በሳምሶን ተክለአብ
ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣ ‹‹ጥያቄ አለኝ››፣ ወይም ‹‹እንዳደረጉ ያድርጓት›› ብሎ አንገቱን እንደ ሰጎን የቀበረውም ሁለተኛ ቤት እንደሌለው የታወቀ ነው፡፡ የአገሩን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ የደምና የአጥንት ዋጋ የሚከፍለውም ሆነ፣ በሕዝብ ላይ እንደ አልቅት ተጣብቆ አገሩን በጥገኝነት የሚቦጠቡጠውም ቢሆን መከረኛዋን ምድር ‹‹አገሬ›› ማለቱ አይቀርም፡፡ ሌላው ቀርቶ ባህር ተሻግሮ ኑሮን ለመግፋት በስደት የሚባክነውም ሆነ መቀመጫውን አሽሽቶ ‹‹በለው…! በለው…!›› ሲል ውሎ የሚያድረው እንኳን ቢያንስ ሲሞት አስከሬኑ የሚላከው ወደ እዚህ ነው፡፡
እናም አገራችን ለመንግሥትም ሆነ ለማንኛውም አንድ ወገን የምትተው አይደለችም፡፡ ይልቁንም መላው ዜጎቿም ሆንን ሁሉም ይመለከተኛል የሚል አካል በአገሩ ጉዳይ መምከርና ስለሰላሟም ሆነ ደኅንነቷ መጨነቅ፣ ብሎም መጪውን ወቅት ለማቃናት ተደራድሮና ተስማምቶ መገኘት ግድ የሚለው ይሆናል፡፡
ይህ ደግሞ አሁንም ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ በተስፋ ብቻ ሳይሆን፣ ከሞላ ጎደል በፈተና የታጠረ መሆኑን አምኖ ከመቀበል መጀመር ይኖርበታል፡፡ በአንድ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች፣ ሥርዓተ አልበኝነቶችና የተለያዩ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአንፃራዊነት ሰላምና መረጋጋት በሚስተዋልባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ልማትና የመሠረተ ልማት ብሎም የዕድገት ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች አጣጥሞና አቃንቶ ወደ ተሻለ ዕድገትና የዴሞክራሲ ምዕራፍ ለመሻገር ሁሉም ወገን በሰከነ የፖለቲካ ትግልና በዕርቅ መንፈስ ኃላፊነቱን መወጣትና መትጋት ትውልዳዊ አደራው ነው፡፡
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚውም ሆነ የማኅበራዊ ዘርፍ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ከስድስት ዓመታት በፊት ለውጡ እንዲመጣ በቀዳሚነት በሕዝብ የተፈለገው የፖለቲካ ጥያቄዎችን እንዲፈታ ነበር፡፡ በተለይም የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ላይ የወደቀው ጫና እንዲነሳ፣ ጠንካራ አገረ መንግሥትና የሕዝቦች አንድነትን ለመመለስና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ የመገፋት ስሜት ሳይመቸውና አሳዳጅ/ተሳዳጅ ሳይኖር፣ በልዩነት ውስጥም ቢሆን ተቻችለው እንዲኖሩ ማድረግ የሕዝቡም፣ የለውጥ ኃይሉም ምኞት እንደነበር በተግባርም ታይቷል፡፡
ሕዝቡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታና በአመለካከትም ሆነ በዕድሜና በሌላ ያሉትን ተፈጥሯዊ ልዩነቶች እንዲያጠብ የሚረዱ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱም የሁሉም ህልም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የተጀመሩ የኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በፍትሐዊነት ሥርጭታቸው ተጠናከሮ እንዲቀጥል፣ እንዲሁም እንደ ሙስናና የመልካም አስተዳዳር ብልሽቶች እንዲታረሙ ያልተመኘም አልነበረም፡፡ ለዚህም በሒደት በሕዝብ ቅቡልነት ያለው፣ አካታች፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተላበሰ መንግሥታዊ ሥርዓት መፍጠርን በጉጉት ሲጠብቅ ነበር፡፡ አሁን ላይ ችግሮቹ ስለመቃለላቸው ሳይሆን ስለመባባሳቸው መነገሩና ጥርጣሬው እንዴት መጣ ብሎ መፈተሽ ያሻል፡፡
በእርግጥም በለውጡ ጅማሬ ሰሞን በርካታ ተግባራት የተስፋ ብርሃን መፈንጠቃቸውና የሕዝቡም ተስፋና ጉጉት ከፍታን በቅርብ የምናስታውሰው ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የለውጡ ኃይል በአመለካከት ልዩነት ሰበብ የታሰሩ ዜጎችን መፍታቱ፣ ጋዜጠኞችና የማኅበራዊ አንቂዎች የሐሳብ ነፃነት እንዲያገኙ፣ የተጋጩና ጫፍና ጫፍ የቆሙ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገራቸው እንዲገቡና እንዲቀራረቡ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ጉዳያቸው እየመከሩ፣ በልዩነታቸውም በነፃነት እየተንቀሳቀሱ በአገራቸው ጉዳይ ያገባኛል የሚሉበት ጊዜ እንዲመጣ፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር አገርን የዘረፉ እንዲጠየቁና የሕዝብ ሀብትም እንዲመለስ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
አሁን መለስ ብሎ ጥያቄ መነሳት ያለበት ጅምሩ ለምን ወደኋላ ተመለስ? የሚለው ጭብጥ ላይ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ምሁራን በአንድ በኩል በጋራ የተገኘው ለውጥ በተቻለ መጠን ሁሉንም ወገኖች ባካተተና ቀደም ሲል አገራዊ ድክመቶች ተብለው የተለዩ ሕግጋትና ሥርዓታዊ ባህሎች እንዲስተካከሉ ጥረት አለመደረጉን በድክመት ያነሳሉ፡፡ በሌላ መልኩ ሰላማዊና ሥልጡን የፖለቲካ መታገያ መንገዶች እየተሰናከሉ በኃይልና በአመፃ ጥቅምን/የሥልጣን ፍላጎትን በአገር ላይ ለመጫን ተደጋጋሚ ሙከራ መታየቱን ይጠቅሳሉ፡፡
በተጨማሪም በሕዝብ ግፊትና በሥርዓቱ ውስጥ ባሉ ለውጥ ፈላጊዎች የተጀመረው አዲስ ዕርምጃ ጥቅሙን ያሳጣውና ያልተዋጠለት ኃይል ‹ሕውሓት› በተሳሳተ ሥሌትም ቢሆን ዋነኛው ተገዳዳሪ መሆኑ፣ በየአካባቢው ለተነሱ የትጥቅ ትግሎችና ፍልሚያዎች በር ከፍቷል ይላሉ፡፡ ሒደቱ ከፍተኛ እስከሚባል አውዳሚ ጦርነት መግባቱ ብቻ ሳይሆን፣ እስካሁን በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልሎች ለቀጠለው ጦርነት የራሱን አሉታዊ ድርሻ እንዳበረከተ በመጠቆም፡፡ በዚህም ሺዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተንገላተዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቃይና ተረጂ ሆነዋል፡፡ በቢሊዮን የሚገመት የአገር ሀብት ለጦርነት ተማግዷል፣ እየተማገደም ነው፡፡ ስለሆነም በቀዳሚነት ከተገባበት ቀውስ ለመውጣት የጋራ ጥረትና የሰከነ የፖለቲካ ውይይት ባህል መጀመር አለበት ባይ ናቸው፡፡
በእርግጥ ተስፋ የተጣለበት ለውጥ በድንገትና ያለ መስዋዕትነት የተገኘ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት አምባገነናዊውን የደርግ ሥርዓት በተራዘመ የትጥቅ ትግል አሸንፎ፣ በተለይም የብሔር መብቶችን በማስከበር፣ የኢኮኖሚ ለውጦችም እንዲመጡ ለማድረግ መሞከሩ የማይካድ ነበር፡፡ ይሁንና ሥርዓቱ ዴሞክራሲን በማጥበቡና በማዳከሙ፣ ፌዴራሊዝም ትክክለኛ መፍትሔ ቢሆንም፣ ልዩነትንና ጎጠኝነትን በማባባሱ፣ ልማት ቢኖርም ኢፍትሐዊነትን (ቀላል የማይባሉ ነፋስ አመጣሽ ባለፀጎች ቢኖሩም ይልሰው፣ ይቀምሰው የሌለው 30 በመቶ ገደማ ዜጋ እንደነበርም ፈፅሞ አይካድም) ሥር እየሰደደ በመሄዱ ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህንን ትውልድ የሚጠቅመው፣ ዞር ብሎ በመመልከት የቱ ችግር ተቀረፈ? የቱ አሁንም ቀጠለ? ወይም ተባባሰ ብሎ መፈተሽ ነው፡፡
ብዙዎች እንደሚናገሩት ዛሬ ላይ እንዳለመታደል ሆኖ የተጀመረው ፖለቲካዊ ለውጥ ገና ተጠናክሮ በእግሩ መቆም አልቻለም፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ በልዩነት ውስጥም ቢሆን ብሔራዊ መግባባት ባለመፈጠሩ በየአቅጣጫው መጎተቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ የሕዝቦች አብሮ የመኖር ታሪክን ለመበጣጠስ በውስጥም በውጭም የሚሸረበው ሴራ ተባባሰ እንጂ አልቆመም፡፡ አንዱ ሕዝብ ከሌላው ጋር በጋራ አብሮ ለመኖር የተሳነው፣ እርስ በርሱ የሚገፋፋ፣ የአንድ አገር ልጆች በሐሳባዊ ክልል ታጥረው የሚሳደዱ፣ ዜጎችም ከማንነት ፍጥጫ ያልወጡና የማስመሰሉን ፖለቲካ የሚገፈፍበት ንግግር ተጠናክሮ አልተጀመረም፡፡
ይህንን አስቸጋሪና አስከፊ ሁኔታ በማስወገድ አገር በተረጋጋና ዋስትና ባለው ሰላምና ዴሞክራሲ እንድትቀጥል ግን ቆም ብሎ ማሰብ የሚያስፈልገው አሁን ነው፡፡ በአስቸኳይ!! በቀዳሚነት ኃላፊነት ወስዶ የብሔራዊ ዕርቅና የሰላም ድርድር መሪ መሆን ያለበት ደግሞ መንግሥት ስለመሆኑ ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች ይስማሙበታል፡፡ እንደ ሕዝብም ልዩነት እንኳን ቢኖር፣ ካረጀውና ከተንሻፈፈው ትርክትና አስተሳሰብ ተላቆ፣ በሕግና ሥርዓት እየተመሩ መኖር ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡
ፖለቲከኞቻችንና የማኅበራዊ አንቂዎችም የብሔር ፉክክርን፣ በተለይም መጠራጠርንና ሽኩቻን አስወግደው በብሔራዊ መንፈስ ሰላማዊ ትግልን በማካሄድ አብሮነትን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ብሎም የፍትሐዊነት አጀንዳን ማራመድ ይጀምሩ ዘንድ ታሪክ አደራ ጥሎባቸዋል፡፡
እንደ አገር ያንዣበበውን አገራዊ የመነጣጠል ትርክት የሚቀርፍ ዕሳቤ ለማራመድ ደግሞ ከእነ የሚነሳበት ቅሬታ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑንም ሆነ፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ ሕገ መንግሥታዊ ድርጅቶችና አሠራሮችን ተቀብሎ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው፡፡ ምናልባት የገለልተኝነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን የዳኝነት አካላትም ሆኑ የሕዝብ ምክር ቤቶችንም ቢሆን ከየትኛውም ኢፍትሐዊ ዕሳቤ ጫና ነፃ እንዲሆኑ በማድረግና ዕድል በመስጠት ወደ መነጋገርና የጋራ መፍትሔ መፈለግ መውሰድ ትኩረት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ በደምሳሳው ለአገረ መንግሥትና ተቋማቱ ዕውቅና ነፍጎ መነሳት ግን ሄዶ ሄዶ አፈ ሙዝን መቀልበስ አያስችልም ይላሉ ምሁራን፡፡
በመንግሥት በኩልም ቢሆን ‹‹አንድ ጊዜ ሥልጣን ከጨበጥኩ ነቅናቂ የለኝም፣ ያልኩት ብቻ ይደመጥ፣ ሌላ አልሰማም፣ ብፈልጥም ብቆርጥም ሁሉም ይቀበል›› የሚል ዕሳቤ እልህ ምላጭ ያስውጣልን የሚጋብዝ እንጂ መደማመጥን አያመጣም፡፡ ይልቁንም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተቃራኒ ወይም ባልተገባ መንገድ የተሠለፉ ወገኖችን ለመመለስ የሚያስችል የማቀራረብ፣ የይቅርታና ወደ ሕግና ሥርዓት የማስገባት ሥራ ላይ ማተኮር ፖለቲካዊ ብልህነት ነው (ሁሉንም የፖለቲካ ችግሮች በኃይል ብቻ መፍታት የሚቻል እንዳልሆነም የዓለምን ታሪክ መመርመር ነው ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች)፡፡
አሁንም ሆነ ለወደፊት ለግጭት የሚጋብዙ ንትርኮችና አለመግባባቶች ተቀልብሰው፣ ፖለቲከኞችም ሆኑ ዜጎች ወደ መቀራረብና መነጋገር ብሎም ስክነት ወደ ተላበሰ የፖለቲካ ባህል ለመግባት ግን ከዕርቅና ከድርድር መጀመር አለበት የሚለውን መውሰድ የሁሉም ኃይሎች ድርሻ ነው፡፡ በበጎ ጅምርና መደማመጥ አገር የማፅናት መሠረት በጋራ ከተጣለ በኋላ/ወይም ጎን ለጎን ደግሞ በአገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታውን ቢያንስ በሥራ ላይ ካለው ሕገ መንግሥት አንፃር መተግበር አስፈላጊ ነው፡፡
እርግጥ እዚህ ላይ እንደ መንግሥት መልካም ጥረቶች፣ ዋስትና የተሰጣቸው ቁም ነገሮች ቢኖሩም በግጭትና አለመግባባት መደፍረሳቸው አይካድም፡፡ የጦርነት መንፈስ የተገዳዳሪ ፖለቲከኞች የተፎካካሪነት ሥነ ልቦናና ብቃት ተዳክሞ፣ የሲቪክ ማኅበራትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፎ መቀዝቀዝ ለመታየቱም ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ስለሆነም በቡድንም ሆነ በግል ቀስ በቀስ ከመዳከም ስሜት እየወጡ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ያገባኛል የሚል የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ባህል ማቆጥቆጥ ይኖርበታል፡፡ መንግሥታዊ ዋስትና ሊሰጠውም ግድ ይላል፡፡
እውነት ለመናገር በአገር ደረጃ በቀደሙት 27 ዓመታት የኢሕአዴግ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መንፈስ ቢቀነቀንም ሁሉም ሕዝብ የሚተማመንበት የምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶችና ገለልተኛ የፀጥታ ተቋማት ካለመኖራቸውም በላይ፣ ገዥው ፓርቲ በሁሉም መስክና መንግሥታዊ ክንፍ በዓውራነት እጁን በሰፊው ያስገባ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ስለዴሞክራሲ በስፋት ቢነገርም፣ በተግባር በቂ ውጤት ሊመጣ አለመቻሉ፣ ጭራሽም ሥርዓቱ የደከመባቸውንና ተስፋ ያሳየባቸውን ተግባራት ሁሉ ዋጋ የሚያሳጣ መጠልሸት ደርሶበታል፡፡ በሕዝብ ቁጣ ለመገፋትም ዳርጎታል፡፡
አሁን ያለው የፖለቲካ ትውልድና አመራር ደግሞ ካለፈው ድክመት በመማር ሕዝብን ባከበረ አኳኋን፣ በሰከነ ፖለቲካና ሥልጡን መንገድ አገር የሚፀናበትን ባህል ማለማመድ ካልጀመረ ወደ ኋላ መመለስ ነው የሚመጣው፡፡ ስለሆነም በተቻለ መጠን በአስተሳሰብና በተግባር ያጋጥሙ የነበሩና እየጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ቀርፎ፣ በዕርቅና በድርድር መንፈስ አዲስ ምዕራፍ የመክፈት ቀዳሚ ኃላፊነት የመንግሥት መሆን አለበት፡፡ በሒደቱ የማይመለከተው ሁሉ መንቦጫረቅ ሳይኖርበት፣ መላው የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎችና ልሒቆች ሚና ጎልቶ መውጣት ይኖርበታል፡፡
ማንም ይጀምረው ማን በሰላማዊና ሕጋዊ መድረክ ተቀምጦ ለአገራችን ችግሮች የጋራ መፍትሔ መሻት የድርድር ብሎም የዕርቅና የአንድነት ውይይት ማድረግ የሚጠቅመው ሁላችንንም መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ እዚህ ላይ አንድ የቀደመ ከያኒ ‹‹ወደ ኋላ እየሄድሽ በሐሳብ ከማለም፣ ቀኑ እንዳይመሽብሽ ትናንት ዛሬ አይደለም›› ሲል እንዳቀነቀነው፣ በቅርብም ሆነ በሩቅ የተፈጠሩ የሴራ ፖለቲካና ጥፋቶችን በማመንዥክ የሚባክን አሁን ሊኖር አይገባም፡፡ ወደፊት ማማተርና ነገን ማለሙ ይበጃልና፡፡
በመሠረቱ በየትም አገር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ባሉት የምድር ክፍሎች ሁሉ መንግሥታት አሉ፡፡ እነዚህ የምድር ገዥዎች በዴሞክራሲና በኢዴሞክራሲ መንገድ ሥልጣን ላይ በመውጣታቸው ምክንያት የሚፈጠር ልዩነት ይለያያቸው እንደሆነ እንጂ፣ ሁሉም ቢሆን እንደ የአቅማቸው የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ሁሉም ሥልጣን ለመጨበጥ መወዳደራቸውም አይቀርም፡፡ ይነስም የብዛም ገዥ በሆነ ሕግ የሚተዳደሩትና በተመጣጣኝ የፖለቲካ ንፍቀ ክበብ የሚታገሉትም ትንሽ አይደሉም፡፡ ማንም ቢሆን ግን ዘለዓለማዊ አይደለም ሂያጅ እንጂ፡፡
ኢትዮጵያውያንም ከዚህ ውጪ አይደለንም፡፡ ነገር ግን አንድነት፣ ፍቅርና ዕርቅን በመስበክ፣ በልዩነት ውስጥ የተበታተነን አመለካከት ወደ አንድ (ብሔራዊ ጥቅምና የጋራ እሴቶች) ከማምጣትና ዴሞክራሲን በቁርጠኝነት ለማስፈን ከመነሳት የበለጠ ተግባር የለምና እንደ ሕዝብ በችግር ውስጥም ቢሆን ለሰላምና መረጋጋት፣ ለሰከነ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ዕውን መሆን መሠለፍ የውዴታ ግዴታችን ነው፡፡ ጦርነትና መተላለቅን የሚያቆመው እንደ ሰጎን አንገት ቀብሮ ከማልጎምጎምም ሆነ ከአያገባኝም ባይነት ወጥቶ ሰላማዊ የትግል ሥልትን መከተልና ማጠናከር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ የዓለም አገሮች እንደሚታየው ለፓርቲ ፖለቲካ ተወዳዳሪነት መዳከምና ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጨንገፍ ብሎም ለጥላቻና የተካረረ የፖለቲካ መስተጋብር መስፈን ዋነኛ ተጠያቂዎች መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሱ ሕዝቡም ነው፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የዕድገት ደረጃ አምባገነንነትንና የብዝበዛ መዋቅርን መቀየር መቻል ወይም ትውልዱን የሚመጥን ለውጥ ማስመዝገብ እንደ ትውልድ ኃላፊነት መቆጠር ይኖርበታል እንጂ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ ነገሮችን ቀባብቶ ማለፍ የሚበጅ አይሆነም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ እንዳለው ሥልጣንን በኃይል ለመያዝም ሆነ፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማዳከም ከተሞከረ ግን የአንድ ወገን (ቡድን) የበላይነት እየሠፈነ፣ ፖለቲካንም ሆነ ኢኮኖሚን (ሥልጣን ያለ ተወዳዳሪ ብሎም ከሕዝብ ፈቃድ ውጪ መያዝ ስለሚፈጥር አገር ለብዝበዛ የተጋለጠ መሆኑ የታወቀ ነው) ያለ ፍትሐዊ ተወዳዳሪነት ጨምድዶ ለመያዝና ለማስለቀቅ ብርቱ ፍልሚያ መፈጠሩም አይቀሬ ነው፡፡ ይህም የሚጋብዘው አገራዊ ውድቀት ነውና ወደ ትክክለኛው መስመር መመለስ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡
በአጠቃላይ መንግሥት በጅምላው የሕዝቡም ይባል የአንድ ወገን ‹‹መብቴ ይከበርልኝ›› ጥያቄ ሲገጥመው፣ መነሻውና አስተሳሰቡ የሌላውን መብት የሚጨፈልቅ አይሁን እንጂ፣ ፈጥኖ ለመፍትሔ ወደ ጠረጴዛ መሳብ ነው የሚጠቅመው፡፡ ለሚነሱ ችግሮች ፈጥኖ መፍትሔ መስጠት እንኳን ባይቻል ሳይካረሩ፣ ለንግግር በር እየከፈቱ ንፋስ ማስመታቱ ባለፉት ዓመታት ከተገባባቸው የፖለቲካ ቀውሶችና ምስቅልቅሎች ያድናል፡፡ ነገሮችን መናቅ፣ ለውስጥ ችግሮች ውጫዊ ሰበብ መደርደርና ነገሮችን ለሴራ ፖለቲካ ማጋለጥ ግን የሚበረታው አደጋው ነው፡፡ ነገ ዛሬ ሳይባል ለሰከነ የፖለቲካ ባህል ግንባታና መደማመጥ ለተላበሰ ድርድር ትኩረት ይሰጥ በሚል ጽሑፌን ልቋጭ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡