ለመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ተሰጥቶ የነበረው ኃላፊነት ለባለሥልጣኑ እንዲሆን የሚያደርግ ድንጋጌ ይዞ በመጣውና የሰላ ትችት እየቀረበበት በሚገኘው የመገናኛ ብዙኃን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ የገቡ አዳዲስ ድንጋጌዎች፣ የሚዲያና የሲቪክ ምኅዳሩን እንደሚያጠቡ በመጥቀስ ማሻሻያው እንዳይፀድቅ በመብት ተቆርቋሪዎችና በሚዲያ አካላት ጥያቄ ቀረበ፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው ረቂቅ አዋጅ በፓርላማው መደበኛ ጉባዔ ቀርቦ አስተያየት ከተሰጠበት በኋላ፣ በምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት የሕዝብ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡
የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በቅርቡ ከ14 የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና የጋዜጠኞች ማኅበራት ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፣ ቋሚ ኮሚቴው ኅዳር 11 ቀን የሕዝብ ውይይት አካሂዶበታል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በሰጡት አስተያየት፣ ረቂቁ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን የሚያጠብ ነው ብለዋል፡፡
የቦርድ አባላት ምልመላን በተመለከተም ማሻሻያው በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ ሁለትና ሦስት ድንጋጌዎች ሙሉ ለሙሉ እንደሚሰርዝ አስረድተዋል፡፡
የቦርድ አባላት ምልመላና የማፅደቅ ሒደት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ እንደሚከናወንና የዕጩዎች ዝርዝር በመገናኛ ብዙኃን ታትሞ ለሕዝብ እንዲሠራጭ፣ የዕጩዎች ምልመላ የኢትዮጵያን ብዙኃነት ያማከለ ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖር የሚያስገድደውን ድንጋጌ ሙሉ በሙሉ ማንሳት ስለሚኖረው አሉታዊ ሚና ገልጸዋል፡፡
ድንጋጌውን መሰረዝ ሕዝብ በመንግሥተ ቋማት አመራሮች ምደባ ላይ ሊኖረው የሚገባውን ተሳትፎና የማወቅ መብት፣ ፍትሕዊ ውክልናና በመንግሥት አሠራር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ አንቀጾቹ ሊሰረዙ አይገባም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በተመሳሳይ የቦርድ አባላት ስብጥርን በተመለከተ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ አምስት (ሀ) መሰረዝ አግባብ አለመሆኑን ኮሚሽናቸው እንደሚያምን ጠቅሰው፣ ድንጋጌው የዘጠኙን የቦርድ አባላት ስብጥር በግልጽ የሚያሳይና ግልጽ የሆነ የውሳኔ አሰጣጥን የሚጠብቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በዚሁ አዋጅ አንቀጽ ዘጠኝ ንፁስ አንቀጽ አምስት (ለ) ላይ በተደረገው ማሻሻያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሥራ አመራር ቦርድ ውስጥ የነበራቸውን ተሳትፎ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸው፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በቦርድ ተሳትፏቸው የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ መገደብ ኮሚሽናቸው እንደማይቀበለውና ይህ ንዑስ አንቀጽ ሊሰረዝ አይገባም ሲሉ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የቦርድ ተጠሪ ሆነው መቅረብን በተመለከተ የቦርድ አባላት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆኑ ታስቦ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የተደነገገ ቢሆንም በማሻሻያው ድንጋጌው መሰረዙን ጠቅሰው፣ ድንጋጌውን መሰረዝ የሥራ አመራር ቦርዱ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት ሥር እንዲወድቅና የቦርዱን ገለልተኝነትና ነፃነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ድንጋጌ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ ስድስትና ሰባት ባለሥልጣኑና ቦርዱ ከመንግሥትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ገለልተኛ መሆን እንደሚኖርባቸው የተደነገገውን በግልጽ የሚጣረስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የተወከሉት አቶ መሠረት አታላይ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ከዓመታት በፊት ሲወጣ አጨብጭበን የተቀበልነው ቢሆንም፣ አሁን የቀረበው ማሻሻያ ነፃነትን የሚገድብና በጣም አስፈሪ ድንጋጌ የያዘ ስለሆነ የሕዝብ አስተያየትንና ዴሞክራሲያዊ መብትን የሚቀማ ነው፤›› ነው ብለዋል፡፡
በሥራ ላይ ያለው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ከመውጣቱ በፊት የመነሻ ጥናት በማድረግና የመጀመሪያ ረቂቁን ለመንግሥት ለማቅረብ በማስተባበር ሚና የነበራቸው አቶ ሰለሞን ጎሹ በበኩላቸው፣ በማሻሻያው ከቦርዱ ተቀምተው ለባለሥልጣኑ እንዲሰጡ የተደረጉ ፈቃድ ማደስ፣ ፈቃድ መስጠት ወይም መቀማት በየቀኑ የሚደረጉ ባለመሆናቸው ታስቦ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መደንገጋቸውን አስረድተዋል፡፡
ፈቃድ መስጠት፣ ፈቃድ መሰረዝ፣ ወይም መሰል ውሳኔ የሚተላለፈው በተወሰነ ጊዜ በመሆኑ ቦርዱ በወር አንድ ጊዜ በሚያደርገው ስብሰባ ለመወሰን ይችላል ተብሎ በአዋጁ የተደነገገ ቢሆንም፣ ተሻሽሎ በመጣው ረቂቅ አዋጅ ፈቃድ መሰረዝ፣ ፈቃድ መስጠት ወይም ማደስ ቀለል ተደርጎ ለባለሥልጣኑ የዕለት ተዕለት ተግባር እንዲሆን ማድረጉ አሳማኝ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ከፖለቲካ ፓርቲ አካላት የፀዳ እንዲሆን ተደርጎ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የተደነገገው ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ታይቶ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ሰሎሞን፣ ምናልባት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓታቸው ጠንካራ በሆኑ አገሮችና ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት ባላቸው አገሮች የፖለቲካ ፓርቲን በማካተት ሊተገበር ቢችልም፣ በኢትዮጵያ ያለው ጉዳይ ያላለቀ በመሆኑ ታስቦ የተደነገገ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚው አቶ ታምራት ኃይሉ በሰጡት አስተያየት፣ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ አድናቆት የተቸረው ቢሆንም በማሻሻያ የቀረቡት ድንጋጌዎች ሚዲያውን ወደኋላ የሚጎትቱ ናቸው ብለዋል፡፡
ሚዲያ እንደ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኖች የዴሞክራሲ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው የቦርድ አመራረጥ ሒደቱ የሕዝብ ተሳትፎ ቢኖረው፣ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምታደርገውን ጉዞ የሚያበረታ እንደሆነ ሲገለጽ የነበረ ቢሆንም አሁን እንደገና ወደኋላ መመለስ ለምን አስፈለገ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
አክለውም የቦርድ አባላት የዕለት ተዕለት ሥራ ውስጥ መግባት የለባቸውም በሚል ሰበብ፣ አንድ የመገናኛ ብዙኃንን ማገድ ወይም ከሥርጭት ማስቆም እንደ ቀላል የዕለት ተዕለት ሥራ ተደርጎ በዚህ መንገድ መደንገግ እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡
አቶ ሳሙኤል ፍቅሬ የተባሉ የሚዲያ ባለሙያ በበኩላቸው በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በዚህ ፍጥነት እንዲሻሻል መደረጉ ከሕግ አወጣጥ መርህ አንፃር ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡ በሥራ ላይያለው አዋጅ ሰፊ ጥናትና ውይይት ተደርጎበት ከወጣ በኋላ በዚህ ፍጥነት እንዲሻሻል መደረጉ አስደንጋጭና ከሕግ አወጣጥ መርህ ያፈነገጠ አካሄድ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
የመገናኝ ብዙኃን ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባሉና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ማዕከል መሥራችና ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ራሳችን ሕግ አርቃቂዎች ሕግ አክባሪዎች ነን ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 የተደነገገውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በማጣቀስ፣ ጋዜጠኛው ድንበር ሳይወስነው በማንኛውም መንገድ ሐሳቡን የመግለጽ መብት እንዳለው አስረድተዋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ጋዜጠኛው ሐሳቡን በሚገልጽበት ጊዜ ጉዳት እንዳይደርስበት መንግሥት ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
የአፍሪካ የመረጃ ነፃነት ስምምነትን አምስት አገሮች ሲፈራረሙ ኢትዮጵያ አንዷ እንደነበረች አስታውሰው፣ አገሪቱ ይህንን ስምምነት ብትፈርምም በኢትዮጵያ መረጃ የማግኘት መብት ግን አስቸጋሪ ነው በማለት፣ ‹‹ሕጉ ተጽፏል ተግባር ላይ ግን የለም፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ሲወጣ ገለልተኝነት በትልቁ መታየት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከመፅደቁ በፊት ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግበት ጠይቀዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ መሱድ ገበየሁ በበኩላቸው የቀረበው ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ባለፉት ዓመታት ተነቃቅቶ የነበረውን የሚዲያና ሲቪክ ምኅዳር መልሶ የሚያጠብ በመሆኑ፣ ማሻሻያው አያስፈልግም ሲሉ ሐሳባቸው ሰንዝረዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድን የበለጠ የሚያጠናክሩት የሙያ ማኅበራትና የሲቪክ ማኅበራት በመሆናቸው፣ የእነዚህ አካላት የቦርድ አባል አለመሆን ምኅዳሩን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚስገባው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ሁለተኛዋ ለጋዜጠኞች የማትመች አገር ናት ያሉት አቶ መሱድ፣ ባለሥልጣኑ ጋዜጠኛው ወይም ሚዲያው የሚሳተፍበት ገለልተኛና ለሕዝብ የሚሠራ የዴሞክራሲ ተቋም ሆኖ መፈጠር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
‹‹ብዙ ችግር ካሳለፈና አሁንም በዚህ ችግር ውስጥ እያለፈ ባለ አገር ውስጥ፣ ሚዲያው ኃላፊነቱን በተሞላበት መንገድ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል ስለሚያስፈልግ ቦርዱ አሁን ያለውን ኃላፊነት ይዞ ይቀጥል፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ከተሰኘ ድርጅት የተወከሉ አቶ አበራ አበበ በሰጡት አስተያየት፣ የማሻሻያው ፍላጎትና ግምገማ ከመንግሥት አካል የመጣ እንጂ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደረገ ውይይት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የተወሰኑ አሉታዊ ጉዳዮች ስለተገኙ ብቻ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ አዎንታዊ ሚና ያላቸውን አንቀጾች ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ማደረግ አስፈላጊ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ በፍጥነት የማሻሻል ሒደት ፖለቲካዊ ዕሳቤ ያለው ይመስላል ብለዋል፡፡ ዕሳቤው የሚዲያ ምኅዳሩን የማጥበብ ፍላጎት ስለመኖሩ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መደበኛ ሚዲያውን እንዲቀጭጭ የማድረግና ሕዝቡ እምነት እንዳያጣበት በማድረግ፣ ለማኅበራዊ ሚዲያ ተጋላጭ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ በመደበኛ ሚዲያ ላይ እምነት ያጣ ሕዝብ ተጠያቂነት ለሌላቸው የማኅበራዊ ሚዲያዎች ተፅዕኖ ሥር እንዲወድቅና ላልተፈለገ አሉታዊ ድርጊት ይጋለጣል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ፣ በአዋጁ ምክንያት የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የማስፈጸም ኃላፊነት ተሰጥቶት ሥልጣን የሌለው አካል ሆኗል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣኑ ይፈጽም ከተባለ እንዲፈጽም ማድረግ፣ ካልሆነ ግን ማፍረስ ነው ብለዋል፡፡
የሚዲያ ተቋማት መንግሥት በሚመራው ተቋም የቦርድ አባል ይሁኑ ከተባለ፣ በቀጣይ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ቀርቦ መታየት ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡ሸ
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት፣ ዜጎች የመረጧቸው ተወካዮች የሚያቋቁሟቸውን ተቋማት ደግሞ ሕግ አውጪው በሚያወጣው ሕግ መሠረት አስፈጻሚው ተግባራዊ ያደርጋል የሚለው ዕሳቤ መያዝ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተሳትፎ የሚለካው በዚህ ዓይነት ውክልና ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹መገንባት የምንፈልገው የዴሞክራሲ ሥርዓት እንጂ፣ ነጥለን የሆኑ ተቋማትን ብቻ በመውሰድ የዴሞክራሲ ተቋማት ማለት ተገቢ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ዮናታን፣ ‹‹በተለምዶ የዴሞክራሲ ተቋማት ስለሚባል ብቻ አጠቃላይ መንግሥታዊ መዋቅሩን ትኩረት አሰጥቶታል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ‹‹ከምንፈልገውና ልንገነባ ከምናስበው የዴሞክራሲ ሥርዓት አንፃር የሚፋለስ የሐሳብ ህፀፅ አለበት፤›› ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ዮናታን አክለውም፣ ‹‹ከፍትሕ ሚኒስቴር በላይ ምን የዴሞክራሲ ተቋም አለ? የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲገነባ ከተፈለገ ፍትሕ እንዳይዛባ በተለያዩ አዋጆችና ሕጎች ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ የሚሠራበት የአሠራር ሥርዓቱ ነው በቁጥጥር ሥርዓት ተጠብቆ መሄድ ያለበት፤›› ብለዋል፡፡ የተወሰኑ ዓይን ውስጥ የገቡ ተቋማትን ብቻ የዴሞክራሲ ተቋም ብሎ ሌላውን ለዴሞክራሲ እንደማይሠራ ዓይነት ምሥል መስጠት ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬከተሩ፣ ‹‹አሁን እየተነሳ ያለው ጉዳይ ሥርዓት የመገንባት ሳይሆን፣ ትናንት ላይ ቆመን የትናንት ቁስል የበዛበት ልምዳችን በስሜት ይህን እንያዘው ይህንን እንቆልፈው እያስባለን ነው፡፡ በዚያ መልኩ ትናንት እየታገልን ትናንትና ላይ ቆመን እንቀራለን እንጂ ነገን መገንባት አንችልም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በርካታ የቦርዱ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ መደበኛ የሆኑ የዕለት ተዕለት ሥራዎች ወር እየተጠበቀ በቦርድ የሚመለሱ ሳይሆኑ፣ በባለሥልጣኑ የዕለት ተዕለት ተግባራት መከናወን ያለባቸው ናቸው፡፡ ቦርዱ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ባለሥልጣኑ አስቸጋሪ ጊዜ ሲያሳልፍ እንደነበር ጠቅሰው፣ ማሻሻያ ያስፈለገው ለባለሥልጣኑ የሚያሠራ ሥልጣን ለመስጠት ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡