መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲውን ካስተዋወቀ ከሐምሌ ወር ወዲህ፣ በበርካታ ምርቶችና አገልግሎቶች ዜጎች ከበድ ያሉ የዋጋ ጭማሪዎች እያረፉባቸው ነው፡፡ ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚገቡ የፋብሪካና የግብርና ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን፣ ብዙዎቹ መንግሥታዊ አገልግሎቶችም በተለያዩ መጠኖች የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በሁሉም የምግብ ምርቶች፣ በሕዝብ ትራንስፖርት፣ በውኃ፣ በኤሌክትሪክ፣ በቴሌኮም፣ በነዳጅ፣ በፓስፖርት፣ በመንጃ ፈቃድ ማውጫና ዕድሳት፣ በተሽከርካሪ ምርመራ፣ በሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ፣ እንዲሁም በሌሎች አገልግሎቶች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስና ታሪፎች በከፍተኛ መጠን ጭማሪዎች ተደርገዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጭማሪዎች የዜጎችን ወገብ እያጎበጡ ነው፡፡ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት የኑሮ ውድነቱን የሚያቀሉ ተግባራት ላይ በፍጥነት መሰማራት ይኖርበታል፡፡ ከእነዚህም መካከል የዋጋ ንረቱን የሚያረግቡ መሠረታዊ ዕርምጃዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ከዜጎች ኑሮ በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር የለም፡፡
መንግሥት ከእነ አይኤምኤፍና ከዓለም ባንክ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ገበያውን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ መሠረት የሚጥሉ ተግባራት ሲከናወኑ፣ በዜጎች ሕይወት ላይ አሉታዊ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ጭማሪዎች ካልታሰበባቸው የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አይቻልም፡፡ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድናት፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም መስኮች ዕምቅ ፀጋዎችና አቅሞች ያላት አገር ውስጥ ሰላም በመጥፋቱ ብቻ በሚፈለገው መጠን መንቀሳቀስ ሳይቻል ዕድገት ማስመዝገብ አይታሰብም፡፡ ከሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራዎች ሲቀላጠፉ፣ መንግሥት መሰብሰብ ያለበት ገቢ አሁን ካለው በጣም በተሻለ ማደግ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ሰላም ጠፍቶ ተፈላጊው ልማት ሳይከናወንና የዜጎች ገቢ ሳያድግ የዋጋ ጭማሪዎች በተከታታይ ሲደረጉ፣ ኢኮኖሚው ራሱን በራሱ ጠልፎ እንደሚጥል የታወቀ ነው፡፡ መንግሥት ገቢውን ሲያሳድግ የዜጎችም ማደግ ይኖርበታል፡፡
መንግሥት የዜጎች ኑሮ ጉዳይ በእጅጉ ሊያሳስበው ይገባል፡፡ አንድ ቤተሰብ ለምግብ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለውኃ፣ ለኤሌክትሪክ፣ ለስልክ፣ ለትራንስፖርት፣ ለልጆች ትምህርት ቤትና ለመሳሰሉት አብቃቅቶ መቆጠብ የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ብቻ ሳይሆን ወርኃዊ ወጪውን መሸፈን እያቃተው ነው፡፡ በመካከለኛ ገቢ ይተዳሩ የነበሩ ቤተሰቦችም ሆኑ ግለሰቦች የኑሮ ውድነቱን መቋቋቋም እየተሳናቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እጅግ በጣም ጥቂት ከሚባሉት በስተቀር ብዙኃኑ ሕዝብ ወደ ከፋ ድህነት አዘቅት ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ሁሉም ምርቶችና አገልግሎቶች በተከታታይ የጨመሩባቸው ዜጎች ገቢያቸው ባለበት እየዳከረ መሆኑን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው፡፡ መንግሥት ይህንን ሁኔታ ተገንዝቦ ለመፍትሔ የሚረዱ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ማመላከት ይጠበቅበታል፡፡ በዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ምክንያት በሌሎች አገሮች የደረሱ ቀውሶችን እዚህም ከማስተናገድ በፊት በጥልቀት ይታሰብበት፡፡
ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች በብዙ አገሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያቀርቧቸው ምክረ ሐሳቦችም ሆኑ አስገዳጅ መደራደሪያዎች፣ ኢኮኖሚን ምስቅልቅል ውስጥ በመክተት የዜጎችን ሕይወት ከማተራማስ በስተቀር ያስገኙት አዎንታዊ ውጤት እንደሌለ የብዙ አገሮችን ተሞክሮ ማየት ይቻላል፡፡ በብዙ አገሮች ዜጎች በብዛት ሥራዎቻቸው እንዲያጡ፣ በተደራራቢ ታክሶች እንዲመቱና ለኑሮ ውድነት እንዲጋለጡ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል አገሮች ብድርና ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ በራቸውን እንዲከፍቱና ያሏቸውን አትራፊ የልማት ድርጅቶች በፕራይቬታይዜሽን ስም ለውጭ ኩባንያ እንዲሸጡ ይገደዳሉ፡፡ የመደራደር አቅማቸው ተስፋ በሚሰጣቸው ብድርና ድጋፍ እየተገደበ በሚወስዷቸው የፖሊሲ ዕርምጃዎች ምክንያት፣ ዜጎች አይተውት ለማያውቁት የኑሮ ውድነት ይጋለጣሉ፡፡ ጥድፊያ የተሞላባቸው የፖሊሲ ዕርምጃዎች በተከታታይ ሲወሰዱ፣ ከምርትና ከምርታማነት ይልቅ ገቢ መሰብሰብ ትልቁ ትኩረት ይሆናል፡፡ በመሀል የዋጋ ንረትን ለማውረድ መደረግ ያለበት ጥረት ተረስቶ ኑሮ ይከብዳል፡፡
ኢትዮጵያ ለማደግ ትልቅ ተስፋ ያላት አገር እንደሆነች ማንም የሚገነዘበው ነው፡፡ መንግሥት በጥናት ላይ የተመሠረቱ አዋጭ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን ሲወስድ፣ የጠፋው ሰላም እንዲመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ፣ እንዲሁም የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን በተለያዩ ማበረታቻዎችና ማትጊያዎች መሳብ ሲችል ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ አያቅትም፡፡ በተለይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የታክስ ዕፎይታና የሚያሠራ ከባቢ መፍጠር መቻል ያስፈልጋል፡፡ ብዙዎቹ ታዳጊ የነበሩ አገሮች ወደ ተሻለ ደረጃ የተሸጋገሩት ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ኢንቨስትመንት ምርጥ መዳረሻ መሆን በመቻላቸው ነው፡፡ በስንት መከራ የተገኘ ኢንቨስትመንትን በረባ ባልረባው እያስመረሩ ሌላ ይመጣል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ሕዝቧ በመልካም ስሜት ለሥራ ታጥቆ የሚነሳባትና የተረጋጋች አገር መገንባት የሚቻለው፣ ሰላም የሚነሱና ኑሮን የሚያከብዱ ድርጊቶችን ገለል በማድረግ ነው፡፡
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ በልዩ ልዩ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ተከታታይ የዋጋ ጭማሪዎች ሲደረጉ፣ ገቢና ወጪ ስለማይመጣጠኑ በዜጎች ላይ ከባድ ችግር እንደሚደርስ የታወቀ ነው፡፡ በተለይ በመንግሥት አገልግሎቶች ላይ በተከታታይ ጭማሪዎች ከሚደረጉ ይልቅ፣ ሁኔታዎች እየታዩ ቀስ በቀስ በሒደት ቢሆን ቢያንስ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ሁሉም ነገር ከአቅማቸው በላይ እየሆነባቸው ሲሆን፣ በተነፃፃሪ የተሻለ ኑሮ የነበራቸው ደግሞ ከዕለት ወደ ዕለት ወደ ድህነት ወለል እየወረዱ ነው፡፡ በዚህ መነሻ መንግሥት የዋጋ ንረቱን የሚያረጋጉ የፖሊሲ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ በተጣበበ ሁኔታ ውስጥ የመንግሥት ገቢ መጨመር ላይ ብቻ ሳያተኩር፣ ምርትና ምርታማነት በብዛት እንዲጨምርና ኢኮኖሚው ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የዜጎች ኑሮ ከአቅም በላይ እየሆነ መቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ ስለተደረሰ መንግሥት በፍጥነት መረጋጋት ይፍጠር!