
በዶሮ፣ እንቁላል ወተትና ሥጋ ልማት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል የተባለው 14ኛው የኢትዮ የዶሮ ዕርባታና አሥረኛው የእንስሳት
ኤክስፖና ዓውደ ርዕይ ከጥቅምት 20 እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
የትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግና ፋርሚንግ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቡኑ አንዳርጌ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በዶሮ ዕርባታ መስክ ኤክስፖ መዘጋጀቱ በዘርፉ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲተዋወቁ በማድረግ፣ የዕውቀት ሽግግር በመፍጠር፣ አዳዲስ ዝርያዎችን በማስተዋወቅና የገበያ ትስስር እንዲኖር በማድረግ በኩል የሚኖረው ጥቅም የጎላ ነው፡፡


በዶሮ ዕርባታ ዘርፍ የሚሰማሩ ግለሰቦች ቁጥር በየዓመቱ በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በዘርፉ ይታዩ የነበሩ የዕውቀትና የግንዛቤ ክፍተቶችም እየተሻሻሉና እየተቀረፉ ያሉ መሆናቸው ሲታይ ለዘርፉ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ያመላክታል ብለዋል፡፡
‹‹በዶሮ ዕርባታ ዙሪያ የመኖ አቅርቦትና በሽታ ፈታኝ ችግሮች ናቸው›› የሚሉት አቡኑ (ዶ/ር)፣ በተለይ የመኖ ጥሬ ዕቃ ዋጋ ዕለት ከዕለት መጨመር ጋር ተያይዞ ለአርቢዎች ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን፣ 90 በመቶ ለመኖ ግብዓት የሚያገለግሉት የአኩሪ አተርና የበቆሎ ምርት በመወደዳቸው ምክንያት የእንቁላል ዋጋ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡
የዶሮ በሽታ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የዶሮ አርቢዎች ትልቅ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ለበሽታው እንደ መንስዔ የሚጠቀሱትም የባዮ ሴኩሪቲና የማኔጅመንት ችግሮች ናቸው፡፡ የባዮ ሴክዩሪቲ ችግር ሲባል፣ ሁሉም አርቢዎች ተመሳሳይ ዕውቀት የሌላቸው በመሆኑ ዶሮዎችን በመከተብ በኩል የሚታይ ክፍተት ነው፡፡


From The Reporter Magazine
ይህም ለዶሮዎች ሥነ ድህነታዊ ሕይወታቸው ካለመጠንቀቅና ፋርሙን በሚገባ ካለመቆጣጠር የተነሳ በሽታው እንዲስፋፋ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ዶሮ አርቢዎች ስለሚያካሂዱት ዕርባታ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በዚህ ዙሪያም የግብርና ሚኒስቴርና የዶሮ አርቢዎች ማኅበር ፖሊሲ በመቅረፅና ደንብ በማዘጋጀት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል፡፡
አቡኑ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የዶሮ በሽታ በወረርሽኝ መልክ በከፍተኛ ደረጃ ሊነሳ እንደሚችል የሚያሳዩ አመላካች ነገሮች አሉ፡፡ በባለፉት ጥቂት ወራት እንኳ ትንሽ ቁጥር የማይባሉ ዶሮ አርቢዎች በበሽታ ምክንያት ከፍ ያለ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
በቀጣይም በተለይ በሸገር አስተዳደር በክላስተር ደረጃ የተሠሩ የዶሮ ዕርባታ ሼዶች ሳይንሱን የተከተሉ ባለመሆናቸው፣ ተቀራርበው በመሠራታቸውና በዘርፉ ላይም እንዲሰማሩ የተደረጉ ግለሰቦች ስለዶሮ እርባታ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ባለመደረጉ በሽታው ዳግም እንዲነሳ መንስዔ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉም ሥጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡
From The Reporter Magazine
በዶሮ እርባታ ዘርፍ በመሰማራት ከ8ሺሕ በላይ ዶሮዎችን እያረቡ የሚገኙት አቶ ማንደፍሮ ሽፈራው እንደሚገልጹት ደግሞ፣ መንግሥት ለዘርፉ ልማትና ዕድገት ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በመድኃኒት አቅርቦት፣ በገበያ ትስስርና ከቴክኖሎጂ አንፃር ከትናንት ዛሬ ብዙ ለውጦችና መሻሻሎችም አሉ፡፡
ሆኖም ዛሬም የዶሮም ሆነ የእንቁላል ዋጋ ውድ ነው፡፡ አቶ ማንደፍሮ እንደ ምክንያት የሚያነሱትም፣ የመኖ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡ የዶሮ ዋጋም እንዲሁ ጭማሪ ማሳየትን ነው፡፡
አንዳንድ ዶሮ አርቢዎች በዶሮ ዕርባታ ዘርፍ ምንም ዓይነት ዕውቀት ሳይኖራቸው በዘርፉ በመሰማራታቸው ለበሽታው መስፋፋት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ እነኚህ አርቢዎች ለዶሮ የሚያስፈልጉ እንደ ክትባት፣ ቫይታሚንና ንጽህና የመሳሰሉትን በአግባቡ የማያሟሉና የማይከታተሉ በመሆኑ በሽታው በወረርሽኝ መልክ እንዲነሳ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የዕንቁላል ዋጋ በገበያ ላይ ባልተለመደ መልክ እንዲወደድ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የመኖ፣ የዕንቁላል ዶሮና የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር ነው የሚሉት አቶ ማንደፍሮ፣ ከእነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች ጋር በተገናኘ የእንቁላል ዋጋ ቢጨምር ብዙም የሚገርም አለመሆኑን፣ ዋጋው እንዲቀንስና ማኅበረሰቡም ምርቱን በቀላሉ እንዲያገኝ ከተፈለገ መንግሥት በመኖ ምርት ላይ የጣለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ መልሶ ሊያጤን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
‹‹የዶሮ ዕርባታ ዘርፍ ዕድገት እያሳየ ይገኛል፡፡ የእንቁላል ምርት፣ የጫጩት ሥርጭትና የሥጋ አቅርቦቱም በመጨመር ላይ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም የዶሮ ምርቶችን የመመገብ ባህሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፤›› ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዝናው ጸሐይነህ ናቸው፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ፣ ኢትዮጵያ ለዶሮ ሀብት ልማት ምቹ ነች፡፡ ነገር ግን የዘርፉ ዕድገት ሲታይ በዚህ ደረጃ ልክ የደረሰ አይደለም፡፡ ለዚህም የዶሮ መኖ አቅርቦትና ጥራት ውስንነት፣ ለዶሮ መኖ ግብዓት የሚያገለግሉ እንደ በቆሎና አኩሪ አተርን የመሳሰሉ ጥሬ ዕቃዎች መወደድ፣ ለመኖ ማቀነባበሪያ የሚውሉ ሚኒራሎችና ቫይታሚኖች ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው ከዶላር መጨመር ጋር ተያይዞ ዋጋቸው ከፍተኛ መሆንና በእርባታው ዘርፍ ቁጥጥር አለመኖር ለችግሮች በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ሌላው የዘርፉ ከፍተኛ ችግር በሽታ ነው፡፡ ይህም በርካታ የዶሮ መንጋዎችን በማጥቃት ከፍተኛ ኪሳራ በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የበሽታ የቁጥጥር ሥርዓታችን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ እንደሆነ፣ መንግሥት ለዶሮ አርቢዎች ሼዶችን እየገነባና እያስተላለፈ የሚገኝበት ሒደት የዶሮ እርባታ ባዮ ሴኩሪቲ ደረጃን ያሟላ አለመሆኑ ለበሽታው መስፋፋት መንስዔ በመሆን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአንድ ቀን ጫጩት ሥርጭት ላይ እጥረት በመኖሩ፣ እንቁላል ጣይና የሥጋ ዶሮ ለማርባት ፍላጎት ባላቸው አርቢዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን በማስታወስም፣ አርቢዎች የአንድ ቀን ጫጩት ለማግኘት እስከ ስድስት ወራት ወረፋ በመጠበቅ ላይ ናቸው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ጫጩት እያስፈለፈሉ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ዝናው፣ የአንድ ቀን ጫጩት አቅርቦትን በተመለከተ ፍላጎቱ አንድ ጊዜ ከፍ፣ በሌላ ወቅት ደግሞ ዝቅ ያለ ነው፡፡ ካቻምና ከጫጩት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ፍላጎቱ ዝቅ በማለቱና ጫጩት እያስፈለፈሉ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ገበያ በማጣታቸው ምክንያት በርካታ ጫጩቶችን ለመቅበርና ለማቃጠል ደርሰዋል፡፡
በዚህም የተነሳ ወደ ስምንት የሚደርሱ ድርጅቶች በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ 292 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶባቸዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ በርካታ የዶሮ አርቢዎች ወደ ገበያው ለመቀላቀል ቢፈልጉም፣ የአንድ ቀን ጫጩት ለማግኘት እየተቸገሩ ይገኛሉ፡፡ አቅራቢዎችም ችግሩ ዳግም ሊከሰት ይችላል በሚል ፍርሃት ምርታቸውን በስፋት በማቅረብ ላይ አይደሉም፡፡ ስለሆነም በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ገበያውን ፈታኝና ተለዋዋጭ እንዲሆን አድርገውታል ብለዋል፡፡
‹‹የመኖ ዋጋ መጨመርና መንግሥት በመኖ ምርት ላይ ታክስ መጣሉ የእንቁላል ዋጋ እንዲጨመር አስተዋጽኦ አበርክቷል፤›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ይህ አስተማማኝ ገበያ እንዳይኖር፣ አምራቹም በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት እንዳይገባና ለገበያ እንዳያቀርብ ያገደው በመሆኑ የእንቁላል ዋጋ ሊንር ችሏል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማኅበር በባህላዊ የዶሮ እርባታ ላይ የተሰማሩትን ሳይጨምር በአነስተኛ፣ በመካከለኛና በማቀነባበር ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ160 በላይ አባላትን ያቀፈ መሆኑን፣ በባለፈው ሳምንት መገባደጃ የተካሄደው 14ኛው የዶሮ አርቢዎች ኤክስፖ አርቢዎች፣ በዓለም አቀፍ ካሉ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲተዋወቁ፣ ከግብዓት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር እንዲገናኙና ምርታቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ በኩል ትልቅ እገዛ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በኢትዮጵያ የሚዘወተረው ባህላዊ የዶሮ እርባታ በመሆኑና ዘርፉ ደግሞ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚኖረው ድርሻ የላቀ ከመሆኑ አንፃር በዘመናዊ ደረጃ ሊስፋፋ እንደሚገባ በኤክስፖው ተጠቅሷል፡፡
ከ14 አገሮች የተውጣጡ ከመቶ በላይ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሀብት ዘርፍ ተዋናዮች፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተገኙበት ኤክስፖ በፕራና ኤቨንትስ በኩል የተዘጋጀ ነው፡፡