በገነት ዓለሙ
ኢትዮጵያ አገራችን ውስጥ ደርግም ኢሕአዴግም ሁለቱም እኩል፣ ለዚያውም በተራ መግለጫ ሳይሆን በአዋጅና በሕገ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አቋቋምን ሲሉ እናውቃለን፡፡ ሁለቱም ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መቋቋሙን ለማስታወቅ የወጣ አዋጅ ቁጥር 2/1980››፣ እንዲሁም ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት መመሥረቱን ለማስታወቅ የወጣ አዋጅ ቁጥር 2/1987›› የሚባሉ ሕጎች አውጥተው በአዋጅ በነጋሪ ለዓለምም፣ ለኢትዮጵያም ተናግረው አሳውቀዋል፡፡ ሁለቱም ገዥ ቡድኖች ዴሞክራሲና ሪፐብሊክ አቋቋምን ቢሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ነፃ ድምፅ ኖሮት፣ ፓርቲዎች ተፍለቅልቀው ነፃና ያልተጭበረበረ ምርጫ አካሂዶ የፈቃዱ ውጤት የሆነ መንግሥት ዓይቶ አያውቅም፡፡
ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ከአዋጅ በላይ ብዙ መሠረታዊ ነገሮች ወጥውጠው የሚሠሩት ታላቅ ድልና ውጤት ነው፡፡ መብቶችና ነፃነቶች በሕግ ከመጻፋቸውም በላይ በተግባር የሚሠሩ መሆን አለባቸው፡፡ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብ፣ ተዘዋውሮ የመቀስቀስና የማደራጀት ነፃነት፣ ክርክር፣ ውይይት በርባሪና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ግምገማ፣ ትንታኔ ደርቶ ሕዝብ ከሐሳቦች መፍለቅለቅና መብላላት ልምድ ሚዛናዊና የበለፀገ ግንዛቤ ስለእያንዳንዱ ፓርቲና ተወዳዳሪ ማግኘት አለበት፡፡ የቡድኖች መንግሥታዊ ገዥነት ወይም ፓርቲ የሚባሉ የፖለቲካ ቡድኖች መንግሥታዊ ሥልጣን የሚይዙበት መንገድ ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመነጭበት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬ ኖሮ የማያውቅ አዲስ ምዕራፍ መከፈት አለበት የተባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ የተቀጣጠለው ትግል የሚለውና የጀመረውም ይህንኑ ነው፡፡
እንዲህ ያለ ሰላማዊ ትግል ጀምረናል፣ ይህንን የመሰለ ሕጋዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴና ትግል ውስጥ ገብተናል ማለት ግን መንግሥት የለንም፣ ወይም መንግሥትም ኖሮን አያውቅም ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን እውነትም እንደ ስሟ ዴሞክራሲያዊና ሪፐብሊካዊ ለማድረግ መብቶችና ነፃነቶች ዕውንና ተግባራዊ መሆን አለባቸው፡፡ የይፋና የፖለቲካ መድረኮቻችን ዥንጉርጉርና የሚጣሉ ሐሳቦችን ጭምር ከማፍራት፣ ከመፈልፈልና በጤናማነት ከማስተናገድ ጋር መተዋወቅና መላመድ አለባቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚደነግገው (አፍሪካ ኅብረት ያፀደቀው፣ የዓለም ሥልጣኔም የመረቀው) መንግሥዊ ሥልጣን የሚያዝበት ብቸኛው መንገድ ዕውን እንዲሆን ደግሞ፣ መንግሥታዊ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው መታነፅ አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ የለውጥና የሽግግር ሥራ በእርግጥም የነባር ሕጎችን የማሻሻል፣ አዳዲስ ሕጎችን የማውጣት፣ ወዘተ ተግባር ያካትታል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግም ከዚህ ጋር የሚስማማ የሕግ ማስከበር ሰላምና ፀጥታ የማረጋገጥን የመንግሥት ግዳጅ በእጅጉ ይጠይቃል፡፡ የመንግሥት የተለመደ ሕግ የማስከበር ሥራ የራሱን፣ ሕግ የማክበርን ግዴታ ጭምር ግድ ያደርጋል፡፡ የሕዝብንም የመንግሥትንም ሕግ የማስከበርና ሰላምና ፀጥታ የማስፈን ተግባር የማገዝን ግዴታ ይጠይቃል፡፡ ወጣም ወረደ ግን የትኛውም መንግሥት ሕግና ሥርዓትን ማስከበር አለበት፡፡ የየትኛውም ዘመናዊ አስተዳደር ኃላፊነት ፀጥታና ሕግ ማስከበር ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ያለ መንግሥት ወይም የአስተዳደር ዕርከን ሕዝብን ከየትኛውም ዓይነት ጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በዝንጉነትም ሆነ በሌላ ምክንያት ሳይወጣ ሲቀር ለሚደርስ ጥፋት ሊጠየቅ ይገባል የሚባለው፣ ይጠየቅ ሲባልም የምንሰማው በዚህ መሠረታዊ ምክንያት ነው፡፡
አያድርስ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ እንዲመጣ፣ አገር የቀውስና የዕልቂት ዓውድማ እንድትሆን ይህንን በምግባሩም፣ በባህርይውም፣ በንግግሩም (ሐሳብን በመግለጽ መብትና ነፃነቱ አማካይነትም) በ‹‹ፀሎቱ››ም በዝምታውም አማካይነትም እንዲመጣ የሚለማመነው፣ መከራ የሚያየው ጥቂት አይደለም እንጂ፣ የመንግሥት ዘመናዊ አስተዳደር ፀጥታና ሕግ ሊያስከብር ባልቻለባቸው ወይም በማይችልባቸው የቀውስና የዕልቂት ሥፍራዎችና አገሮች፣ በጭካኔ አስተዳደርም/በፈላጭ ቆራጭ አምባገነን መንግሥት አማካይነትም ቢሆን ፀጥታን ማግኘት ተመሥገን የሚያሰኝበት ሁኔታና ታሪክ እዚህ ጎረቤታችን ሶማሊያ ውስጥ አይተናል፡፡ ሕዝብ ሊያግዘው ይገባል የምለው ሕግ የማስከበርና ፀጥታና ሰላም የማስጠበቅ ሥራ የሚከናወነው ደግሞ የመንግሥት አውታራትን ከፓርቲ ታማኝነትና መዳፍ የማላቀቅ የማሻሻያ ሒደት ውስጥ ተሆኖ፣ በተለይም የፀጥታ ኃይሎች የሙያ ጥበባቸውንና ዕውቀታቸውን የሚፈታተኑ ብልሽቶችን ገና በማራገፍ ሒደት ውስጥ መሆናቸው ሌላም ተጨማሪና ‹‹ግራ የሚያጋባ›› ችግር አለበት፡፡ የፖለቲካ ኃይሎች ትግል ሰላማዊ ብቻ አይደለም፡፡ ጥቃት በቃል፣ ውድመት ወንጀል ሁሉ ትግል ሆኗል፡፡ የመሣሪያ ትግልም ጭምር፡፡
ዋናው ጉዳዬና መልዕክቴ የየትኛውም መንግሥት ዋነኛውና መሠረታዊው ተግባር ሕግና ሥርዓት፣ ፀጥታና ሰላም ማስከበር መሆኑን አስረግጦ ለመናገር ነው፡፡ ዴሞክራሲያችን ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የማድረግ ግዳጃችን፣ ወደ ሕገ መንግሥታዊነት የመሸጋገር ሥራችን ገለልተኛ ተቋማትን የግድ ይላል፡፡ ከየትኛውም ቡድን ፈንታ ለሕዝቡ የሚታመን፣ በሕዝብ ፈቃድ ሥር የሚኖር፣ በገለልተኛ ተቋማት ላይ የተዋቀረ አገዛዝ/አስተዳደር ይፈልጋል፡፡ ይህ በሌለበት ወይም ባልነበረ፣ ባልተገነባና ባልተሠራበት መዋቅር ላይ ዴሞክራሲን ማደላደል ይቸግራል፡፡ አሁን አነሰም በዛም እንደ ነገሩ የምናጣጥመው ዴሞክራሲ መሠረት የያዘ ዋስትና ያለው ከመንግሥት/ ባለሥልጣኖቻችን ‹‹መልካም ፈቃድ››ም፣ ከሌላ አካል ጥቃትም የተጠበቀ አይደለም፡፡ ይህ እንደነገሩ የምንለው ዴሞክራሲ አለ ሲሉት የሕልም እንጀራ፣ የለም ሲሉት አለሁ የሚል፣ አለ የሚባል ዴሞክራሲ አሁንና እስካሁን በምናውቀው መልኩ ያለው የቀድሞው አፈናና ጥርነፋ በመነሳቱና በመላላቱ እንጂ፣ የገዛ ህልውናውን አውጆና መሠረት ይዞ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ መሠረትና መደላደል ይፈልጋል፡፡ የመንግሥታዊ አውታራትን ከፓርቲ ታማኝነትና ወገናዊነት ማላቀቅን ይፈልጋል፡፡ ይህንን ዋና የለውጥ ጎዳና ዋናው መንገዳችን ብለን ባለመያዛችን፣ በሌላ አነጋገር የመንግሥትን የዚህን ጅምር ጥረት አለማገዝ ማለትም በሁለመናውም ባይሆን፣ በአብዛኛው የመንግሥትን ሕግ የማስከበር ተግባር አለማገዝ ጭምር በመሆኑ፣ ፀጥታና ሰላም ማስከበር አበሳ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡
ተወደደም ተጠላም መንግሥት ሕግ የማስከበሩን ተግባርና ግዴታውን ‹‹የሚፆመው›› አይደለም፡፡ ወይም የዛሬን እለፉኝ የሚለው ተግባር አይደለም፡፡ መንግሥትነቱን ራሱን ሳይተው የሚያወራርደው ተግባር አይደለም፡፡ ሕግ የማስከበር ተግባር፣ ወንጀል የመከላከል የመንግሥት ሥራ የፖለቲካ ትግልን በሕጋዊና በሰላማዊ ተፎካካሪነት ውስጥ መታጠሩን ማረጋገጥን ይጨምራል፡፡ የመንግሥት ሕግን የማስከበርና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ዋና ሥራና ይህንንም አቅም ማገዝ ማለትም ይህንንም ‹‹‹አቋም›› መያዝ ማለት ጭምር ነው፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖ፣ በዚህ ሁሉ ችግርና አበሳ ውስጥ ግን ሕግ የማስከበር ግዴታና ተግባር ከመንግሥት ራስና ከመንግሥት ጫንቃ አይወርድም፡፡ ደግሜ ልበለው፣ መንግሥት መንግሥትነቱን ሳይተው ሕግ የማስከበር፣ የሕዝብ ደኅንነት የመጠበቅ ሥራ፣ ሥራዬ አይደለም ሊል አይችልም፣ አይቻለውም፡፡ አሁን ይህንን ሁሉ መንደርደሪያ መዘርዝር ወደ ተገደድኩበት ዋና ጉዳዬ ልመለስ፡፡
መብቶቻችንና ነፃነቶቻችንን፣ እንዲሁም ዴሞክራሲያችንን ከስም ጌጥ ያለፈ ትርጉምና ሕልውና እንዲኖራቸው ሁሉምና እያንዳንዱም ሥርና ሥርዓት በያዘ ዴሞክራሲያዊ መደላድል ላይ ተንሠራፍተው መቀመጥ አለባቸው፡፡ ሁሉም መብቶች እኩል፣ እኩያ ናቸው ማለት ግን ልዩ ልዩነት የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የተለያዩ በዘመናቸውና በየአገራቸው የጊዜ ልዩነት/ዘመንም ሆነ ርዕዮተ ዓለም ሳይገድባቸው የመናገር፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን እኩያነት የበለጠ ቦታ ሲሰጡት፣ ይህንን ነፃነት የነፃነቶች ሁሉ አዝማች/ግንባር ቀደም ሲያደርጉት እንመሰክራን፡፡ በእኛ አገር ቋንቋ ሐሳብን የመግለጽና የፕሬስ ነፃነት ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› ነው ይላሉ፡፡
‹‹Our liberty depends on the freedom of the press, and that cannot be limited worth out being lost.››
Thomas Jeffeerson (1788).
‹‹The matrix, the indepensable condition of nealy every other form of freedom.››
US Supreme Court (1937) Benjamin Ni Cardozo
‹‹The inevitable general staff of all liberties, the only effective guardian of every other rights.››
Karl Marx (1852)
‹‹The unsleeping guardian of every other right that free men prize, it is the most dangerous foe of tyranny.››
Winston Churchil
ሐሳብን የመግለጽና የንግግር፣ የፕሬስ ነፃነትን ጨምሮ ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ ውስጥ መከበርና መጠበቅ አለባቸው የሚለው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ሥርዓትም፣ ከሌሎች የተለያየ ስያሜና አገልግሎት ካላቸው በዓላት በተጨማሪ በየዓመቱ ጥቅምት 23/ኖቬምበር ሁለትን ‹‹International Day to end Impunity for Crimes Against Journalists›› አወጀ፡፡ ለአሥረኛ ጊዜ የተከበረው በጋዜጠኞች፣ በፕሬስ ወይም ሚዲያ ላይ በአጠቃላይ ሐሳብን በመግለጽና በንግግርና በፕሬስ ነፃነት ላይ ጥቃት ፈጽሞ ሳይጠየቁ መቅረትን ለማውገዝ፣ ለመከላከልና ለመዋጋት የተሰየመው ይህ ክብረ በዓል ቀደም ብሎ እንደተወሳው የጋዜጠኞችን ደኅንነት፣ የሚያየውን በሰላም ሥራ መሥራት ከሌላው ደኅንነት ይበልጥ ከፍ የሚያደርጉበትና ይበልጥ የሚቆረቆርበት ምክንያት አለው፡፡ ምክንያቱም ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› ዓይነት ነው፡፡ ዝንጀሮ የሠራ አካላቷን በሙሉ እሾህ ተሰግስጎባት ለአደጋ ጊዜና ለክፉ ጊዜ የደረሰላትን አጋዥ ሁሉ ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› ያለችው ከአንዱ የሰውነት አካሏ ሌላውን በማስቀደም ወይም በማብለጥ ሳይሆን፣ የመቀመጫዋ ከወጣላት በኋላ ሌላውን እሷም ጭምር እያገዘች፣ እየረዳችና ከሁሉም በላይ ደግሞ እየመራችና እያስተባበረች ሌላው ሰውነቷ ላይ የተሰገሰገውን እሾህ ማውጣት ስለሚረዳት ነው፡፡ የፕሬስ/የሚዲያ ነፃነት ፊት አውራሪነትና ግንባር ቀደም መሪነትም ዴሞክራሲ ውስጥ ይህንን ያህል ፊት አውራሪነትና ቀዳሚ ነው፡፡
ይህንን የሚያውቁትና በዚህም መሠረት ለዴሞክራሲ የመዋደቅን ግን የንግግርና ሐሳብን የመግለጽ የፕሬስ ነፃነት ሥር መያዝና ተመቻችቶ መንሠራፋት አድርገው የሚቆጥሩት ብቻ ሳይሆኑ፣ የዴሞክራሲ ጠላቶችም አሳምረው ያውቁታል፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን ከማንም በላይ ከማወቃቸው የተነሳ ዴሞክራሲ የማደላደሉን፣ ነፃና ገለልተኛ ተቋም የመገንባቱን የአገር ሥራ እዚህ ስስ ብልት ላይ እናጥቃው ብለው ይረባረቡበታል፣ ይዘምቱበታል፡፡ የወረራውና የጥቃቱ ዓይነት ልዩ ልዩ ዓይነት ልክና መልክ አለው፡፡ የንግግርና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን ራሱን፣ ለዚያውም በዚህ ቀውጢና ባልጠና ወቅት ዴሞክራሲን፣ በእሱም ስም የንግግር ነፃነትን የግርግር መደገሻ ያደርጉታል፡፡ ለዚያውም የሐሳብ ውድድሮችን፣ የሚቃረኑ ሐሳቦችን ፀብ የለሽ ፍልሚያ የማስተናገድ ባህልም ሆነ ልምምድ በሌለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ፣ መብቴ ነው ማለትን ኃላፊነት አለብኝ ከማለት ጋር ያፋቱታል፣ ያጣሉታል፡፡ ዴሞክራሲና የንግግር ነፃነት እንዲህ ያሉ የግርግር መደገሻ አድርገው የሚማግጡበት ‹‹ወዳጆች››፣ የወዳጅ አጥቂዎች አሉት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ሥር ሰድዶ የኖረው ፀረ ዴሞክራሲያዊነትና የለየለት አፈና፣ ሥልጣኔ ውስጥ አብረው የተፈጠሩትን ቅንብሮች ሁሉ የሚከለክልና አላስቀምስ አላስደርስ የሚል ነበር፡፡ ለምሳሌ በንግዱ ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ ከትናንት ወዲያም፣ ትናንትም፣ ድኅረ ጣሊያንና ደኅረ አብዮት፣ ዛሬም ድኅረ ኢሕአዴግ በንግድ ሕጎች እንደተወሰነው የማተም፣ የማሳተም፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን፣ የመረጃ፣ የጋዜጣ ሥራ ሁሉ ‹‹የንግድ ሥራ›› ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ዘመን የመረጃና የመረጃ ነክ ሥራ አጠቃላይ የመንግሥት የሞኖፖል ሥራና መብት ሆኖ የቆየው በተጠቀሰው በንግድ ዘርፉ ውስጥ የሥምሪት መስኩን በመከለል ወይም በመከልከል፣ ወይም የፈቃድ ሥርዓቱን በማጥበብና በመቆልመም ብቻ ሳይሆን ሌላም የእኛ አገር ፈጠራ የሆነ ዘዴ/ሥልት ነበር፡፡ ለምሳሌ ብርሃንና ሰላም ጋዜጣና ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከተለያዩ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የአሳታሚነት ሥራ ከማተሚያ ቤት ባለቤትነት ጋር በጭራሽ ተገናኝቶ አያውቅም፣ አይፈቅድምም፡፡ ጋዜጣ ማተም የሚችሉ ማተሚያ ቤቶች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በመሆናቸው፣ የመንግሥት ባለቤትነታቸውም በገዥ ፓርቲ፣ እስከ ገዥ ፓርቲ (ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት በደረሰ/ደረጃ ባለው የቦርድ ሊቀመንበርነት) ሰው የመመራት ወግ ያላቸው በመሆኑ፣ ልዩ ልዩ መንገዶች ስትራቴጂክ ማሰናከያዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡
ሕግ የማውጣትና የሕግ ረቂቅ/ሐሳብ ለተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ ሥልጣንን የሚጨምረው የሕግ አወጣጥ ሥርዓቱ ራሱ፣ በተለይም የ1984 ዓ.ም.ን የፕሬስ ሕግ ለመተካት መጀመርያ ከተረቀቀው የ1995 ዓ.ም. ረቂቅ የፕሬስ ሕግ ጀምሮ የነበረው ዘመቻና ትግል ጋዜጠኝነትን የማጥቂያ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ አሁንም ከሕግ ማሻሻልና ከ‹‹ሚዲያ ፖሊሲ›› መውጣት በኋላ ጋዜጠኝነትን፣ የፕሬስ ነፃነትን የማጥቂያ መሣሪያነታቸው ያልመከነና በርካታ ሥውርና ግልጽ የሕግም የአሠራርም መሣሪያዎች አሉ፡፡
ለተወሰነ ጊዜ ፈክቶና ቦግ ብሎ እስከ አዟሪ ድረስ የወረደ የሥራ ዕድል ፈጥሮ የነበረው የኅትመት ሚዲያ ዛሬ ሪፖርተርንና አዲስ አድማስን ከቆጠሩ በኋላ ሌላ ስም መጥራት አይቻልም፡፡ የእነሱም ሕልውና አታሚዎቻቸው እንዳሳደሯቸው የሚወሰን ነው፡፡
እስራት አሁንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ራሱን እስኪደንቀውና አልገባህ እስኪለው ድረሰ ሚዲያን፣ ጋዜጠኛነትን የማጥቂያ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል፣ ለዚያውም ያለ ተጠያቂነት፡፡ የተሻረው የሚዲያ ሕግ ራሱ በሚዲያ ‹‹አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ካልወሰነ በስተቀር በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 59/2 እና (3) (የጊዜ ቀጠሮ) መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት›› ይል የነበረ ቢሆንም፣ አዲሱ ሕግም የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉንም ፈቃድ አንስቶ ማንም በሚዲያ ላይ ለተሠራ ጥፋት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ አይደረግም ቢልም ሕጉ፣ ዳኞች የሚሉት መሆኑ ቀርቶ ‹‹ሕግ አስፈጻሚ››ዎች የሚሉት ሕግ እየሆነ መጥቶ ዛሬ ‹‹ለተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በእስር እንዲቆይ›› በፖሊስ በሚቀርብ ጥያቄ ላይ የሚሰጥ የ‹‹አይፈቀድም›› የፍርድ ቤት ውሳኔ፣ ያለ ሕግ ይግባኝ የሚባልበት እስከመሆን የጥቃት መሣሪያ ሆኗል፡፡
አሁን አሁን ደግሞ የአገርን የሰብዓዊ መብት ‹‹አፈጻጸም››ን የሚዘግቡት ዜናዎችና ሪፖርቶች እንደሚገልጹት፣ ‹‹ባልታወቁ ሰዎች›› በንብረት ላይ የሚፈጽሙ (የወንጀል ዓይነቶች) ስርቆት፣ ከባድ ሥርቆት ጭምር ተራ ውንብድናና ከባድ ውንብድና፣ እንዲሁም ዝርፊያ ጭምር ፕሬስን/ሚዲያን የማጥቂያ መሣሪያዎች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ወይም ይህ ሆኗል ማለት የአገር ግንዛቤ እየሆነ ሄዷል፡፡ ይህንን የመሰለውን በንብረትና በሀብት መብት ላይ የሚፈጸም የደፈጣ ጥቃት አንገብጋቢ፣ አሳሳቢ፣ አደገኛና የነፃነትና የመብት የ‹‹ሞት ባልንጀራ››፣ የሚያደርገው፣ የፕሬስ ነፃነትን ራሱን የሚመታና የሚያጠቃ በመሆኑ ነው፡፡
ይህንን በሚገባ ለማስረዳት በአንድ ወቅት አገራችን በሕግ የደነገገችውን ‹‹የጽሑፍን ሚስጥር ስለማክበር›› ድንጋጌ ይዘትና በዚያው ልክ በሕግ የተዘረጋውን የአሠራር ሥርዓት አጭር ‹‹ታሪክ›› ላቅርብ፡፡ ይህ ይዘቱን፣ ዝርዝር አፈጻጸሙንና ታሪኩን የማቀርብለት ሕግ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ዘመን ዴሞክራሲና ሪፐብሊክ ገነባን፣ መሠረትን ከማለታችን በፊት በ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የተደነገገ ነበር፡፡ የወቅቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በወንጀል ሥራ ተካፋይ ስለመሆን ከሚደነግገው ምዕራፉ በተጨማሪ ታትመው በሚወጡ ጽሑፎች በሚሠራ ወንጀል ተካፋይ መሆንንም ለብቻው ይመለከት ስለነበር፣ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ‹‹የጽሑፍን ሚስጥር ማክበር›› የተወሰነ የዋስትና መርህ ያቋቁማል፡፡ በዚህም መሠረት በፕሬስ ወይም በሚዲያ ወይም በራሱ በሕጉ ቋንቋ ‹‹በጋዜጣ ወይም በየጊዜው እየታተመ በሚወጣ ጽሑፍ ጥፋት በተሠራ ጊዜ [ዋና አዘጋጁ] የጽሑፉን ሚስጥር የመጠየቅ መብትን ድጋፍ በማድረግ፣ ደራሲውን ለመግለጽ ያልፈለገ እንደሆነ የጽሑፉን ደራሲ ለማወቅ የተለመዱትን የምርመራ ዘዴዎችና ሕግ›› የሚያዘውን የግዴታ ተግባር ለመፈጸም አይቻልም ይላል፡፡ ይህ ድንጋጌ ‹‹ኤክሰፕሸን›› ቢኖረውምና የማይሠራበት ሁኔታ በራሱ በሕጉ ቢደነግግም፣ የይዘቱ ትርጉም ግን የሚደንቅና ዕውን እንዲህ ያለ ሕግና ጥበቃ አለን? ነበረን? የሚያሰኝ ነው፡፡ አንድ ዋና አዘጋጅ፣ ማለትም የፕሬስ ወይም የሚዲያውን ይዘት ሕጋዊነት የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት ዋና አዘጋጅ፣ ይህንን ጽሑፍ የጻፈውን ሰው ግለጽ ቢባልና እንቢ ቢል፣ አልገልጽም፣ አለመግለጽ መብቴ ነው ቢል በሕግ የተደነገጉት የምርመራ ዘዴዎችም ሕግ የሚያዘው የግዴታ ተግባርም በእሱ ላይ አይፈጸምም፣ አይፈጽሙበትም፡፡
ይህ ራሱ ምን ማለት ነው? ዋና አዘጋጁ ደራሲውን፣ ወይም ጸሐፊውን ወይም ምንጩን አይገልጽም የማለት መብት አለው፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሰውየውን/ምንጩን ወይም ደራሲውን ለማወቅ ፖሊስ በአገር የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ቤት ወይም ቢሮ መበርበርና ዕቃ መያዝ አይችልም፣ ፍርድ ቤት የብርበራ ማዘዣ አይሰጥም ማለት ጭምር ነው፡፡ እንዲያውም በዚያው የወንጀል ሕግ የተደነገገውን ማለትም የሰውን ንብረት ለመፈተሽ፣ ለመበርበር ወይም ዕቃውን ለመያዝ የተሰጠውን ሥልጣን ከመጠኑ በማሳለፍ ወንጀል (አንቀጽ 415/ወይም 422)፣ እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ ሰውን ስለመያዝና ስለማሰር (አንቀጽ 415 ወይም 423) የተከላከለውን ወንጀል በመፈጸም ክስ ይከሳል፡፡ በተለመደ አሠራር፣ እንዲያውም በታወቀ አሠራር ጸሐፊውን ምንጩን አልናገርም ማለት ሌላ የወንጀል ድርጊት ቢሆን ኖሮ ዋና አዘጋጁ ተከሳሹን ወደ ፍርድ ቤት እንዳይቀርብ ደብቀሃል (አንቀጽ 445)፣ ለፍርድ ዕርዳታ መስጠት እንቢ ብለሃል (አንቀጽ 448) ተብሎ ይከሰሳል፡፡ ይህ ግን የመናገርና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፉ ከፍ ሲል የጠቀስናቸው ታላላቅ፣ ዕውቅና ስም ያላቸው ሰዎች የሌሎች መብቶችና ነፃነቶች ሁሉ ማስፈጸሚያ ነው ያሉት መብት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጉ ፀንቶ በቆየበት ዘመን የኖረበት ሁኔታ ከ‹‹ተፈጻሚነት›› ይልቅ ተዘንግቶ ከእነ መኖሩም ተረስቶ ይልቁንም ተጎሳቁሎ የነበረ ቢሆንም፣ ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ግን ይህንን በመሰለው መልኩ እንኳን ወደ 1997 ዓ.ም. የወንጀል ሕጉ አለመሸጋገሩ ነው፡፡ ከ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ጋር አብሮ ተሰናብቷል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ፣ በገዛ ራሱ ምክንያት በሚያዝና ሌላ ዓላማ ባገለገለ (ዌክፕናይዝድ በሆነ) ‹‹የሕግ አወጣጥ›› ጥፋት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ 1996 ዓ.ም. አዋጅ ቁጥር 414/1996 ሆኖ የታወጀው በ1996 ዓ.ም. ነው፡፡ የወንጀል ሕጉን ባወጀው ሕግ አዋጅ ቁጥር 414/96 አንቀጽ አንድ አጭር ርዕስ መሠረት የሕጉ ስያሜ ራሱ የ1996 ዓ.ም. የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ነው፡፡ ይህ ሕግ በ1996 ዓ.ም. ታወጀና ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲፀና ተደረገ፡፡ ሕግ ሆኖ ከተሠራና ከፀደቀ በኋላና ነገር ግን የተፈጻሚነት ዘመኑን ከግንቦት 1 ቀን አንስቶ በመጠባበቅ ላይ ባለበት በ1997 ዓ.ም. የካሌንደር ዘመን ውስጥ ግን አንድ እንግዳ ነገር ተፈጠረ፡፡ በ1992 ዓ.ም. ምርጫ የተቋቋመው ሁለተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን ውስጥ (1997) መጋቢት 20 ቀን 1997 ዓ.ም. በዋለው 20ኛ መደበኛ ስብሰባው አጀንዳ ላይ በተራ ቁጥር ሁለት አማካይነት ‹‹የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግን አስመልክቶ የሕግና አስተዳደር የሴቶችና የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች አዘጋጅተው ባቀረቡት ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ…›› እንዲሰጥ ተጠየቀ፣ ውሳኔም ሰጠ፡፡ በዚህ አማካይነት ስለሕግ ማሻሻል ሳይነገር፣ ስለሕግ አወጣጥ ሳይነገር የወንጀል ሕጉ ‹‹ተጨማሪ ጭነት›› ይዞ ‹‹እንዲያልፍ››፣ ይህም ‹‹ጭነት›› ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ ረቂቅ የፕሬስ ሕግ ሆኖ አገር ሲያስፈራራ የባጀው የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሕግ ሐሳብ ዋናና መሠረታዊ ድንጋጌዎች ሆነው ተገኙ፡፡ ፕሬስ፣ ሚዲያ፣ ጋዜጠኛነት ማለት ይህንን ያህልና ይህንን የመሰለ አደጋና ጥቃት ሲደርስበት ኖሯል፡፡
አሁን ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ፣ እንዲሁም በዚሁ አማካይነት የ2011ን (እ.ኤ.አ. የ2019) የዓለም የፕሬስ ነፃነትን ቀን አዲስ አበባ ካስተናገደች በኋላም ራሱ፣ የገዛ ራሳችን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት እንደሚነግረን/እንደሚያስረዳን ዝም ብለው በዝምታም የማይጣጣሉና የማይገፏቸው መልስ ማግኘት መከላከያም ሊበጅላቸው፣ ሁለተኛም እንደገናም እንደማይደገሙ መተማመኛ ሊሰጥባቸው የሚገቡ በአሳሳቢና በከፋ ደረጃ ተመድበው የሚታዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶች አሉብን፡፡
እዚህ ውስጥ የዘፈቀደ እስርና አስገድዶ መሰወርንም እንሰማለን፡፡ መብቶች ሁሉ እኩያዎችና እኩል ቢሆኑም ሐሳብን በነፃ የመግለጽና የፕሬስ ነፃነት እኩያነት ግን ከሌሎች ያይላል ለሚሉም ሆነ፣ ለማንም ሰው ከፍተኛ አሳሰቢ ጉዳይ እየሆነ የመጣው ሚዲያ ባለሙያ ላይ፣ ጋዜጠኛ ላይ፣ ወይም የጋዜጠኝነት ተቋም ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በግልጽና በአደባባይ ‹‹በሕግ አምላክ››፣ ‹‹ልብ አድርጉልኝ›› የማይሉት ሥውርና አደገኛ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ በዚህ ጥቃት ምክንያት በሙያውና ሙያው በሚያጠነጥንበት ኢንዱስትሪና ኢኮኖሚ ውስጥ የተፈጠረው ሥጋትም በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ‹‹አምሳያ የሌለው››፣ ‹‹ተደርጎም ተሰምቶም የማይታወቅ›› የማይባል ጥቃትና አደጋ ሲያጋጥም እኔ በበኩሌ በመንግሥት፣ በከፍተኛው የመንግሥት አስፈጻሚና አስተዳደራዊ የሥልጣን አካል ደረጃ ድርጊቱን የሚያነውር፣ የሚያወግዝና ቁጣውን የሚያስተላልፍ መግለጫ መስጠት አለበት ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ‹‹እኛ ማለት ይህ አይደለንም›› እንዲባል እፈልጋለሁ፡፡ ድርጊቱን የፈጸሙት በይፋና በአደባባይ የሚሰማው ወሬ/ክስ እንደሚለው ‹‹ነካካቸው አትስጣቸው ጤና›› የተባሉ ወይም የተባሉ የመሰላቸው ‹‹ልብ አውቃዎች›› ከሆኑም፣ ነገሩን በአደባባይና በይፋ በዚህ ደረጃ ማውገዝ የሕግ ማስከበር የመንግሥት ሥራ የፖሊሲ ማዕቀፍ ያበጃል፡፡ ድርጊቱ መፈጸሙና ዘርፉ ላይ እንዲህ ያለ ጥቃት የመድረሱ ወሬ/ዜና ሊያንቀሳቅሳቸውና ‹‹ጤናም›› እንቅልፍም ሊነሳቸው የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች የሚጠቅሳቸው ባለጉዳዮች፣ ባለቤቶች፣ ‹ተቆጣጣሪ›ዎች አሉ፡፡ የመንግሥትም መንግሥታዊ ያልሆኑም አካላት፡፡ መቼ ነው ይህንን ድርጊት ሲቃወሙ፣ በእሱ ላይ ቁጣቸውን ሲገልጹ የምንሰማው?
በሚዲያ ተቋም ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከላይ ከላይ ሲያዩት የስርቆት፣ የዘረፋ (የከባድም የቀላልም) ወይም የውንብድና ወንጀል ነው፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነውና በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የወጣው ሕግ የሚያበጀው መጠበቂያ እንደሚያሳየው፣ በሚዲያ ላይ ወይም በአንድ ጋዜጠኛ ላይ የሚሠራ ለምሳሌ ተራ ‹‹የኪስ ማውለቅ›› ድርጊት ተራ ‹‹ውስልትና›› ብቻ አይደለም፡፡ ኢንፎርሜሽን፣ ምንጭ ላይ ጭምር ማነጣጠር ነው፡፡ ለዚህም ነው በየዓመቱ ጥቅምት 23 ቀን በዓለም ዙሪያ የሚከበረው በሚዲያ/በጋዜጠኛ ላይ ጥቃት ፈጽሞ ሳይጠየቁ መቅረትን የሚዋጋው ንቅናቄ በአሁኑ ደረጃ ከዚህ በላይም አልፎ በሚዲያና በጋዜጠኝነት ላይ የሚፈሙ ወንጀሎች ክስ አቀራረብ በይርጋ የማይታገድ፣ በምሕረት ወይም በይቅርታ የማይታለፍ እንደሆነ በመንግሥታቱ ድርጅት ደረጃ እየታገለና ውጤትም እያስመዘገበ የሚገኘው፡፡
ይህንን ሁሉ ስንል ግን እንዲህ ያለ ፋይዳና ቦታ ያለው መብትና ነፃነት የሌሎች ነፃነቶች ሁሉ አንቀሳቃሽ ነው ሲባል ግን፣ ሙያውንም ባለሙያውንም የምንከላከለውና የምንጠብቀው ከደመኛ ‹‹ጠላቶቹ›› ብቻ ሳይሆን፣ ከራሱም ከባለሙያውና ከወዳጁ ጭምር ነው፡፡ የሚዲያውም ተቀዳሚ ተግባር፣ ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› ተግባርና አደራ የመናገር ነፃነቱን ራሱን የሚያጎናፅፈውን ሰላምና ዴሞክራሲ ሥር እንዲይዝ ተቋማዊ መደላድል ላይ እንዲደላደል መታገልና መትጋት እንጂ፣ በተለይም ዴሞክራሲው ራሱ በጨቅላነትና በ‹‹በጊዜያዊነት› በሚላወስበት ሰዓት የግርግር መደገሻ መሆን የለበትም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡