በዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ
- መነሻ
ይህን ለመጻፍ ያነሳሳኝ የሚከተለው አጋጣሚ ነው። አራት ኪሎ አቅራቢያ ለከተማው እንግዳ የምትመስል ልጅ፣ ከቅጥቅጥ አውቶቡስ ወርዳ አብረዋት የተሳፈሩትን ሰዎች ‹‹ብልፅግና የቱ ጋ ነው?›› በማለት ደጋግማ ብትጠይቅም የሚጠቁማት አጣች። ተሳፋሪዎቹን ትታ አላፊ አግዳሚውን መጠየቅ ጀመረች። አብዛኛው ሰው ‹‹አላውቅም›› በሚል ቸልታ ያልፋት ያዘ። ስልክ ደወለችና አድራሻውን አጣራች። ዘመዶቿ ወይም ወዳጆቿ ‹‹ብልፅግና ጋ እንገናኝ›› ብለዋት ይመስለኛል። ስልኩን ዘግታ ‹‹የብልፅግና ጽሕፈት ቤት የት ነው?›› የሚል ጥያቄ ቀጠለች። አንድ መንገደኛ፣ ‹‹ሕንፃው ከሆነ ያውልሽ፣ ብልፅግናውን ግን እርሺው›› ብሎ ጽሕፈት ቤቱን በርቀት ጠቆማት። ይህ ጉዳይ ከዚህ ቀደም በቀልድ መልክ የተነገረው ለፍትሕ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ነበር። በዕውን ሲገጥመኝ ደነቀኝ። ነዋሪው በዚህ ደረጃ ለብልፅግና በተለይም ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት ባይተዋር ነው ወይ የሚል በውስጤ ተኝቶ የከረመ አንድ ጥያቄም ቀሰቀሰብኝ።
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የከተማ ልማትና የነዋሪዎችን ኑሮ በተመለከተ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ወይም ዓይነተኛ የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ አይደለም። ከታዘብኩትና ከሰማሁት፣ እንዲሁም በጥቂቱ ካነበብኩት በመነሳት የተያዘው የዕድገትና የልማት አካሄድ ሊፈጥራቸው የሚችሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጤቶችን ለመጠቆም ነው። በመሆኑም፣ በዚህ ጽሑፍ የሚነሱ ነጥቦች በእኔ የዕይታ አድማስ፣ ልምድና የግንዛቤ ደረጃ የተቃኙና አንድ ሴናሪዮን ብቻ የሚያሳዩና ናቸው። የእኔን ዕይታ ከማጋራት ባሻገር፣ ጉዳዩ ሰፊ ጥናት ጊዜና ገንዘብ የሚፈልግ በመሆኑ ሌሎች ወገኖች፣ በዋናነትም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት (የመንግሥት፣ የሙያ ማኅበራትና የጥናት ተቋማት ወዘተ) ጥናት በማድረግ በበቂ መረጃ የተደገፉ ድምዳሜዎች ላይ እንዲደርሱና የመፍትሔ ሐሳቦችን እንዲያካፍሉ ለመኮርኮር ነው።
- የፎቶ ጉዳይ ‹‹ይህ ፒፓ አይደለም››
እ.ኤ.አ. በ1929 ሬኔ ማግሪቴ የሚባል ቤልጂየማዊ ሠዓሊ የሲጋራ ማጬሻ ፒፓ (Pipe) ሣለና ‹‹This is not a Pipe››፣ ማለትም ‹‹ይህ ፒፓ አይደለም›› የሚል ርዕስ ሰጠው። ምክንያቱን ሲያስረዳ በዚህ ሥዕል ላጨስበት አልችልም፡፡ ላጨስበት የማልችለው ሥዕል ሥር ‹‹ይህ ፒፓ ነው›› ብዬ ብጽፍ እየዋሸሁ ነው ሲል አብራራ። ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ሥዕል የገሃዱን ዓለም እውነታ ሙሉ በሙሉ አይወክልም፡፡ ቢወክል እንኳን ከገሃዱ ዓለም ውስጥ ቁንጽል ቅጽበትን ወይም የገሃዱን ዓለም ከፊል ገጽታ ነው የሚል ነው። ፎቶም ተመሳሳይ ባህሪይ አለው። ሥዕል ብዙ መቶ ዓመታትን ያስቆጠረ ሥነ ጥበብ ሲሆን ተመልካቾች ሥዕል ፈጠራ መሆኑን ከሞላ ጎደል ስለሚረዱ ሥዕል ምን ያህል የገሃዱን ዓለም እውነታ ይወክላል የሚለውን ጉዳይ ይገነዘባሉ። በሌላ በኩል ፎቶ አንድ መቶ ዓመታትን ያህል ብቻ ያስቆጠረ ጥበብ ሲሆን፣ ከመነሻውም የገሃዱን ዓለም እውነታ እንደሚወክል ተደርጎ የታመነ ቴክኖሎጂ ነው። በዚህ ረገድ ከሥዕል ይልቅ ፎቶ ይበልጥ አታላይ ሊሆን ይችላል።
ፎቶ ከተንቀሳቃሽ አካል ላይ የተሽሞነሞነች ወይም የጠለሸች ገጽታን፣ እንዲሁም ከተቀያያሪ ኹነት ውስጥ የተመረጠች ቅጽበትን ማስቀረት ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ፎቶ በአንድ ጊዜ የሚይዘው (Capture የሚያደርገው) ፍሬም ውስጥ ሊገባለት የሚችለውን ያህል የገሃዱን ዓለም ክፍል ነው። ይህ ደግሞ እውነታን በሁለት መልኩ ያደበዝዛል። የካሜራው ሌንስ እንዳተኮረበት አንፃር መልካሙን ወይም ጥፉውን ገጽታ ብቻ በማሳየት እውነታን ማድበስበስ አንደኛው ገጽታው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ያ ገጽታ በዚያች ቅጽበት የነበረውን እውነታ ብቻ ስለሚያስቀር ከዚያ በፊትና ከዚያ በኋላ ስለሚከናወነው ጉዳይ ወይም ስለተደረገው ለውጥ ፎቶ አይናገርም፡፡ ለምሳሌ የፀሐይ ግባትን በፎቶ ማየትና ፀሐይ ራሷ ስትጠልቅ በዓይን ማየት ተመሳሳይ ስሜት አይሰጥም፡፡ ጀምበር ከመግባቷ በፊትም ሆነ በኋላ ያለውን ገጽታና ክንውንም በፎቶ ማሳየት አይቻልም፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ ፎቶ አንሺው አካል ፍላጎትና ዓላማ የገሃዱን ዓለም አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ገጽታ በፎቶ በማስቀረት ተመልካችን ማታለል ይቻላል።
በሌላ በኩል ፎቶዎች ላይ ያልነበራቸው ውበት፣ ሙቀትና ድምቀት እየተጨመረባቸው ቅጽበትንና አንድ ገጽታን የመወከል ተግባራቸውን እየሳቱ ነው። ከዚህ ቀደም በእጅ ሥራ አሁን ደግሞ ፎቶ ሾፕ፣ ፊልተርና መሰል ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ፎቶን በማግነንና ያለቅጥ በማድመቅ ተመልካችን ማታለል ይቻላል። በምሽት የሚነሱ ፎቶዎችም የብርሃንን የማታለል ባህሪ (Deceptivness) በመጠቀም ፎቶዎችን ይበልጥ አማላይና አታላይ ለማድረግ የሚያስችል አቅም አላቸው። አበባው መላኩ ‹‹የእጅ ሥራ›› በሚል ግጥሙ የኋለኛውን ጉዳይ የሚያብራራ ስንኝ ቋጥሯል፡፡
‹‹…እውነት አሁን እኔ ነኝ…?
እውነት ይህንን ከሆንኩ፣
እሱን አንተ ነህ ካልከኝ፤
ብጉር የነደለውን ጉንጬን፣
የለሰነውን ታምር ንገረኝ፤
ሽራፊ ነጥብ አፍንጫዬን፣
በስንደዶ ለውጦ አድምቆ፤
ዕብድ ያሰመረበት ግንባሬ፣
ጠባሳው ፈለጉ ጠፍቶ፤
ሕንፃ ሥላሴነቴን ሊያስንቅ፣
ጥፉ መልኬን ውበት ተክቶ፤
ሥጋ ለባሽ ጠገነኝ፣
በእጅ ሥራው፣ በፎቶ።››
ገጣሚው በእጅ ሥራ ፎቶውና በገሃዱ ዓለም ባለው ‹‹እሱ›› መካከል ያለው ልዩነት ቢደንቀው ‹‹እውነት አሁን እኔ እሱን ነኝ?›› ሲል ይጠይቃል። ግጥሙ ይቀጥልና፣ ገጣሚው ሳንጆርጅን ያስመስለውን የእጅ ሥራ ፎቶ ለእናቱ ሲሰጣቸው፣ እናቱ አገላብጠው ካዩ በኋላ ታቦታቸው ሊቀ ሰማዕቱ እንዲታደጋቸው ‹‹ዘልዳው ድረስ!›› ይላሉ በድንጋጤ።
በፎቶና በገሐዱ ዓለም መካከል ከዚህ በላይ የተጠቀሱና ሌሎችም ክፍተቶች ቢኖሩም፣ በግለሰብ፣ በተቋማትም ሆነ በመግሥታት ደረጃ ፎቶ ገሃዱን ዓለም እንደሚወክል ተደርጎ የማማለልና የማታለል ሥራ ሲሠራበት ይስተዋላል። በፊልተርና በሜክአፕ ውጪያችንን አሳምረን ችግራችንን በውስጣችን ይዘን ለመብለጭለጭ መዳከራችን የየግላችን ሀቅ ነው። ቅባችን፣ መብለጭለጫችን፣ የተጠና ፈገግታችን ለፎቶ በቂ ነው። ነፍስና መንፈሳችንን ግን አይወክልም። ይህንን ሥነ ልቦናችንን የተረዳ የሚመስለው የእኛው መንግሥትም ፎቶን እንደ ፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሲጠቀም ይስተዋላል። በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደርና መሰል ልማቶችን ብንመለከት፣ ከተማዋ እንደ ጨረቃ በፊት ገጿ ደምቃና አሸብርቃ በጀርባ በኩል ደግሞ ጠልሽታና ደክርታ ያለች ቢሆንም፣ የተመረጡ ገጽታዎቿን በፎቶ በማስቀረት እንዲሁም በከተማዋ አደባባዮች በተሰቀሉ ስክሪኖች ውበትና ልማቱን በስሎው ሞሽን በማሳየት ከፊል እውነታን ለመሸፈን ሲጥሩ ይስተዋላል። አዲስ አበባን እንደ ፎቶ ሞዴል ብንወስድ ከላይ እየተኳለችና ሽፋኗን እያሳመረች ጉስቁልና፣ ውንብድናና ትርክምክሟ በፎቶዎቿ እየተሰወሩ ይመስላል። የተገፊዎቿን መፈናቀል፣ ስቃይና ሐዘንም በተመረጡ ፎቶዎች እየተጋረደ ይመስላል። ከዚህ በተቃራኒ ውበቱ የማይጥማቸውና ልማቱ የማይዋጥላቸው ደግሞ መጥፎ ገጽታዎችን (ጎርፍ ያዘለ አስፋልት፣ የጠወለገ ዘንባባ፣ የተቦረቦረ የእግረኛ መንገድ፣ ወዘተ) ብቻ በፎቶ በማስቀረት አሉታዊ ገጽታዎችን ለማጉላት ሲሞክሩ ይስተዋላል።
ፎቶ፣ በእጅ ሥራ ፎቶ ሾፕና መሰል ዓይነት ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎች ሲጋነንና ሲደምቅ ተመልካቾች የሌለን ነገር በመፈለግ መባዘን እንዲሁም ቅብን በማሳደድ ጊዜና ገንዘባቸውን እንዲያጠፉ ያነሳሳል። በዚህ ረገድ ፎቶ የማይያዝ የማይጨበጥ በተመልካቾች ዘንድ ጉጉትን የሚፈጥርና ቃል የሚገባ፣ ነገር ግን ጉጉትንና መባዘንን ለማርካት አቅም የሌለው የማታለያ መሣሪያ ነው። መጓጓትን አለማርካት ወይም ፍላጎትን አለማሟላት (ቃልን አለመተግበር) ተመልካቹን ወይም ጠባቂውን ዕርካታ ይቀንሳል ወይም ያበሳጫል። ልጅ ሳለን ለበዓል ልብስ ለመግዛት ገበያ ስንሄድ በተለያዩ ቀለማት መብራቶች ያሸበረቁ ቡቲኮች ውስጥ ገብተን የሚያምር ልብስ ገዝተን እንወጣለን። ቤት ደርሰን ስናየው ቀለሙ ሌላ ነው፣ ጥራቱም የወረደ ይሆናል፡፡ ዕርካታችን ወደ ንዴት ይቀየራል። መብራቱ ነበር የሚያጭበረብረን። በቅብና መሰል ማድመቂያዎች የተጋነኑ ልማቶችም ቃል እየገቡ ቃላቸውን አይጠብቁም፡፡ በዚህ ረገድ የኮሪደር ልማቱና ከዚያም በፊት በከተማዋ የተሰቀሉ ዲም ላይት መብራቶች እውነታን የማግነኛ መሣሪያ ይመስላሉ። ሕንፃና ዛፍ ላይ ብልጭልጭ መብራት መጠምጠምም ሆነ መሬት ላይ መብራት መትከል የሕንፃውን ውበት በማድመቅና የመንገዱን መልክ በማግነን እውነተኛውን ልማትና ትክክለኛውን ውበት ያድበሰብሰዋል። በብልጭልጭ መብራቶች ካሸበረቁ ሕንፃዎች ጀርባ ጭርንቁስ መንደሮች፣ ላሚኔት የተደረጉ ሕንፃዎች ውስጥ ዘላቂነታቸው ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገቡ መሠረተ ልማቶች (ሊፍት፣ ውኃ፣ የእሳት መከላከያ፣ ንፁህና በቂ መፀዳጃ ቤት) በተጥበረበረች ከተማ አውራጎዳናዎች ላይ የሚንከላወሱ ግራ ገብ ነዋሪዎች… ወዘተን መመልከት በፎቶ በምትቀርበውና በገሃዱ ዓለም ባለችው ከተማ መካከል ያለውን ክፍተት ለማጤን ያስችላል።
- ባይተዋር ጎዳና
አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያን አንገብጋቢ ጉዳዮች በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። በአንደኛው ወገን የሚታዩና የሚዳሰሱ ችግሮች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህም አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ በግብርናና ተያያዥ ሙያዎች የሚተዳደር እንደመሆኑ ከግብርና (መንገድ፣ መስኖ፣ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ወዘተ) እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች (ጤናና ትምህርት) ጋር የተያያዙ መሠረተ ልማቶችን መጥቀስ ይቻላል። ውኃና መብራት፣ የመጓጓዣ አገልግሎትና የመኖሪያ ቤት ወዘተን መጨመርም ይቻላል። በሌላኛው ወገን የማይታዩና የማይዳሰሱ ግን ለአገር መቆምና ለማኅበረሰብ አንድነት መጠንከር አስፈላጊ ጉዳዮች ሲሆኑ በዋናነትም ሰላም፣ ፍትሕና የመንቀሳቀስ ነፃነትን መጥቀስ ይቻላል። አዲስ አበባን እንደ አብነት ብንወስድ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ካሉባቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች አንፃር የኮሪደር ልማት አስፈላጊ ቢሆንም፣ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ፕሮጀክት አይደለም። የሕዝቡን ኑሮና መንግሥት ለልማቱ ያለውን ረሃብና ጥማት (Passion) ስናነፃፅር፣ ልማቱ ለአብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ባዕድ ወይም ባይተዋር ይመስላል።
ይህ ማለት ግን ኮሪደሩና ተያያዥ ልማቶች አያስፈልጉም ማለት አይደለም፡፡ አዲስ አበባ እንደ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫነቷና እንደ የአፍሪካ መዲናነቷ፣ እነዚህና መሰል መሠረተ ልማቶች ያስፈልጓታል፡፡ በኮሪደሩና ተያያዥ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚዝናኑና መንፈሳቸውን የሚያድሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ወይም ልማቱን የሚያደንቁ ጎብኚዎች የሉም ማለትም አይደለም። ኮሪደሩ ውብ አይደለም ማለትም አይደለም። ውብ ነው እንጂ፡፡ እጅግ በጣም ያምራል! ግራና ቀኝ የተሠሩ የእግረኛ መንገዶች ለእግረኛ በጣም ምቹ ናቸው። በአቅራቢያው የተሠሩ መዝናኛዎች፣ በዙሪያው ያሉ ቤቶች ፅዳትና ቅርፅ፣ የአረንጓዴ ቦታዎች ተክልና መልከዓ ምድር ማየት መንፈስን ያድሳል። በልዩ ልዩ ኅብር ያሸበረቁ አበባዎች እንዲሁም ሳሮች የተተከሉባቸው ሥፍራዎችና ዲዛይናቸው ይመስጣል። በሚደንሱ ውኃዎች አቅራቢያ ልጆች ሲጫወቱ እንዲሁም በአግዳሚ ወንበሮች ዙሪያ ወጣቶች ፎቶ ሲነሱና ቪዲዮ ሲቀረፁ ማየትም ይማርካል። በመስታወት የተከለሉና የ‹‹LED Light›› ማስታወቂያ የተለጠፈባቸው የንግድ ቤቶችም በጣም ያምራሉ። በምሽት ዎክ የሚያደርጉ ነዋሪዎች በኮሪደሩ ላይ ሲረማመዱ እንዲሁም በአረንጓዴ ቦታዎችና ተወዛዋዥ ውኃዎች አቅራቢያ (ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ) ወላጆችና ልጆች ተቀራርበው ሲዝናኑ ማየትም ተጨማሪ ጥቅሙ ይመስላል። እንደ አዲስ እየተቀደዱ ያሉ መንገዶችና እየተዘረጉ ያሉ ድልድዮችና ተነሎች ሲወድቁና ሲነሱ፣ ሲጠማዘዙና ከዓይን ሲሰወሩ መመልከት ፐ! ያሰኛል። እነዚህ መሠረተ ልማቶች የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥም ዓይነተኛ ሚና አላቸው።
ሆኖም ይህ ዓይነቱን ውበትና ልማት ብዙኃኑ የከተማው ነዋሪዎች እንደ ፎቶ የሚመለከቱትና ‹‹ዕፁብ ድንቅ!›› ብለው በርቀት አድንቀው የሚያልፉት ዓይነት እንጂ የሚኖሩትና የሚያጣጥሙት አይደለም። ሠዓሊው ‹‹ይህ ፒፓ አይደለም!›› እንዳለው ሁሉ በውበትና ልማቱ ከመደመምና ከመቆዘም ባለፈ አብዛኛው ነዋሪ ኑሮውን አያከናውንበትም፡፡ ተወዛዋዡን ውኃ (Fountain) ኑሮን አያፀዱበትም። ማለትም ውኃው ምግብ ለመሥራት፣ ሻወር ለመውሰድ፣ ልብስ ለማጠብ፣ ሽንት ቤት ለማፅዳት፣ ዕቃ ለማጠብ፣ ወይም መሰል የግልና ማኅበራዊ የንፅህና አገልግሎቶችን ለማከናወን አይውልም። ብልጭልጩን መብራትም ኑሮን አያሞቁበትም። ማለትም መብራቱን ምግብ አያበስሉበት፣ ቤት አያበሩበት፣ ልብስ አይተኩሱበት፣ ወይም ተመሳሳይ የቤትና የማኅበራዊ ጉዳዮችን አይፈጽሙበትም። የተንጣለለው መንገድም ይነዱበትና ይራመዱበታል እንጂ ማጀት ሆኖ ገመና አይሸፍን ወይም አልጋ ዘርግተው አያድሩበትም። ሳሩም ቢሆን ሰላጣ አይሆን ወይም ለግጦሽ አይውል።
እንዲህ ዓይነቱ የከተማ ውበትና ልማት አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ እንደማይመለከተውና የእኔነት ስሜት በሌለው ባይተዋርነት በሩቁ ሲመለከት ይስተዋላል። ኑሯቸውና ከተማቸው የማዶ ለማዶ የበይና የበይ ተመልካች ግንኙነትን በመፍጠር በገዛ ከተማቸው ባይተዋርነት ተጠናውቷቸው ግራ የሚጋቡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች መታየት ጀምረዋል። ይህ ደግሞ በሁለት መልኩ ሊከሰት ይችላል። በአንድ በኩል የኮሪደሩ ልማት ከሥራቸው ያፈናቀላቸው፣ ከኑሯቸው የነቀላቸውና ከማኅበራዊ ሕይወታቸው የነጠላቸው ሰዎች ኮሪደሩን ከማድነቅና በውበቱ ከመመሰጥ ይልቅ ወደመጠየቅና መናደድ እየተዘዋወሩ ነው። በሌላ በኩል ሰው ተወልዶ ባደገባት፣ እትብቱን በቀበረባት ከተማ የትዝታ ቦታዎቹ ፈርሰው በሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ሲተኩ፣ ነዋሪው በአገሩ እያለ በከተማው እየተንቀሳቀሰ፣ ከትዝታው ስለሚነጠል በገዛ ከተማው ባይተዋር እንዲሆን ያደርገዋል።
ከፍተኛ የውኃ ችግር እንዳለባትና ወደፊትም ችግሩ እንደሚባባስ በሚነገርላት ከተማ፣ የከተማዋ አስተዳደር የኮሪደሩ መናፈሻዎችና ተያያዥ ሥፍራዎች ላይ ውኃ ሲያባክን ይስተዋላል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ጄሪካን ይዘው ውኃ ፍለጋ ሲንከራተቱ፣ የከተማዋ አስተዳደር (በዶፍ ዝናብ ጭምር) ውኃ በቦቴ መኪና እያዞረ አረንጓዴ ሥፍራዎችንና ችግኞችን ሲያጠጣና ፋውንቴይን ሲለቅ ማየት ግራ ያጋባል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች በጨለማ ተውጠው የከተማዋ አስተዳደር (በጠራራ ፀሐይ ጭምር) የመንገድ መብራት ሲያበራ፣ ውኃ በመብራት ሲያስደንስ እንዲሁም የዘንባባ ግንድን በመብራት አጎበርና ስካርፍ ሲያስጌጥ ማየትም ምን እየተከናወነ ነው ያሰኛል።
አልፎ አልፎ እስቲ ውበቱን ላድንቅ፣ ጎዳናውን ላጣጥም፣ መንፈሴንም ላድስ ብዬ እወጣና ኮሪደሩ ላይ ስናፈስና ስደሰት አመሻለሁ። በየመሀሉ ኑሮዬ እየታወሰኝ ደስታዬ ይቀንሳል። ለምራመድበት መንገድ እየዋለ ያለው አሸዋ፣ አርማታና ሲሚንቶ ምን ያህል ኮንዶምኒየም ይሠራ ይሆን? የሚል ጥያቄ ይመጣብኛል። የማየው ልማትና የምዝናናበት ውበት በማንና በምን ዋጋ የተገኘ ይሆን? የሚል ጥያቄም ውል ይለኛል። ተወዛዋዡን ውኃና ተንቦግቧጊውን መብራት እያጣጣምኩ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ዎክ ሳደርግ አምሽቼ ቤት ስገባ ብዙውን ጊዜ ወይ ውኃ አይኖርም ወይም መብራት ጠፍቶ ይጠብቀኛል። ውበቱና ልማቱ ወዲያው ይደበዝዝብኛል። ይህ ጉዳይ ከዓመታት በፊት ወርልድ ባንክ ስፖንሰር ባደረገው የጎዳና ሩጫ ውድድር ላይ የተሳተፈ የከተማዋን ነዋሪ ያስታውሰኛል። የተሳታፊዎቹች ቲሸርት ጀርባ ላይ ‹‹ድህነትን ጨርሰን እናጥፋ›› (Let’s Eradicate Poverty) የሚል መፈክር ተለጥፎ ነበር። ይህ የከተማዋ ተሳታፊ ድህነትን አሯሩጦ፣ ሜዳልያውን አንግቶ፣ ቤት ገብቶ ‹‹ምሣ›› ሲል ምሣ የለም። በጎዳና ያሯሯጠው ድህነት በጓሮ በር ማጀት ገብቶ ቆየው።
አንዳንድ የልማቱ ገጽታዎች ለከተማዋ ማንነት ጭምር ባይተዋር ይመስላሉ። ለምሳሌ የዘንባባ ዛፍ ከአዲስ አበባ አየር ንብረት ጋር እምብዛም አይሄድም። የመብራት ቋሚዎቹ ሳይቀሩ በዘንባባ ቅርፅ የተሠሩ ናቸው። ካደጉ በኋላ እየተተከሉ ያሉትን የዘንባባ ዛፎች ሳስተውላቸው ለከተማዋ ባይተዋር ሆነው የሚንቀዋለሉ ይመስሉኛል። ይህ ግን የዘንባባ ዛፍ አይተከል ማለት አይደለም። እንደ ሌሎች አገር በቀልና ባዕድ ዛፎች ሁሉ የዘንባባ ዛፎችም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢ የኅብር አንድ ሰበዝ ሆነው ሲታዩ ያምራሉ። ለከተማዋም ጌጥ ይሆናሉ። ለምሳሌ በአንዳንድ የመናፈሻ አካባቢዎች የዘንባባ ዛፎች ከዝግባ፣ ወይራ፣ የጠመንጃና ሌሎች ዛፎች ጋር ፀድቀው ሲታዩ ውበታቸው ይማርካል። ብቻቸውን እንደ ጅብራ ተገትረው ጎዳናውን ሞልተው ሲታዩ ግን በባይተዋርነት የሚንቀዋለሉ ባዕዳን ይመስላሉ።
በሌላ በኩል በሳይክል መሞች ላይ ጥቂት ልጆችና ወጣቶች ሲመላለሱባቸው ቢማርኩም፣ ዳገትና ቁልቁለት የሚበዛው የአዲስ አበባ መልከዓ ምድር ምን ያህል ለሳይክል ይመቻል የሚል ጥያቄን ያጭራል። ቀደም ብሎ ከለገሐር እስከ መዘጋጃ ቤት ድረስ በአረንጓዴ ቀለም በተዘረጋው የሳይክል መም ላይ በሳይክል የሚጓዙ ሰዎች አይታዩም፡፡ መሙ ጭራሽ የእግረኛ መንገድ ሆኗል። ከዚህ አንፃር ያን ያህል ሕንፃ የሚናድለትና ቤቶች የሚጠረጉለት የሳይክል ተጠቃሚ አለን ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ለዘመናት ከልጅ እስከ አዋቂ ሳይክል ሲጠቀሙ የነበሩ ማኅበረሰቦች (ባሕር ዳርና ሐዋሳን በዋናነት ማንሳት ይቻላል) አሁን በብዛት ሳይክሉን ትተው ሞተር ሳይክል እየተጠቀሙ መሆኑ ሲታይ፣ የሳይክል ነገር ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በአዘቦት ቀናት ምሽቶችና በሰንበት ቀናት በአግዳሚ ወንበሮች ላይ ተቀምጠው የሚዝናኑ ሰዎች ቢኖሩም፣ በኮሪደሩ ግራና ቀኝ እንዲሁም በመናፈሻዎች አቅራቢያ የተተከሉ ጥቂት የማይባሉ አግዳሚ ወንበሮች ሰው አልባ ሆነው ሲታዩም ለከተማዋ ባይተዋር ይመስላሉ።
የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ጉዳይ ከኮሪደር ልማቱ በፊት የተሞከረና በየጊዜው መሻሻል የታየበት ልማድ ቢሆንም ባለን የሥልጣኔና የዕድገት ደረጃ ፕላቲክ፣ ጠርሙስና ጣሳዎችን ከወረቀቶችና ድብልቅ ቆሻሻዎች ለይቶ ለመጣል የደረስን አይመስልም። የተጠቀምንበትን ሽንት ቤት ውኃ የመቸለስ ልምድ የሌለን እንኳን በርካቶች ነን። ከዚህ አንፃር በተለያዩ የኮሪደሩ ጥጎች የተቀመጡ ቆሻሻን ለይቶ መጣያ ቅርጫቶች፣ ባደጉት አገሮች የሚዘወተሩ ቢሆንም ለእኛ ኑሮና ለከተማዋም ባይተዋር ይመስላሉ። ብዙ ሀብት የፈሰሰባቸው እነዚህና መሰል መሠረተ ልማቶች ከከተማዋ ማንነት እንዲሁም ከነዋሪዎቿ ፍላጎትና አቅም ጋር የተዛመዱ አይመስሉም።
- የሚከፈል ዋጋ
ውበትና ንፅህና የከተሜነት አንድ መገለጫ ቢሆንም፣ ከከተማው በፊት ወይም እኩል ነዋሪው ኑሮው ቢፀዳና ትዳሩ ቢያምር መልካም ነው። ሕንፃና መንገድ አሸብርቆ አብዛኛው ነዋሪ ከጠወለገ፣ ውበቱ እያደር ይደበዝዛል። አንድ ዛፍ በዚያ ደረጃ ውኃ፣ ሲቀርብለት፣ መብራት ሲበራለት፣ ከለላ ሲደረግለት፣ ጠበቃ ሲቆምለት፣ ወዘተ ነዋሪውን እያደር ሊያናድድ ይችላል። የማይኖሩትና የማያጣጥሙት ውበት ዋጋ ያስከፍላል፣ አደጋም አለው። የደርግ መንግሥት በግዳጅ ያስተከላቸው ዛፎች አገዛዙ ሲወድቅ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንደጨፈጨፋቸው ያስተውሏል። ወደ አደጋው ከመሄዳችን በፊት አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ለከተማዋ ኮሪደር ማማር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ ዋጋ እንደሚከፍል ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ በቀጥተኛ መልኩ እየተከፈሉ ያሉ ዋጋዎችን ብናይ ቀጥተኛ ክፍያ፣ መፈናቀልና የሥነ ልቦና ጉዳትን መጥቀስ ይቻላል።
- አብዛኛው ነዋሪ (መምህራን፣ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶችና ሾፌሮች ወዘተ) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ በውድም ሆነ በግድ ለልማቱ ገንዘብ ያዋጣል። ነዋሪው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ልማቶች እንዲሠሩለት የሚወጣው ገንዘብ ለኮሪደርና መሰል ልማቶች ላይ ሲውል፣ አንገብጋቢ የሆኑ ልማቶች ወደ ኮሪደርና ተያያዥ ልማቶች ፈሰስ ሊደረጉ ይችላሉ። እዚህ ጋ ‹‹የኮሪደር ሥራውና መሰል ልማቶች በሕዝቡ ጥያቄ መሠረት ነው ወይ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ያሉት?›› የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው።
- በርካቶች በኮሪደሩና መሰል ልማቶች ምክንያት ከሥራቸው ተፈናቅለዋል፣ ከመኖሪያቸው ተነቅለዋል፣ ከማኅበራዊ ሕይወታቸው ተለይተዋል። በርካታ የሥራ ቦታ የነበሩ ቦታዎች በልማቱ ምክንያት ተነስተው በምትካቸው አረንጓዴ ቦታዎች፣ ተወዛዋዥ ውኃ፣ መናፈሻ፣ የመኪና ማቆሚያዎች ተተክተዋል። በዚህም የኑሮ መሠረታቸው (ሥራቸው) እና ማኅበራዊ ሕይወታቸው ተቃውሷል።
- ከኢኮኖሚ ቀውስ ባሻገር ልዩ ልዩ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች የተዳረጉ ተነሺዎች አሉ። ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ከመኖሪያ ቦታቸው ሲነሱና በሌላ አካባቢ (ከከተማ ዳርቻዎች) ቦታና ቤት ሲሰጣቸው የማኅበራዊ ሕይወታቸውና የኑሮ ትስስራቸው ስለተበጣጠሰ ከፍተኛ ችግር እንደደረሰባቸው ይነገራል። በዚሁ ምክንያት በብቸኝነት የሚሰቃዩ እንዲሁም መነሳትና መፈናቀሉ ፋታ በማይሰጥ ሁኔታ በጥድፊያ የተደረገባቸው (ልማቱ በቅጡ ሳይዘጋጁ ስለመጣባቸው) ሀብት ንብረታቸው ዋጋ ሲያጣና ከኑሯቸው ድንገት ሲነቀሉ በንዴትና በድንጋጤ የተጎዱ መኖራቸውንና፣ ጉዳቱም እስከ ሞት እንደደረሰ ይነገራል። ልማቱ በቀጥታ ሰዎችን ለሞት ላይዳርግ ይችላል። ከዚህ በፊት በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ ባሻገር ድንጋጤና ፍርኃቱ ለሞት ዳርጓቸዋል። በኦሽዊትዝ ኮንሰንትሬሽን ካምፕ ውስጥም ከናዚ ወታደሮች ጅምላ ግድያ ባሻገር በፍርኃት በርካቶች መሞታቸውን ቪክተር ፍራንክል፣ ‹‹Man’s Search for Meaning›› በሚል መጽሐፉ ያስረዳል። በተዘዋዋሪ መንገድ የሚከፈሉ ወይም እየተከፈሉ ካሉ ዋጋዎች ውስጥ የሚከተሉትን ለአብነት ያህል ማንሳት ይቻላል፡፡
- ለብዝኃነት ግብዓት የሚሆኑ ማኅበራዊና ባህላዊ ተቋማት መፈራረስ፣ እንዲህ ዓይነት ልማትና ተያይዘው የሚመጡ መፈናቀሎች እየተስፋፉ ከሄዱ፣ ማፈናቀሉ በግለሰቦች ኑሮና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከሚያደርሰው ቀውስ ባሻገር፣ ለብዝኃ ዴሞክራሲ (Diverse Democracy) ማበብ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን የመናድ አደጋ አለው። አንድ አገር ሕዝብን የሚያስተሳስሩ ማኅበራዊ ተቋማትን (Social Capitals) ቦንዲንግ ሶሻል ካፒታል (Bonding Social Capital) እና ብሪጂንግ ሶሻል ካፒታል (Bridging Social Capital) በሚል በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። ቦንዲንግ ሶሻል ካፒታል (Bonding Social Capital) ተመሳሳይ ማንነት ያላቸው የልዩ ልዩ ቡድኖች አባላትን እርስ በርስ የሚያስተሳስሩ ክሮች ናቸው። እንደ ቤተሰብ፣ ቤተ ዘመድ፣ ጎሳና ሃይማኖት ቡድኖች ውስጥ በአባላቱ መካከል ያሉ የማንነት ውሎችንና መተሳሰሮችን ያጠናክራሉ። ቦንዲንግ ሶሻል ካፒታል ወደ ውስጥ በመመልከትና የውስጥ ግንኙነትን ለማጠንከር መልካም ቢሆንም፣ ሌሎች ማንነቶችንና ቡድኖችን ስለሚዘነጉ፣ ለአብሮነት ጋሬጣ ከመሆን ባሻገር በተለያዩ ማንነቶች መካከል ጥላቻን ለመዝራትና ግጭትን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ።
በሌላ በኩል የተለያዩ ማንነቶች ባሏቸው ቡድኖች መካከል የሚፈጠሩ ግንኙነቶችን የሚፈጥሩና ትስስርን የሚያጠናክሩ ማኅበራዊ ተቋማት ብሪጂንግ ሶሻል ካፒታል (Bridging Social Capial) ይባላሉ። እነዚህ ማኅበራዊ ተቋማት በተለያዩ ማንነቶች ወይም ቡድኖች አባላት መካከል መተሳሰርን ስለሚፈጥሩ ለብዝኃ ዴሞክራሲ (Diverse Democracy) ማበብ ዓይነተኛ ሚና አላቸው። እንደ ዕድር፣ ዕቁብ፣ ማኅበርና መሰል ተቋማት ወይም ማኅበረሰቡ ለረዥም ጊዜያት ያዳበራቸው በጎ ልማዶች (ደቦና ቅርጫን ማንሳት ይቻላል) ከተለያዩ መደቦች፣ ሃይማኖቶችና ጎሳዎች ወዘተ የሚመጡ ሰዎችን የማገናኘትና የማሰናኘት አቅም አላቸው። እነዚህ ተቋማትና በጎ ልምዶች አብዛኛውን ጊዜ የሚገኙት ማኅበራዊ ትስስሩ ጠንካራ በሆነና ለረዥም ጊዜ በአንድ አካባቢ በኖሩ ሰዎች መካከል ነው። እነዚህ ተቋማት በሠፈር ደረጃም ሊመሠረቱ ይችላሉ። ገጣሚ ምሥራቅ ተረፈ በጨው በረንዳ የግጥም መድበሏ ውስጥ ‹‹ጎረቤቶቼ›› በሚል ግጥሟ ይህን ጉዳይ በስሱ ትዳስሳለች፡፡
‹‹በዘይነባ ምክር፣ በፋጤ ቸርነት፣ በባዬ ድንች ወጥ፣
በአይሻ ፈገግታ፣ በወርቅ ውኃ ቁጣ፣ በዘሪሁን ቁንጢጥ፣
እንዳልተገነባ፣ እኔ ያልኩት እኔ፣ ውለታው ሊረሳ
‹አንተ የማነህ?› ሲሉት፣ የአባቱን ስም ብቻ በኩራት አነሳ።››
ከጥቂት ዓመታት በፊት በ‹‹UN Habitat›› በወጣ መረጃ መሠረት፣ 70 በመቶ የሚጠጋው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መንደሮች የቆረቆዙ (Slum Area) መሆናቸውን ያሳያል። የኮሪደሩ ልማት ከዋና ዋና ጎዳናዎች ተሻግሮ ወደ ነባር መንደሮች እየገባ ነዋሪዎችን የሚያፈናቅል ከሆነ (ምልክቶች አሉ) አደጋው ይበልጥ አሳሳቢ ይሆናል። ብሂላችን ‹‹ሰው በገዛ አገሩ ባይተዋር ከሆነ፣ መልካም ጉርብትና ቀረ ተበተነ›› እንዲል፣ ልማቱን ተከትሎ ታሪካዊና ነባር መንደሮች ሲፈርሱና በርካቶች ሲፈናቀሉ፣ ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ባሻገር ለብዝኃ ዴሞክራሲ አስፈላጊ የሆኑ እነዚህ ማኅበራዊ ተቋማትና በጎ ልምዶች ሊዳከሙ ወይም ሊፈርሱ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ከግለሰብ በላይ ማኅበረሰባዊና አገራዊ አደጋ ያረግዛል። በተለይ በእኛ አገር ዓውድ አሁን ባለንበት ዘመን (የማንነት ፖለቲካ በገነገነበትና አብዛኛው ሰው ከራሱ ቡድን ወይም ማንነት ውጪ አሻግሮ ለማየት በተቸገረበት ጊዜ) እነዚህ ተቋማት አብሮነትን ለማጠንከር ብቻ ሳይሆን ግጭትን ለመከላከል ዓይነተኛ ግብዓት ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃም እንደ ህንድ ያሉ ብዝኃነት ያላቸው አገሮች ያጧቸውና እየተቸገሩባቸው ያሉ ተቋማት ናቸው።
- የኑሮ ጣዕምና ትዝታን መነጠቅ፣ ሰው ተወልዶ ባደገባት፣ እትብቱን በቀበረባት ከተማ የትዝታ ቦታዎቹ ፈርሰው በሰማይጠቀስ ሕንፃዎች ሲተካ፣ ነዋሪው በአገሩ እያለ በከተማዋ እየተንቀሳቀሰ ከትዝታው ይነጠላል። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ባይተዋርነት የሚከሰተው ከአገር ከወገን ርቀው በሰው አገር ሲኖሩ ቢሆንም፣ ሰው ባገሩ እያለ፣ በገዛ ከተማው የተንቀሳቀሰ በሰው አገር ያለ ይመስል የቅርታ ስሜት እየወረሰው ባይተዋር እንዲሆን ያደርገዋል። አንዲት የከተማዋ ነባር ነዋሪ ፒያሳ ሄዳ ግራጫ ሕንፃዎችን፣ አረንጓዴ መናፈሻን ወይም ሰፋፊ ጎዳናዎችን ታይ ይሆናል፡፡ ውበትና ድምቀታቸው ግን የደመና ግላጭ ይሆንባታል፡፡ ዕድሜ አይኖረውም። አንድ የከተማዋ ነባር ነዋሪም አራት ኪሎ ሄዶ ትልልቅ ሕንፃዎችን፣ ንፁህ ጎዳናዎችን፣ ሰፋፊ መገዶችን ያያል፣ ግን ላይጥሙት ይችላሉ። በሌሎችም የኮሪደሩ አካባቢዎች የሚገኙ ነባር ነዋሪዎች ታሪክና ትዝታ ከልማቱ ጋር እየተቀበረ ሲሄድ፣ መነጠልና መነጠቅን ይፈጥራል።
የቀለም ነገርም ጣዕምን የሚነጥቅ ሌላ ጉዳይ ይመስላል። ዓይናችን ወርቤክ ሕንፃን በቡኒ (አልተለወጠም)፣ ደንበልን ደግሞ በጥቁርና በቢጫ ቀለማት ነው የለመደው። ብሔራዊ ቴአትርን ከጎን በኩል ከነበሩት የቀለማት ኅብር ውጪ ማየት አንዳች ነገር ያጎድላል፡፡ የቀለማቱ ኅብር ራሱን የቻለ ትርጉምም ይኖረዋል። ባደጉት አገሮች ጭምር የጡብ ሕንፃዎች የራሳቸውን ቀለም (በርገንዲ) ይዘው ነው የሚገነቡት። አንዳንድ ተቋማትና ድርጅቶች የየራሳቸው ቀለምና ብራንድ ይኖራቸዋል። እነዚህ ልዩ ልዩ ቀለማት በነጭና ግራጫ ሲተኩ የሕንፃዎቹንና የድርጅቶቹን ማንነት ይቀይራል፡፡ ብዝኃነት ያደበዝዛል፡፡ የከተማዋን ውበት ይቀንሳል። ጣዕምንም ይቀሽባል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ከተሞች ለነባርና አሮጌ መንደሮች አስፈላጊውን ዕድሳትና ጥገና በማድረግ ለነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ያደርጋሉ። ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው በመገንባትም የቱሪስት መስህብ ያደርጓቸዋል። እነዚህ ነባርና አሮጌ የከተማ ክፍሎች ጭርሱን ሲጠፉ የሚያጎድሉት ነገር አለ። የከተማ ክፍሎች ጭራሹን ሲጠፉ የሚያጎድሉት ነገር አለ። የሰው ልጅ ከቁሳዊ ሀብት በተጨማሪ ከትዝታ ጋር ከባድ ቁርኝት ያለው መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ውስብስብ ፍጡር በመሆኑ፣ ምንም እንኳን ለጊዜውና ለላንቲካ ያህል የአዳዲስ ገጽታዎችን ውበት ቢያደንቅም፣ ውሎ ሲያድር አንዳች ነገር እንደጎደለ እየተሰማው ግርና ቅር ይለዋል። ድምፃዊት ማንአልሞሽ ዲቦ የትዝታን ኃይል ስታወሳ እንዲህ ትላለች፤
‹‹ሀብት ንብረትማ፣ ሠርተው ያገኙታል፣
በሽታም ቢጠና፣ ታምመው ይድኑታል፣
ባላንጣ ቢነሳ፣ በሕግ ይዳኙታል፣
የትዝታን ነገር እንዴት ያደርጉታል?!››
- ለአብዛኛው ሰው ኑሮ ምቹ አለመሆን፣ ከዚህ ቀደም በተለመደው መልኩ የከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ለነዋሪዎቿ ምቹ መሆኗ እያበቃ ለጥቂት ሀብታሞች የምትመች ከተማ እየሆነች ያለ ይመስላል። የኮሪደሩን መሠረተ ልማቶች ባለመኪኖች ሊንፈላሰሱበት ይችላሉ። እግረኞችም እንደ ልባቸው ይራመዱባቸዋል። ከዚህ በዘለለ አብዛኛው ነዋሪ በውበቱ ከመደመምና ከመቆዘም ባሻገር የሚያዝ የሚጨበጥ ጥቅም አያገኝበትም። ከዚህ ቀደም ለአብዛኛው ሰው ወይም ለመደበኛ የከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎት ይውሉ የነበሩ ሥፍራዎች (Open Spaces) በልማቱ ምክንያት እየተነሱ ለውበት ሲውሉ ወይም ለግል ባለሀብት ሲሰጡ፣ በእነዚህ ሥፍራዎች ይጠቀሙ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች መሸሸጊያ ሊያጡ ይችላሉ።
አነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም ሥፍራዎች የነፃ ገበያ ተቀፅላ በሆኑ የፋይናንስና መሰል የንግድ ድርጅቶች እየተተኩ ነው። ምግብ ቤቱ መለዋወጫ፣ ካፌው ባንክ፣ ዳቦ ቤቱ ሚኒ ሱፐር ማርኬት፣ ጁስ ቤቱ አይስክሬም መሸጫ፣ ልብስ ቤቱ የጉዞ ወኪልና የስጦታ መሸጫው ሊኩየር ስቶር ወዘተ እየሆኑ በመሸጋሸግ ላይ ናቸው። ኢንተርኔት ካፌ፣ ፕሪንትና ፎቶ ኮፒ ቤቶች፣ ጉልት፣ የጀበና ቡና፣ ልብስ ሰፊ፣ ጫማ ጠራጊና ጠጋኝ፣ ባለሚዛን፣ ባለሎተሪ፣ ባለመፋቂያ፣ የመገድ ላይ ትንንሽ ምግብ ቤቶች (እርጥብ፣ ቆሎ፣ በቆሎና ሳምቡሳ ወዘተን ጨምሮ) ሱቅ በደረቴ፣ ሸገር ዳቦ (ሸገር ዳቦና አትክልት) እና መሰል አብዛኛው ሰው ይጠቀምባቸው የነበሩ ቦታዎችና አገልግሎቶች ደብዛቸው እየጠፋ ነው። ከኮሪደሩ ልማት በፊት አንድ ሰው ውኃ ቢጠማው ወደ አንዱ ሱቅ ጎራ ብሎ በተመጣጣኝ ዋጋ ከሱቅ ወይም ከሱቅ በደረቴዎች ላይ መግዛት ይችላል፣ አሁን ግን ሱቅ አይገኝም። ቢገኝም ዋጋው በጣም ውድ ነው። እንደ ልብ ሻይ ቡና ለማለት፣ ጫማ ለማስጠረግም ሆነ ከመደብር በቅናሽ ዋጋ አስፈላጊ ሸቀጦችን ለመግዛት ኮሪደሩ አይመችም። አንድ ሰው ሽንቱን ቢወጥረው እንዲሁም ዝናብ ቢመጣበት ወይም ፀሐይ ቢያቃጥለው ለማረፊያና ለመተንፈሻ የሚሆኑ ቦታዎች እየጠፉ ነው። በርግጥ ከፊሉ የኮሪደሩ ልማቶች የፈጠሯቸው የሕንፃ ሥር ሥፍራዎች ነዋሪውን ከክረምት ዝናብና ከበጋ ሀሩር ያስጠልላሉ። ከፊሉ ደግሞ ጭራሽ መጠለያ ነስተውታል።
ከላይ በተጠቀሱት ኢመደበኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ ወገኖች እርስ በርስ ተገበያይተው ነው ኑሯቸውን የሚገፉት። ከዚህም በላይ እነዚህ ወገኖች በመደበኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ለተሰማሩና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ በርካቶች ምርትና አገልግሎትን በቅናሽ ዋጋ ያቀርባሉ። ለአብነት ያህል በመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ በፅዳት ሠራተኝነትና በጥበቃነት ተቀጥረው የሚኖሩ ብዙ ወገኖች ምግብና መጠጣቸውንም ሆነ አልባሳታቸውን የሚገበዩት በኢመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ ከተሰማሩ ሰዎች ላይ ነው። የኮሪደሩ ልማት እነዚህን ዘርፎች የሚያዳክም ወይም ጨርሶ የሚያጠፋ ከሆነ፣ በመሪር ድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለአትራፊ ትላልቅ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች አሳልፎ መስጠት ይሆናል።
- ከልማት በኋላ የሚፈጠር የዋጋ መናር፣ ኮሪደርና መሰል ልማቶችን ተከትሎ የልዩ ልዩ አካባቢዎች ዋጋ (Property Value) ይጨምራል። ከዚህ ቀደም በዋና ዋና ጎዳናዎች አቅራቢያ ቤት ለመግዛትም ሆነ ለመከራየት እምብዛም አስቸጋሪ አልነበረም። ልማቱን ተከትሎ የአካባቢው ዋጋ ስለሚጨምር፣ ቤት ለመከራየትም ሆነ ለመግዛት ዋጋው አይቀመስም። ኮሪደሩን ተከትለው እየተከፈቱ ባሉ የንግድ ቤቶች፣ የመመገቢያና የመዝናኛ ሥፍራዎች ውስጥ ለመጠቀምም (በዕድሳት፣ በውጭ ምንዛሪ መጨመር፣ በቦታ ዋጋ መናርና በኪራይ መጨመርና መሰል ምክንያቶች) ዋጋቸው ጭማሪ ስለሚያሳይ፣ ለብዙኃኑ ነዋሪ አዳጋች ይሆናል።
- በልማት ወቅት የሚደርስ ስቃይና እንግልት በዚህ ረገድ የሚፈጠረው ስቃይና እንግልት ጊዜያዊ ቢሆንም፣ በመንገድ መዘጋጋትና ከትራፊክ መጨናነቅ ወይም በድምፅና አየር ብክለቶች ምክንያት በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራና የንግድ እንቅስቃሴ ይስተጓጎላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነጋዴዎች ገቢያቸው ይቀንሳል። የገበያተኛው የትራንስፖርት ወጪም ይጨምራል። የውኃ፣ የስልክ፣ የመብራትና መሰል አገልግሎቶች ይቆራረጡባቸዋል። በልማቱ ላይ በቀጥታ የሚሳተፉ ወገኖች ግብዣና ሽልማት ሲደረግላቸው የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነው አብዛኛው ነዋሪ ብዙውን ጊዜ ይዘነጋል። ይህንን ጠንቅቆ መረዳትና አስፈላጊውን ዕውቅና መስጠት ከከተማው አስተዳደር የሚጠበቅ ተግባር ነው።
- ያንዣበበ አደጋ
ይህ ክፍል በቀጥታ ከኮሪደሩ ልማት ጋር የሚገናኝ ሳይሆን ከአጠቃላይ የልማት አካሄድና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለኒዮሊበራል ከበርቴዎችና ድንበር ተሻገሪ ድርጅቶቻቸው ከመክፈት ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ጉዳዮችን ይመለከታል። ከሌሎች አገሮች ልምድ በመነሳት ሊፈጠሩ ከሚችሉ አሉታዊ ጉዳዮች ውስጥ አንዱንና ዋነኛውን (የኑሮ ደረጃ ልዩነትን Inequality) ዘለላ በመምዘዝ ለማብራራት ይሞክራል። በዚህም ውስጥ የኑሮ ደረጃ ልዩነቱ ሊያመጣቸው የሚችሉ ማኅበራዊ ቀውሶችን በመለየት፣ ጉዳዩን ለማብራራት ይሞክራል።
- የኑሮ ደረጃ ልዩነትና ማኅበራዊ ቀውስ
ጥቂቶችን ያማከለና ብዙኃኑን ያገለለ መሠረተ ልማት ተቀዳሚ ፍላጎቶቻቸው በማይጣጣሙ የአንድ አገር የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ልዩነት የመፍጠር ዕድል አለው። እንዲህ ዓይነቱ ዕድገትና የልማት አካሄድ ከአካታችነቱ ይልቅ አግላይነቱ ያመዝናል። በብዙኃኑና በጥቂት ዜጎች መካከል የኑሮ ደረጃ ልዩነትን የመፍጠር አቅም አለው፡፡ በእርግጥ የኑሮ ደረጃ ልዩነት ባለፉት 30 ዓመታት ጀምሮ እየተስፋፋ የመጣ ጉዳይ መሆኑን አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ። ሆኖም የበርካታ ታዳጊ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው፣ ታዳጊ አገሮች በራቸውን ለነፃ ኢኮኖሚና ለኒዮሊበራል ከበርቴዎች በራቸውን ሲከፍቱ በተለያዩ ምክንያቶች የኑሮ ደረጃ ልዩነቱ እየተባባሰ ይሄዳል። ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል። ከዚህ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ዓውድ ሊነሱ የሚችሉ ጥቂት ምክንያቶች ተቀምጠዋል፡፡
- በዋነኞቹ የምጣኔ ሀብት ቲዎሪዎች እንደሚባለው በአንድ አገር ዕድገት ሲመጣ፣ በረከቱ ወደ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል የመስረፅ ወይም ለታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል የመድረስ (Trickle Down የማድረግ) ዕድሉ አነስተኛ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሚመዘገቡ የምጣኔ ሀብት ዕድገቶች ከሞላ ጎደል ኢንክሌቭ (Inclave) መሆናቸውን ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ማለትም ዕድገቱ የሚደርሳቸው በላይኛው ዕርከን ላይ የሚገኙ ጥቂት ሰዎች ናቸው እንጂ በህልዮት ደረጃ እንደሚባለው ዕድገትና ብልፅግናው ለሰፊው ሕዝብ አይደርስም። በእርግጥ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚታይ ጉዳይ ነው።
- በእኛ አገር የባህል ሥሪት ምክንያት ሀብት ከላይኛው ወደ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል የመስረፅ ዕድሉ አነስተኛ ነው። ይህን በተመለከት ሳሙዔል ዮሐንስ ‹‹Ethiopia Creating a Culture of Progress›› በሚል መጽሐፋቸው የሚከተለውን ሐሳብ የያዘ አመክንዮ ያቀርባሉ፡፡ የእኛ አገር ደሃና ሀብታም ያላቸው ግንኙነት የድልድይ ሳይሆን የመሰላል ዓይነት ነው። አብዛኞቹ ሀብታሞች ብቻቸውን ወደ ላይ ለመውጣትና የሚከተላቸውን ለመጣል ወይም አንዴ ደርቡን ከወጡ በኋላ መንሰላሉን ለማሽቀንጠር ሲጣጣሩ አብዛኛው ደሃ ደግሞ አብሮ ከመንጠላጠል ይልቅ ወደ ላይ የወጣውን ጎትቶ ለማውረድ ይተጋል። ጸሐፊው በኢትዮጵያውያን ባህል ውስጥ የሚስተዋለው አጥፊ ግለኝነት መሆኑን፣ ይህም የካፒታሊዝም ምሰሶ ተደርጎ ከሚወሰደው ዓይነት ግለኝነት (Individualim እንደሚለይ ያብራራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው ግለኝነት የሚወለደው የመንፈስ ከፍታ ወይም ይሉኝታ (Difidence) ወይም ወኔ ከማጣት በመሆኑ አጥፊ ነው፡፡
ከዚህ በተቃራኒ በካፒታሊዝም ጎልቶ የሚወጣው ግለኝነት ከሞላ ጎደል የግለሰብን ኢኮኖሚያዊ ግብ ወይም ጥቅም በማሳካት ሒደት ውስጥ ግለሰቡ ሌሎች ወገኖቹን ይጠቅማል ከሚል አዎንታዊ አመለካከትና ወኔ የሚመነጭ ነው፡፡ አጥፊ ግለኝነት ግን የግል ሀብትን (ከፍ ሲልም ሕይወትን) ለማኅበረሰብ ጥቅም ማዋል ግለሰቡን ይጎዳል ከሚል ፍርሐት የሚወለድ ሲሆን በውስጡ ባለሀብቱ ገንዘቡን ሊያውልለት የሚገባ ኅብረተሰብ ወይም ወገን የለም የሚል አመለካከትን ያዘለ ነው፡፡ ከዚህ ሲብስ ደግሞ ሌላው ሰው ወይም ወገን ባለሀብቱን ለማጥቃት፣ ለማጥፋት ወይም በእርሱ ተጠቃሚ ለመሆን የተቀባበለ ነው ከሚል ጠማማ እምነት የሚመነጭ ሲሆን፣ ሀብቱን በመጠቀም ራሱን ጠቅሞ ወገንን ከመጥቀም ይልቅ ሌላው ወገን እንዳያጠቃው በመጠበቅ ከተቻለም ቀድሞ በማጥቃት ወይም በማጥፋት ላይ ያተኩራል፡፡ እንዲህ ያለው ጠማማ አመለካከት ወይም ቆራጥነት በካፒታሊዝም ግለኝነት ውስጥም ይኖራል፡፡ ሆኖም ራስን ጠቅሞ ሌሎችን በመጥቀም ላይ በሚያተኩር የመንፈስ ከፍታ ወይም ብሩህ ዕሳቤ (Enlightened Self Interest) እና በሕግ የበላይነት (Rule of Law) ምክንያት ይለዝባል፡፡ በአጥፊ ግለኝነት ግን ሌሎች እንዲያብቡና እንዲበለፅጉ ከማገዝ ይልቅ ግለሰቡ ኪሳራን ወደ መቀበልና የግል ጥቅምን ጭምር ወደ መተው ያጋድላል፡፡ የሌሎች ማደግና መለወጥ ትርፉ ጠላት ማፍራት ነው የሚል አመለካከትም አለው፡፡
የሳሙዔል ዮሐንስ ‹‹Ethiopia: Creating a Culture of Progress›› መጽሐፍ በጉዳዩ ዙሪያ የሚከተለውን ድምዳሜና የመፍትሔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ኢትዮጵያ በእንዲህ ዓይነት ማኅበራዊ መዋቅርና የባህል ትብታብ ውስጥ ሆና ጠንካራ የፖለቲካ ሥርዓተ ለማቆም ወይም ሲቪል ማኅበረሰብን (Civil Society) ለማጠናከር ይቸግራታል፡፡ ሙሉ ትኩረቷን በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የቅርፅና ይዘት ለውጦች (Transformation) ላይ የምታደርግ ከሆነ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣትም ይከብዳል፡፡ ከዚህ አንፃር ባህል ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ጥያቄው ‹‹እንዲህ ያለውን የባህል ለውጥ ሊያመጣ የሚችለውና ማምጣትም ያለበት ማነው? ወይም የትኛው አካል ነው?›› የሚል ነው፡፡ መልሱ ዞሮ ዞሮ የሚያርፍበት ቀድሞውኑ እንዲህ ዓይነት የባህል አመለካከት እንዲፈጠር ጉልህ ድርሻ የተጫወቱት የሃይማኖት/የእምነት ተቋማት፣ የትምህርት ሥርዓቱ፣ እንዲሁም ሕዝባዊ ውይይቶች (Public Discourse) ላይ ነው የሚያርፈው፡፡
- ባደጉት አገሮች እንደተለመደው የእኛ አገር ሀብታሞች ‹‹ፋውንዴሽን›› በመመሥረት ያካበቱትን ሀብት ወደታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚያሰርጉበት ልምድ ኢምንት ነው። ማለትም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ጥቂት ናቸው። በርግጥ ድርጅት መሥርተው ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው። ሆኖም ያደጉት አገሮች ባለሀብቶችና ድርጅቶች የማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በተለያየ መልኩ ይወጣሉ። በእኛም ሀገር አንዳንድ ባለሀብቶች በምግባረ ሰናይና የችሮታ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል። ነገር ግን ለዚሁ ዓላማ የሚሆኑ ተቋማትን መሥርተው ሲንቀሳቀሱ አይታይም።
- ገበያ የሚዋቀርበት መንገድ መደበኛና ኢመደበኛ ኢኮኖሚን የሚያያይዝ ከሆነ ሀብትን ከላይ ወደታች የማስረግ አቅም አለው። ሆኖም አሁን በተያዘው የልማት አካሄድ ለኢመደበኛ ኢኮኖሚ ትኩረት የመንፈግ አዝማሚያ አለ። በኮሪደርም ሆነ በከተማ ልማት እንዳየነው ኢመደበኛ ኢኮኖሚው እምብዛም ቦታ አላገኘም። በዚህ አካሄድ በሁለቱ መካከል ያለው ድልድይ ከተሰበረ የልማትና ዕድገቱ በረከት ወደ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሊሰርፅ አይችልም። በቀላል ቋንቋ አንድን ጫማ ጠራጊ (ሊስትሮን) ከኮሪደር ላይ ማንሳት ወይም ከከተማ ማጥፋት ይህን ድልድይ የሚሰብር አካሄድ ነው። በዚህ ረገድ ማልኮም ኤክስ ካዲላክ መኪናውን የገዛው የሙዚቀኞችን ጫማ በመጥረግ መሆኑን በመጽሐፉ አስፍሯል። (ይቀጥላል)
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በስደትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያደርግ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያ፣ በኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ጥናት ፕሮጀክት ላይ ከመሥራታቸውም በላይ ‹‹መንገደኛ›› እና ‹‹እላፊ›› በተሰኙ መጻሕፍት በአንባቢያን ዘንድ የሚታወቁ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ እየገለጽን በኢሜይል አድራቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡