፈጸመው ሰውና ድርጊቱ በተፈጸመበት ሰው መካከል ጣልቃ ገብቶ፣ ሌላ ማንም የሕግ አስፈጻሚ/አስከባሪ (ፖሊስ) ሆነ ዳኛ ሳይሳተፉበት ‹‹አብሮ በመኖር ባህላዊ እሴት›› አማካይነት በተፈጠሩ ‹‹ስምምነቶች/ጫናዎች›› (ይሉኝታ፣ ሃይማኖት፣ ዝምድና፣ መከባበር፣ ጉርብትና፣ ‹‹ማግባቢያ ቃላት››፣ ወዘተ) በደልን መተውና ‹‹መታረቅን›› ያበረታታል፡፡ ‹‹አንተም ተው፣ አንቺም ተይ›› በሚል የሰፈር ሽማግሌ፣ ጓደኛ፣ ዘመድ፣…ጥፋት አድራሹና ጉዳት የደረሰበት ሰው/ቡድን ይዳኛሉ (ዳ ይጠብቃል)፡፡ ዳኝነቱ አጥፊውን በተገቢው መንገድ የሚቀጣ፣ ጥፋት የተፈጸመበትንም ሰው ተገቢውን ካሳ (እርካታ) ሊያገኝ በሚችልበት መልኩ የሚዳኝ ነው በማለት ማመን ይቻል ይሆን?
‹‹ከሕጋዊ ዳኝነት›› ይልቅ ‹‹ባህላዊ ዳኝነት›› ጥሩ ነው በማለት በጥቅሉ ደግፈው የሚቆሙለት ሰዎች ቀላል እንዳልሆኑ አውቃለሁ፡፡ ባህላዊ ዳኝነት (ሽምግልና) አጥፊው በቀላል እንዲታለፍ የማግባባት ሥራን ይሠራል፡፡ ‹‹ነግ በእኔ ነው›› የሚል ባህላዊ እሴት በማኅበረሰቡ ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኝ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሞራላዊና የመተዛዘን ባህል የጎላበት ሒደት አለው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ‹‹ነግ በእኔ›› ሕጋዊነትን (በሕግ አግባብ መዳኘትን) ያጠናክራል ብሎ ማሰብ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡
ዕርቅና ይቅር ባይነት መልካም ባህላዊ እሴቶች መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ ዋናው ስጋቴ ‹‹ነግ በእኔ›› ውስጥ የተጠቂው ግለ-ሰብ ጉዳት ስለሚያይል ነው፡፡ አጥቂውን የሚያስተምር ሚዛናዊ ቅጣት ሊኖር ይገባል፡፡ ‹‹ባህላዊ ዳኝነት›› (ሽምግልና) አጥፊን ሚዛናዊ ቅጣት በመስጠት የማስተማር ኃይሉ ደካማ ይመስለኛል፡፡ የቅጣት ደረጃና መጠን ስለሌለው፣ ተበዳይ የዕርቅ ሒደቱን በተፅዕኖ የተቀበለ እንጂ፣ ያልተካሰ ሊመስለው ይችላል፡፡ በይሉኝ በመታመቁ ይሄ ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ነግ በእኔ›› የሚለው አባባል ሐዘኔታን ያቀፈ የመረዳዳት እሴት አካል ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ፣ ከላይ ለሽምግልና ከተገለጸው ዕሳቤ ጋር አንድ አድርጋችሁ እንዳትወስዱብኝ ማሳወቅ እሻለሁ፡፡ ‹‹ነግ በእኔ›› ራስን በሌላው ቦታ አድርጎ መመልከትን የሚያጎላ የሞራል ቅርስ ያለው የአገራችን እሴት ነው፡፡
‹‹ባህላዊ ዳኝነት›› እና ‹‹ሕጋዊ ዳኝነት›› ሁለቱም የየራሳቸው ጥንካሬና ድክመት (ያለመመቸት) አላቸው፡፡ የባህላዊ ‹‹ዳኝነት›› ጥንካሬዎችና ድክመቶች ምን ምን ናቸው? ‹‹የሕጋዊ ዳኝነትስ?›› ሕጋዊነትን ለማስከበር የትኛው የበለጠ ይጠቅማል? ሁለቱንም እንደ አግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሁኔታዎችስ ምን ምን ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ መመለስ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃር የሁለቱን ‹‹ዳኝነቶች›› ጥቅምና ጉዳት በአጭሩ ለማቅረብና ሕጋዊነትን ይበልጥ ለማጠንከር መወሰድ ስላለባቸው ዕርምጃዎች ወደ መጠቆም ላምራ፡፡
ሀ. ‹‹ባህላዊ ዳኝነት››/ (‹‹ሽምግልና››)
‹‹ባህላዊ ዳኝነት›› ሕጋዊ ዳኝነትን በማገዝም ሆነ በመተካት የማይናቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የኖረ የአገራችን መልካም እሴት ነው፡፡ እኔ ‹‹ባህላዊ ዳኝነት›› (‹‹ሽምግልና››) የምለው፣ ከቀደሙ አባቶቻችን ጀምሮ ሲወርድ ሲወራረድ የቀጠለውንና ባልተጻፈ ሕግ ላይ ተመሥርቶ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ዕርቅና ሰላም እንዲወርድ በልማድ የሚከናወነውን ‹‹ዳኝነት›› (‹‹ሽምግልና››) ነው፡፡ የማስታረቅና የይቅር ባይነት ባህሎች የአገሪቱ መልካም እሴቶች ናቸው፡፡ ‹ዋሽቶ ማስታረቅ›› እንጂ ማጣላት እንደ ነውር የሚታይበት የማኅበረሰብ እሴት ለረዥም ዘመናት በተግባር ላይ እየዋለ ከእኛ ዘመን ደርሷል፡፡ ባህሉ በገጠርም በከተማም የሚገኝ ሲሆን፣ በአብዛኛው ግን በገጠር ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ ሲሠራበት የቆየ፣ አሁንም የሚገኝ ዕርቅን የመመሥረቻ መንገድ ነው፡፡ ሽምግልና የሚሰየሙት ሰዎች ግን በዕድሜ ከፍ ያሉ፣ በማስተዋል የበሰሉ፣ በአዎንታዊነትና በጥሩ ሥነ-ምግባራቸው የሚከበሩቱ ናቸው፡፡ ከሕጋዊ ዳኝነት (ፍርድ ቤቶች) ይልቅ ባህላዊ ዳኝነት (‹‹ሽምግልና››) የሚመረጥባቸው መንገዶች በርካታ ናቸው፡-
- የተጻፉ ሕጎችንና የሕግ አስፈጻሚዎች (ፖሊሶች) መኖርን (ጣልቃ ገብነትን) አይጠይቅም፣
- የፍርድ ተቋማትን፣ የዳኞችን መሰየምና የሕግ ጠበቆችን ማቆም አይጠይቅም፣
- በመንግሥት የተሾሙ ዳኞች ወደ ሚገኙበት ሥፍራ በመጓዝም ሆነ ጠበቃን በማፈላለግ የሚባክን ጊዜ አይኖርም፣
- ጠበቃን በማቆም ሊኖር የሚችል ከፍተኛ ወጪ የለም፣
- ተበዳይ የሚዳኘው (ዳ ይጠብቃል) ጉዳዩን በሚያውቁ የኅብረተሰቡ አባላት (ሽማግሌዎች) በመሆኑ፣ በዳይ ተበዳይን ‹‹ለመርታት›› ወይም የሕግ ጠበቃው ‹‹ገቢውን ለማሳደግ›› በማሰብ የሚፈጽመው ‹‹ፍርድ የማጓተት›› ጥረት አይገጥምም፣
- ክስን ለመርታት ሲባል በሚደረግ ረዥም ሙግት፣ የበዳይና የተበዳይ ሚስጥር እንዲባክንና ማንም እንዲያውቀው አይሆንም፡፡ አብረው በሚኖሩ ነዋሪዎች ተመስክሮ በሚያውቋቸው ሽማግሌዎች ዳኝነቱ በዚያው በሚኖሩበት ሥፍራ ይቋጫል፣
- በተጠራቀሙ ወዝፍ ጉዳዮች ሳቢያ ጉዳዩ/ሽምግልናው አይጓተትም፣
- ‹ባህላዊ ዳኝነት›› (‹‹ሽምግልና››) የባህላዊ አብሮ የመኖር እሴቶች ላይ (በተለይም ሃይማኖትን፣ ባህልን፣ ዝምድናን፣ ጉርብትናን፣ ሽምግልናን፣ ወዘተ) መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ ዳኝነቱ ከተከናወነና ዕርቅ ከወረደ በኋላ ፍርድ ተዛብቶብኛል በማለት ለበቀል የሚያነሳሳ ስሜት በእጅጉ የቀነሰ ይሆናል፣
- ‹‹የባህላዊ ዳኝነት›› እንደየ ብሔረሰቡ ባህል፣ ሃይማኖት፣ የሽምግልና ሥርዓት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣…ወዘተ ሊለያይ ይችላል፡፡ በ‹‹ባህላዊ ዳኝነት›› አንድ ወጥ የዳኝነት ብይን መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደ ጉዳዩ አግባብ የሚለያይና የበዳይን፣ የተበዳይንና እነሱም የሚገኙበትን ኅብረተሰብ ተጨባጭ ሁኔታዎችና ባህላዊ እሴቶችን የሚያገናዝብ ጭምር ነው፡፡ አንዳንድ ሥፍራ የሕግ ዕውቀት ያላቸው ሽማግሌዎችም ጭምር ሊሳተፉበት ይችላሉ፡፡
- ሽምግልና፣ በሁለት ግለ-ሰቦች መካከል ለተፈጠረ አለመግባባት መፍትሔ የሚያስገኝ ቢሆንም፣ ‹‹ከፍርድ ቤቶች ሕጋዊ ዳኝነት›› ይልቅ በቡድኖችና በብሔረሰቦች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን (ፖለቲካዊ ያልሆኑትን) በማስታረቅ ለአገር ሰላም የሚያበረክተው ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቱ የጎላና ፍቱን መሆኑ በታሪክ የተመዘገበ ነው፡፡
ለ. ‹‹ሕጋዊ ዳኝነት›› (በፍርድ ቤት በዳኞች የሚሰጥ ዳኝነት)
‹‹ሕጋዊ ዳኝነት›› (በፍርድ ቤት ተቋማት የሚከናወነው) በተጻፉ ሕጎች ላይ የተመረኮዘ ዳኝነትን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ ከመንግሥት የላዕላይና የታህታይ መዋቅር እውን መሆንና፣ ሕግን ከማስፈጸም የአስተዳደር ሥልት ጋር እያደገ የመጣ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ሕግን ተላልፎ የተገኘ ግለሰብም ይሁን ቡድን የሚዳኝበት (ዳ ይጠብቃል) አሠራር በሕግ አግባብ የተደነገገ አካሄድ አለው፡፡ ለአንድ ዓይነት የሕግ መተላለፍ (ጥፋት) የተለያየ የፍርድ አካሄድ (ብይን/ዳኝነት) አይኖርም ማለት ይሆናል፡፡ በደል የደረሰበት ግለሰብ ወይም ቡድንም ቢሆን በሕግ በተደነገገ ዳኝነት ፍትሕን ማግኘቱን ለማረጋገጥ በሕጋዊ መንገድ ዳኝነትን ወደ ሚያገኝበት ሥፍራ (የፍርድ ቤት/ተቋም) ቀርቦ በግሉ ወይም በጠበቃ አማካይነት በደሉን በሕግ አግባብ እንዲያቀርብ የሕግ ድጋፍ አለው (ሕግም ያስገድደዋል – ለተበዳዩም ለሕጉም ሲባል)፡፡
ሕጎች ሲጻፉ የኅብረተ-ሰቡን ሥነ-ልቡናዊ ደረጃና አኗኗር ያጤኑና፣ የአገሪቱንም በሕግ ላይ ተመርኩዞ የማስተዳደር ብቃትን፣ የግልና የጋራ ሰላምን በማስከበር ላይ የተመረኮዙ እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡ ሕግ ዘመናዊና ወቅታዊ ነው፡፡ ከባህላዊ ዳኝነት በቅርፅም በይዘትም ይለያል፡፡ ከዚህ አንፃር ‹‹ሕጋዊ ዳኝነት›› ‹‹ከባህላዊ ዳኝነት›› የሚለይባቸውንና የሚመሳሰልባቸውን አንዳንድ ጉዳዮች ቀጥሎ ለማሳየት ልሞክር፡-
- ‹‹ሕጋዊ ዳኝነት›› አካሄዱና አፈጻጸሙ በተጻፉ ሕግጋት፣ ሕግ አስተርጓሚ አካላት (ዓቃቤ ሕግ፣ ዳኞች፣…)፣ እና በሕግ አስከባሪ/አስፈጻሚ ኃይሎች (ፖሊስ፣ ደኅንነት፣…) መዋቅሮች እየታገዘ የሚከናወን ነው፣
- አንድ የተጻፈ ሕግ በይዘቱ የተወሳሰበ ሊሆን ስለሚችል፣ የሕግ ዕውቀት የሌለው ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን ሊተረጉመው አይችልም፡፡ በመሆኑም በሕግ ለመዳኘት (ዳ እንደ አግባቡ ማጥበቅና ማላለት) ዳኝነት ሰጪውም (ዳኛው) ይሁን ተቀባዩ (የከሳሽ ወይም የተከሳሽ ጠበቃዎች) የሕግ ዕውቀት (ሙያ) ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይሁንና ዳኝነትን የሚቀበሉቱ ክፍሎች (ከሳሽና ተከሳሾች በአብዛኛው) የሕግ ዕውቀት ስለማይኖራቸው በሕግ ባለሙያ (ጠበቃ) እንዲወከሉና ጉዳያቸውን እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡
- ሕጋዊ ዳኝነት በቀጥታ የሚጠቀመው ሕግንና የፍትሕ አካላትን (ሕግ ተርጓሚዎችንና አስፈጻሚዎቸን) በመሆኑ፣ ውሳኔዎቹም በሕግ አግባብ ተበዳይን የሚክሱና በዳይን የሚቀጡ ስለሚሆኑ፣ አንድ አገር ሕጋዊነትን እንድታስከብር ተቀዳሚ ምሰሶ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ዜጎች ሕግን እንዲያከብሩና በሕግም እንዲመኩ መንገድን ይጠርጋል፡፡
ሕግ በአግባቡ ከተተረጎመና ሕጋዊነትም በትክክል ተግባራዊ ሊሆን ከቻለ፣ ለሰላም፣ ለአገር ዕድገትም ሆነ ለሰብዓዊ መብት መከበር ወሳኝ ሚና አለው፡፡
- ለሕግ ጥብቅና መቆም (የሕግ ጠበቃ) አስፈላጊ የሆነ ሙያ ቢሆንም፣ ሊቆምለት እንደሚሞክረው የተወሳሰበ ሕግ ሁሉ ጠበቃውም የተወሳሰበ ባህርይ ያለው ወደ መሆን አዝማሚያ ሊያመራ ይችላል፡፡ ጠበቃ የሕግ ባለሙያ እንደመሆኑ የሚተዳደረው ከጥብቅና በሚያገኘው ገቢ ነውና፣ ገቢው የሚዳብርበትን ሒደት ማጤኑ የማይቀር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሁልጊዜም ጥብቅና የሚቆምለት ሰው/ቡድን እንዲያሸንፍለት ይሠራል፡፡ ብዙውን ጊዜ ‹‹አሸናፊ›› ከሆነ ብዙ ደንበኞችን ያገኛል፡፡ በዝናው ሳቢያም የሚከፈለው የገንዘብ መጠን እያደገለት ይሄዳል፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ጊዜ ወደ ፍትሕ ሸንጎ (ፍርድ ቤት) ይዞ የሚቀርበው ጉዳይ ‹‹አሸናፊ›› እንዲሆንለት የማያደርገው ጥረት አይኖርም ተብሎ ይታሰባል (ዳኞችን በተለያዩ አቀራረቦች በማነሁለል ጭምር)፡፡ ይህ በራሱ ሁለት መስመሮችን እንዲከተል የሚገፋፋው ሊሆን ይችላል፡፡
አንደኛው የእንጀራ መንገድ (Business) ነው፡፡ የእንጀራን መንገድ ብቻ በመከተል፣ በተገኘ መረጃ (ሐሰትም ይሁን እውነት) ‹‹ሕጋዊ ክርክርን›› ወደ ማሸነፍ እንዲያዘነብል ሊያደርገው ይችላል፡፡ ይህ ጉዳይ በመላው ዓለም የሚታይ የጠበቆችና የዳኝነት ‹‹ድክመት›› ነው፡፡
ሁለተኛው መንገድ፣ ሕግ ለቆመለት መሠረታዊ ዓላማ ብቻ ለመሥራት (ለእውነት መቆም) በሕሊና መወሰንን ይጠይቃል፡፡ በተጠቀሱት ሁለት ምክንያቶች ጥብቅና መቆምም ሆነ ጠበቃን ማቆም ከባድ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡
በአመዛኙ ‹‹ባህላዊ ዳኝነት››/‹‹ሽምግልና›› ከእነዚህ ሁኔታዎች ‹‹የጠራ›› ነው፡፡ ምናልባትም ‹‹ባህላዊ ዳኝነት›› ተመራጭ የሚሆነው በእነዚህና አጠቃላይ ሰላምን ለአገር ለማምጣት ካለው እሴት አኳያ ሊሆን ይችላል በማለት ማመን ይቻላል፡፡
‹‹ባህላዊ ዳኝነት ወይም ሽምግልና››፣ ሲያበረክት የኖረው ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከሕጋዊ ዳኝነት አንፃር የሚኖረው ጥንካሬ ቢጠናና ለሕጋዊነት መከበር ጉልህ አስተዋጽኦን የሚያበረክትበት ሁኔታ ቢታይ መልካም መሆኑን አምናለሁ፡፡ ተጠንቶ ያለ ይኖር ይሆን?
ባህላዊ ዳኝነት/ሽምግልና ለተጻፉ ሕጎች ተፈጻሚነትና ሕጎችን የማስፈጸም ብቃትን የሚገዳደር አዝማሚያ ሊኖረው ይችላል ብዬ ባምንም፣ ለአንድ አገር ‹‹ሕጋዊና ባህላዊ የዳኝነት ስልቶች›› አስፈላጊዎች መሆናቸው እሙን ነው፡፡ እንደ ኅብረተ-ሰቡ የኢኮኖሚ፣ የትምህርት (አስተሳሰብ/አመለካከት)፣ የባህል፣ ወዘተ ዕድገት አንዱ ሌላውን እያገዙ እስከተወሰነ የአገሪቱ የዕድገት ደረጃ ድረስ ሊዘልቁ እንደሚችሉም እገምታለሁ፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ባህላዊ ዳኝነት እየተስፋፋ ቢሄድ ለአገሪቱ ሕጋዊነት መስፈን አዎንታዊ ወይስ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታል? የሚለውን ተወያይቶ የሽምግልናን (የባህላዊ ዳኝነትን) መጠኑንና ተፅዕኖውን ለመገምገምና ለሕጋዊነት መጎልበትና ለአገር ሰላም አስተዋጽኦው ከፍ እንዲል ማድረግ ወሳኝ ይመስለኛል፡፡
እንደ ሕዝቡ ባህል፣ የሃይማኖት መሠረትና የፖለቲካ ስሪት የአገር ሰላም መከበር ላይ ሽምግልና ሊጫወት የሚችለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ በባህላዊ ዳኝነት ሁሉም ጉዳይ እየተዳኘ አገር ሰላም ቢሆን ደስታውን አልችለውም፡፡ ሦስት አበይት ችግሮች ግን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
አንደኛው፣ ፖለቲካ የፈጠራቸው ችግሮች ሁሉ በሽምግልና እንዲፈቱለት የሚፈልግና ለፖለቲካ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔን ለመስጠት ያልተዘጋጀ የፖለቲካ ኃይል ሊኖር መቻል ነው፡፡
ሁለተኛው፣ ሽምግልናን አቃልሎ የሚመለከት ምክንያታዊነት የጎደለው በሶሻል ሚዲያ ዳኝነት የተለከፈ ግልብ ትውልድ መኖር ነው፡፡
ሦስተኛው፣ ሽማግሌዎች ራሳቸው በፖለቲካ ተፅዕኖ ሥር ሊወድቁና ሽምግልናን ተዓማኒነት ሊያሳጡት የመቻላቸው ዕድል ሰፊ መሆን ነው፡፡ ተዓማኒነትን ያጣ ሽምግልና እንኳን ሁለት ደመኛ ወገኖችን ሊያስታርቅ፣ ማንንም (እርስ በእርስ እንኳን) ማቀራረብ የሚችል አይመስለኝም፡፡
ሁሉም ነገር በሽምግልና ዕልባት ቢያገኝ ምንኛ መታደል ነበር? የጥንት አባቶቻችን ምን ጥበብ ቢኖራቸው ነው በባላጋራዎች መካከል የፈሰሰን ደም ሲያደርቁና አብሮ መኖርን ሲያጎለብቱ የኖሩት? ሁሌም ይደንቀኛል፡፡ ዛሬ ላይ፣ ሥጋት አድሮብኝ ለተጻፈ ሕግ መተግበር (ለሕጋዊነት) ባደላ በፍፁም አትፍረዱብኝ፡፡ ሕግ አንድ ወቅት ላይ ምስክርና ፈራጅ ሊሆን ይችላል በማለት ስለማስብም ጭምር ነው ለሕግ በአግባቡ መተግበር ማድላቴ፡፡ ለመሆኑ ከሕጋዊነት አንፃር የባህላዊ ዳኝነት/ሽምግልና ሕጋዊ ተቀባይነትስ እስከምን ድረስ ይሆን? አቅሙ ያላችሁ ወጣት የትውልዱ አባላት አጥኑት (የማስተርስ ወይም የዶክትሬት ማሟያ ጽሑፍ ሊሆናችሁ የሚችል ሐሳብ ነው)፡፡ ረጋ በማለት አብላሉት፡፡ ራሳችሁንም አብራችሁ አጥኑት፡፡
ሰላም!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡