ዓርብ ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. የጂቡቲ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ ገብቶ በአፋር ክልል ጥቃት አደረስ የሚለው ዜና ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡
የጂቡቲ መንግሥት ጥቃቱን ያደረሰው በድሮን መሆኑ መነገሩ፣ እንዲሁም በጥቃቱ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተጎዱ መባሉ ጉዳዩ የበለጠ ትኩረት እንዲስብ አድርጎ ነበር፡፡ ዓርብ ዕለት ጂቡቲ በኢትዮጵያ ድንበር ጥቃት አደረሰች የሚለው ወሬ የተጎዱ ሰዎችን ከሚያሳዩና ለማየት ከሚያሰቅቁ ፎቶግራፎች ጋር ተያይዞ፣ በማኅበራዊ ገጾችና በተለያዩ የዜና አውታሮች መሠራጨቱ ትልቅ ትኩረት ቢስብም ነገር ግን ጥቃቱ ከዚያን ቀን ቀደም ብሎ ሐሙስ መካሄዱን ዘግይተው የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
ያም ሆነ ይህ ግን በሁለት ወራት ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመ ነው የተባለው ጥቃት ነፍሰ ጡርና ሕፃናትን ጨምሮ በትንሹ ለስምንት ሰዎች ሕልፈት ምክንያት መሆኑ ተነግሯል፡፡
የተለያዩ ፖለቲከኞችን ጨምሮ የአፋር ተወላጅ ማኅበራዊ አንቂዎችና ሌሎችም፣ ይህን የጥቃት ዜና አባሪ በማድረግ ኢትዮጵያ ድንበሯም ሆነ የአየር ክልሏ ተጥሶ ዜጎቿ በጎረቤት አገር መንግሥት የሚገደሉባት ሉዓላዊነቷን መጠበቅ ያቃታት አገር እየሆነች ነው የሚል መረጃ በሰፊው ማጋራት ቀጠሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የአፋር ክልል መንግሥትና ሌሎችም የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ኦፊሴላዊ መረጃ ስለጉዳዩ ሳይሰጡ ቆይተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የጂቡቲ መንግሥት የመከላከያ ሚኒስቴር ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው ኦፊሴላዊ መግለጫ ለጥቃቱ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ የጂቡቲው መግለጫ ጥቃቱ አዶርታ በተባለና በጂቡቲ ሉዓላዊ ግዛት ሥር በሚገኝ መንደር መፈጸሙን ጠቁሟል፡፡ ቦታው ከኢትዮጵያ ድንበር ስድስት ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ መሆኑን በመጥቀስ ለሳምንት ቅኝት በማድረግ፣ በአሸባሪ ድርጅት አባላት ላይ ክትትል በማድረግ፣ ዒላማ የሆኑ አሸባሪዎችን በጥንቃቄ በመለየት የተፈጸመ ነው ሲልም አስታውቋል፡፡ በአጠቃላይ ስምንት አሸባሪዎችን መግደሉንና ጥቃቱ የተፈጸመበት ቦታም የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ሰላማዊ ሰዎችን ለማገት፣ መሠረተ ልማትን ለማውደም፣ እንዲሁም የአሳሌ ሐይቅና የታጁራ ወደብ የንግድ ኮሪደርን ለማወክ ማዕከል አድርገው የሚጠቀሙበት ቦታ እንደሆነ ገልጾ ነበር፡፡ በጥቃቱ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አላስፈላጊና ያልታሰበ ጉዳት መድረሱን ያመነው የጂቡቲ መከላከያ መግለጫ፣ የጉዳቱን መጠን ለማወቅ ምርመራ መደረግ መጀመሩንና ከዚህ ጎን ለጎንም ለተጎጂዎች ሰብዓዊ ዕርዳታም መላኩን አመልክቶ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ሪፖርተር ያናገራቸው የአፋር ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የጂቡቲ መንግሥትን መግለጫ ፈጽሞ ሐሰት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የአፋር ሕዝብ ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መሐመድ ዳውድ ድርጅታቸው ከሌላኛው ከአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ጋር ሆኖ በጉዳዩ ላይ የጋራ መግለጫ ማውጣቱን ገልጸዋል፡፡ የጥቃቱን ምንነትና የደረሰውን ሁኔታ መረጃ ሲያሰባስቡ መሰንበታቸውን፣ ከጥቃቱ ቆስለው የተረፉና በዱፍቲ ሆስፒታል በሕክምና የሚገኙ ሰዎችን በማነጋገር ጭምር መረጃ መሰብሰብ መቻላቸውን ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት ጥቃቱ የደረሰው በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ መሆኑን ማረጋገጣቸውንና የጂቡቲ መንግሥት መግለጫ ሐሰት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
‹‹ጥቃቱ የተፈጸመው በአፋር ክልል ዞን አንድ ውስጥ በሚገኘው ኤልዳር ወረዳ ሲያሩ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ቦታ ለጂቡቲ ቅርብ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ነው ያለው፡፡ የጂቡቲ መንግሥት በየጊዜው ድንበር ጥሶ ገብቶ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ጥቃት ማድረሱ እየተለመደ የመጣ ድርጊት ሆኗል፡፡ በቅርብ ወራት በተመሳሳይ አፋምቦ ወረዳ ገብቶ በዲሽቃና በሞርታር ጥቃት አድርሷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ዝምታ ቢመርጥም ነገር ግን ይህን መሰል ጥቃት በአፋር በኩል ከጂቡቲ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ እየተቃጣ ይገኛል፡፡ ጉዳዩ የፖለቲካ ጨዋታ ያለው ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ድንበሩን መጠበቅ ሲገባው የውጭ መንግሥት የፀጥታ ኃይል ድንበሩን አልፎ ጥቃት መፈጸሙ በእኛ አመለካከት ተቀባይነት የለውም፡፡ የጂቡቲ መንግሥት ለምንድነው በግዛቴ ውስጥ ነው ጥቃት ያደረስኩት እያለ ተራ ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ ዝም የሚባለው? የአፋር ክልል መንግሥትም ቢሆን ይህንን ነገር ማጋለጥ አለበት፤›› በማለት ነው የተናገሩት፡፡
አቶ መሐመድ ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ መግለጫው ይህን በተመለከተ ግልጽ አቋም መያዛቸውንና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲከበር መጠየቃቸውን አስረድተዋል፡፡ የጂቡቲ መንግሥት በተለምዶ ፍሩድ (Front for the Restoration of Unity and Democracy/FRUD) የሚባለውን ትጥቅ አንግቦ የሚንቀሳቀሰውን የአፋር ተወላጆች የፖለቲካ ቡድንን ለመውጋትና ምሽጎቹን ለመደምሰስ በሚል ዘመቻ እንደሚያደርግ መናገሩን በመጥቀስ፣ የአሁኑ ጥቃትም የዚሁ አካል ስለመሆኑ የተጠየቁት አቶ መሐመድ ጉዳዩ እንደዚያ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹አፋር ክልል ውስጥ የተባለው ቡድን በፍፁም አይንቀሳቀስም፡፡ አሁን ጥቃት በፈጸሙበት አካባቢ የተባለው ቡድን በፍፁም የለም፡፡ እነሱ ያሉት ኤርትራ ግዛት ውስጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የአፋር ክልል መንግሥት ቡድኑን እንደሚደግፉት አንዳችም ማረጋገጫ የለም፡፡ ቡድኑ ይልቁንም የኤርትራ አፋሮች ወገን ነው፡፡ እኛ የምናውቀው የኤርትራ መንግሥት እንደሚደግፋቸው ነው፡፡ በኤርትራና በጂቡቲ መካከል እስከ ዛሬም ያልተፈታ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ አለ፡፡ በዚያ አካባቢ ነው የቡድኑ እንቅስቃሴ ያለው፡፡ የጂቡቲ መንግሥት ይህን አሳቦ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃት መፈጸሙ ሆን ተብሎ የተደረገና ሰላማዊውን የአፋርን ሕዝብ ለማሸበር ነው፡፡ ነገሩ ዝም መባሉ ደግሞ የሕዝቡን ቁጣ ሊቀሰቅስ የሚችል ችግር ይሆናል ብለን እንገምታለን፤›› ብለዋል፡፡
የጂቡቲ ፓርላማ በትጥቅ የሚታገለውን የፍሩድ ቡድን እ.ኤ.አ. ጥቅምት 2022 ነበር በሽብርተኝነት የፈረጀው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ቡድኑ ከጥቂት ቀናት በፊት በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ጥቃት ከፍቶ ሰባት ወታደሮችን ገድሎ አራት ደግሞ ማቁሰሉን፣ እንዲሁም ስድስት ወታደሮች የገቡበት አለመታወቁን ተከትሎ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የጂቡቲ ፓርላማ በሰጠው ድምፅ በከፍተኛ ድጋፍ የፍሩድ ቡድንን አሸባሪ ኃይል ነው ሲል ፈርጆታል፡፡ በጂቡቲ መቀመጫውን ያደረገው ቀጣናዊው ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ማኅበር (ኢጋድ) ጥቃቱን ወዲያው አውግዞት የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያም በተናጠል የቡድኑን ጥቃት ማውገዟ ይፋ ተደርጎ ነበር፡፡
ትንሽቱ አገር ጂቡቲ የቀጠናው ኃያል አገር ስትባል የኖረችውን ኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ጥሳና የአየር ክልልም አልፋ በኢትዮጵያውያን ላይ ጉዳት ስታደርስ ለምን ዝም ተባለ የሚለው ቁጭት ከአፋር የተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል ብቻ ሳይሆን፣ ከብዙ አቅጣጫዎች ሲንፀባረቅ ነው የሰነበተው፡፡ ከሁለት ወራት ቀደም ብሎ የጂቡቲ መንግሥት በተመሳሳይ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በአፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ ጥቃት አደረሰ ከመባሉ እንዲሁም ከዚያ ቀደም ይሰሙ ከነበሩ ተመሳሳይ ክሶች ጋር ተዳምሮ ጉዳዩ የተጋጋለ ሙግት ሲደረግበት ነው የሰነበተው፡፡ ጂቡቲ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ተደጋጋሚ ጥሰት የፈጸመችው የኢትዮጵያን ውስጣዊ አለመረጋጋት ተገን አድርጋ ነው የሚለው መላምት ደግሞ ብዙዎችን ሲያስቆጭ ነው የሰነበተው፡፡
ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ጋር ድንበር ከመዋሰን ባለፈ ከ90 በመቶ በላይ የወጪና የገቢ ንግዷን የምታካሂድበት ወደብም ናት፡፡ ሁለቱ አገሮች አንድ አገር ሆነው የኖሩበት ዘመን እንደነበር ታሪክ ቢያስረዳም፣ ተነጣጥለው ሁለት ሉዓላዊ አገር ከሆኑ ወዲህም ቢሆን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ሁለንተናዊ ግንኙነታቸው ሳይነጣጠል የዘለቀ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያና ጂቡቲ ከወደብ አገልግሎት በተጨማሪ በሕዝቦቻቸው ማንነትና ቋንቋ የተሳሰሩም ናቸው፡፡ ጂቡቲ ውስጥ አፋርና ሶማሌዎች በዋናነት እንደሚኖሩት ሁሉ፣ በኢትዮጵያም ሁለቱ ሕዝቦች በሰፊው የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ተዛምዶ በሁለቱ አገሮች መካከል የመኖሩን ያህል እንደ ሰሞኑ የድሮን ጥቃት ሁሉ የሁለቱን አገሮች የሚፈታተኑ ችግሮች መከሰታቸው ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ አንዳንዶች የዚህን መነሻና ምንጭ ሲናገሩ ጂቡቲ ቀን ጠብቃ ጎረቤት ኢትዮጵያን የሚጎዳ እንቅስቃሴ ስታደርግ የቆየች መሆኗን ያስረዳሉ፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ ተመራማሪውና የዲፕሎማሲ ታሪክ አጥኚው በለጠ በላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ የትብብርና የውዝግብ ታሪክ›› በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ስለጂቡቲ በርካታ ሐሳቦችን አስፍረዋል፡፡ ‹‹ከተቀሩት የጎረቤት አገሮች ጋር ሲነፃፀር ኢትዮጵያ ለጂቡቲ የምትሰጠው ቦታ በእጅጉ ይለያል፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት የግለሰቦችና የፓርቲ ግንኙነት መደረጉ ይበቃ ይሆናል፡፡ ከሱዳንና ከሶማሊያ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ደግሞ ከተወሰኑ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር የሚፈጠሩ ተግባቦቶች በቂ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ከጂቡቲ ጋር ግን ከግለሰብና ከቡድን ባለፈ የአገር ለአገር (የመንግሥት ለመንግሥት) ግንኙነት ከማድረግ የተለየ አማራጭ የለም፡፡ ከኤርትራ፣ ከሱዳንና ከሶማሊያ ጋር ያለው ግንኙነት ቢበላሽ የኢትዮጵያ ህልውና ከመቀጠል አይስተጓጎልም፡፡ አንዳንዴም በተሻለ መንገድ የሚመራበት ዕድል ጭምር ተከስቷል፡፡ ጂቡቲን በተመለከተ ግን የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ ይልቁንም ጂቡቲ ኢትዮጵያ ከምትፈልጋት በላይ ኢትዮጵያ ጂቡቲን ትፈልጋለች፡፡ በተለይም አሁናዊ ነባራዊ ሁኔታ ሲታይም ኢትዮጵያ በጂቡቲ ላይ ያላት ጥገኝነት በማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤›› በማለት ጽፈዋል፡፡
በለጠ (ዶ/ር) እንደሚተርኩት ኢትዮጵያ በውስጥ ፖለቲካዋ መዳከሟ ወይም መጠናከሯ ከጂቡቲ ጋር ያላትን ግንኙነት ደረጃ ሲወስን ቆይቷል፡፡ ‹‹በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥታት በአንፃራዊ መልኩ ሲዳከሙ ከጂቡቲ ወገን የሚመጡ ጫናዎች ሲበረክቱና የሚከፈሉ መስዋዕትነቶችም ሲጨምሩ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥታዊና አገራዊ ቁመና ስታበጅ የትብብርና የወዳጅነት አዝማሚያው ከጂቡቲ ወገን ሲጨምር ነው የታየው፤›› በማለት ተመራማሪው አክለዋል፡፡
ያም ቢሆን ግን ኢትዮጵያን መዳከሟን እያየ ሊጎዳት የማይፈልግ የጎረቤት አገር ጥቂት መሆኑን ብዙዎች ያወሳሉ፡፡ ለምሳሌ የትግራይ ጦርነት በፈነዳበት ወቅት ሱዳን ቀን ጠብቃና አጋጣሚውን ተገን አድርጋ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት አድርሳለች የሚለውን ሐሳብ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር በቅርብ ዓመታት ተናግረውታል፡፡ ሱዳኖች የትግራይ ጦርነትን መቀስቀስ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ድንበር መግባታቸውንና አወዛጋቢውን የአልፋሽቃ መሬት መያዛቸውን ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ደግሞ በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት መክፈታቸውን፣ ያሸተ ሰብልና ብዙ ንብረት መዝረፋቸውን ይጠቅሱታል፡፡
የትግራይ ጦርነት መቀስቀስ ለኤርትራም የቆየ ቂም መወጫና በቀል መፈጸሚያ አጋጣሚ ፈጥሮላታል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ የኤርትራ መንግሥት ኃይሎች ድንበር አልፈው በትግራይ ጦርነት የተካፈሉት በሕወሓት አስገዳጅ ጠብ አጫሪነትና ጦርነቱን ቀጣናዊ የማድረግ ፍላጎት የተነሳ መሆኑን ብዙዎች ይከራከራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩን ከዚህ በተቃራኒ የሚያዩት ወገኖች ኤርትራ አጋጣሚውን ተጠቅማ በሕወሓት ላይ ያሳደረችውን የቆየ ቂም ለመወጣት፣ አለፍ ሲልም በትግራይ ሕዝብ ላይ ወረራና ዘረፋ ለመፈጸም አውላዋለች የሚለል ጠንካራ መከራከሪያ ሲያቀርቡ ይደመጣል፡፡
ከደቡብ ሱዳን የተነሱ ታጣቂዎችም ቢሆን ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ብዙ ኪሎ ሜትሮች ዘልቀው ገብተው የወርቅ ዘረፋና ወረራ ያደረጉት፣ የኢትዮጵያን መዳከም አስልተው ነው የሚል ሐሳብ የሚያነሱ አሉ፡፡ ሶማሊያም ብትሆን የኢትዮጵያን አለመረጋጋት በማየት ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማድረስና የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይልን አልፈልግም ብላለች የሚሉም አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደከም ባለችባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ እንደ ኬንያ ካሉ ጎረቤቶቿ በስተቀር ዙሪያዋን የከበቡ ብዙ አገሮች መንግሥታት ሊያጠቋትና ጫና ሊያደርጉባት ሞክረዋል የሚሉት እነዚህ ወገኖች፣ የጂቡቲም ሰሞነኛ ዕርምጃ ከዚህ የተለየ አለመሆኑን ነው የሚያክሉት፡፡
የጂቡቲ የአገርነት አፈጣጠር ታሪክ እንደሚጠቁመው ከሆነ እ.ኤ.አ. በ1977 ነበር ራሷን የቻለች ነፃ አገር ለመሆን የበቃችው፡፡ በወቅቱ ዋና ዋና ጎሳዎች በሆኑት አፋርና ኢሳ ማኅበረሰቦች መካከል የፖለቲካ ሥልጣን ይገባኛል ፉክክር ከፍተኛ እንደነበርም ይነገራል፡፡ ያም ሆኖ የአፋር ማኅበረሰብን እወክላለሁ የሚለው ፍሩድ የተባለው ኃይል እ.ኤ.አ. በ1994 የሰላምና የብሔራዊ ዕርቅ ስምምነት ከመንግሥት ጋር በመፈራረሙ የጂቡቲ ችግር ይፈታል የሚል እምነት አሳድሮ መቆየቱ ይጠቀሳል፡፡ ይሁን እንጂ ቃል የተገባው የሥልጣን ክፍፍል ባለመተግበሩና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጂቡቲ ባለመፈጠሩ ቡድኑ ከመንግሥት ጋር ዳግም ወደ ግጭት እንዲገባ እንዳደረገው ይነገራል፡፡ ሥልጣን በአንድ ጎሳ በተለይም በኢሳ ማኅበረሰብ የበላይነት ወደቀ የሚል ሙግት የሚያነሳው የአፋሩ ቡድን በሒደት በትጥቅ ወደ መታገል መግባቱም ይገለጻል፡፡
ጂቡቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ይህን ቡድን እያሳበበች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጥሳ ገብታ ጥቃት ትፈጽማለች የሚለው ክስ ጎልቶ ቢደመጥም፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ በቅጡ ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጥ እስካሁን አልታየም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ዝምታን የመረጠው ደግሞ ጂቡቲ ለኢትዮጵያ ያላትን ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ላለማጣት ሲል እንደሆነ ይነገራል፡፡
ይሁን እንጂ ጂቡቲ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ የምትገባውና ሉዓላዊነት ስትጥስ የምትታየው ሌላም ድብቅ አጀንዳ የጂቡቲ መንግሥት ስላለው እንደሆነ የአፋር ሕዝብ ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲው ሊቀመንበር አቶ መሐመድ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የጂቡቲ መንግሥት ከሶማሊያ መንግሥታት ጋር አብሮ የታላቋ ሶማሊያ አጀንዳን ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መካከል የወሰን ይገባኛል ውዝግብ መነሳት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ሆን ብሎ ጣልቃ በመግባት፣ ከሶማሌ ክልል ኃይሎች ጋር ወግኖ በአፋር ክልል ላይ ጥቃት ማድረስ መቀጠሉ ይታወቃል፡፡ የጂቡቲ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ መግባቱና በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ጥቃት ማድረሱ ሁሉ መላው ኢትዮጵያን የሚፈታተን ችግር ነው፤›› ይላሉ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ዝም መባል የለበትም የሚሉት ፖለቲከኛው፣ ጂቡቲ በዚህ ከቀጠለች የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ችግር በአፋር ክልልም ሆነ በሌሎች አጎራባች ክልሎች ውስጥ ሊፈጠር እንደሚችል ነው ሥጋታቸውን ያስረዱት፡፡
ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የባህር በር አጀንዳን ለፓርላማ አባላት ይፋ ሲያደርጉ በታሪክ፣ በጂኦግራፊ፣ በኢኮኖሚና በዘር ባሏቸው መነሻ ምክንያቶች ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት እንደሚገባት ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹አፋሮች ጂቡቲም አሉ፣ ኤርትራም አሉ፡፡ እስከ ዛሬ ዓመት ድረስ አፋሮች ሡልጣን ሲመርጡ የጂቡቲና የኤርትራ አፋሮች መጥተው በውክልና አሳይታ ነው ሡልጣናቸውን የሚመርጡት፡፡ ሆኖም ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ አፋሮች በቀጭኑ ተሰምሮ ከቀይ ባህር ጋር እንዳይገናኙ ተደርጓል፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጀንዳ አርገው ያነሱት የባህር በር ጉዳይ በሒደት ደግሞ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ጎልቶ እንዲነሳ ተደረገ፡፡ ይህ ደግሞ ከሶማሊያ በኩል ጠንካራ ምላሽ የፈጠረ ሲሆን፣ ሶማሊያ ኤርትራና ግብፅን ጭምር አሰባስባ በኢትዮጵያ ላይ ከባድ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በዚህ ወቅት ጂቡቲ ገላጋይ መስላ ስትቀርብ፣ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን በመጠቀም ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት እንድትተውና ከሶማሊያ ጋር መግባባት እንድትፈጥር የጂቡቲ ባለሥልጣናት ሐሳብ ሲሰጡ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ጂቡቲ ከአስታራቂነት ይልቅ ከሶማሊያ ጎን የመቆም አዝማሚያ ይታይባታል ያሉ አንዳንድ ወገኖች፣ ታጁራ ወደብን ለኢትዮጵያ ተጠቀሚ ብትልም የባህር ኃይል በወደቡ ማስፈር እንዳትችል መከልከሏን አንድ ምክንያት አድርገው ሲያቀርቡት ቆይተዋል፡፡ ጂቡቲ ከዚህ በተጨማሪም ከቻይና እስከ አሜሪካና ፈረንሣይ በድምሩ ወደ አሥር ለሚጠጉ አገሮች የባህር ኃይል የጦር ሠፈር የፈቀደች ሲሆን፣ ለጎረቤቷ ኢትዮጵያ ግን ተመሳሳይ ፈቃድ ለመስጠት ማመንታቷ አገሪቱ ለኢትዮጵያ ተአማኒ ጎረቤት እንዳልሆነች ማሳያ ነው ሲሉም ተከራክረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ከሰሞኑ ጂቡቲ እየፈጸመችው ነው ከተባለው ጣልቃ ገብነትና የሉዓላዊነት ጥሰት ጋር ተዳምሮ፣ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወዴት ይወስደዋል የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ እንዲሆን አድርጎታል፡፡