የ2016 ዓ.ም. መጨረሻ ሳምንት ዿጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በከሳሾች እነ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ (አራት ሰዎች) ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍትሐብሔር ተረኛ ችሎት ክስ ቀርቦ፣ በተከሳሾች እነ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አምስት ሰዎች) ላይ ተጥሎ የነበረው የባንክ ሒሳብና የጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ዕግድ፣ ከትናንት በስቲያ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ተነሳ፡፡
ዕግድ ተጥሎባቸው የነበሩትን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ኮሚቴው ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ያከናወነው የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ዕግድን ያነሳው፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ፍትሐብሔር ተረኛ ችሎት ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዞ የነበረው፣ ዕግድ የተጣለበት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የተጣለበትን ክስ በመቃወም ዕግዱ እንዲነሳለት ባቀረበው አቤቱታ ላይ ከሳሾች (እነ አትሌት ኃይሌ) አስተያየታቸውን ለመስማት ነበር፡፡
በሦስት ጠበቆች የተወከሉት ከሳሾች የፍርድ ቤቱ መጥሪያ እንዳልደረሳቸው፣ ነገር ግን የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ዕግዱ እንዲነሳ ይግባኝ መጠየቃቸውን በሚዲያ ሰምተውና ለመስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዙን አውቀው እንዳቀረቡ ማስረዳታቸውን የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ያብራራል፡፡
ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ የመጥሪያ አደራረስ ላይ ከፍተኛ የሥነ ሥርዓት ጉድለት መኖሩን፣ ተከሳሾች ባቀረቡት የአቤቱታ ግልባጭ ላይ ቃለ መኃላ የፈጸመው አካል ሰም የማይታወቅና የፍርድ ቤት ሕጋዊ ክብ ማኅተም የሌለው መሆኑን አስረድተው፣ ፍርድ ቤቱ ስለአቤቱታው ትክክለኛነት ማረጋገጫ ሳይሰጣቸው ወይም መጥሪያው ከፍርድ ቤት የወጣ ስለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ሳያረጋግጥላቸው አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ከቴኒስ ፌዴሬሽን ውጭ ለሌሎቹ ከሳሾች መጥሪያው እንዳልደረሰ አረጋግጦ፣ ነገር ግን ከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካይነት በችሎት ስለተገኙ፣ በቀረበው አቤቱታ ላይ ያላቸውን አስተያየት ቢሰጡ ተገቢውን ትዕዛዝ ለመስጠት፣ መሠረታዊ የክርክር ሒደት ሚዛናዊነትንና ፍትሐዊነት ለመጠበቅ እንደሚረዳ ገልጾ፣ በመሆኑም ምንም እንኳን ለእያንዳንዱ ከሳሽ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ የደረሰበት ማረጋገጫ ባይቀርብም፣ ከሳሾች (እነ አትሌት ኃይሌ) በጠበቆቻቸው አማካይነት በችሎት ስለተገኙ፣ ከሳሾች ከመጥሪያ አደራረስ ጋር ያቀረቡት (ያነሱት) ቅሬታና ጥያቄ ተቀባይነት ስለሌለው ፍርድ ቤቱ እንዳለፈው አስረድቷል፡፡
የከሳሾች ጠበቆች ሌላው ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ፣ የክሱ ጉዳይ የከሳሾችን መብትና ጥቅም ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፣ ከሰፊው ሕዝብ መብትና ጥቅም ጋራ የተያያዘ መሆኑን ነው፡፡ በኦሊምፒክ ኮሚቴ የባንክ ሒሳብ ዕግድ ላይ አስተያየት ለመስጠትም ሰፊ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰው፣ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለችሎቱ እንዳስረዳው፣ ከቴኒስ ፌዴሬሽን በስተቀር ከሳሾች የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ለእያንዳንዳቸው መድረሱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ባይቀርብም፣ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት ይዘው እንዲቀርቡ፣ በአንድም ሆነ በሌላ አግባብ ቀጠሮ መያዙን አውቀው ስላላቀረቡ፣ እንዲሁም ከጉዳዩ አንገብጋቢነትና ውስብስብነት አንፃር የቀረበው ‹‹ዕግድ ይነሳልኝ›› አቤቱታም ግልባጭ በችሎት ተሰጥቷቸው አስተያየት እንዲሰጡ ዕድል ቢሰጣቸውም አስተያየት ለመስጠት ባለመቻላቸው፣ መብታቸው ታልፎ፣ ተከሳሾች መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ባቀረቡት ‹‹ዕግድ ይነሳልኝ›› አቤቱታና የክስ ይዘት መርምሮ ብይን ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን እንዳብራራው፣ ተከሳሾች ባቀረቡት የዕግድ ይነሳልኝ አቤቱታ እንዳስረዱት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተቋቋመው በዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ቻርተርና መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ነው፡፡ ተቋሙ በመንግሥት ስፖርት ፖሊሲ መሠረት፣ ስፖርቱን የሚመራና በመንግሥት ድጋፍ የሚተዳደር ተቋም ነው፡፡ ነገር ግን የኮሚቴው አባል ባልሆኑና አቤቱታ ለማቅረብም መብትና ጥቅም በሌላቸው ሰዎች አማካይነት የቀረበውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ፣ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ዕግድ፣ የተቋሙን አገራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴዎችን የሚገድብና የተቋሙን ቢሮ ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ የሚያደርግ መሆኑን በማብራራት፣ ዕግዱ እንዲነሳለት መጠየቁን አስረድቷል፡፡
ከሳሾች (እነ አትሌት ሻለቃ ኃይለ) ‹‹ዕግዱ ሊነሳ ይገባል? ወይስ አይገባም›› በሚለው ላይ አስተያየት መስጠት እየቻሉ ‹‹ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን›› ብለው መጠየቃቸው ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ መብታቸው መታለፉን በብይኑ አስታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ካቀረበው የክስ ዓይነትና ከተጠየቀው ዳኝነት አንፃር፣ በዋናው የክስ ጉዳዩ ላይ በመደበኛ ችሎት ተገቢው ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ፣ የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ሊነሳ ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መመርመሩን አስታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 151፣ 152 እና 154 (1) ድንጋጌ መሠረት፣ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ፍርድ እስከሚሰጥ ድረስ፣ ለክርክሩ ምክንያት በሆነው ጉዳይ ላይ የሚሰጥ ፍርድ የሚፈጸምበት ንብረት እንዳይበላሽ፣ እንዳይጠፋና ሌላ አላስፈላጊ ጉዳይ እንዳይደርስበት፣ ከፍርድ በፊት ባለበት ሁኔታ ተከብሮ እንዲቆይ ለማድረግ፣ የሚሰጥ ዋስትና ማቅረቢያ፣ ማስከበሪያ፣ የመያዥያና ጊዜያዊ ማግኛ ትዕዛዞች፣ በዋናው ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ፍርድ እስከሚሰጥ ድረስ፣ የተከራካሪ ወገኖች ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት፣ እንግልት ለመቀነስ እንደሚቻል በድንጋጌዎቹ መብራራቱን አስረድቷል፡፡
በዕግድ ትዕዛዙ ላይ ቅሬታ የተሰማው ወገን ዕግዱ እንዲነሳ፣ እንዲሻሻል ወይም እንዲሰረዝ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ለማቅረብ መብት ያለው መሆኑንና እንዲሁም ፍርድ ቤቱ የቀረበው አቤቱታ በበቂ ምክንያት የተደገፈ መሆኑን በተረዳ ጊዜ፣ ከላይ የተጠቀሱትን ለማድረግ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 158 መሠረት ሥልጣን እንዳለውም አብራርቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከሕጉ ድንጋጌ አንፃር ዿጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የተሰጠው ዕግድ፣ ከሳሾች ካቀረቡት የክስ ዓይነትና ከጠየቁት ዳኝነት አንፃር ሲታይ፣ ከሳሾች (እነ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ) በተከሳሾች ላይ የሚጠይቁት የገንዘብ ክፍያ ስለሌለ፣ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስም የተከፈተው የባንክ ሒሳብ ታግዶ የሚቆይበት በቂ የሆነ ሕጋዊ ምክንያት አለማግኘቱን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በተለያዩ ባንኮች የከፈተው የባንክ ሒሳብ ታግዶ እንዲቆይ መደረጉ፣ የተቋሙ ህልውና መቀጠል አለመቀጠል ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተቋሙ የአገሪቱን መንግሥትና ሕዝብ በመወከል፣ በተለያዩ መድረኮች ላይ በመገኘት፣ የአገሪቱን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚከለክል በመሆኑ፣ ዕግዱ ተነስቶ በጉዳዩ ላይ የቀረበው ክርክር ለመታየት የሚከለክለው በቂ የሆነ የሕግ ምክንያት እንደሌለም አብራርቷል፡፡
ተቋሙ ባቀረበው ‹‹ዕግድ ይነሳልኝ›› አቤቱታ ላይ ያቀረባቸው (የጠቀሳቸው) ምክንያቶች የሚያሳዩት፣ ተቋሙ የተቋቋመው በዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ቻርትና መተዳደሪያ ደንብ ነው፡፡ አገራዊ ክንውኖችና እንቅስቃሴዎችን በበላይነት የሚመራ፣ ነፃና ገለልተኛ ተቋም ነው፡፡ በአገር፣ በአኅጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ አገሪቱን በመወከል፣ የአገሪቱን ጥቅምና ጥሩ ስም ከፍ ለማድረግ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣትም ሆነ አጠቃላይ የዕለት ተዕለት አስተዳደራዊ ሥራዎችን እንዳይሠራ፣ የሠራተኞች ደመወዝ፣ የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎችን እንዳይፈጽም የሚያደርግ የዕግድ ትዕዛዝ ነው፡፡
በመሆኑም በከሳሾች የቀረበው የክስ አቤቱታን ዕግድ የሰጠው ፍርድ ቤት፣ ሥልጣን ያለው መሆን አለመሆኑ፣ ከሳሾች ክሱን ማቅረብ የሚያስችላቸው ሕጋዊ ችሎታ፣ መብትና ጥቅም ያላቸው መሆን አለመሆኑን፣ እንዲሁም ጉዳዩ የክስ ምክንያት ያለው መሆን አለመሆኑን፣ ፍርድ ቤት መደበኛ ሥራ ሲጀምር የሚታይ ሆኖ ሳለ፣ በተቋሙ የባንክ ሒሳብና ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ያሳለፈው ውሳኔ፣ ተቋሙና በሚመሩት አካላት ላይ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ዕግድ መጣሱ ከፍተኛ ጉዳት መኖሩን በመረዳቱ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 158 ድንጋጌ መሠረት፣ ዕግዱ የተነሳ መሆኑን አብራርቶ ብይን ሰጥቷል፡፡ ዋናው የክስ አቤቱታ ፍርድ ቤቱ መደበኛ ሥራውን ሲጀምር ለመደበኛ ችሎት እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን፣ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ በዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ ኤደን አሸናፊ (ዶ/ር)፣ በአቶ ዳዊት አስፋውና በአቶ ገዛኸኝ ወልዴ ላይ የፍትሐብሔር ክስ መመሥረታቸውን ረቡዕ መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም. መዘገባችን ይታወሳል፡፡