ፒፕል ቱ ፒፕል የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ባዘጋጀው ፕሮግራም በካንሰር ሕክምና ዙሪያ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልና ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የፒፕል ቱ ፒፕል የኢትዮጵያ ተወካይ ዘውዱ ተረፈወርቅ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ፒፕል ቱ ፒፕል 25ኛ ዓመቱን በማስመልከት ‹‹ካንሰርና የሴቶች ጤና›› በሚል የካንሰር ሕመም ላይ ትኩረት ያደረገ ኮንፍረንስ አካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ታዋቂ ሐኪሞችና ተመራማሪዎች በካንሰርና በሴቶች ጤና እንዲሁም በክሮኒክ ሕመሞች ዙሪያ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ይህም ድርጅቱ በሕክምና ትምህርት ዙሪያ በየዓመቱ ሲሰጥ የቆየውና ዘንድሮም የቀጠለ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዘውዱ (ዶ/ር)፣ ፒፕል ቱ ፒፕል ‹‹የሦስት ማዕዘን አጋርነት›› (ሪያንጉላር ፓርትነርሺፕ) በሚባል ፕሮግራሙ፣ ውጭ አገር የሚገኙ የትምህርትና የጤና ተቋማት አገር ውስጥ ከሚገኙ ተመሳሳይ ተቋማት ጋር የሦስትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር ድጋፍና ዕገዛ እንዲያገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ላለፉት ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሕክምና ትምህርትን በማሳደግና በማስፋፋት በኩል የራሱን ጉልህ አሻራ ከቀደመው ጊዜ በተሻለ ለመተግበር በ25ኛ ዓመት ምሥረታው ላይ ሁለት ፕሮግራሞችን ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
የደም ካንሰር ሕክምናና በዚሁ ዘርፍ የድኅረ ምረቃ ተከታታይ ትምህርት ለመጀመር መታቀዱን የሚናገሩት ተወካዩ፣ በውጭ አገር የሚኖሩ የፒፕል ቱ ፒፕል አባል የሆኑ ባለሙያዎች ባሉበት አገር በመሆንና ወደ አገር ቤት በመምጣት ትምህርቱን የሚሰጡ ይሆናል፡፡
ድርጅቱ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልና ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ጋር በትብብር በሚሰጠው ትምህርት፣ በተያዘው ዓመት በሄማቶሎጂ አንኮሎጂ ፌሎሺፕ ፕሮግራም ሦስት ሐኪሞችን በሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም እያሠለጠነ ይገኛል፡፡
ፒፕል ቱ ፒፕል ከዚህ ቀደም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚገኘውን የሕክምና ኮሌጅ የማጠናከር ሥራ ሲሠራ መቆየቱን የጠቀሱት ዘውዱ (ዶ/ር)፣ በሕክምና ትምህርት ዘንድ በአገሪቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተና ትርጉም ያለው ሥራ እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው ብለዋል፡፡
የኒሮሎጂ ፌሎሺፕ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ያስጀመረውና የተወሰኑ ተማሪዎችን ወደ ውጭ አገር በመውሰድ በሰብ ስፔሻሊቲ ደረጃ እንዲሠለጥኑ ያደረገው ፒፕል ቱ ፒፕል ስለመሆኑ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት ዘውዱ ተረፈወርቅ (ዶ/ር) ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ፒፕል ቱ ፒፕል የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ባከበረበት ወቅት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልና ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ በድርጅቱ የገንዘብ ድጋፍ የተቋቋመው ‹ፌሎውስ ስማርት ሩም› በድርጅቱና በሆስፒታሉ የሥራ ኃላፊዎች ጉብኝት የተደረገበት ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፒፕል ቱ ፒፕል (ፒቱፒ) በኢትዮጵያና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል የጤና እንክብካቤን፣ ልማትንና ትምህርትን ለማሻሻል የተመሠረተ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። ፒቱፒ እ.ኤ.አ. በ1999 በእናውጋው መሐሪ (ፕሮፌሰር) ተመሥርቶ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ከቀረጥ ነፃ 501(c) (3) ዕውቅና አግኝቷል። የፒቱፒ የኢትዮጵያ ፕሮግራሞች ማስተባበሪያም በአዲስ አበባ ይገኛል።
ፒቱፒ በተቋማት መካከል ድልድይ ለመፍጠር ዳያስፖራውን መሠረት አድርጎ የተቋቋመ ሲሆን፣ በምዕራባውያንና በታዳጊ አገር ተቋማት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገኙ ዳያስፖራዎች መካከል ግንኙነትን የሚፈጥርና የሚያጠናክር የሦስት ማዕዘን አጋርነት የተሰኘ ፍልስፍና እንዳለው ይናገራል።
በኢትዮጵያ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሥራትም 25 ዓመታትን አሳልፏል፡፡