መንግሥት በመላ አገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን ለመወሰን ቢያስብም፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የበለጠ ይሆናል በሚል ሥጋት ከመወሰን መቆጠቡ ተሰማ።
ሪፖርተር ለጉዳዩ የበለጠ ቅርበት ካላቸው አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን እንደሰማው፣ መንግሥት በመላ አገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ የሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን ለመወሰን ጥናት አካሂዶ አጠናቋል። ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ የሠራተኞች የሥልጠናና የክህሎት ደረጃ፣ እንዲሁም የአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ለሠራተኞች የሚከፈል ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን ወስኖ ተግባራዊ ማድረግ ከሚኖረው ጠቀሜታ ይልቅ ጉዳቱ የሚያይል በመሆኑ፣ ማዘግየትን እንደመረጠ ሪፖርተር ለጉዳዩ ቅርበት ከሆኑት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ለማወቅ ችሏል።
‹‹ጥናቱን ጨርሰናል፣ ነገር ግን የሚያስከትለው ተፅዕኖ ስላለ ምክክር እያደረግንበት ነው፤›› ሲሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።
መንግሥት በአገሪቱ ያሉ ሠራተኞች ያሉበትን ሁኔታና የሚያገኙት ደመወዝ ኑሯቸውን ለመግፋት ከበቂ በታች መሆኑን እንደሚረዳ የተናገሩት የመረጃ ምንጩ፣ መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን በዚህ ወቅት ከመወሰን ይልቅ ለማዘግየት የፈለገው ለሠራተኞች ጥቅምና ሊፈጠር የሚችለውን ማኅበራዊ ቀውስ በመገንዘብ እንደሆነ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ከሚገኙት ሠራተኞች ውስጥ አብዛኞቹ በቂ ሥልጠና የሌላቸው ዝቅተኛ ተከፋይ ሠራተኞች መሆናቸውን የጠቀሱት ምንጩ፣ እነዚህን ሠራተኞች በቂ ሥልጠናና ክህሎት ሳይኖራቸው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን በሕግ መወሰን ሠራተኞቹን መልሶ እንደሚጎዳ ተናግረዋል።
የመረጃ ምንጩ እንደሚለት፣ መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን በሕግ ቢወሰን አሠሪዎች የሠለጠኑና ክህሎት ያላቸው ሠራተኞችን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ አብዛኛውን ዝቅተኛ ተከፋይ ሠራተኛ ከሥራ ውጪ በማድረግ ማኅበራዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል።
‹‹ዝቅተኛ የደመወዝ መጠንን በሕግ ማስቀመጥ ሥራ አጥነትን፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ቀውስን ሊያስከትል ይችላልና ይህንን ሁኔታ ማገናዘብ ይጠይቃል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ እንዲዘገይ ተደርጓል፤›› ብለዋል።
የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ስተርን የተሰኘው የቢዝነስና የሰብዓዊ መብት ጥናት ማዕከል እ.ኤ.አ. በ2019 ባወጣው ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ጀማሪ ሠራተኞች የሚከፈለው ወርኃዊ ደመወዝ 26 ዶላር ወይም ከ750 ብር ያነሰ መሆኑንና ይህም ከዓለም ዝቅተኛው ደመወዝ እንደሆነ በመጥቀስ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍኤስኤስ)፣ ‹‹የሴት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታና ለውጦች በኢትዮጵያ፣ በተመረጡ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች የተገኙ ተሞክሮዎች›› በሚል ርዕስ ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች (በዋናነትም ሴት ሠራተኞች) የሚከፈላቸው ደመወዝ የመሠረታዊ ፍላጎቶች ወጪዎቻቸውን በቅጡ እንደማይሸፍኑ፣ ይህም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየናረ በመጣው የዋጋ ግሽበት የበለጠ መባባሱን አስታውቋል።
ኤፍኤስኤስ በተመረጡ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ላይ ባካሄደው ጥናት፣ በፋብሪካዎቹ ውስጥ የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች ሲቀጠሩ 1,280.86 ብር ያገኙ እንደነበር፣ በአሁኑ ጊዜ በፋብሪካዎች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በወር በአማካይ 2,066 ብር እንደሚከፈላቸው አረጋግጧል።
በጥናቱ ውስጥ የተሳተፉ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ለሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ በዳሰሳ ጥናት ከተሳተፉት ውስጥ 32 በመቶ የሚሆኑት ሴት ሠራተኞች የሚያገኙት ገቢ የዕለት ተዕለት ወጪያቸውን በተገቢ መንገድ እንደማይሸፍንላቸው ጥናቱ አመላክቷል፡፡
በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች በቂ ክፍያ አለማግኘታቸውን ከመቅረፍ አንፃር በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ አለመሆኑን፣ እንዲያውም መንግሥት ኢትዮጵያ ከዓለም አገሮች በጣም ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ሠራተኞች ያሉባት አገር መሆኗን በኩራት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ መጠቀሚያ ማድረጉን ኤፍኤስኤስ በአሉታዊነት አንስቷል።
የተሻሻለው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ በሚደነግገው መሠረት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ባገናዘበ መንገድ አነስተኛ ደመወዝ እንዲወሰን፣ ለዚህም የደመወዝ ቦርድ ተቋቁሞ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን እንዲወስን በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም ምላሽ አለመገኘቱንና ጉዳዩን ችላ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መጠንን በተመለከተ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ጥናት ተደርጎ መጠናቀቁን ስለማሳወቃቸው በመጠቆም፣ ኮንፌዴሬሽኑ ይህንን ጉዳይ ያውቅ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቂ፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መጠን የሚወስነው የደመወዝ ቦርድ ከተቋቋመ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኮንፌዴሬሽኑ የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን በመንግሥት በኩል ሥራ ስለመጀመሩም ሆነ ጥናት ስለመደረጉ የሚያውቀው ጉዳይ እንደሌለ ገልጸው፣ ጉዳዩ መንግሥት ብቻ ሳይሆን አሠሪም ሆነ ሠራተኛው ጭምር የሚሳተፍበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መጠንን በሚመለከት ቦርድ ከተቋቋመ በኋላ ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም እንደሚያደርግ፣ ይህ ጽሕፈት ቤት ‹‹የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መጠን ስንት ይደረግ?›› የሚለውን ጥናት ካካሄደ በኋላ ቦርዱ እንዲወስን የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዝቅተኛ ደመወዝ ወለል መጠን ሲወሰን አጠቃላይ ማኑፋክቸሪንግ ላይ ያለው ሠራተኛ፣ በፋብሪካ፣ በእርሻ፣ እንዲሁም በመንግሥት የልማት ድርጅት ውስጥ ያሉ ሠራተኞችን ከገበያ ወይም ከሥራ ወጪ እንደማያደርግ አክለው ገልጸዋል፡፡
‹‹የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መጠን በዓለም አቀፍ መረጃ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህ መሠረት የደመወዝ ወለሉ መጠን ቢወሰን ይህንን መክፈል የማይችል ድርጅትም ሆነ ፋብሪካ እንደማይኖር አስረድተዋል፡፡
የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መጠን እንዲኖር የአሠሪዎች ተወካዮች ተሰባስበው መስማማታቸውን ገልጸው፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጭምር ‹‹መንግሥት ይህንን ጉዳይ መቼ ነው የሚወስነው?›› በማለት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ይወሰናል በማለት ሲጠብቁ ቆይተው ውሳኔው በመዘግየቱ በራሳቸው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መጠን የወሰኑ ተቋማት እንዳሉ፣ ለአብነትም የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አንዱ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የየዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መጠን ቢወሰን አንድም ምርትና ምርታማነት ይጨምራል፣ በሌላ በኩል ደግም ሠራተኛው በተነሳሽነት እንዲሠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡