በጭጋጋማው የጎንደር ከተማ ማለዳ ከጥዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ነዋሪዎች እንደየሚናቸው በባለሦስት እግሯ ባጀጅ፣ በሰማያዊው ሚኒባስ፣ በግል ተሽከርካሪዎችና በእግራቸው ወዲያ ወዲህ ሲሉ ከሚታዩ ነዋሪዎች ብዙ ፊቶች ላይ ያልተፈታ ቋጠሮና ድባቴ ይታያል።
በአማራ ክልልም ይሁን ከዚሁ ክልል ውጭ ካሉ አብዛኞቹ ከተሞች የቀደመና ወደ አራት ምዕት ዓመት የተጠጋ የዘለቀ የከተሜነትና የነገሥታት ታሪክ ያላት ጎንደር፣ ከ17ኛው ምዕት ዓመት እስከ 19ኛው ምዕት አጋማሽ ድረስ የኢትዮጵያ ዘውዳዊ ሥርወ መንግሥት ዋና ከተማ የነበረችው ጎንደር፣ በታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶቿ በሕንፃም ታሪኳ የምትታወቀው ጎንደር፣ የሥልጣኔ የባህልና የሃይማኖት ማዕከል በመሆን ያገለገለችው ጎንደር፣ አሁን ላይ ለሚመለከታት የከተማዋ ዕድገት እስክንመጣ ቆመሽ ጠብቂኝ የተባለች ትመስላለች።
እግር ጥሏቸው ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ቅድሚያ ከሚመርጧቸው የታሪካዊ ቅርሶች ቀዳሚ የጎብኚዎች መዳረሻ የሆነች ከተማ ነች ጎንደር፡፡ ከተማዋ አንድም ከማዕከላዊ መንግሥት መቀመጫ ባላት ርቀት፣ አልያም ዘመናትን እየተፈራረቁ ከሚነግሡ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት ትኩረት ማጣት፣ ወይንም ተወላጁና አገሬው ይችን ታሪካዊ ከተማ እየተሰናበተ ወደ ሌሎች ከተሞችና ውጭ አገሮች በስደት በመሄዱ ዝናዋ ታሪካዊ እንጂ አሁናዊ ዕድገቷና ውበቷ አይመስልም።
በእርግጥ በኢትዮጵያ ታሪክ በተለይም በደርግ (1967-1983) ከነበረው ሥርዓት ከዚያም ኢሕአዴግ አገሪቱን በመራበት ወቅት ከአገር ወደ አውሮፓና አሜሪካ የተሰደደው የጎንደር ተወላጅ ከሌሎች በርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለየ ቁጥሩ ከፍ ያለ ስለመሆኑ ራሳቸው ጎንደሬዎች ጭምር ይመሰክራሉ፡፡
ይህ ሆኖ እያለ ግን የጎንደር ከተማ በየወቅቱ የሚፈራረቀው የመንግሥት ሥርዓት ምንም አልሠራም ቢባል እንኳ፣ የጎንደር ተወላጅ ዳያስፖራ ባለ 400 ዓመት ታሪክ ያላትን ይች ከተማ አሁን ካለችበት ቁመና በተሻለ ማልማት የሚችልበት አቅም መፍጠር ይችል እንደነበር የሚናገሩ አሉ። እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡
ሌላው ይቅርና ከዕድሜ ጠገቧ ጎንደር ዘግይተው የተመሠረቱ በአማራ ክልል ያሉ ከተሞችን ብቻ በማየት ጎንደርን እምብዛም የለማች ከተማ ብሎ መናገር አያስደፍርም፡፡ በጎንደር ከተማ ቆመው የሚታዩት ዕድሜ ጠገብ ሕንፃዎች የጣሊያን ወቅትን ጨምሮ ቀደም ብለው የተሰሩና ብዙዎቹ ቅርስ ተብለው ሊመዘገቡ የሚችሉ እንጂ በበርካታ ከተሞች እንደሚታዩት ወደ ሰማይ ያደጉ ዘመን አፈራሽ ሕንፃዎች ዓይነት አይደሉም።
የጎንደር ከተማን የሚያውቋት ‹‹እናትዋ ጎንደር›› ‹‹ሽሙንሙኗ ጎንደር›› ‹‹እናታለም ጎንደር›› ሌሎችንም ሰም በመስጠት በዘፈኖቻቸው ስንኞችና በግጥሞቻቸው ሲያሞግሷት መስማት የተለመደ ነው።
‹‹ለጥምቀት ጎንደር ካልተሄደ ምኑን ጥምቀት አከበርን›› የሚባልላት ከተማ፣ ጎንደር ገብቶ በባህላዊ አዝማሪ ቤቶቿ ለዛ ያላቸው አገርኛ ሙዚቃዎች፣ ሽለላና ፉከራ ተቋድሶ መመለስ የብዙዎች የማይረሳ ትዝታ ነው፡፡
ጎንደር ‹‹አረጀች እያሉ ሰዎቹ ሲያሙሽ፣
ሙሽራ ነሸ ጎንደር ይሰፋል ልብስሽ›› በሚልም ተዘፍኖለታል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ጎንደር በጦርነትና በግጭት ምክንያት በጠፋው ሰላም፣ በሥራ አጥነት ችግር፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ዘራፊና አስገድዶ አጋቾች በደቀኑት አደጋ የከተማዋ ዝና ድባቴ ውስጥ የገባ ይመስላል፡፡ ጎንደር በአመዛኙ በንግድ በግብርና እና በቱሪዝም የምትተዳደር ቢሆንም ሁሉም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደቀደመው ጊዜ አልሆነልንም የሚሉት በርካቶች ናቸው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የጀመረውና ከዚያም በአማራ ክልል በፌዴራል መንግሥቱና በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ጋር በሚደረገው ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጎንደርን ጨምሮ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ባለው የፀጥታ ችግር በኢትዮጵያ መቀመጫቸውን ያደረጉ የውጭ አገር ዲፕሎማቲክና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለዜጎቻቸው የእንቅስቃሴ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የጣሉት ገደብ ጎንደርን ጨምሮ በርካታ ከተሞችን የእንግዳ ያለህ ያሰኘ ክስተት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በእርግጥ መንግሥት አገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ‹‹ተመነደገች አደገች ለውጥ አመጣች እንግዳው ጎረፈ ገቢም ገባልኝ›› እያለ ቢሆንም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ተቃራኒ ይመስላል፡፡ ሪፖርተር በቅርቡ በሠራቸው ዘገባዎች ጎንደርን ጨምሮ በርካታ ቱሪስት በማስተናገድ የሚታወቁት የአክሱም ላሊበላና ሌሎች መዳረሻዎች በዓመት አንድ ሺሕ የሚሞላ እንግዳ አልመጣልንም የሚል ስሞታ ከከተሞቹና ከአስጎብኝ ድርጅቶች መስማቱን ዘግቦ ነበር።
ከሰሞኑ ደግሞ ሪፖርተር በጎንደር ከተማ ተዘዋውሮ እንደተመለከተውና አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎቹን እንዳነጋገረው የተደበላለቀ የሚመስል ስሜትን ተጋርቷል።
መብራት በመጥፋቱ በጄኔሬተር የሚሠሩ መደብሮች፣ በሮቻቸውን ከፍተው እንግዳ የሚጠብቁ ሬስቶራንቶች፣ መንግስት በኮሪደር ፕሮጀክቱ በሠራቸው ጎዳናዎች ቆመው ፎቶ የመነሳት፣ ሰብሰብ ብሎ ተቀምጦ መበሻሸቅ፣ ለነዳጅ የተሠለፉ ለዓይን የሚታክቱ የባጃጅ ሠልፎች ተስተውለዋል፡፡ አጠቃላይ የከተሜው ነዋሪዎች ስሜት ደግሞ ልማት ላይ ነን እንሥራበት፣ ስለሚባለው ጉዳይ መስማትም ማየትም አልፈልግም የሚመስሉ ለሁለት የተከፈሉ ስሜቶችን ተመልክተናል፡፡
የፋሲል ግንብ ዕድሳት የፈጠረው ድብልቅ ስሜት
ሌላኛው ክስተት በቅርቡ ዕድሳት ተከናውኖለት ለሕዝብ ክፍት የሆነውን የአፄ ፋሲለደስ ግንብ ድኅረ ዕድሳት ይዞት የወጣውን መልክ በተመለከተ ቦታው ላይ ባሉት ነዋሪዎችና በከተማዋና ከአገር ውጭ የቅርሱ ተቆርቋሪዎች ነን የሚሉ አካላትን ለሁለት የከፈለው አስተያየት ተመልክቶታል፡፡
ይህ በዩኔስኮ የተመዘገበ ዕድሜ ጠገብ ቅርስ በእርግጥም ዕድሳት ሊደረግለት ይገባል በሚለው ጉዳይ ያን ያህል የሰፋ ልዩነት ባይደመጥም ዕድሳቱ ይዞት የመጣው መልክ ግን አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል።
በፎቶግራፍም ይሁን በቪዲዮ ተቀርፆ በርካቶች የሚታወቀው የፋሲል ግንብ ቀለም በአመዛኙ ወደ ቢጫነት የሚያደላ ሸራማ ቀለምን የያዘ ሲሆን፣ ይህ ቀለሙ ከጎንደር ከተማ ሕንፃዎች ቀለም ጋር የተጋመደ የራሱ የሆነ የከተማ ይዘት ያለው ነው የሚሉ አካላት ዕድሳቱ ይዞት የመጣው ወደ ነጭ ያመራ ቀለም በመቀባቱ ሆነ ተብሎ የቀለም ይዘቱ እንዲቀይር ተደርጓል ይላሉ፡፡
በእርግጥም ግንቡ ከታደሰ በኋላ ይዞት የመጣው ቀለም ቀድሞ የነበረውን የደበዘዘ ይዞታውን ወደ ነጭነት የቀየረው መሆኑን ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ለመረዳት ችሏል። ይሁን እንጂ ዕድሳቱ የተከናወነው ለዓመታት በ12 ጉድጓዶች ተቀብሮ በተብላላ ኖራ ከመሆኑም በላይ ስመ ጥር የሚባሉ ትላልቅ የሕንፃ ባለሙያዎች መክረው ዘክረው የሠሩት መሆኑን ከሕንፃ ባለሙያዎቹና ከከተማ አስተዳደሩ ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡
በተጨማሪም ዕድሳቱ የተሠራው ግንቡ መጀመሪያውኑ በተሠራበት ኖራ ስለመሆኑን ይጠቅሱና ፀሐይ አቧራና ዝናብ ለዘመናት ሲፈራረቅበት ወደ ደብዛዛ ቢጫ ቀለም መቀየሩን በመጥቀስ ይሄኛው ዕድሳትም ወደዚያኛው ቀለም መቀየሩ አይቀሬ መሆኑን ይናገራሉ።
በጥገና ዕድሳቱ በአማካሪነት እንዲሁም በጥናት የተሳተፉት አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ለአንድ ሚዲያ በስጡት አስተያየት ‹‹የፋሲል ግንብ ሕንፃ ከመቶ ዓመታት በፊት ሲገነባ በአነስተኛ ድንጋዮችና በኖራ ሲሆን፣ ለረጅም ዓመታት በዝናብ፣ በፀሐይና በተፈጥሯዊ ሒደቶች ውስጥ ሲያልፍ በርካቶች የሚያውቁትን አሁን ያለበትን መልክ›› እንዳመጣ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የፓርላማ አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ የሕንፃው ቀለም ወደ ነጭ መቀየሩን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ በሰጡት አስተያየት ‹‹ነባር ገጽታውን ከመጠበቅ በላይ ሥነ ውበት ላይ ትኩረት ያደረገ ጥገና መከናወኑን ወደ ነጭነት የተጠጋው አዲሱ የግንቦቹ ገጽታ በጥገናው ሒደት እውነተኛ ነባር ገጽታውን የመጠበቅን መርህ (authenticity) ከመጨነቅ ይልቅ ለሥነ ውበቱ የተጋነነ ትኩረት መሰጠቱ አመላካች ነው፤›› ብለዋል።
አክለውም የዚህ ችግር ዋነኛ ምንጭ ደግሞ የግንቦቹን ተፈጥሯዊ የማርጀት፣ የመደብዘዝና ተያይዞ የሚመጣውን የሥነ ውበት ለውጥ ሒደትን ከመረዳትና ከመጠበቅ ውሱንነት ጋር የተያያዘም ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
የቅርስ ጥበቃ ዋነኛ ትኩረት የሆነውን የቅርሱን አካላዊ መንፈስና ሐቀኝነት የመጠበቅ መርሆ (Preserving the Spirit and Authenticity of the Structure) ላይ ከማተኮር ይልቅ ‹‹አዲስ›› አስመስሎ የማቅረብ ሥነ ውበቱ ላይ ትኩረት መደረጉንና ሌሎችንም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸው አካላት አጥጋቢ ማብራሪያ ይስጡኝ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ በላይ ግን ሪፖርተር ካነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች መካከል አንድ በዕድሜ ገፋ ያሉ ግለሰብ እንደሚሉት፣ ‹‹ከምንም በላይ ሕንፃው እጃችን ላይ ከመውደሙ በፊት ዕድሳት የተደረገለት መሆኑ የሚነሳውን ወሬ ውድቅ ያደርገዋል፤›› ይላሉ።
ግለሰቡ አክለውም ቅርሱ አደጋ ላይ የነበረና ሕዝቡ የሰሚ ያለህ እያለ በነበረበት ወቅት በመታደሱ ከምንም በላይ ዕረፍት ሰጥቶኛል ይላሉ። ይህ ዓይነቱ አስተያየት በብዙ የከተማው ነዋሪዎች ዘንድ የሚደመጥ አስተያየትም ነው።
በተወሰነ መልኩ በከተማዋ ውስጥ በአስጎብኘነት እንዲሁም በባለሦስት እግር ተሽከርካሪ የታክሲ አገልግሎት ሲሰጡ ከነበሩ ሁለት ግለሰቦች ሪፖርተር በወሰደው አስተያየት ደግሞ የሕንፃው ቀለም እንዲቀይር ታስቦበት የተሠራ ነው ይላሉ። ለዚህ ዕሳቤ ማጠናከሪያ የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ መንግሥት በአገሪቱ ከጀመረው የኮሪደር ፕሮጀክት ጋር በተገኘ በበርካታ ከተሞች ውስጥ ሕንፃዎችን ወደ ግራጫ ቀለም የመቀየር ሒደት ጋር ይገናኛል፡፡
የባለሦስት እግር ተሽከርካሪ የታክሲ አገልግሎት ሰጪው እንደሚሉት፣ ከፋሲለደስ ግንብ ዕድሳት መልስ በጎንደር ፒያሳ አካባቢ የሚገኙ ዕድሜ ጠገብና ወደ ቢጫ ያደሉ ሕንፃዎች ወደ ግራጫ መቀየራቸውን ይጠቅሱና ይህ አጠቃላይ ጎንደር የምትታወቅበትን የከተማ ቀለም ይዘት የመቀየር ዕርምጃ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡
ሥጋት ያጠላበት አሁናዊ ሁኔታ
በጎንደር ከተማ መንግሥት በጀመረው የ1.8 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት የከተማ አስተዳደሩ ሕገወጥ ግንባታን ለመከላከል ከተማዋን እንደ አዲስ ለመሥራትና በጣሊያን ወቅት የተሠሩ ቤቶችን አሁናዊ ይዘት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየሠራ መሆኑን በመጥቀስ ሥራው አሁንም እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት በርካታ ሕንፃዎች ቀለማቸው ወደ ግራጫ ተቀይሮ በሕንፃዎቹ አናት ላይ መብራት ተገጥሞ ሌሊቱን ሲያበሩ የሚያድሩ ሕንፃዎች በመጥቀስ ጎንደር የነበራትን ታሪካዊ ቀለም አጥታለች የሚሉ ድምፆች ይሰማሉ፡፡
ከጎንደር ከፋሲለደስ ግንብ ዕድሳትም ይሁን ከቀጠለው የኮሪደር ፕሮጀክት የበለጠ በጎንደር ከተማና አካባቢው የተንሰራፋው አስገድዶ በመሰወር ወይም በማገት ገንዘብ ጥየቃ ሕፃናት፣ ሴቶችና በዕድሜ የገፉ አዛውንት ጭምር አደጋ ውስጥ መጣሉ፣ የሥራ አጥነት፣ ጨለማን ተገን አድርገው የሚደረጉ ጥቃቶች፣ የነዳጅ ዋጋ መናር፣ የሰዓት ዕላፊ፣ የሥራ አጥነትና የንግድና ቢዝነስ መቀዛቀዝ የብዙዎች የልብ ትርታ ነው፡፡
የከተማዋ ባለሥልጣናት የዕገታ ተግባር መሻሻል አለ ቢሉም ነዋሪዎች ግን አሁንም በርካቶች ይህንኑን ሥጋት ፍራቻ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ በከተማዋ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እምብዛም አይታዩም፡፡
የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በነዳጅ ማደያዎች መንግሥት ባወጣው የመሸጫ ታሪፍ ቤንዚን ማግኘት ተስኗቸው በሕገወጥ መንገድ በጥቁር ገበያ ከሚሸጡ ቸርቻሪዎች በሊትር በ300 ብር ሲገዙ መመልከት ተችሏል። ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ከተሰጣቸው ጥቂት አሽከርካሪዎች መካከል አብዛኛው ዕድሜያቸውን በወታደርነት ያገለገሉት አንድ በዕድሜ ገፋ ያሉ የባጃጅ አሽከርካሪ ምሽቱን ለመሥራት የጦር መሣሪያ ከእጃቸው እንደማይለያቸው ይናገራሉ፡፡
አሽከርካሪው እንደሚሉት ምንም እንኳ የሰዓት ዕላፊ ቢታወጅም በዛፍ ሥርና ሰዋራ ቦታዎችን በመምረጥ ተሽከርካሪም ይሁን እግረኛ ማለፍ የማይችልበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው፣ አልፎ አልፎም የባጃጅ አሽከርካሪዎች ራሳቸው ተመሳጥረው በድንገት ያገኙትን አፍነው እንደሚወስዱ ይናገራሉ፡፡
በጎንደር ከተማ ቡና ቤቶች የባህላዊ ምሽትና አዝማሪ ቤቶች ወደ ከተማዋ የሚሄዱ ቱሪስቶች የሚወዷቸው መዝናኛ ቤቶች ናቸው፡፡ አሁን ላይ በከተማዋ ያሉ የምሽት ቤቶች የተወሰኑት ዝግ ሲሆኑ የተወሰኑት አዝማሪዎች ቤቱን በባዶው ሲያሞቁ ያመሻሉ፣ በእንግዳ የተጠሙት ቤቶቸ አንድም ሁለትም ሰው ሲገባ የተለየ አቀባበል ይሰጡታል፡፡
በየጎዳናውና በሕንፃዎች ሥር በተከፈቱ የጀበና ቡና መሸጫዎች በርካታ ወጣቶች ተቀምጠው ያወራሉ፡፡ ከወጣቶች መካከል አንድ የዩንቨርሲቲ ምሩቅ ከወራት በፊት ለሥራ ፍለጋ በተሽከርካሪ ወደ ባህር ዳር በመጓዝ ላይ በነበረበት መንገድ ላይ በድንገት በተፈጠረ ድንገተኛ ተኩስ በመደናገጥ ወደ ጎንደር መመለሱንና ‹‹ከመሞት መሰንበት ይሻላል›› በሚል እናቱ ቤት ያለ ምንም ሥራ ለመቀመጥ መወሰኑን ይናገራል፡፡
የጎንደር ወቅታዊ ሁኔታ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲገለጽ የከተማዋ ውበት የደበዘዘ፣ የከተሜው ነዋሪ ስሜት የተደበላለቀ፣ የከተማዋ የልማት ቁመና ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር ያልተግባባ ቢመስልም በከተማዋ ስለሚከናወነው የኮሪደር ፕሮጀክት ክንውን ግን የከፋ የተቃርኖ ድምፅና አስተያየት አይስተዋልም፡፡