ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 Best and reliable news source in Ethiopia
[ክቡር ሚኒስትሩ ከድርጅት ሥልጠና መልስ ወደ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ከስልካቸው ላይ እንድ ነገር እያነበቡ አገኟቸው]
- እንዴት ሰነበታችሁ?
- ውይ… መጣህ እንዴ?
- እ… ስልክሽ ላይ ያተኮርሽው ምን አግኝተሽ ነው?
- አይገርምህም?
- ምኑ?
- መገጣጠሙ?
- የምኑ?
- አንተ ከሥልጠናው ስትመለስ እኔ ደግሞ አለቃችሁ የሰጡትን ማሳሰቢያ እያነበብኩ ነው ያገኘኸኝ።
- የምን ማሳሰቢያ ነው?
- በሥልጠናው ለተሳተፉ አመራሮች የሰጡት ማሰሰቢያ ተብሎ የወጣ ዜና ነው።
- ምን ይላል?
- የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር…
- እ…?
- አመራሩ አገራዊ የመሻገር ትልሞችን በታላቅ ርብርብና ቅንጅት ማሳካት አለበት ይላል።
- ታዲያ ምኑ ነው አንቺን እንዲህ የመሰጠሽ?
- የቃሉ መደጋገም አስገርሞኝ ነው።
- የትኛው ቃል?
- መሻገር… ሽግግር የሚለው ቃል
- ተደጋገመ ስትይ?
- ይኸው የእናንተ አለቃም ዛሬ ብለዋል።
- ምን አሉ?
- አገራዊ የመሻገር ትልሞች ብለዋል።
- ታዲያ መቼ ተደጋገመ?
- ተደጋግሟል። አንዴ ብቻ መስሎህ ነው ያሉት?
- አዎ።
- ሌላም ብለዋል።
- ምን አሉ?
- ዕውቀት መር ሽግግርን ማፅናት ያስፈልጋል ብለዋል።
- እህ…?
- ከዚህ በፊትም ሲናገሩ መስማቴን አስታውሳለሁ።
- ምን ብለው?
- የሽግግር ፍትሕ ብለው።
- አዎ። አሱ ግን ሌላ ጉዳይ ነዋ?
- እናነተ ብቻ ሳትሆኑ ሌሎችም ሲሉ ሰምቻለሁ።
- ማን ሲል ሰማሽ?
- ተቃዋሚ ፓርቲዎች።
- ምን አሉ?
- ይህንኑ ቃል ሲናገሩ ሰምችለሁ።
- ምን ብለው?
- የሽግግር መንግሥት… ግን…
- ግን ምን?
- ሰሞኑን በሽግግር ላይ ሽግግር ሳያደርጉ አይቀርም።
- እንዴት? ምን ማለት ነው?
- ሰሞኑን የቀየሩት መሰለኝ።
- ምኑን?
- የሽግግር መንግሥት ሲሉ የነበረውን።
- ምን ብለው ቀየሩት?
- የሽግግር ሒደት።
- እውነትም ልክነሽ ይኼ ቃል ተደጋግሟል።
- እኔ እኮ ብያለሁ።
- አንቺን ግን ምን አሳሰበሽ?
- ለምን አያሳስበኝም?
- ምን ያሳስብሻል?
- ጥሩ ነገር ቢሆንስ?
- እና ቢሆንስ?
- ከሆነማ እኔም እደርጋለሁ።
- ምን?
- የራሴን እጀምራለሁ።
- የራስሽን ምን?
- ሽግግር።
- ምን እያልሽ ነው?
- ምነው?
- ወዴት ነው የምትሻገሪው?!
- እኔ እሻገራለሁ አላልኩም።
- እና ምን እያልሽ ነው።
- እጀምራለሁ ነው ያልኩት
- ምኑን?
- ሒደቱን።
- እ… እኔ ደግሞ ሌላ ነገር የፈለግሽ መስሎኝ ነበር።
- ምን?
- የሽግግር ባል።
- እሱን ወደፊት አየዋለሁ።
- በምን?
- በሽግግር ፍትሕ!
[ክቡር ሚኒስትሩ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ያለበትን ደረጃ በተመለከተ የሰጡት መረጃ ለምን በጥርጣሬ እንደታየ አማካሪያቸውን እየጠየቁ ነው]
- አክቲቪስቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ትችት የሰነዘሩብን ለምንድነው? የምታውቀው ነገር አለ?
- ምንም የሰማሁት ነገር የለም።
- እንዴት?
- እኔ እኮ ማኅበራዊ ሚዲያ ብዙም አልከታተልም ክቡር ሚኒስትር።
- ይኸውልህ፣ ያኔ ሥልጣኔ ባልነበረበት ዘመን እንኳ ንጉሡ አማካሪዎቻቸውን ‹‹እረኛ ምን አለ›› ብለው ይጠይቁ ነበር። ይህን ታውቃለህ?
- ሲባል ሰምቼያለሁ።
- ታዲያ እንዴት ማኅበራዊ ሚዲያ አልከታተልም ትለኛለህ?
- ክቡር ሚኒስትር ማኅበራዊ ሚዲያ ፈጽሞ አልከታተልም ማለቴ እኮ አይደለም።
- እና ምን ማለትህ ነው?
- ከሥራ ሰዓት ውጪ ነው የምከታተለው ማለቴ ነው።
- ስለዚህ ምክንያቱን ታውቃለህ ማለት ነው?
- የምኑን?
- ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ባቀረብነው መረጃ ላይ ለምን ትችት እንደተሰነዘረብን?
- ጥቃቅን ጉዳዮችን መዘው ለማጯጯኽ ሞከሩ እንጂ የከፋ ትችል አይደለም።
- ጥቃቅን ቢሆኑም ስህተት ፈጽመናል እያልከኝ ነው?
- አዎ። ግን ትርጉም የማይሰጡ ጥቃቅን ጉዳዮች ናቸው።
- ያቀረብኩት መረጃ የተሰናዳው በማክሮ ኢኮኖሚ ቲሙ አይደለም እንዴ?
- ነው?
- ታዲያ እንዴት ስህተቱ ሊፈጠር ቻለ?
- የተሰናዳውን መረጃ ለማጠናከር ብለው እርሶ ያካተቷቸው አንዳንድ ነጥቦች ነበሩ።
- ስህተቱን የሠራኸው አንተ ነህ እያልከኝ ነው?
- ስህተት የሚባል አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
- እና ምንድነው?
- ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መረጃ ሲያጣቅሱ የተፈጠሩ ጥቃቅን ስህተቶችን ነው ለማጯጯኽ የሞከሩት።
- ስህተቶቹ ምንድናቸው
- ኢኮኖሚያችን ከሰብ ሰሀራ አፍሪካ ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ከምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ደግሞ አንደኛ ነው ያሉት ላይ መጠነኛ የደረጃ መዛባት ነው የተፈጠረው።
- እንዴት? የእኛ ደረጃ የተሳሳተ ነው?
- ከሰሐራ በታች አምስተኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን ያሉት ትክክል ነው።
- ከምሥራቅ አፍሪካስ አንደኛ አይደለንም?
- አንደኛ ነን፣ ግን ሩዋንዳ በሽርፍራፊ ነጥብ ትቀድመናለች።
- ሩዋንዳ ትቀድመናለች?
- ክቡር ሚኒስትር በስብርባሪ ነጥብ ነው የምትበልጠን።
- ለነገሩ ሩዋንዳና ኢትዮጵያ አንድ ናቸው።
- ልክ ነው።
- አዎ። እኔ ኦኮ በደንብ ነው የማውቃቸው።
- አዎ። ለተወሰኑ ዓመታት እዚያ እንደነበሩ አውቃለሁ።
- እሱ ብቻ አይደለም።
- እ…?
- ቆይ ወዲህ ቀረብ በል ሌላ ሚስጥር ልንገርህ።
- እሺ..
- የዘር ሐረጋችንም አንድ ነው።
- ክቡር ሚኒስትር እውነቶትን ነው?
- ይኼ ብቻ መሰለህ?
- እ…?
- ቁርጥ እኛን ነው የሚመስሉት።
The post [ክቡር ሚኒስትሩ ከድርጅት ሥልጠና መልስ ወደ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ከስልካቸው ላይ እንድ ነገር እያነበቡ አገኟቸው] first appear on ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 Best and reliable news source in Ethiopia and is written by በጋዜጣዉ ሪፓርተር