ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 reliable news source in Ethiopia

[ክቡር ሚኒስትሩ የደኅንነት ኃላፊው ጋር ደውለው የተፈጠረውን ነገር እያጣሩ ነው]
ሃሎ?
- ሃሎ… ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር።
- ምንድነው የምሰማው?
- ምን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
- ስታዲየም አካባቢ ምንድነው የተፈጠረው?
- አባሎቻችንን ልከን ተጨማሪ ማጣራት እያደረግን ነው። ነገር ግን…
- ግን ምን?
- አሳሳቢ ነገር አለመሆኑን አረጋግጠናል።
- ታዲያ ለምንድነው በርካታ የሕግ አስከባሪ አባላት እንዲሰማሩ የተደረገው?
- የተፈጠረው ነገር ከስታዲየሙ ሳይወጣ ለመቆጣጠር ታስቦ ነበር።
- ስለዚህ አሁን በቁጥጥር ሥር ውሏል ማለት ነው።
- ሥጋት እንጂ የተፈጠረው ነገር እንኳ ያን ያህል ትከረት ሊሰጠው የሚገባ አልነበረም።
- ምንድነው የተፈጠረው?
- የአንዱ ክለብ ደጋፊዎች ታዳሚው ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማት ጀምረው ነው።
- ምን እያሉ ነው ተቃውሞ ያሰሙ የነበሩት።
- ውረድ እያሉ።
- ውረድ?
- አዎ!
- ማንን ነው ውረድ የሚሉት?
- ክቡር ሚኒስትር እኛም ሌላ ነገር መስሎን ነበር የሠጋነው… በኋላ ግን…
- እ… ግን ምን?
- አባሎቻችን ቦታው ላይ ደርሰው ሲያጣሩ ነገሩ ሌላ ሆኖ አግኝተውታል።
- ምን ሆኖ አገኙት?
- የስም መመሳሰል ነው ክቡር ሚኒስትር።
- የስም መመሳሰል ስትል ምን ማለትህ ነው?
- አለቃን አልነበረም ማለቴ ነው።
- ምኑ?
- ይውረድ የሚሉት።
- እና ማንን ነው?
- አሠልጣኙን ነው።
- እና አሁን በቁጥጥር ሥር ውለዋል?
- ምኖቹ?
- ተቃውሞውን ሲመሩ የነበሩ ደጋፊዎች?
- አልተያዙም።
- ለምን?
- ነገሩ ስፖርታዊ ጉዳይ መሆኑን ስለተረዳን እንዲበተኑ ብቻ ነው ያደረግነው።
- እንዴት?
- አቤት ክቡር ሚኒስትር?
- ወረድ የሚሉት በአሠልጣኙ ስም አስታከው ቢሆንስ?
- አሃ…. እሱን አልመጣልኝም ነበር።
- በል በአስቸኳይ በቁጥጥር ሥር አውሏቸውና በደንብ አጣሩ!
- ምኑን?
- የጀርባ ታሪካቸውን።
[ ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው ] - አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለግኩት ክቡር ሚኒስትር?
- እርስዎማ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግዎትም። ምን ገጠሞት?
- እኔማ ምን ይገጥመኛል፣ አንተኑ ልጠይቅህ እንጂ?
- ምን?
- እውነት ለመናገር የማየው ነገር አሳስቦኛል።
- ይንገሩኝ ምንድነው ያሳሰበዎ?
- ሌት ተቀን የሚሠራው ነጋዴ እየከሠረ ነው።
- መቼም የውጭ ኃይሎች የፈጠሩብንን ችግር ያውቁታል።
- ከእሱ አይገናኝም ክቡር ሚኒስትር!
- እንዴት?
- ሌት ተቀን የሚሠራ ታታሪ ነጋዴ ችግር እሱ አይደለም።
- ምንድን ነው?
- ታታሪ ነጋዴ እየመነመነ ሳለ በተቃራኒው ግን…
- በተቃራኒው ምን?
- በድንገት ሀብታም የሚሆኑ ሰዎች እንደ አሸን እየፈሉ ነው።
- ምን ማለትዎ ነው?
- ጠንክሮ መሥራት ሀብት የሚፈጠርበት መንገድ መሆኑ ቀርቶ ሌላ መንገድ ተፈጥሯል እያልኩ ነው።
- የምን መንገድ?
- ሲነጋ ሀብታም መሆን የሚቻልበት መንገድ።
- እሱ እንዴት ሊሆን ይችላል?
- እኔም የገረመኝ እሱ ነው፡፡
- ምኑ ነው የገረመህ?
- ሲነጋ ሀብታም ሆነው መገኘታቸው፡፡
- እሱማ ሊገርምህ አይገባም፡፡
- እንዴት አይገርመኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በቀላሉ የሚጣራ ስለሆነ ነዋ!
- ምኑ ነው በቀላሉ የሚጣራው?
- ሌሊቱን ሲሠሩ አድረው ያፈሩት ሀብት ከሆነ ነዋ!
- ካልሆነስ ክቡር ሚኒስትር?
- ካልሆነማ በቁጥጥር ሥር ይውላሉ፡፡
- እስከ መቼ ነው በቁጥጥር ሥር የሚቆዩት?
- እስከሚጣራ!
The post [ክቡር ሚኒስትሩ የደኅንነት ኃላፊው ጋር ደውለው የተፈጠረውን ነገር እያጣሩ ነው] first appear on ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 reliable news source in Ethiopia and is written by በጋዜጣው ሪፓርተር