ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 Best and reliable news source in Ethiopia
ከተማሪዎች ማዕድ
ከመመገቢያ ክፍሉ የሚነገሩ ታሪኮች የአብዛኛውን መምህራን ዓይን በእንባ የሚያራጥቡ ናቸው፡፡ አንዳንዴም ከሕፃናት ይጠበቃል ተብለው የማይታሰቡ ድርጊቶች መታየት የመምህራንን ልብ የሚያርዱ ሆነዋል፡፡
የተማሪዎች ምገባ መጀመር የብዙዎችን ሸክም ያቀለለ፣ የተማሪዎችንም ረሃብ ያስታገሰ ቢሆንም፣ ተማሪዎች ከቤታቸው ይዘው የሚመጡት ጭንቀት ለመምህራኑም እፎይታን ነስቷል፡፡ ከቤት የከተመው ድህነት የልጆቹን አዕምሮ ተቆጣጥሮ ከትምሀርት ቤት ዘልቋል፡፡
በሰላም በር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅድመ መደበኛ (መዋዕለ ሕፃናት) መምህርቷ ብዜ ከበደ፣ በትምህርት ቤቱ የሚመገቡ ተማሪዎች ሁኔታ እንደሚያስጨንቃት ትገልጻለች፡፡ በየዕለቱ ከሕፃናቱ የምትሰማው ታሪክ እንደሚያሳዝናትም ታክላለች፡፡
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተማሪዎች ከሆኑት ሕፃናት መካከል አንዱ ቁርስ እየበሉ በነበረበት ሰዓት ያላትንም ታስታውሳለች፡፡
ተማሪዎች ቁርስ እየበሉ በነበረበት ሰዓት አንድ የቅድመ መደበኛ ተማሪ የቁርሱን ከፊል ያስቀራል፡፡ ለምን አትጨርስም ብላ ስትጠይቀው ‹ለወንድሜ እቤት ይዤለት እሄዳለሁ› ይላታል፡፡ ‹‹በወቅቱ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም›› የምትለው መምህርት ብዜ፣ በልጅነታቸው እንዲህ ዓይነት ተፅዕኖ ውስጥ መግባታቸው እንደሚያሳዝናት በዚህ አይነት ሁኔታ ትምሕርት እንዴት ይከታተላሉ በሚል እንደሚያሳስባት ትገልጻለች፡፡
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተማሪዎች ቁርስ የሚመገቡት አራት ሰዓት ላይ በመሆኑ እስከዚያ ድረስ መቆየት አቅቷቸው የሚራቡ ስለመኖራቸውም ታክላለች፡፡
ተማሪዎቹ ቤታቸው በቀን አንዴ እራታቸውን እንኳን ይበላሉ ተብሎ ቢታሰብም፣ ይህንን የማያገኙም አሉ፡፡ የአንድ ተማሪ ታሪክም እንዲሁ ነው፡፡ ጠዋት ክፍል ስትመጣ አፏ ነጭ ሆኖ ነበር፡፡ አቅምም አልነበራትም፡፡ ምን ሆነሽ ነው ተብላ ስትጠየቅ ‹‹እርቦኝ ነው እራት አልበላሁም›› ትላለች፡፡ ለቁርስ ከተዘጋጀው ከሰጧት በኋላ ልጅቷ ነቃ ብላ መጫወት ጀመረች፡፡
መምህራን ጉዳዩን ለወላጅ ለማሳወቅ እናቷን ያስጠራሉ፡፡ እናትም ‹‹ቤቴ ምግብ የለም፡፡ ልጆቼን እማበላው ስለሌለኝ ትምህርት ቤት በበሉት ያድራሉ፤›› ትላለች፡፡ ይህን የሰማችው መምህርቷ ለተወሰኑ ጊዜያት ለእናትዬዋ ምግብ እየቋጠረች ትልክ እንደነበር ነግራናለች፡፡
ቁርስ በልቶ ምሳ የማይደግም ባለበት ሁኔታ ለኢትዮጵያ ልጆች የተማሪ ምገባ መምጣቱ ‹‹እንደ መምህር የማመሠግነው ነው›› ያለችው መምህርቷ፣ ከምገባ ባሻገር የሚያሳስባት አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የሚልኩት ምግብ እንዲበሉ መሆኑ ነው፡፡ ወላጆች ሲሯሯጡ ስለሚውሉ የልጆቻቸውን ትምህርት ብዙም እንደማይከታተሉ፣ ይህ ደግሞ በተማሪዎቹ የመማር ሒደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረም ትገልጻለች፡፡
ወርልድ ቪዥን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀንን አስመልክቶ ድጋፍ በሚያደርግበት ሰላም በር ትምህርት ቤት የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ የሕፃናት ፓርላማ አባላትና አመራሮች ከመንግሥት ተወካዮች ጋር የተወያዩበትን መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡
በፍሬሕይወት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ ኢክራም ሲራጅ፣ የኢትዮጵያ የሕፃናት ፓርላማ አባልና የአዲስ አበባ የሕፃናት ፓርላማ የበጎ አድራጎትና የአካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናት፡፡
በዕለቱ የፓናል ውይይቱን የመራችው የ16 ዓመቷ ኢክራም ለሪፖርተር እንደገለጸችው፣ ከመንግሥት ሆነ ከረጂ ድርጅቶች በተለያየ መንገድ የተጀመረው የተማሪ ምገባ የምታደንቀው ነው፡፡
‹‹በተማሪና በቤተሰብ በተለይ በክልል አካባቢ ያለውን ችግር እናውቀዋለን›› ያለችው ኢክራም፣ የተማሪ ምገባ ፕሮግራምን ‹‹የተማሪዎችን ህልውና ያስቀጠለ ነው›› ስትል ትገልጸዋለች፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለች፣ የተማሪ ምገባ ተጠቃሚ እንደነበረች፣ እንደ ሕፃናት ፓርላማ አባልነቷ ከጥናትና ከተሞክሮዋ በመነሳት የተማሪዎች ምገባ በአዲስ አበባ ደረጃ በጣም ጥሩ እንደሆነ፣ በክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች ተማሪዎችን የማይመጥንና ተደራሽ እንዳልሆነ፣ ባለው ሀብትና በጀትም ሁሉንም ማዳረስ እንደማይቻል ገልጻለች፡፡
የተደራሽነትና የጥራት ችግር ቢኖርም፣ ከችግሩ ይልቅ የመጣው ለውጥ እንደሚበልጥ አክላለች፡፡
ወደ ክልል ተዘዋውራ የተማሪ ምገባውን ባታይም፣ የተለያዩ ጥናቶችንና የሚቀርቡ ሪፖርቶችን በማየት፣ ከክልል የኢትዮጵያ ሕፃናት ፓርላማ አባላት ጋር በስብሰባዎች ሲገናኙ ከሚወያዩት በመነሳት የተደራሽነት ችግር እንደሚነሳ ነግራናለች፡፡
ምገባው በመንግሥት ቢሸፈንም፣ ተማሪዎችን በቤት ውስጥም መከታተል ወሳኝ እንደሆነ በማስታወስ በልማድ ‹‹ልጅ ከበላ፣ ከጠጣና ከተማረ ምን ጎደለ›› የሚለው አመለካከት መቀየር እንዳለበት ትመክራለች፡፡
ተማሪዎች በአብዛኛው የወላጅ ዕገዛና የሚያስጠናቸው እንደማያገኙ፣ ባገኙት መድረክ ሁሉ የወላጅ ክትትልና ድጋፍ የሚያነሱት ጥያቄ መሆኑን በማስታወስም፣ ወላጆች ወደ ልጆቻቸው ቀርበው እንዲወያዩና እንዲጠይቁ ትጠቁማለች፡፡
‹‹ራሴ ተማሪ ሆኜ አውቀዋለሁ፡፡ በራሴ ነው የማጠናው፡፡ ሆኖም እናቴ አጥኚ ትለኛለች፣ ትከታተለኛለች፡፡ ሌሎች ተማሪዎች ጎበዝ ሆኑም አልሆኑ በራሳቸው ያጠናሉ፡፡ የወላጅ ክትትልና ድጋፍ ስለማያገኙም ወድቀው ይቀራሉ፤›› ብላለች፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን መመገብ መንግሥት፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ብቻቸውን የሚችሉት ባለመሆኑ፣ ዓለም አቀፍና አገር በቀል ድርጅቶች እየተተገበረ ለሚገኘው፣ የተማሪዎች ምገባ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ድጋፍ ከሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ወርልድ ቪዥን ነው፡፡
‹‹ኢነፍ›› በተባለው የሦስት ዓመት ፕሮጀክቱ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን በተለያየ መንገድ ለመድረስ እየሠራ የሚገኘው ወርልድ ቪዥን የአድቮኬሲና የውጭ ግንኙነት ተባባሪ ዳይሬክተር አቶ ካሱ ከበደ እንዳሉት፣ ወርልጅ ቪዥን ‹‹ኢነፍ›› የተሰኘ ዘመቻውን የጀመረው አምና ነው፡፡
ዘመቻውም የሕፃናትን ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለማስወገድ አልሞ የተጀመረ ዓለም አቀፍ ትግበራ ነው፡፡ ዘመቻውን በየካቲት 2016 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ድርጅቱ፣ በዘመቻው አማካይነት 3.4 ሚሊዮን ሕፃናትን በተለያዩ መንገዶች ለመድረስ አስቦ ሥራው ተጀምሯል፡፡
ከመንግሥትና አጋር አካላት ጋር በመተባበርም ሕፃናትን ለመድረስ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ወደተግባር እንዲለወጡ፣ ባሉት ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች አማካይነት ሕፃናት እንዳይራቡና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ወርልድ ቪዥን እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ካሱ ገልጸዋል፡፡
ዘመቻውን በዋነኝነት ከመንግሥት ጋር አጋር ሆኖ እየሠራ መሆኑን፣ ከአገር በቀል፣ ከዓለም አቀፍ፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከማኅበረሰብ አቀፍ ድርጅቶች ጋር እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
ሦስት ዓመት ለሚፈጀው የ‹‹ኢነፍ›› ዘመቻ 9.4 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን፣ 3.4 ሚሊዮን ሕፃናትን ለመድረስ መታቀዱንም አስታውሰዋል፡፡
በአዲስ አበባ ጥሩ የሚባል የተማሪ ምገባ ተሞክሮ መኖሩን፣ ይህ በርካታ ሕፃናትን፣ ወላጆችንና ቤተሰብን መደገፉንና ተሞክሮው ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አካባቢዎች መስፋት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
በመንግሥትና በአጋር አካላት የሚተገበረው የተማሪ ምገባ ሥርዓት ለተማሪዎች በሚፈለገው ደረጃ በመድረስ በኩል ከፍተቶች እንዳሉበት፣ የድርቅና የግጭት ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሕፃናት አገልግሎቱን ማግኘት አለባቸው ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት፣ ወርልድ ቪዥንና ሌሎች እየሠሩ ቢገኙም፣ ብቻቸውን ችግሩን መቅረፍ ስለማይችሉ ኅብረተሰቡን ማሳተፍና ለችግሩ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡
የተማሪ ምግባ ፖሊሲ ቢኖርም አተገባበሩ ላይ በርካታ ፈተናዎች ስላሉበት ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ በድርጅታቸው በኩል ካለው ችግር ጋር የሚመጣጠን በጀት ባይኖርም፣ የፀጥታ ሁኔታዎች ችግር ቢሆኑም በተገኘው መንገድ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከህጻናት ፓርላማ አባላት ጋር በነበረው ውይይቱ ትምህርት ሚኒስቴርን በመወከል የተገኙት አቶ መኳንንት ዳኘው፣ ከሕፃናት ፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የዓምናን ተሞክሮ በማንሳት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከአንድ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተለያየ መጠንና ደረጃ በተተገበረው የተማሪ ምገባ ወደ 7.5 ሚሊዮን ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከመንግሥት በጀት በተጨማሪ አብዛኞቹ ክልሎችም ከፍተኛ በጀት መድበዋል፡፡
ሆኖም የተማሪ ምገባ ወጥ ቤት፣ ማብሰያ፣ መታጠቢያ፣ መጋዘን፣ መመገቢያ አዳራሽና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች የሚያስፈልጉት መሆኑ በተለይ ወደ ክልሎች ሲሄድ በእነዚህ ዙሪያ ክፍተቶች አሉ፡፡
ፕሮግራሙ ትምህርትን፣ ጤናንና ግብርናን አቀናጅቶ መሰራት ቢጠበቅበትም፣ ተቀናጅቶ በመሥራት በኩል ክፍተት መኖሩን፣ በጀት ቢመደብም ካለው በርካታ ፍላጎት አንፃር ውስን መሆኑን በማንሳት፣ ችግሮችን ለመቅረፍ የማኅበረሰብ፣ የባለሀብቶችና የረጂ ድርጅቶች ቀጣይ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡
The post ከተማሪዎች ማዕድ first appear on ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 Best and reliable news source in Ethiopia and is written by ምሕረት ሞገስ