በአማራ ክልል በሰሜን ጦርነት ወቅት በሕገወጥ ሁኔታና ለምርመራ ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ 11,000 ሰዎች በፖሊስ ታስረው እንደነበርና የመንግሥት ባለሥልጣናት ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፣ በእስር ወቅት የደረሰባቸውን የመብት ጥሰት በሚመለከት ዳኞች እንዳይጠይቁ ትዕዛዝ ተላልፎላቸው እንደነበር ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በወንጀል ተጠርጥረው በታሰሩና በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ሆነው ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ተቋማዊና ተደጋጋሚ የመብት ጥሰቶችን ለመለየት ምክረ ሐሰቦችን በማቅረብ፣ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን ለማሻሻል በዓይነቱ የመጀመሪያ በሆነው ብሔራዊ ምርመራ ግኝቶች ሪፖርት ላይ ነው።
ሪፖርቱ በቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በአማራ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች፣ ከሚያዚያ 2010 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን፣ ተጎጂዎችና የዓይን እማኞች ቃለ መሐላ ፈጽመው ያሳወቁትን ዝርዝር ጉዳይ፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የፖሊስ ኮሚሽኖች፣ የፍትሕ ቢሮዎች፣ የፍርድ ቤት ኃላፊዎችና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ምላሽና አስተያየት አጠናቅሮ አቅርቧል።
በዚህም መሠረት በአማራ ክልል በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በእስር ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ሆነው ነፃነታቸውን ከተነፈጉና የመብት ጥሰት ከተፈጸመባቸው መካከል የተወሰኑት ለኮሚሽኑ ምስክርነታቸውን አሰምተዋል።
በሰጡት ምስክርነት መሠረት በክልሉ የዘፈቀደና ሕገወጥ እስራቶች መፈጸማቸውን የገለጹ ሲሆን፣ 18 ተጎጂዎች ከሚኖሩበት አካባቢዎች ርቀው መታሰራቸውን ሲያሳውቁ፣ ሌሎች ሁለት ደግሞ ከምሽት 3፡30 ሰዓት በኋላ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።
አምስት ተጎጂዎች ከአንድ ጊዜ በላይ በዘፈቀደ መታሰራቸውንና አንድ ምርመራ ተጠናቅቆ ቢለቀቁም ይህ ነው ተብሎ ባልተገለጸ ሌላ ምክንያት እንዲታሰሩ መደረጋቸውን አሳውቀዋል።
በክልሉ ተጎጂዎችና ምስክሮች በቁጥጥር ሥር ከዋሉባቸውና በእስር ላይ ቆይተው ነፃነታቸውን ከተነፈጉባቸው ሁኔታዎች መካከል፣ የተጠርጣሪዎችን ቤተሰብ አባላት በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ መብቶቻቸውን በተግባር በመጠቀማቸው ምክንያት የተፈጸመ እስራት፣ እንዲሁም ኢ መደበኛ በሆኑ የማቆያ ማዕከላት ውስጥ ማቆየት የሚሉት በኢሰመኮ ብሔራዊ ምርመራ ግኝቶች ሪፖርት ላይ ተጠቅሰዋል።
የተወሰኑ ተጎጂዎች በተጠርጣሪዎች ምትክ መታሰራቸው የተጠቀሰ ሲሆን ይህም ተጠርጣሪ የሆነው ሰው ዘመዳቸው ወይም የቤተሰባቸው አባል ስለሆነ፣ የእነሱን እስራት በማወቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲመጣ ለመገፋፋት እንደሆነም ተነግሯል።
መሰል ወንጀሎች ከተፈጸሙባቸው መካከል ምስክርነቱን ለኢሰመኮ የሰጠ አንድ ተጎጂ፣ ማክሰኞ መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ,ም. ፖሊስ በቁጥጥር ሊያውለው በተንቀሳቀሰበት ወቅት፣ የፖሊስ አባላት ላይ በመተኮስ የሁለት አባላት ሕይወት እንዲያልፍ አድርጓል የተባለ ተጠርጣሪ ዘመድ ይገኝበታል። ተጎጂው የተጠርጣሪው ዘመድ በመሆኑ ምክንያት በምዕራብ ጎጃም ዞን ዋድ ፖሊስ ጣቢያ ከአንድ ወር በላይ መታሰሩንና በቆይታውም ፍርድ ቤት አለመቅረቡን አስረድቷል።
በሌላ በኩል በሕግ የተረጋገጡ መብቶቻቸውን በመጠቀማቸው ምክንያት በፖሊስ የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውም ተገልጿል። በሪፖርቱ ላይ የተካተተ አንድ ተጎጂ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች መንግሥትን የሚቃወም ይዘት ያለው ልጥፍ አውጥተሃል በሚል የትኖራ በሚባል ኢ መደበኛ የሆነ የማቆያ ቦታ መታሰሩን ገልጿል።
ሌሎች 14 ሰዎችም በባህርዳር ድብ አንበሳ ሆቴል በወቅታዊ ክልላዊ ሁኔታዎች ላይ ለመወያየት በመሰብሰባቸው ምክንያት በፖሊስ ተይዘው በክልሉ የልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸውም ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል አንድ ሌላ በደቡብ ጎንደር ፎገራ ወረዳ እንደሚኖር የገለጸ ተጎጂ ደግሞ፣ እሱና ሌሎች መንግሥት በርብ ወንዝ ላይ ለሚያካሂደው የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ልማት ተነሺዎች ምትክ የእርሻ መሬትም ይሁን ካሳ ስላልተሰጣቸው፣ ይህ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው ምክንያት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል።
እንደተጎጂው ማብራሪያ በአካባቢው ችግሩ የደረሰባቸውን አርሶአደሮች በመወከል፣ በመንግሥት ላይ ክስ የመሠረቱ ሰዎች ከፍርድ ቤት ሲወጡ ከደጃፍ ላይ ጠብቆ ያላግባብ ያሰራቸው ፖሊስ፣ ተወካዮቻቸውንና ጠበቆቻቸውን መንግሥትን ምትክ መሬት መጠየቅ እንዲያቆሙ ማስፈራራቱንና በኋላም ጉዳያቸው በመንግሥት ትዕዛዝ በእንጥልጥል እንዲቆይ (Suspend) መደረጉን አሳውቋል።
በሌላ በኩል ኢ መደበኛ የታሳሪዎች ማቆያ ቦታ በምሥራቅ ጎጃም የትኖራ፣ በአዊ ዞን ቲሊሊና በደቡብ ጎንደር ጋይንት እንደሚገኙም ተገልጿል። ከእነዚህ ባሻገር የፖሊስና የመከላከያ ካምፖች በተጠርጣሪዎች ማቆያ ሥፍራነት ማገልገላቸውም ተጠቅሷል።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ ያካተታቸው ተጎጂዎች በየትኖራ እስከ 900 ሰዎች፣ በቲሊሊ እስከ 700 ሰዎች እንዲሁም በጋይንት ደግሞ ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎችን መመልከታቸውንና በቆይታቸው ርዝማኔ ሒደትም ቁጥሩ እየጨመሩ መምጣቱን ማሳወቃቸው ተብራርቷል።
የአማራ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ፣ መንግሥት “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ሲል በሚጠራው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በክልሉ 11,000 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበርና ይህም ከፖሊስ የምርመራ አቅም በላይ እንደነበረ አሳውቀዋል።
በቁጥጥር ሥር የማዋያ ትዕዛዞች በፌዴራል መንግሥት ጭምር ይተላለፉ እንደነበር የገለጹት ተወካዩ፣ ሰዎችን በሕግ ጥላ ሥር የማዋልና የምርመራ ሒደቶች በትክክል አለመተግበራቸው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት መሆናቸውን፣ ምክር ቤቱም በወቅቱ ፖሊስ በሚያከናውናቸው የተወሰኑ ጉዳዩች ላይ ክትትል በማድረግ ሪፖርት ማስገባቱንና የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት መሞከሩን ተናግረዋል።
ይሁንና ምስክርነታቸውን ለኢሰመኮ ያሰሙት ተጎጂዎችና ምስክሮች የተፈጸመባቸውን አሰቃቂ የማሰቃየት ወንጀሎች፣ ኢ ሰብዓዊ አያያዝና ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የማድረግ የመብት ጥሰቶች ጥልቀት አስረድተዋል።
በመተማ ታስሮ በራሱና ሌሎች አብረውት በነበሩ ሰዎች ላይ ኢ ሰብዓዊ አያያዝና ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የማድረግ ጥሰቶች እንደተፈጸመባቸው የገለጸ አንድ ተጎጂ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና ወደ መፀዳጃ ቤት ለመሄድ ከሚፈቀድላቸው ወቅት በስተቀር በጨለማ ክፍሎች ታስረው እንዲቆዩ መደረጋቸውን ገልጿል።
በተጨማሪም በማቆያዎች የታሰሩ ሰዎች ተሠልፈው በተያያዘ ገመድ እጆቻቸውን በብረት ሰንሰለት ታስረው መመልከቱንም አሳውቋል።
ለኢሰመኮ ምስክርነታቸውን የሰጡ 20 ተጎጂዎች ሁሉም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ባለው 48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ ትንሹ የእስር ቆይታ ጊዜ ሦስት ቀን ሲሆን እስከ 83 ቀናት ድረስ ፍርድ ቤት ሳይወሰዱ የታሰሩ መኖራቸውንም የኢሰመኮ ሪፖርት ጠቁሟል። በሌላ በኩል ተጎጂዎች በፖሊስ ጣቢያዎች፣ ኢ መደበኛ ማቆያ ሥፍራዎችና እስር ቤቶች ፍርድ ቤት ሳይሄዱ እስከ አንድ ዓመት ድረስ የታሰሩ መኖራቸውን አሳውቀዋል።
በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩና በአሁን ወቅት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌደር የሆኑት ወርቁ ያዜ፣ ቀደም ባለው ጊዜ ዳኞች ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ወቅት የደረሰባቸው የመብት ጥሰት ስለመኖሩ ይጠይቁ እንደነበርና ተጠርጣሪዎችም የመደብደብና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ አያያዞች ሲኖር ሪፖርት ማድረግ የተለመደ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁንና ይህ አሠራር የመንግሥት ባለሥልጣናት ዳኞችን የመብት ጥሰቶች መኖር አለመኖርን በተመለከተ ተጠርጣሪዎችን እንዳይጠይቁ በማዘዛቸው መቆሙን ገልጸዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ በዩኒቨርሲቲያቸው የተደረገ ጥናት ግኝት፣ ግለሰቦች በሐሰተኛ የሽብርተኝነት ወንጀል ስም በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ከአምስት እስከ ሰባት ወራት ለሚደርስ ጊዜ አልፎም እስከ አንድ ዓመት ድረስ በእስራት የሚቆዩበት አሠራር እስከ 2014 ዓ.ም. ክረምት ወቅት ድረስ ቀጥሎ መቆየቱን ማረጋገጡን ጠቁመዋል።
‹‹በሕግ እስኪረጋገጥ ድረስ እንደ ንፁህ የመቆጠር መብትና በቁጥጥር ሥር የዋሉበትን ምክንያት የማወቅ መብት እጅግ አልፎ አልፎ የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው። የሕግ የበላይነት ሳይሆን የሰዎች የበላይነት በመኖሩ ፖሊስ ሕግን ሳይሆን የመንግሥት ባለሥልጣናትን ትዕዛዝ አስፈጽሟል፤›› ማለታቸውን የኢሰመኮ ሪፖርት ያሳያል።
በተጨማሪም በመንግሥት ባለሥልጣናት ትዕዛዝ የሚታሰሩና የሚፈቱ መኖራቸውንም አሳውቀዋል ተብሏል።
የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የሕግ አማካሪ በበኩላቸው፣ የዘፈቀ እስራቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ያለ ችግር ነው ማለታቸው ሲጠቀስ፣ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥሰት ወደመፈጸም የማያመራ መንገዶችን ፖሊስ መጠቀም ይኖርበታል ብለዋል።
በተጨማሪም የክልሉ ፕሬዚዳንት ማረሚያ ቤቶችንና የማቆያ ማዕከሎችን ከጎበኘ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ የመብት ጥሰት ሪፖርቶችን መቀበሉን ጠቅሰው፣ ከፖሊስና ዓቃቤ ሕጎች ይልቅ የዞንና ወረዳ አስተዳዳሪዎች ማን መታሰር አለበት በሚለው ላይ ሲወስን ታይቷል ማለታቸው ተገልጿል።
አማካሪው አክለውም የክልሉ ፍርድ ቤቶች የባለሥልጣናትን ውሳኔዎች ሲያፀድቁ መታየቱን ገልጸው፣ ፍርድ ቤቶች እውነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የዋስትና መብቶችን ሊመለከቱና አቅማቸውንም ሊያጠናክሩ እንደሚገባ መግለጻቸው ተጠቅሷል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ታደሰ አያሌው ተቋማቸውን በመወከል ተጎጂዎችን ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፣ ነገር ግን የቀረቡት ምስክርነቶች ላይ የተጠቀሱት የመብት ጥሰቶች ተጋነዋል ብለዋል።
አካላዊ ጥቃቶች (Physical Assaults)፣ የዘፈቀደ እስራቶች እንዲሁም ኢ መደበኛ በሆኑ የማቆያ ማዕከላት እስራቶች መፈጸማቸውን ዕውቅና በመስጠት፣ የፖሊስ ማቆያ ማዕከላት የነበረው ሎጂስቲክስ እጥረት የተራዘመ የማቆየት ሁኔታዎችን መፍጠሩን፣ ይህም በ‹ሕግ ማስከበር ዘመቻ› ወቅት ተባብሶ እንደነበር ገልጸዋል።